ረመዳንን እንዴት እናሳልፈው?

0
8031

ሰዎች ሁሉ የፆም ጊዜ በመምጣቱ ቢደሰቱና ኸይርና በረካ እንደሚያገኙ ተስፋ ቢያደርጉም ወሩን አላህ እንደሚፈልገው በኢባዳና በኸይር ሥራ የሚያሳልፉት ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንዳውም ከረመዳን ውጭ የማይኖሩ ብዙ ከሸሪዓ ውጭ የሆኑ ነገሮች በረመዳን ሲከሰቱ ይታያል፤ ለምሳሌ ኢስራፍ (ብክነት)፣ ሶላትን ማሳለፍ፣ የቲቪ ፕሮግራሞችን በመከታተል በጣም ማምሸት፣ በጨዋታና መንገድ ላይ በመቆም ጊዜን ማባከን፤ ይህ ሁሉ የሚደረገው ድካምን ምክንያት በማድረግና የፍጡር ሰዓት እስከሚደርስ ራስን ዘና ለማድረግ በሚል ሰበብ ነው።

ሰለፎች በረመዳን የነበራቸውን ሁኔታ ብናጤነውና እንዴት ጊዜያቸውን ኸይር ሥራዎችን በመስራት ያሳልፉ እንደነበር ብናይ እነሱ የነበሩበትና እኛ ያለንበት ሁኔታ በጣም የተራራቀ እንደሆነ ባወቅን ነበር።

وكل خير في اتباع من سلف   وكل شر في ابتداع من خلف

“ኸይር ሁሉ ያለፉትን ደጋግ አቦዎች በመከትል ነው፤ ሸር ሁሉ ደግሞ ተተኪዎች በሚያመጡት አዲስ ፈጠራ ነው።”

ረመዳንን ሰለፎች እንደኖሩት እንዴት መኖር እንችላለን?


አንደኛ
፡- የፆም ህግጋቶችን መጠበቅ

የረመዳን ፆም ከኢስላም ማዕዘናት አንዱ ነው፤ ይህ ማዕዘን ደግሞ ሁለት ነገሮች ካልተሟሉ በቀር አይረጋገጥም፤

1. ፆማችንን ለአላህ ብቻ ማድረግ (ኢኽላሰ)። ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-

 إنما الأعمال بالنيات وإنما لكل إمرئ ما نوى

“ሥራዎች ሁሉ በኒያ ናቸው፤ ሰው ሁሉ የሚያኘው ያሰበውን (የነየተውን) ነው።”

2. ስንፆም ነቢያችንን (ሰ.ዐ.ወ) መከተል (አል-ኢቲባዕ)። ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-

من أحدث في أمرنا هذا ما ليس منه فهو رد

“በዚህ ዲን ከሱ ያልሆነን አዲስ ነገር የፈጠረ ሰው ተቀባይነት የለውም።”

ስለዚህ ማንኛውም ፆም ለመፆም ያሰበ ሙስሊም ሁሉ ፆሙ ትክክል እንዲሆን ዘንድ እነዚህን ሁለት ቅድመ ግደታዎች መጠበቅ ግድ ይሆንበታል።

ኢኽላስን መጠበቅ ሲባል ቀልብን ወደ አላህ (ሱ.ወ) ብቻ በማዞር የፆሙን ምንዳ ከሱ ብቻ መጠበቅ ማለት ሲሆን፤ ኢቲባዕ (መከተል) ማለት ደግሞ የፆምን ህግጋቶች አውቆና ተረድቶ በህጉ መሠረት በመፆም ፆሙ ትክክለኛና ሸሪዓውን የተከተለ እንዲሆን ማድረግ ማለት ነው።

ታዲያ አንድ ሙስሊም የፆምን ግዴታዎች፣ ፆምን የሚያበላሹ ነገሮችንና የፆም ማዕዘናትን ሳያውቅ ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ተከትሏል ሊባል ይችላልን?

ክቡር ወንድሜ! ፆምህ የነቢያችንን (ሰ.ዐ.ወ) መመሪያ የተከተለ ይሆን ዘንድ የፆምን ህግጋት እንድትማርና ያልገባህን ነገር የእውቀት ባለቤቶች እየጠየቅክ እንድትረዳ እንዲሁም የግንዛቤ መፍጠሪያ ፕሮግራሞች ላይ በመገኘት እንድትከታተል አደራ እልሃለሁ፤ ምክንያቱም አለማወቅ አንድ ሰው በፆም ጊዜ የተከለከሉ ወይም ፆምን የሚያበላሹ ነገሮች ላይ እንዲወድቅ ምክንያት ሊሆን ስለሚችል።

ይህን በተመለከተ ልናስተውላቸው የሚገቡ ጉዳዮች እንደሚከተለው በአጭሩ ተጠቅሰዋል።

አንደኛ፡-የፆም ማዕዘናት (አርካን) አራት ናቸው፤ እነሱም
 1. ኒያ (ማሰብና መወሰን)
 2. ከሚያስፈጥሩ ነገሮች መከልከል
 3. ጊዜ (ጎኅ ከመቅደዱ እስከ ፀሐይ መጥለቅ)
 4. የሚፆመው ሰው፡- ፆም የሚጠበቅበትና ቢፆም ተቀባይነት የሚያገኘው ሰው ሙስሊም የሆነ፣ ለአቅመ አዳም ወይም አቅመ ሄዋን የደረሰ(ች)፣ የመፆም አቅም ያለው(ላት) እና ፆምን ከሚከለክሉ ነገሮች (ለምሳሌ እንደ ወር አበባ…ነፃ የሆነች) መሆን አለበት።
ሁለተኛ፡-ፆምን የሚያበላሹ ነገሮች
 1. በቀኑ ክፍለ ጊዜ የግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈፀም
 2. በፍላጎቱ ፍቶተ ሥጋ (መንይ) ማፍሰስ
 3. እያወቀ መብላትና መጣጥት
 4. ከመብላትና መጣጣት ጋር ተመሳሳይ የሆነ ነገር ማድረግ፤ ለማሳሌ የምግብ መርፌ እንደ መውሰድ
 5. መታገም
 6. አውቆ ማስታወክ
 7. የወር አበባና የውልደት ደም መፍሰስ።
ሦስተኛ፡- በፆም ጊዜ የሚጠሉ ነገሮች:በፆም ጊዜ የሚጠሉ ነገሮች ብዙ ቢሆኑም አንዳንዶቹን እንደሚከተለው እንጠቅሳለን
 1. በውዱእ ጊዜ ስንጉመጠመጥና በአፍንጫችን ውሃ ስንስብ በጣም ማስገባት
 2. ሳያፈጥሩ አቀጣጥሎ መፆም
 3. ምራቅን አጠራቅሞ መዋጥ።
አራተኛ፡- ዋጅብ ከሆኑት የፆም አዳቦች
 1. ከውሸት መራቅ
 2. ከሐሜት (ጊባ) መራቅ
 3. ነገር ከማዛመት (ነሚማ) መቆጠብ
 4. በውሸት ከመመስከር መቆጠብ
 5. ሰዎችን ከማታለል መቆጠብ።
አምስተኛ፡- የሚፈለጉ የፆም አዳቦች
 1. ሱህረን (የለሊት ምግብ) ማዘግየትና ፍጡርን ማቻኮል
 2. ምላስን አላስፈላጊ ካልሆነ ትርፍ ንግግር መቆጥብ
 3. ፆመኛን ማሰፈጠር
 4. በሰደቃና በሌሎች ጥሩ ሥራዎች ወደ አላህ መቃረብ።

ክቡር ወንድሜ! ህግጋቶቹንና መስፈርቶቹን ሳይጠብቁ የረመዳንን ወር በኢማንና በሂሳብ የመፆም ደረጃ አይረጋገጥም፤ ፆም መራብና መጠማት ብቻ አይደልም፤ ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡- “ውሸት መናገርና በሱም መሥራት ያልተወ ሰው ምግብና መጠጡን መተው ለአላህ ጉዳዩ አይደልም።”

ስለዚህ የፆም ኅግጋቶችን መማርና በነሱም መስራትን አትዘንጋ፤ ይህን የሚያደርጉት ትንሾች ናቸውና።

ሁለተኛ፡- ፈርድ (ግደታ) የሆኑ ነገሮችን ጠብቆ መስራት

ሶላት የዲን ምሰሶ ስለሆነ ፆም ተቀባይነት የሚኖረው ሶለት ተቀባይነት ሲያገኝ ብቻ ነው። አንዳንድ ሰዎች ፆመኛ ሆነው እያለ ሶለትን ሲያሳልፉና ችላ ሲሉ ይታያሉ። ሶላትን በጊዜዋ ጠብቆ መስገድ ከፆም ቅድሚያ የሚሰጠው ዋጅብ መሆኑ እየታወቀ እነዚህ ሰዎች ፆመኛ ሆነው ሰላት ማሳለፍ እንዴት ሊዋጥላቸው ቻለ? ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-

العهد الذي بينا وبينهم الصلاة فمن تركها فقد كفر

“በኛና በነሱ (ካፊሮች) መካከል ድንበሩ ሶላት ናት፤ የተዋት ሰው በእውነት ከፍሯል (ክዷል)።”

ሳቢት አል-በናኒ እነዲህ ይላሉ፡- “አንድ አላህን የሚገዛ ሰው ማንኛውንም ኸይር ሥራ ቢሰራም ሁለት ሥራዎችን ማለትም ሰላትና ፆምን እሰካልያዘ ድረስ በምንም አይነት አላህን ተገዥ (ዓቢድ) ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም እነሱ (ሶላትና ፆም) ከደሙና ከሥጋው ጋር የተዋሀዱ ኢባዳዎች ናቸው።”

ሙባረክ ቢን ፉዳላ እንዲህ ይላሉ፡- “ሳቢት አል-በናኒን ታመው ልጠይቃቸው ገባሁ፤ ባልደረቦቻቸውን ያስታውሱ ነበርና ልንጠይቃቸው ስንገባ እንዲህ አሉ ‘ወንድሞቸ ሆይ! ማታ ለመስገድ ስሞክር በፊት እንደምሰግደው ልሰግድ አልቻልኩም፤ ፆምም እንደ በፊቱ ልፆም አልቻልኩም፤ ወንድሞቸ ጋር ሄጀ ከነሱ ጋር አላህን ለማውሳትም አልቻልኩም፤ ያ አላህ ከሦስቱ ነገሮች ከከለከልከኝ በዱንያ ላይ ለአንድ ሰዓት እንኳ አታቁየኝ።” ይህን ተናግረው ወዲያው ሞቱ።

አንዳንድ ሰዎች በረመዳን ፊልምና ድራማ እያታለላቸው፤ ወይም እንቅልፍና ገፍላ እያሸነፋቸው ከሶላት ሲዘነጉ ይስተዋላሉ፤ይህንን ጉዳይም ቀላል አድርገው ያዩታል፤ አላህ ዘንድ ግን ትልቅ ነገር ነው።

ሦስተኛ፡- ተራዊህ ሶላትን ጠብቆ መስገድ

ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-

من قام رمضان إيماناً واحتساباً غُفر له ما تقدم من ذنبه

“የረመዳንን ወር አምኖና ምንዳውን አስቦ የቆመ ሰው ያለፈው ወንጀሉ ይማርለታል።”

በሳኢብ ቢን ዘይድ ዘገባ እንደተገለጸው በተራዊህ ሶላት አሰጋጁ በመቶ የሚቆጠሩ የቁርኣን አንቀፆችን ያነብ ነበር፤ ቂያሙ ከመርዘሙ የተነሳ አንድኛችን ዱላውን ተደግፎ ይቆም ነበር፤ ወደ ቤታቸው ይመለሱ የነበረው ጎህ ሊቀድ አካባቢ ነበር።

በተራዊህ ሶላት ልብ ልንለውና ልንጠብቀው የሚገባው ጉዳይ ኢማሙ ሶላት እስከሚጨርስ ድረስ አብሮ መቆየትና መስገድ እንዳለብን ነው፤ የአላህ መልክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡- “ኢማሙ እሰከሚጨርስ ድረስ አብሮ የቆመ ሰው ሌሊቱን በሙሉ እንደቆመ ይጻፍለታል።” አንድ ሰው አምኖና ምንዳ ፈልጎ ረመዳንን አሳልፏል ሊባል የሚቻለው የተራዊህ ሶላትን ሳይሰላችና አላስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ሳይጠመድ በትክክል አሟልቶ ሲሰግድ ነው። በተለይም በዚህ ዘመን የሚፈታተኑ ነገሮች ስለበዙና የተለያዩ የቲቪ ቻነሎች በፍጡር ሰዓት የተለያዩ የሚያማልሉ ፊልሞችና ድራማዎችን በማቅረብ ሰዎች በወቅቱ ወደ መስጊድ እንዳንሄዱ ያዘናጋሉ፤ በዚህም ምክንያት ብዙ ሰዎች ከተራዊህ ሶላት ወደ ኋላ ይቀራሉ፤ በመሆኑም ይህን ተረድተን የረመዳን ቂያም (ተራዊህ) ሶላትን ጠብቀንና ነቅተን መሰገድ ይኖርብናል ማለት ነው።

አራተኛ፡- ዚክርና ቁርኣን መቅራት ማብዛት

አብደላህ ኢብኑ ዓባስ (ረ.ዐ) እንዲህ ብለዋል፡- “የአላህ መልክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ከሰዎች ሁሉ ቸር ነበሩ፤ በረመዳን ወር ጅብሪል ሲያገኛቸውና ቁርኣንን ሲያነብላቸው ልግስናቸው በጣም ይጨምር ነበር፤ ጅብሪል በረመዳን ወር በየሊሊቱ ያገኛቸውና ቁርኣንን ያጠኑ ነበር፤ የአላህ መልክተኛ ጅብሪል ጋር በሚገናኙ ጊዜ ኸይርን በመለገስ ከአውሎ ነፋስ በላይ ፈጣን ይሆኑ ነበር።”

አላህ (ሱ.ወ) ቁርኣንን እንዳላቀው ሁሉ የረመዳንን ጊዜያት አላቀው፤ በረመዳን ወር ቁርኣንን ማንበብ መቅራት ምንዳውን እጥፍ ድርብና ኸይሩ የበዛ አደረገው።

ዙህሪይ (አላህ ይዘንላቸውና) ረመዳን ሲገባ ሐዲስ መቅራትና ከኡለማዎች ጋር መቀመጥ ትተው ሙሉ በሙሉ ቁርኣንን ወደ ማንበብ ይዞሩ ነበር። ሱፍያነ አስ-ሰውሪይ (አላህ ይዘንላቸውና) ረመዳን ሲገባ ሁሉንም ኢባዳ ትተው ቁርአን ወደ መቅራት ይዞሩ ነበር…።

ቁርኣን መቅራታችን የበለጠ ፍሬ እንዲኖረው በማሰተንተንና በርጋታ ልንቀራ ይገባል። እንዲሁም ከነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) የመጡ አዝካሮችን ሁልጊዜ ጠብቀን ማለት አለብን፤ አዝካሮች ሸይጣንን ማባረሪያና የአላህን ውዴታ ማግኛ መንገዶች ናቸው፤ በተለይም የጠዋትና የማታ አዝካሮችንና ሌሎች ክፍት የሆኑትን በተለይም “ላኢላሀኢለላህ”፣ “አልሐምዱሊላህ”፣ “ሱብሃነላህ” እና ኢስቲግፋር ላይ መትጋት አለብን። ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) የሱብሂ ሶላት ከሰገዱ በኋላ ፀሐይ እሰከምትወጣ ድረስ በሰገዱበት ቦታ ተቀምጠው ይቆዩ ነበር።

ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ማለታቸው ተረጋግጧል፡-

من صلى الفجر في حماعه ثم قعد يذكر الله حتى تطلع الشمس ثم صلى ركعتين كانت له كأجر حج وعمرة تامة تامة تامة

“የፈጅርን ሶላት በጀመዓ ሰግዶ ፀሐይ እስከምትወጣ ድረስ አላህን እያወሳ የተቀመጠና ከዚያም ሁለት ረከዓ የሰገደ ሰው ሙሉ የዑምራና የሐጅ ምንዳ ይጻፍለታል።”

አምስተኛ፡- መለገስና መመፅወት

አነስ (ረ.ዐ) ባስተላለፉት ሐዲስ ነቢያችን “ከሰደቃ በላጩ የረመዳን ሰደቃ ነው፤” ብለዋል። በሌላም ሐዲስ ሰደቃና ፆምን በአንድ ላይ መሥራት ጀነትን እንደሚያስኝ ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ሲሉ ይገልጹልናል፡-

إن الجنة غرفاً يرى ظهورها من بطونها، وبطونها من ظهورها ! قالوا لمن يارسول الله؟ قال: لمن طيّب الكلام، وأطعم الطعام وأداما لصيام، وصلى بالليل والناس نيام

“ጀነት ውሰጥ ውጪው ከውስጥ ውስጡ ከውጭ የሚታዩ ክፍሎች አሉ” ሲሉ “አንቱ የአላህ መልክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ለማን ናት? (ለማን ነው የምትሰጠው)” ተባሉ ነቢዩም “ንግግሩን ላሳመረ፣ ምግብ ላበላና ፆምን ላዘወተረ፣ ሰዎች ተኝተው በሌሊት ለሰገደ ነች።” ሲሉ መለሱ።

በአንድ ወቅት የሚለምን ሰው ኢማም አህመድ ኢብኑ ሐንበልን ምግብ ጠየቃቸው፤ ኢማሙ ለፍጡር ያዘጋጇቸውን ሁለት ዳቦዎች አንስተው ሰጡትና ሳይበሉ አድረው ፆመኛ ሆነው ዋሉ።

የሰደቃና የልግስና አይነቶች የተለያዩ ሲሆኑ ከነሱም መካከል ለሰዎች ምግብ አዘጋጅቶ ማብላት አንዱ ነው። ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-

أيما مؤمن أطعم مؤمناً على جوع أطعمه الله من ثمار الجنة ومن سقى مؤمناً على ظمأ سقاه الله من الرحيق المختوم

“አንድ ሙእሚን የተራበን ሰው ካበላ አላህ (ሱ.ወ) ከጀነት ፍራፍሬዎች ያበለዋል፤ የተጠማ ሰውን ያጠጣም አላህ (ሱ.ወ) ከታሸገችው የጀነት ጠጅ ያጠጣዋል።”

ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-

من فطر صائماً كان له مثل أجره لا ينقص من أجر الصائم شيئاً

“ፆመኛን ያስፈጠረ ሰው ከፆመኛው ምንዳ ምንም ሳይቀንስ ያስፈጠረውን ሰው ምንዳ ያህል ያገኛል።”

ሰለፎች ፆመኛ ሆነው ለማፍጠሪያ ያዘጋጁትን ምግብ አሳልፈው ለሌሎች ይሰጡ ነበር፤ ከነዚህም መካከል አብደላህ ቢን ዑመር (ረ.ዐ)፣ ዳውድ አጣኢይ፣ ማሊክ ቢን ዲናርና አህመድ ኢብኑ ሐንበል ይገኙበታል። አብደላህ ቢን ዑመር (ረ.ዐ) ከየቲሞችና ከሚስኪኖች ጋር ካልሆነ አያፈጥሩም ነበር።

ስድስተኛ፡- በመጨረሻዎቹ አስር ቀናት ኢዕቲካፍ መግባትና ኢባዳ ማብዛት

የኢዕቲካፍ ሱና በቁርኣንና በሐዲስ የተወሳ ቢሆንም ብዙ ሰዎች ማድረግ እየቻሉ ችላ ሲሉት ይታያሉ። ሰለፎች ኢዕቲካፍ ለመግባት እጀግ ይተጉ ነበር፤ ምክንያቱም ኢዕቲካፍ በራሱ ትልቅ ምንዳ ያለው ነገር ከመሆኑም በላይ በመጨረሻዎቹ የረመዳን አስር ቀናት ስለሚደርግ ለይለተል ቀድርንም በመስጀድ ውስጥ ሆኖ በኢባዳ ለማሳለፍ እድል ስለሚሰጥም ጭምር ነው።

ኢዕቲካፍ መግባት ሌሎች እንደ ቁርኣን፣ ሶለት፣ ዚክርና ዱዓ ያሉ ኢባዳዎችን ለመስራት ያግዛል። አቡ ሁረይራ (ረ.ዐ) እንዲህ ብለዋል፡- “ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) በየረመዳኑ አስር ቀናት ኢዕቲካፍ ይገቡ ነበር፤ የመሞቻቸው አመት በሆነው የመጨረሻ አመት ደግሞ ሃያ ቀናት ኢዕቲካፍ ተቀመጡ።”

ኢዕቲካፍ የራሱ የሆነ ህግጋቶች ያሉት ስለሆነ ኢዕቲካፍ ለመግባት ያሰበ ሰው እነዚህን ህግጋቶች ማወቅና ኢዕቲካፉን በሸሪዓው መሠረት በትክክል መስራት ይገባዋል።

ሰባተኛ፡- ለይለተል ቀድርን መጠባበቅና ዱዓ ማብዛት

ፆም ዱዓን ተቀባይነት እንዲኖረው ምክንያት ከሚሆኑ ነገሮች ስለሆነ የረመዳንን ወር ሙሉ በዱዓ መጠናከር ይኖርብናል። ዱዓ ሰፊ የኸይር በርና በቀላሉ የመዳረሻውም መንገድ ነው፤ ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-

أعجز الناس من عجز عن الدعاء

“ደካማ ሰው ማለት ከዱዓ የደከመ ነው።”

በተለይም አንድ ሙስሊም የረመዳንን ወር ሌሊቶች ህያው ሲያደርግ የ “ሱሑር” ወቅትን ስለሚያገኝ ይህ የሱሑር ወቅት የተባረከ፣ ዱዓ ተቀባይነት የሚያገኝበትና ወንጀል የሚታበስበት ጊዜ በመሆኑ በዱዓ መበረታታትና ማብዛት ተገቢ ይሆና።

ክቡር ወንድሜ ሆይ! የታላቋ ሌሊት የለይለተል ቀድር ብዙ ኸይራትና ቱሩፋቶች እንዳያልፍህ ተጠንቀቅ፤ ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ስለ ለይለተል ቀድር እንዲህ ማለታቸውን አስታውስ፡-

من قام ليلة القدر إيماناً واحتساباً غُفر له ما تقدم من ذنبه

“ለይለተል ቀድርን አምኖና ምንዳዋን አስቦ የቆመ ሰው ያለፈው ወንጀሉ ተማረለት።”

ይህች ከአንድ ሺህ ወራት የምትበልጥ ሌሊት ወንጀሎች ሁሉ ምህረት የሚያገኙባትና ደረጃዎች ከፍ የሚሉባት ታላቅ ሌሊት ሰለሆነች እጅግ ልንጠባበቃትና ልንተጋባት ይገባናል፤ ምናልባትም አላህ (ሱ.ወ) የሷን ትልቅ ኸይር ሊሰጠን ተስፋ ይደረጋልና።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here