የፆም ትሩፋቶች

0
4352

የረመዳን ወርን ትሩፋቶችና በዚህ ወር ውስጥ የሚሠሩ መልካም ተግባራትን ምንዳ እንመልከት።

1. አቡ ሁረይራ አላህ ሥራቸውን ይውደድላቸውና እንዳወሩት የአላህ መልክተኛ (ሰላትና ሰላም በሳቸው ላይ ይውረድ) ረመዳን በቀረበ ጊዜ እንዲህ ይሉን ነበር፡-

قد جاءكم شهر مبارك افترض عليكم صيامة تفتح فية ابوب الجنة و تُغلق فية أبواب الجحيم و تُغل فية الشياطين , فية ليلة خير من ألف شهر , من حُرم خيرها فقد حُرم

“የተባረከው ወር መጣላችሁ ይህን ወር እንድትፆሙት አላህ በእናንተ ላይ ግደታ አድርጓል፣ የጀነት በሮች በዚህ ወር ውስጥ ይከፈታሉ፣ የገሃነም በሮች ደግሞ ይዘጋሉ፣ ሰይጣኖችም ይታሰራሉ። በዚህ ወር ውስጥ ከአንድ ሺህ ወር የምትበልጥ አንድ ሌሊት አለች የእርሷን ጥሩ ነገር የተነፈገ ሰው በእርግጥ (ጥሩ የተባለ ነገር ሁሉ) ተነፍጓል።” (አህመድ፣ ነሳኢይና በይሃቂይ ዘግበውታል)።

2. ዐርፈጃህ እንዲህ አሉ “አንድ ቀን ዑትባህ ኢብኑ ፈርቀድ ስለ ረመዳን ሲናገር እርሱ ዘንድ ነበርኩኝ። ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ባልደረቦች የሆነ አንድ ሰው ወደ እኛ ገባ። ዑትባህ ይህንን ሰው ባየው ጊዜ አፈረና ዝም አለ። ከዚያም ሰሀባው ስለረመዳን እንዲህ በማለት ተናገረ፡- ‘ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) አንዲህ በማለት ሲነገሩ ሰምቻለሁ፡-የእሳት በሮች ይዘጋሉ፣ የጀነት በሮች ይከፈታሉ፣ ሰይጣናት ይታሰራሉ፣ መላእኩ ረመዳን እስከሚያልቅ ድረስ በየቀኑ እንዲህ በማለት ይጣራል፡- አንተ ለመልካም ነገር የምትጣደፈው ሆይ ተበሰር፣ አንተ ለመጥፎ ተግባር የምትሮጠው ሆይ ተቆጠብ’።” (አህመድና ነሳኢይ የዘገቡት ሲሆን ሰነዱም ጠንካራ ነው)

3. አቡ ሁረይራ አላህ ሥራቸውን ይውደድላቸውና እንዳወሩት የአላህ መልክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

الصلوات الخمس و الجمعة إلى الجمعة و رمضان إلى رمضان مكفرات لما بينهن إذا اجتنبت الكبائر

“አምስቱ የግዴታ ሶላቶች፣ ጅመዓ እስከ ጁመዓ፣ ረመዳን እስከ ረመዳን ከባባድ ወንጀሎችን እሰከ ተከለከልክ ድረስ በመካከላቸው ላለው ጊዜ ወንጀልን ያብሳሉ።” (ሙስሊም ዘግበውታል)

4. ከአቡ ሠዒድ አል-ኹድሪይ አላህ ሥራቸውን ይውደድላቸውና እንደተወራው ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ፡-

من صام رمضان و عرف حدودة و تحفظ مما كان ينبغى ان يتحفظ منة , كفر ما قبلة

“ድንበሮቹን አውቆ ረመዳንን የፆመ፣ መጠበቅ ከሚገባው ነገር የተጠበቀ ያለፈው ወንጀሉ ይታበስለታል።” (አህመድና በይሃቂይ ዘግበውታል)

5. አቡ ሁረይራ አላህ ሥራቸውን ይውደድላቸውና እንዳወሩት የአላህ መልክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

من صام رمضان إيماناً و إحتساباً غفر له ما تقدم من ذنبة

“ረመዳንን ከውስጡ አምኖና አስቦ የፆመ ያለፈው ወንጀሉ ይማርለታል።” (አህመድና አስሀቡ አስ-ሱነን ዘግበውታል)

አላህ (ሱ.ወ.) ይህንን የተባረከ ወር ደርሰው፣ በትክክል ፆመው በእርሱ መስፈሪያ ከሚመነዱት ያድረገን!! አሚን!!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here