የሰደቃ ትሩፋትና ዓይነቶች (ክፍል 1)

0
11657

ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ይሁን ሶላትና ሰላም በተከበሩት ነቢያችን ሙሐመድ በቤተሰቦቻቸውና በሶሓቦቻቸው ላይ ሁሉ ይሁን፡፡

አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ ይላል፡-

قُل لِّعِبَادِيَ الَّذِينَ آمَنُوا يُقِيمُوا الصَّلَاةَ وَيُنفِقُوا مِمَّا رَزَقْنَاهُمْ سِرًّا وَعَلَانِيَةً مِّن قَبْلِ أَن يَأْتِيَ يَوْمٌ لَّا بَيْعٌ فِيهِ وَلَا خِلَالٌ

ለእነዚያ ላመኑት ባሮቼ በእርሱ ውስጥ ሽያጭና ወዳጂነት የሌለበት ቀን ከመምጣቱ በፊት ሶላትን በደንቡ ይሰግዳሉ፡፡ ከሰጠናቸውም ሲሳይ በምስጢርም በግልጽም ይለግሳሉ፡፡ (ስገዱ ለግሱም) በላቸው፡፡ (ኢብራሂም፡31)

وَأَنفِقُوا فِي سَبِيلِ اللَّهِ وَلَا تُلْقُوا بِأَيْدِيكُمْ إِلَى التَّهْلُكَةِ ۛ وَأَحْسِنُوا ۛ إِنَّ اللَّهَ يُحِبُّ الْمُحْسِنِينَ

በአላህም መንገድ ለግሱ፡፡ በእጆቻችሁም (ነፍሶቻችሁን) ወደጥፋት አትጣሉ፡፡ በጎ ሥራንም ሥሩ፤ አላህ በጎ ሠሪዎችን ይወዳልና፡፡ (አል-በቀረህ፡ 195)

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا أَنفِقُوا مِمَّا رَزَقْنَاكُم مِّن قَبْلِ أَن يَأْتِيَ يَوْمٌ لَّا بَيْعٌ فِيهِ وَلَا خُلَّةٌ وَلَا شَفَاعَةٌ ۗ وَالْكَافِرُونَ هُمُ الظَّالِمُونَ

እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በርሱ ውስጥ ሽያጭ (መበዠት)፣ ወዳጅነትም፣ ምልጃም የሌለበት ቀን ከመምጣቱ በፊት ከሰጠናችሁ ነገር ለግሱ ከሓዲዎችም በዳዮቹ እነርሱ ናቸው፡፡ (አል-በቀረህ፡ 254)

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا أَنفِقُوا مِن طَيِّبَاتِ مَا كَسَبْتُمْ وَمِمَّا أَخْرَجْنَا لَكُم مِّنَ الْأَرْضِ ۖ وَلَا تَيَمَّمُوا الْخَبِيثَ مِنْهُ تُنفِقُونَ وَلَسْتُم بِآخِذِيهِ إِلَّا أَن تُغْمِضُوا فِيهِ ۚ وَاعْلَمُوا أَنَّ اللَّهَ غَنِيٌّ حَمِيدٌ

እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ካፈራችሁትና ከዚያም ለእናንተ ከምድር ካወጣንላችሁ ከመልካሙ ለግሱ መጥፎውንም (ለመስጠት)አታስቡ በእርሱ ዓይኖቻችሁን ጨፍናችሁ እንጂ የማትወስዱት ስትኾኑ ከእርሱ (ከመጥፎው) ትሰጣላችሁን? አላህም ተብቃቂ ምስጉን መኾኑን ዕወቁ (አል-በቀረህ፡ 267)

فَاتَّقُوا اللَّهَ مَا اسْتَطَعْتُمْ وَاسْمَعُوا وَأَطِيعُوا وَأَنفِقُوا خَيْرًا لِّأَنفُسِكُمْ ۗ وَمَن يُوقَ شُحَّ نَفْسِهِ فَأُولَٰئِكَ هُمُ الْمُفْلِحُونَ

አላህንም የቻላችሁትን ያክል ፍሩት፤ ትዕዛዙን ስሙም፤ ታዘዙም፤ ለግሱም፤ ለነፍሶቻችሁ መልካምን (ይሰጣችኋልና)፤ የነፍሱንም ንፍገት የሚጠበቅ ሰው እነዚያ እነሱ ፍላጎታቸውን የሚያገኙ ናቸው። (አት-ተጋቡን፡ 16)

የሰደቃን ትሩፋት ከሚያመለክቱ ሐዲሦችም መካከል የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፡-በርሱና በአላህ መካከል አንድም አስተርጓሚ ሳይኖር አላህ የማያናግረው አንድም ሰው የለም፡፡ (አንዳችሁ) ወደ ቀኙ ይመለከታል ያሳለፈውን ነገር እንጂ ምንም አይታየውም፡፡ ወደ ግራውም ይመለከታል፡፡ ያሳለፈውን ነገር እንጂ ምንም አያይም፡፡ ወደ ፊትለፊቱም ይመለከታል ፊት ለፊቱ እሳትን እንጂ ምንም አያይም፡፡ በግማሽ ተምርም (በመመፅወት) ቢሆን እሳትን ፍሩ፡፡” (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)

በቁርኣንና ሆነ ሐዲሥ ትእዛዝ የተላለፈባቸውን በምጽዋት የሚያነሳሱ መልእክቶችን በጥልቀት ስንመለከት ከሷ የሚበልጡ መልካም ስራዎች ይኖራሉ ብሎ ለመገመት ይከብዳል፡፡ ለዚህም ይመስላል ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንዲህ እስከማለት ደርሰዋል፡- “ስራዎች እንደሚፎካከሩ ተነገረኝ፡፡ ሰደቃ (ምጽዋት) እኔ የሁላችሁም በላጭ ነኝ ትላቸዋለች፡፡” አሉ፡፡

የሰደቃ ትሩፋትና ፋይዳ

 1. ሰደቃ የአላህን ሱብሃነሁ ወተዓላ ቁጣ ታበርዳለች፡፡ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም በሚስጢር የምትሰጥ ሰደቃ የልዕልና ባለቤት የሆነውን የአላህን ቁጣ ታበርዳለች፡፡” ብለዋል፡፡
 2. ውሃ እሳትን እንደሚያጠፋው ሁሉ ሶደቃም ወንጀልን /ሐጢኣትን/ ታጠፋለች፡፡”
 3. በግማሽ ተምርም ቢሆን እሳትን ፍሩ፡፡” ማለታቸውን አይተናል፡፡ 
 4. ሰደቃ የሚሰጥ ሰው የትንሳኤ ቀን በሰጠው ሰደቃው ጥላ ስር ነው የሚሆነው፡፡ ከዑቅበህ ኢብኑ ዓምር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንደተላለፈው የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ሲሉ ሰማኋቸው አለ፦ በሰዎች መካከል ፍርድ እስኪሰጥ ድረስ እያንዳንዱ ሰው በሰደቃው ጥላ ስር ይቆያል፡፡” የዚድ “አቡ መርሰድ ደረቅ ዳቦም ይሁን ሽንኩርት ነገር ሰደቃ ሳይሰጥ አንድም ቀን አያሳልፍም ነበር፡፡” ብሏል፡፡ ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም የማንም ጥላ በሌለበት በትንሳኤ ቀን በአላህ ጥላ ስር ከሚውሉት መካከል በቀኙ የሚሰጠውን ነገር ግራው እንኳን ልታውቅ በማትችልበት መልኩ ምፅዋት የሚሰጥ ሰው አንዱ ነው፡፡” ብለዋል፡፡ 
 5. በሽተኛችሁን በምጽዋት አክሙ፡፡” ብለዋል፡፡ ኢብኑ ሸቂቅ አንዲህ ብሏል፡- ኢብኑ አልሙባረክን አንድ ሰው ከሰባት አመት ወዲህ በጉልበቱ ላይ ስለወጣውና የተለያዩ ዓይነት መድሃኒቶችን በመጠቀም ስለታከመው፣ ሃኪሞችንም ጠይቆ ምንም ውጤት ስላላገኘበት አንድ ቁስል ሲጠይቀው “ውሃ የተቸገሩ ሰዎች አካባቢ ሂድና የውሃ ጉድጓድ ቆፍር፡፡ እዚያም ምንጭ ይፈልቅና ይህን ደምህን ያስቆምልሃል ብዬ እመኛለሁ፡፡” አለው፡፡ሰውዬውም እንደተባለው ባደረገ ጊዜ ከህመሙ ተፈወሰ፡፡
 6. ሰደቃ ለቀልብ በሽታዎችም መድሃኒት ናት፡፡ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ስለ ቀልቡ መድረቅ ለነገራቸው አንድ ሰው ቀልብህ እንዲለሰልስ ከፈለግክ ድሃ አብላ፡፡ የወላጅ አጥ /የቲም/ን ራስ አብስ፡፡”
 7. ሰደቃ ከጠማማ፣ ከበዳይ እና ከከሀዲ ሰው ብትቀርብ እንኳ የተለያዩ የመከራ ዓይነቶችን ለመመለስ ከፍተኛና የሚገርም ተጽእኖ አላት፡፡ የልዕልና ባለቤት የሆነው አላህ በሷ አማካይነት በርካታ የመከራ ዓይነቶችን ይመልሳል፡፡ ይህም እያንዳንዱ ሰው የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ ብዙዎችም ሞክረው አረጋግጠዋልና በዚሁ ይመሰክራሉ፡፡
 8. አንድ የአላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ባሪያ ከእውነተኛ የበጎነት ደረጃ የሚደርሰው ምጽዋት በመስጠት ነው፡፡ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ ብሏል፡-

لَن تَنَالُوا الْبِرَّ حَتَّىٰ تُنفِقُوا مِمَّا تُحِبُّونَ ۚ وَمَا تُنفِقُوا مِن شَيْءٍ فَإِنَّ اللَّهَ بِهِ عَلِيمٌ

“የምትወዱትን እስከምትለግሱ ድረስ በጎን ሥራ (ዋጋውን) አታገኙም፡፡ ከምንም ነገር ብትለግሱ አላህ ያውቀዋል፡፡” (አሊ ዒምራን፡ 92)

 1. በየቀኑ ባሮች በሚያነጉበት ቀን ሁለት መላእክት ይወርዳሉ፡፡ አንደኛው ‹አላህ ሆይ ለሚለግስ ሰው ተካለት፡፡› ይላል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ‹አላህ ሆይ! የሚሰስትን ሰው አጥፋበት፡፡› ይላል፡፡”
 2. ሰደቃ የሚሰጥ ሰው ሀብትና ገንዘቡ ይባረክለታል፡፡ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሰደቃ ከሀብት አንዳችም ነገር አይቀንስም፡፡” ብለዋል፡፡

لَّيْسَ عَلَيْكَ هُدَاهُمْ وَلَٰكِنَّ اللَّهَ يَهْدِي مَن يَشَاءُ ۗ وَمَا تُنفِقُوا مِنْ خَيْرٍ فَلِأَنفُسِكُمْ ۚ وَمَا تُنفِقُونَ إِلَّا ابْتِغَاءَ وَجْهِ اللَّهِ ۚ وَمَا تُنفِقُوا مِنْ خَيْرٍ يُوَفَّ إِلَيْكُمْ وَأَنتُمْ لَا تُظْلَمُونَ

“እነርሱን ማቅናት በአንተ ላይ የለብህም፡፡ ግን አላህ የሚሻውን ሰው ያቀናል፡፡ ከገንዘብም የምትለግሱት (ምንዳው) ለነፍሶቻችሁ ነው፡፡ የአላህንም ፊት (ውዴታውን) ለመፈለግ እንጂ አትለግሱም፡፡ ከገንዘብም የምትለግሱት ሁሉ (ምንዳው) ወደናንተ ይሞላል፡፡ እናንተም አትበደሉም፡፡” (አል-በቀራ፡ 272)

በአንድ ወቅት ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ስላረዷት አንዲት ፍየል ዓኢሻን አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና በጠየቋት ጊዜ “ትከሻዋ እንጂ ምንም አልቀረም፡፡” አለቻቸው፡፡ እርሳቸውም ትከሻዋ ሲቀር ሁሉም ቀርቷል፡፡” አሏት፡፡

إِنَّ الْمُصَّدِّقِينَ وَالْمُصَّدِّقَاتِ وَأَقْرَضُوا اللَّهَ قَرْضًا حَسَنًا يُضَاعَفُ لَهُمْ وَلَهُمْ أَجْرٌ كَرِيمٌ

“የመጸወቱ ወንዶችና፣ የመጸወቱ ሴቶች፣ ለአላህም መልካምን ብድር ያበደሩ ለእነርሱ መልካም ምንዳ አልላቸው፡፡” (አልሐዲድ፡ 18)

مَّن ذَا الَّذِي يُقْرِضُ اللَّهَ قَرْضًا حَسَنًا فَيُضَاعِفَهُ لَهُ أَضْعَافًا كَثِيرَةً ۚ وَاللَّهُ يَقْبِضُ وَيَبْسُطُ وَإِلَيْهِ تُرْجَعُونَ

“ያ ለአላህ መልካም ብድርን የሚያበድርና ለእርሱ (አላህ) ብዙ እጥፎች አድርጎ የሚያነባብርለት ማነው? አላህም ይጨብጣል፤ ይዘረጋልም፤ ወደ እርሱም ትመለሳላችሁ፡፡” (አልበቀራ ፡ 245)

 1. የሰደቃ ባለቤት ‹የሰደቃ በር› በሚባል ልዩ በሆነ የጀነት በር ይጠራል፡፡ አቢ ሁረይራ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ባስተላለፉት ሐዲስ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም በአላህ መንገድ ላይ ሁለት ጥንድ ነገሮችን የመፀወተ ሰው በጀነት ውስጥ ‹አንተ የአላህ ባሪያ ሆይ! ይህ በላጭ ነገር ነው፡፡› ተብሎ ይጠራል፡፡ የሰላት ሰው የሆነ እንደሆነ በሰላት በር ይጠራል፡፡ የጂሃድ ባለቤት የሆነ ሰው በጂሃድ በር ይጠራል፡፡ የሶደቃ ባለቤት የሆነ ሰው በሰደቃ በር ይጠራል፡፡ የፆም ባለቤት የሆነ ሰው በረያን በር ይጠራል” አቡበክር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ‹የአላህ መልእክተኛ ሆይ! አንድ ሰው በነኚህ ሁሉ በሮች ሊጠራ ይችላል ወይ?› አላቸው፡፡ እሳቸውም ‹አዎን አንተ ከነርሱ መካከል ትሆን ዘንድ እመኛለሁ፡፡› አሉት፡፡
 2. ሰደቃ በአንድ ቀን ውስጥ ከሌሎች መልካም ስራዎች ጋር ማለትም ከፆም፣ ጀናዛን ከመከተልና በሽተኛን ከመጠየቅ ጋር የተሰባሰበ እንደሆነ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ለዚያ ሰው ጀነትን ይሰጠዋል፡፡ በሐዲስ እንደተላለፈው የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም አንድ ቀን ለሰሓቦቻቸው ‹ከናንተ መካከል ፆመኛ ሆኖ ያነጋ ማነው?› አሉ፡፡ አቡበክር ‹እኔ ነኝ› አለ፡፡ ‹ከናንተ ውስጥ ጀናዛን የተከተለ ማን አለ?› አሉ አቡበክር ‹እኔ› አለ፡፡ ‹በሽተኛ የጠየቀስ ማን አለ?› አሉ፡፡ አቡበክር ‹እኔ ነኝ› አለ፡፡ የአላህ መልእክተኛም ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ‹እነኚህ ነገሮች በአንድ ሰው ውስጥ አይሰባሰቡም ጀነት የገባ ቢሆን እንጂ፡፡› አሉ፡፡
 3. ሰደቃ መስጠት ደረትን ያሰፋል፣ ለቀልብ እረፍት ይሠጣል፣ ያረጋጋዋልም፡፡ ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ስለ ስስታምና ለጋሽ ሰው ምሳሌ ሲያስቀምጡ፡- ምሳሌያቸው ከብረት የሆነ ጡሩር ደረታቸው ላይ እስከ አንገታቸው ድረስ እንደለበሱ ሁለት ሰዎች ነው፡፡ ለጋሹ ሰውዬ በለገሰ ቁጥር ትሰፋለታለች፡፡ ቆዳውም እስኪሸፈን ድረስ ታለብሰዋለች፡፡ ስስታም ሰው ደግሞ አንድን ነገር ለመስጠት ባሰበ ቁጥር እሱ ማስፋት ቢፈልግም እንኳ እያንዳንዷ ቀለበት ቦታዋን ጥብቅ እንቅ አድርጋ ትይዛለች፣ አትሰፋም፡፡› ብለዋል፡፡

በቡኻሪና ሙስሊም እንደተዘገበው “ለጋሽ በለገሰ ቁጥር ቀልቡ ይሰፋል፣ ደረቱም ይከፈታል፣ አንደ ጠሩሩ ሁሉ በለገሰ ቁጥር ትሰፋለታለች፡፡ ይሰፋል፣ ይላቀቃል፣ ይሰፋለታል፡፡ ደስታው ይጠነክራል፣ ደስታው ይበዛል፣ ሰደቃ ከዚህ ውጭ ሌላ ጥቅም ባይኖረው እንኳ አንድ ባሪያ ይህንኑ በመፈፀም ብዙ መጠቀም ይችላል፡፡ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ ብሏል።

وَالَّذِينَ تَبَوَّءُوا الدَّارَ وَالْإِيمَانَ مِن قَبْلِهِمْ يُحِبُّونَ مَنْ هَاجَرَ إِلَيْهِمْ وَلَا يَجِدُونَ فِي صُدُورِهِمْ حَاجَةً مِّمَّا أُوتُوا وَيُؤْثِرُونَ عَلَىٰ أَنفُسِهِمْ وَلَوْ كَانَ بِهِمْ خَصَاصَةٌ ۚ وَمَن يُوقَ شُحَّ نَفْسِهِ فَأُولَٰئِكَ هُمُ الْمُفْلِحُونَ

እነዚያም ከበፊታቸው አገሪቱን መኖሪያ ያደረጉት እምነትንም የለመዱት ወደ እነርሱ የተሰደዱትን ሰዎች ይወዳሉ፡፡ (ስደተኞቹ)ከተሰጡትም ነገር በልቦቻቸው ውስጥ ቅሬታን አያገኙም፡፡ በእነርሱ ላይ ችግር ቢኖርባቸውም በነፍሶቻቸው ላይ ሌላውን ይመርጣሉ፡፡ የነፍሱንም ንፍገት የሚጠበቅ ሰው እነዚያ እነሱ ምኞታቸውን አግኚዎች ናቸው። (አል-ሐሽር፡ 9)

 1. “ይህች ዓለም ለአራት ሰዎች ናት፡፡ አላህ ሀብት እና እውቀት ሰጥቶት በሱ ጌታውን የሚፈራና ዘመዶቹን የሚቀጥል፣ የአላህንም ሐቅ በአግባቡ የሚወጣ ይህ ትልቅ ደረጃ ላይ ነው ያለው፡፡” ብለዋል፡፡
 2. “በሁለት ነገሮች እንጂ ቅናት የለም፡፡ ይኸውም፡- አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ቁርኣንን ሰጥቶት ሌት ተቀን የሚቆምበት ሰው እና አላህ ገንዘብ ሰጥቶት ሌት ተቀን የሚለግስ ሰው፡፡” ሁለቱንም የለገሰ ሰው ምን ያህል ሊያተርፍና ሊጠቀም እንደሚችል ደግሞ ልብ እንበል፡፡
 3. አንድ ባሪያ ከነፍሱና ከሀብቱ የሚጠበቀውን የሰጠ እንደሆነ በሱና በአላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ መካከል የነበረውን ቃልኪዳን አሟልቷል፡፡ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ ብሏል፡-

إِنَّ اللَّهَ اشْتَرَىٰ مِنَ الْمُؤْمِنِينَ أَنفُسَهُمْ وَأَمْوَالَهُم بِأَنَّ لَهُمُ الْجَنَّةَ ۚ يُقَاتِلُونَ فِي سَبِيلِ اللَّهِ فَيَقْتُلُونَ وَيُقْتَلُونَ ۖ وَعْدًا عَلَيْهِ حَقًّا فِي التَّوْرَاةِ وَالْإِنجِيلِ وَالْقُرْآنِ ۚ وَمَنْ أَوْفَىٰ بِعَهْدِهِ مِنَ اللَّهِ ۚ فَاسْتَبْشِرُوا بِبَيْعِكُمُ الَّذِي بَايَعْتُم بِهِ ۚ وَذَٰلِكَ هُوَ الْفَوْزُ الْعَظِيمُ

አላህ ከምእምናን ነፍሶቻቸውንና ገንዘቦቻቸውን ገነት ለእነሱ ብቻ ያላቸው በመኾን ገዛቸው፡፡ በአላህ መንገድ ላይ ይጋደላሉ፡፡ ይገድላሉም፤ ይገደላሉም፡፡ በተውራት በኢንጅልና በቁርኣንም (የተነገረውን) ተስፋ በእርሱ ላይ አረጋገጠ፡፡ ከአላህም የበለጠ በኪዳኑ የሚሞላ ማነው? በዚያም በእርሱ በተሻሻጣችሁበት ሽያጫችሁ ተደሰቱ፡፡ ይህም እርሱ ታላቅ ዕድል ነው፡፡ (አት-ተውበህ፡ 111)

 1. ሰደቃ አንድ ባሪያ እምነቱ እውነተኛ ስለመሆኑ ማመላከቻ ነው፡፡ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሰደቃ ማስረጃ ነው፡፡” ብለዋል፡፡
 2. ሰደቃ ገንዘብን ያፀዳል፡፡ በዛዛታ፣ በመሀላ እና በውሸት በኩል ገንዘብ ላይ የሚደርሰውን ቆሻሻ ያጠራል፡፡ ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ነጋዴዎችን ሲመክሩ ይህ ንግድ ዛዛታና መሀላ የተቀላቀለበት ነው፡፡ በሰደቃ አጥሩት፡፡” ብለዋል፡፡

. . . ይቀጥላል

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here