ውሃ እና የውሃ አይነቶች (ጦሀራ – ክፍል 1)

0
5024

ጦሃራ – መግቢያ

ንፅህና (ጦሃራ) በቋንቋ ትርጓሜው ከቆሻሻ ነገሮች መጥራት ማለት ነው። “ነዟፋም” ከቆሻሻ መጥራት ማለት ነው። ስለዚህ ጦሃራና ነዟፋ ተመሳሳይ ናቸው። በሸሪዓው ትርጉሙ ጦሃራ ዉዱእ በማድረግ ከሐደስ [1] ንፁህ መሆን፣ በትጥበት ደግሞ ከጀናባ መጥራት ማለት ነው። በተጨማሪም ከቁሳዊ ነጃሳዎች- ከሽንት፣ ከደም፣ ከመዝይ እና ከስውርና መንፈሳዊ ቆሻሻዎች መፅዳትም ጦሃራ ነው። ለምሳሌ፦ ከልብ ኃጢያቶች መፅዳት፤ በአካል ከሚሰሩ- ዝሙትን ከመሰሉ- ኃጢያቶች መፅዳት ጦሃራ ነው።

ኢስላም ለንፅህና ሰፊ ቦታን ሰጥቷል። በሁሉም የህይወት ዘርፍ ላይ ንፅህናን በጉልህ አስተምሯል። በዱንያም ይሁን በዲን ጉዳዮች ላይ የንፅህናን አስፈላጊነት ሰብኳል። ኢስላም ውስጥ ንፅህና አንኳር ነገር ነው። መሰረታዊነቱን በአፅንኦት ገልጧል። ሙስሊም- እውነተኛ- ከሚባልባቸው መስፈርቶች መሀል አንዱ ነው። አንዳንድ ሙስሊሞች በዚህ ጉዳይ ላይ ክፍተት ካለባቸው ተወቃሾች ናቸው። ውግዝ እና ኃጢያተኛም ናቸው። በቸላተኝነታቸው ምክንያት ነፍሳቸውና ሌሎች ላይ ክፋት ፈፅመዋል።

ማህበረሰብን እና ግለሰብን ሊያወድሙ ከሚችሉ የልብ በሽታዎች- ከኩራት፣ ከምቀኝነት፣ ከመጥፎ ጥርጣሬ፣ ከንቀት- መጥራት አላህ በሙስሊሞች ላይ በሙሉ ግዴታ ያደረገው ነገር ነው። ስለዚህ ጉዳይ ደንታ ቢስ የሆኑ ሰዎችን ስለውጤታቸው አስከፊነት አስጠንቅቋል። ልክ እንዲሁ አካላትን ኃጢያት ውስጥ እንዳይወድቁ መጠበቅ ማንም ሙስሊም የማይጠራጠረው ኃይማኖታዊ ግዴታ ነው።

ከዚህም ጋር- የአላህን ሐቅ ለመወጣት- አካላትን ከትንሹ ሐደስ እና ከትልቁ ሐደስ ማፅዳት፣ አካላቱን ወይም ልብሱን ከሚነኩ ነጃሳዎች መጥራራት እና የግል ንፅህናውን መጠበቅ ግዴታው ነው። ይህም ሰፊ መለኮታዊና ነብያዊ ትንታኔ የተሰጠበት ጉዳይ ነው። ለብዙ አምልኮዎችም መስፈርት ተደርጎ ተቀምጧል።

አፍን ከአስፀያፊ ሽታዎች ማጥራት፣ አካልን ከአስቸጋሪ ቆሻሻዎች መጠበቅ፣ ልብስን ከፀያፍ ነገሮች ማላቀቅ፣ የሚኖርበት ቤቱን ንፁህ ማድረግ፣ የመኖርያ መንደሩን ንፅህና መጠበቅ ሁሉም ኢስላማዊ ግዴታዎች ናቸው። ሰዎች መልካም፣ ውብ፣ አስደሳች ህይወት እንዲኖራቸው ሲባል በኢስላም የተደነገጉ መመሪያዎች ናቸው። የሰዎችን ህይወት ከሚቀስፉ ወረርሺኞች ለመጠበቅ ኢስላም ተከታዮቹን ያዘዘባቸው ትእዛዛት።

በሶላት ወቅት- ከነጃሳ እንዲጠሩ፣ በቀን አምስት ጊዜ ዉዱእ እንዲያደርጉ፣ ልብሳቸውን፣ አካላቸውን እና የመስገጃ ቦታቸውን ንፅህና እንዲጠብቁ፣ ጀናባ ከሆኑ እንዲታጠቡ ሙስሊሞች የታዘዙት በእነዚህ ሶላቶች ላይ አላህን ማምለክን ለማስፈቀድ ብቻ ነው ብሎ የሚያስብ ሰው ካለ ተሳስቷል።

ዘካ አምልኮ ነው። ጾም አምልኮ ነው። አላህን ማውሳት- ዚክር- አምልኮ ነው። ዱዓ ማድረግ፣ አላህን እርዳታ መለመን አምልኮ ነው። እነዚህን አምልኮዎች ለሚፈፅም ሰው ለምን በንፅህና አልታዘዘም? ዉዱእ ማድረግ እና ጀናባን ማስወገድ አልተደነገገም? መልሱን አላህ ያውቀዋል!

ምናልባት ሶላት ሙስሊሞች በመስጂድ ተሰብስበው የሚሰግዱት ሰጋጆች አጠገባቸው ከሚገኘው ወንድማቸው ጋር የሚቆሙበት የአምልኮ አይነት ስለሆነ ይሆናል። ሰጋጁ አጠገቡ ያለውን ወንድሙን ሽታ ያሸታል። ንፅህናውን እና ሁኔታውን በማየት ይነካል። ስነምግባሩንና መንፈሱንም ይጋራል። ስለዚህ ሙስሊም ሰዎችን በሚያሸሽ ሁኔታ ላይ መኖር የለበትም። ስለዚህ ነው መልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ.) “ቀይ ሽንኩርት፣ ባሮ ወይም ነጭ ሽንኩርት የበላ ሰው መስጂዳችንን ይራቅ።” የሚል ትእዛዝ ያስተላለፉት።

ስለዚህ ለሶላትና ለመሰል አምልኮዎች የተደነገጉት ንፅህናዎች ለአምልኮ የታለሙ ብቻ አይደሉም። ይልቅ ሌሎችም ዓላማዎችና ጥበቦች አሏቸው። ሙስሊም ለሙስሊም የሚኖረውን ቅርበት ማጠናከር፣ ወደርሱ በመጠጋት እና እርሱን በመቅረብ እንዲፅናና፣ ፍቅራቸውን ለመጨመር የታለሙም ናቸው። አላህ ጌጣችሁን ያዙ ማለቱን፣ መልእክተኛው ሙስሊሞች በማንኛውም ሶላት ላይ ሲዋክ (የጥርስ መፋቂያ) እንዲጠቀሙ ማዘዛቸውን፣ የጁሙዓ ቀን ላይ ሽቶ መቀባት ማበረታታቸውን፣ ገላ መታጠብን ማዘዛቸውን ከተመለከትን ንፅህና ከአምልኮ ባሻገር ሌላም ፋይዳ እንዳለው እንረዳለን።

ለንፅህና ትኩረት ካለመስጠቱ የተነሳ በእርድ ደም ተጨማልቆ፣ በወናፍ ሽታ ጠረኑ ተለውጦ፣ በላቡ እምቅ ጠርንቶ፣ የሰውነቱ ቀለም በጭቅቅት ተሸፍኖ አንድ ሰው መስጂድ መምጣት ይችላልን? መልሱን ስለሽንኩርቶች ፍርድ ስንናገር አሳልፈነዋል። እንደውም የጠቀስናቸው ሰዎች ሁኔታ ነጭ ሽንኩርት ከበላ ሰውም የከፋ ነው።

በዚህ ተከታታይ መጣጥፍ ውስጥ ንፅህና እና ተያያዥ የሆኑት ሱነኑል-ፊጥራን፣ ሲዋክን፣ ግርዛትን፣ ስለፂም ወ.ዘ.ተ. አንስተናል። ኢስላም ለአካላዊ ንፅህና ብቻ ሳይሆን ለውበትም መጨነቁን ያሳያል።

የኢስላም ዋነኛ ማእዘን  የሆነውን ሶላትን ለመፈፀም የሰጋጁ ሰውነት፣ ልብስና የመስገጃ ስፍራ ቁሳዊ ከሆኑ ርክሰቶች (ነጃሳዎች) ንፁህ መሆን አለበት። በተጨማሪም ዉዱእና ገላን መታጠብ ግዴታ ከሚያደርጉ አነስተኛና ከፍተኛ ርክሰቶች (ሐደሱል-አስገር እና ሐደሱል-አክበር) ንጹህ መሆን አለበት። ይህ ለሶላት- እንደመስፈርት (ሸርጥ)- የተቀመጠ ነው። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) “አላህ ያለ ንጽህና የተፈጸመ ሶላትን አይቀበልም።” በማለት ተናግረዋል። ስለሆነም ስለ ሶላት ከማውራታችን በፊት ስለጦሀራና ተያያዥ ጉዳዮች መረዳት ያስፈልጋል። የንፅህና ቁልፉ ደግሞ ውሃ ነውና ስለውሃ ሸሪዓው ያስቀመጣቸውን ነገሮች በማንሳት እንጀምር።

ውሃ እና የውሃ አይነቶች

አንደኛው የውሃ አይነት፦ “አል-ማኡል ሙጥለቅ”

አል-ማኡል ሙጥለቅ (ስድ ውሃ) ይባላል። ከምንም ተቀጽላ ጋር ሳይቆራኝ በራሱ “ውሃ” የሚል ስያሜ የሚገባው ነው። ስለዚህ የፅጌሬዳ ውሃን የመሰሉ በቅፅል የሚወሱ የውሃ አይነቶች እዚህኛው የውሃ አይነት ውስጥ አይካተቱም።

ማኡል-ሙጥለቅን ለሸሪዓዊ ንፅህና መጠቀም ይፈቀዳል። ለራሱም ንፁህ (ጧሂር) ነው። ሌሎችንም ነገሮች ንፁህ ያደርጋል (ሙጦሂር ነው)። ከዚህ የውሃ አይነት ሥር ተከታዮቹን የውሃ አይነቶች መዘርዘር እንችላለን።

  1. የዝናብ፣ የቁር እና የበረዶ ውሃ

አላህ (ሰ.ወ) እነዚህን የውሃ አይነቶች አስመልክቶ እንዲህ ይላል፦

وَيُنَزِّلُ عَلَيْكُم مِّنَ السَّمَاءِ مَاءً لِّيُطَهِّرَكُم بِهِ

“ውሃውንም በእርሱ ሊያጠራችሁ በእናንተ ላይ ከሰማይ ባወረደላችሁ ጊዜ (አስታውሱ)።” (አል-አንፋል፤ 11)

በሌላም አንቀፅ ላይ እንዲህ ይላል፦

وَأَنزَلْنَا مِنَ السَّمَاءِ مَاءً طَهُورًا

“ከሰማይም አጥሪ ውሃን አወረድን።” (አል-ፉርቃን፤ 48)

አቡሁረይራ (ረ.ዐ) በዘገቡት ሐዲስ ውስጥም፡-

كان رسول الله صلى الله عليه وسلم إذا كبر في الصلاة سكت هنيهة قبل القراءة ، فقلت : يا رسول الله – بأبي أنت وأمي – أرأيت سكوتك بين التكبير والقراءة ما تقول ؟ قال : أقول اللهم باعد بيني وبين خطاياي كما باعدت بين المشرق والمغرب ، اللهم نقني من خطاياي كما ينقى الثوب الابيض من الدنس ، اللهم اغسلني من خطاياي بالثلج والماء والبرد

“የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ሶላት ውስጥ ተክቢራ አድርገው ከገቡ በኋላ ቁርኣንን ማንበብ ከመጀመራቸው በፊት ትንሽ ዝም ይሉ ነበር። ‘የአላህ መልእክተኛ ሆይ! እናቴና አባቴ ይሰዉሎትና በተክቢራና ቁርአን ማንበብ መሃል ዝምታዎት ላይ ምን እንደሚሉ ንገሩኝ?’ አልኳቸው። ‘አላህ ሆይ! በምስራቅና ምእራብ መሀል እንዳራራክ በእኔና በኃጢያቴ መሀል አርቅ። አላህ ሆይ ነጭ ልብስ ከቆሻሻ እንደሚፀዳው ከኃጢያቴ አፅዳኝ። አላህ ሆይ በውሃ በቁር እና በበረዶ ከኃጢያቴ እጠበኝ’።” (ከቲርሚዚ በቀር ሁሉም ጀመዓዎች ዘግበውታል)።

  1. የባህር ውሃ

ይህ የውሃ አይነት በአቢሁረይራ (ረ.ዐ) ሐዲስ ውስጥ ተዘግቦ እናገኘዋለን።

سأل رجل رسول الله صلى الله عليه وسلم فقال يا رسول الله ، إنا نركب البحر ، ونحمل معنا القليل من الماء فإن توضأنا به عطينا ، أفنتوضأ بماء البحر ؟ فقال رسول الله صلى الله عليه وسلم : هو الطهور ماؤه ، الحل ميتته

“አንድ ሰውዬ የአላህን መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብሎ ጠየቃቸው- ‘የአላህ መልእክተኛ ሆይ! እኛ ባህር ላይ እንጓጓዛለን። ጥቂት ውሃ ይዘን እንጓዛለን። በርሱ ዉዱእ ካደረግን እንጠማለን። በባህር ውሃ ውዱእ እናድርግ?’። ከዚያም መልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ.) ‘እርሱ ውሃው ንፁህ ነው። ውስጡ የበከተ እንስሳም ይፈቀዳል።’ ብለው መለሱ።” (አምስቱ ዘግበውታል። ቲርሚዚ የሐዲሱ ትምህርት መልካም እና ሰነዱ ትክክለኛ ነው ብለውታል)።

  1. የዘምዘም ውሃ

ከዓሊይ ቢን አቢጣሊብ (ረ.ዐ) እንደተዘገበው፦

أن رسول الله صلى الله عليه وسلم دعا بسجل من ماء زمزم فشرب منه وتوضأ

“የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) በዘምዘም ውሃ የተሞላ ባልዲ አስመጡና ከርሱ ጠጡ ዉዱእም አደረጉበት።” (አሕመድ ዘግበውታል)

  1. ረዥም ጊዜ በመቆየት ወይም ውሃው በሚኖርበት ሥፍራ ውስጥ ባሉ ውሃው ላይ ተፅእኖ እንዳያሳድር መከላከል የሚሳኑ እና ከውሃው መነጠል በማይቻሉ ነገሮች (አልጌንና የዛፍ ቅጠሎችን በመሰሉ ነገሮች) ሽታው፣ ቀለሙ ወይም ጣዕሙ የተለወጠ ውሃ

በእነዚህ ሁኔታዎች በሙሉ ውሃው በስድ-ውሃ- ከመባል አልተገለለም። ስለዚህ ለንፅህና ብቁ በመሆኑ ላይ ዑለሞች አልተለያዩም።

ከላይ ባብራራናቸው ጉዳዮች ላይ የምንነሳበው “ውሃ” ሚለው ስያሜ በስድ የሚጠራ ነገር ሁሉ ለንፅህና ከመሆኑ ነው። አላህ እንዲህ አለ፦

فَلَمْ تَجِدُوا مَاءً فَتَيَمَّمُوا َ

“ውሃን ባታገኙ ንጹሕን የምድር ገጽ አስቡ።” (አል-ማኢዳ፤ 6)

ሁለተኛው የውሃ አይነት፦ “አል-ማኡል ሙስተዕመል”

አል-ማኡል-ሙስተዕመል (ጥቅም ላይ የዋለ ውሃ)፦ ይህ የውሃ አይነት ዉዱእ ከሚያደርግ ወይም ገላውን ከሚታጠብ ሰው የሚረጭ ወይም የሚንጠባጠብ ውሃ ነው። ብይኑም አል-ማኡል ሙጥለቅ (ስድ ውሃ) ላይ የጠቆምነው ብይን ነው። ምንም ልዩነት የለውም። ምክንያቱም የምንመለከተው የውሃውን መሰረት ነው። ንፁህ ነበር። ከንፅህናው የሚያስወጣው ምንም ምክንያት አላገኘንበትም። በአል-ረቢዕ ቢንት ሙዐዊዝ ሐዲስ ውስጥ የነብዩን (ሰ.ዐ.ወ) ዉዱ አስደራረግ እንማራለን።

ومسح رأسه بما بقي من وضوء في يديه

“እጃቸው ላይ በተረፈ ውሃ ራሳቸውን አበሱ።” (አሕመድ እና አቡ ዳዉድ ዘግበውታል)

የአቡዳዉድ ዘገባ እንዲህ የሚል አገላለፅ አለው፡-

أن رسول الله صلى الله عليه وسلم مسح رأسه من فضل ماء كان بيده

“የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እጃቸው ላይ በነበረ ትርፍ ውሃ ራሳቸውን አብሰዋል።”

وعن أبي هريرة رضي الله عنه أن النبي صلى الله عليه وسلم لقيه في بعض طرق المدينة وهو جنب ، فانخنس منه فذهب فاغتسل ثم جاء فقال : أين كنت يا أبا هريرة ؟ فقال : كنت جنبا ، فكرهت أن أجالسك وأنا على غير طهارة ، فقال : سبحان الله إن المؤمن لا ينجس

አቡ ሁረይራ (ረ.ዐ) በዘገቡት ሐዲስ፦ “ጀናባ (ርክሰት) ሆኖ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) የመዲና መንገድ ላይ አገኙት። ከርሳቸው ተደብቆ ሄደና ታጥቦ መጣ። ‘የት ነበርክ?’ ብለው ጠየቁት። ‘ጀናባ ነበርኩ። ንፁህ ሳልሆን ከርሶ ጋር መቀመጥ ጠልቼ ነው።’ አለ። ‘ሱብሓነላህ! ሙእሚን አይነጀስም (አይቆሽሽም)’ አሉ።” (ጀመዓዎች ዘግበውታል)

ሐዲሱ ከርእሳችን ጋር በምን ተገናኘ? ልብ እንበል! ሐዲሱ ሙእሚን አይነጀስም እያለን ነው። እንዲያ ከሆነ ደግሞ ጀናባ የወረደበትን ውሃ የሙእሚንን አካል በመንካቱ ብቻ ንፅህናው የጎደለበት ማድረግ ትክክል አይሆንም። ሰውየው አካሉን ማስነካቱ ንፁህ አካሉን ከንፁህ ውሃ ጋር ከማነካካት ውጪ ሌላ ክስተት አይደለም። በዚህ ንኪኪ ደግሞ ውሃው አይለወጥም።

ሦስተኛው የውሃ ክፍል:- ንፁህ የሆኑ ነገሮች ተቀላቀሉት

ሳሙናን፣ ዘዕፈራንን፣ ዱቄት እና ሌሎችም ንፁህ ከሆኑ ማለያየት ከማይቻሉ ነገሮች ጋር የተደባለቀ ውሃ ነው። እንዲህ አይነቱ “ውሃ” ከመባል እስካልወጣ ድረስ ንፁህ ነው። ውሃ ከመባል ከወጣ ግን ለራሱ ንፁህ ሲሆን ሌሎችን ንፁህ ማድረግ ግን አይችልም።

አሕመድ፣ ነሳኢይ፣ ኢብኑ ኹዘይማ ከኡሙ ሃኒእ በዘገቡት ሐዲስ

أن النبي صلى الله عليه وسلم اغتسل هو وميمونة من إناء واحد : قصعة فيها أثر العجين

“የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) እና መይሙና (ባለቤታቸው) ከአንድ እቃ ታጥበዋል። የሊጥ ፋና ካለበት ሳፋ ላይ ውሃ እየጠለቁ ታጥበዋል።”

እነዚህ ሐዲስ ላይ ውሃ ንፁህ ከሆኑ ነገሮች ጋር ተደባልቋል። ነገርግን ውሃ ከመባል በሚወጣበት ያህል አልተለወጠም። ስለዚህ እንዲህ አይነቱ ውሃ ለንፅህና ብቁ ነው።

አራተኛው የውሃ አይነት፦ ነጃሳ የነካው ውሃ

ይህ ሁለት አይነት ሲሆን እነሱም፦

  1. ነጃሳው ጣዕሙን፣ ቀለሙን ወይም ሽታውን ቀይሮት ከሆነ። በዚህ ሁኔታ ይህን ውሃ ለሸሪዓዊ ንፅህና (ለጦሀራ) መጠቀም አይፈቀድም። ይህ ዑለሞች በሙሉ ይስማሙበታል። ኢብኑል-ሙንዚር እና ኢብኑል-ሙለቂን የዑለሞችን ስምምነት (ኢጅማዕ) አጣቅሰውልናል።
  2. ውሃው ውሃ ከመባል ካልወጣ፤ ሽታው፣ ጣዕሙ ወይም ቀለሙ ካልተቀየረ ለንፅህና ይሆናልን? እዚህ ላይ ልዩነት አለ። ውሃው ትንሽም (ቀሊል) ብዙም (ከሲር) ቢሆን ንፁህ (ጧሂር) ነው፤ ሌላንም ንፁህ ያደርጋል (ሙጦሂር) የሚል አቋም ያላቸው ዑለሞች አልሉ።

ከአቢ ሰዒድ አል-ኹድሪይ እንደተዘገበው፦

قيل يا رسول الله أنتوضأ من بئر بضاعة ؟ فقال صلى الله عليه وسلم : الماء طهور لا ينجسه شئ

“የአላህ መልእክተኛ ሆይ! በቡዳዓ ጉድጓድ ውሃ ዉዱእ እናድርግ? ተብለው ተጠየቁ። እርሳቸውም (ሰ.ዐ.ወ.) ‘ውሃ ንፁህ ነው ምንም ነገር አይነጅሰውም።’ አሉ።” (ሻፊዒይ፣ አሕመድ፣ አቡዳዉድ፣ ነሳኢይ እና ቲርሚዚይ ዘግበውታል። አሕመድ ‘የቡዳዓ ጉድጓድ ሐዲስ ሶሒሕ ነው።’ ብለዋል። የሕያ ኢብኑ መዒን እና አቡ ሙሐመድ ቢን ሐዝምም ሐዲሱን ሶሒሕ ብለውታል)። ኢብኑ ዓባስ፣ አቡ ሁረይራ፣ አል-ሐሰኑል በስሪይ፣ ኢብኑል-ሙሰየብ፣ ዒክሪማ፣ ኢብኑ አቢ ለይላ፣ አል-ሰውሪይ፣ ዳዉድ አል-ዛሂሪይ፣ አን-ነኸዒይ፣ ማሊክ እና ሌሎችም ይህን መንገድ መርጠዋል። አል-ገዛሊይ እንዲህ ይላሉ፦ “ውሃ ላይ የሻፊዒይ መዝሀብ እንደ ማሊክ ቢሆን እወድ ነበር።”

አምስቱ የዘገቡት

إذا كان الماء قلتين لم يحمل الخبث

“ውሃ ሁለት ቁለት (227 ሊትር) ከሆነ ቆሻሻን አይሸከምም።”

የሚለው የዓብዱላህ ቢን ዑመር (ረ.ዐ) ሐዲስ የሻፊዒይ መዝሀብ የሚመሰረትበት ሐዲስ ነው። ውሃን ለሁለት ይከፍሉታል። ትንሽ ውሃ እና ብዙ ውሃ። ትንሽ ውሃ ከሁለት ቁለት ያነሰ ውሃ ነው። ነጃሳ ከገባበት- ሽታው፣ ቀለሙ ወይም ጣዕሙ ባይለወጥም- ይነጀሳል። ብዙ ውሃ- ሽታው፣ ጣዕሙ ወይም ቀለሙ እስካልተለወጠ ድረስ- ግን ነጃሳ በመግባቱ ምክንያት አይነጀስም።

ሐዲሱ ሙድጠሪብ (ሰነዱ ወይም ትምህርቱ /መትኑ/ የተናጋ) ነው። ሰነዱም ትምህርቱም የተናጋ እና ልዩነት ያለበት ሐዲስ ነው። ከደካማ የሐዲስ አይነቶች አንዱ ነው። ኢብኑ ዐብዲልበር አት-ተምሂድ የተሰኘው መፅሃፍ ላይ “ሻፊዒይ መንገዳቸውን የመሰረቱበት የቁለተይን ሐዲስ ደካማ ነው። የእስትንታኔም ሆነ የመረጃ መሠረቱ ደካማ ነው።” ብለዋል።


[1] ሐደስ ማለት በአካላት ላይ የሚከሰት የሶላትን ተቀባይነት የሚያሳጣ በዓይን የማይታይ ምናባዊ ነገር ነው። ሐደስ ሁለት አይነት ነው። ትጥበትን ግዴታ የሚያደርግ ወይም ሐደሱል-አክበር (ትልቁ ሐደስ) እና ዉዱእን ግዴታ የሚያደርግ ወይም ሐደሱል-አስገር (ትንሹ ሐደስ)።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here