በረመዳን ለህብረተሰብ የሚሆኑ 50 ጠቃሚ ምክሮች

1
12384

በረመዳን ምን አይነት ማህበራዊ ስራዎች ማከናወን እንደምንችል ጥቆማ የሚሰጡንና የሚያግዙን ተግባራዊ ሀሳቦች እንደሚከተለዉ በዝርዝር ቀርበዋል፡፡ አብዛኛዎቹ በተለያየ ቦታ ሊተገበሩ የሚችሉ ስለሆኑ እያንዳንዱ ሰዉ አመቺ የሆነለትንና ሊተገብረው የሚችለዉን መምረጥ ያስችለዋል፡፡  እዚህ የቀረቡት ሀሳቦች በረመዳን እንዴት ማህበራዊ ስራ መስራት እንደምንችል በምሳሌነት የተነሱ

እንጂ እነዚህ ብቻ ያለመሆናቸዉን ተገንዝበን ከምንኖርበት ተጨባጭ ጋር አስፈላጊና ተስማሚ የሆኑ ሌሎች ተግባሮችን ፈጥረን መስራት እንደሚጠበቅብን ማስታወስ እንፈልጋለን፡፡

ከታች የተዘረዘሩት ሀሳቦች ለመተግበር አመቺ ይሆን ዘንድ በየዘርፉ የተሰበሰቡ ሲሆኑ በቤት፣ በመንገድ ላይ፣ በመስጂድ፣ በሰፈር፣ ለታዋቂ ሰዎች፣ ከሰፊዉ ህብረተሰብ ጋር፣ ከክበቦች ጋር፣ ለተለያዩ ድርጅቶች፣ ሴቶች፣ ወንድና ሴት፣ ህፃናት፣ ለተማሪዎችና በማህበራዊ ድረ-ገፅ ለምናዉቃቸዉ ሁሉ እንዴትና በምን መልኩ ሃሳባችንን ለማድረስ በሚያመች መልኩ ተቀምጠዋል፡፡

የህብረተሰባዊ ስራ አስፈላጊነት

ዛሬም ቢሆን እኛ ሙስሊሞች ህብረተሰቡ ዉስጥ ገብቶ ስለመስራት አስፈላጊነትና አሳሰቢነት በቅጡ የተገነዘዘብን አይመስልም፡፡ ኢስላማዊ ስራ ማለት የሰዉን ልጅ ወደ መልካም ነገር፣ ልቅና፣ መልካም እሴትና መርህ እንዲሁምመልካም ስነ ምግባር መጣራት ነዉ፡፡ በተጨማሪም ለሰዉ ልጆች የሚቻለዉን ሁሉ ቁሳዊና ሞራላዊ ድጋፍ ማድረግ ኢስላም የመጣበት አለማ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ ይላል፡-

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا ارْكَعُوا وَاسْجُدُوا وَاعْبُدُوا رَبَّكُمْ وَافْعَلُوا الْخَيْرَ لَعَلَّكُمْ تُفْلِحُونَ
“እናንተ ያመናችሁ ሰዎች ሆይ! (በስግዴታችሁ) አጎንብሱ፣ በግንባራችሁም ተደፉ፣ ጌታችሁንም ተገዙ፣ በጎንም ነገር ሥሩ፣ ልትድኑ ይከጀልላችኋልና፡፡” (አል ሃጅ፤ 77)
የአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንድህ ብለዋል፡-
 أَحَبُّ النَّاسِ إِلَى اللَّهِ أَنْفَعُهُمْ لِلنَّاسِ ، وَأَحَبُّ الأَعْمَالِ إِلَى اللَّهِ سُرُورٌ تُدْخِلُهُ عَلَى مُسْلِمٍ ، أَوْ تَكْشِفُ عَنْهُ كُرْبَةً ، أَوْ تَطْرُدُ عَنْهُ جُوعًا ، أَوْ تَقْضِي عَنْهُ دَيْنًا ، وَلأَنْ أَمْشِيَ مَعَ أَخٍ لِي فِي حَاجَةٍ ، أَحَبُّ إِلَيَّ مِنْ أَنْ أَعْتَكِفَ فِي هَذَا الْمَسْجِدِ يَعْنِي مَسْجِدَ الْمَدِينَةِ شَهْرًا ، وَمَنْ كَفَّ غَضَبَهُ سَتَرَ اللَّهُ عَوْرَتَهُ ، وَمَنْ كَتَمَ غَيْظَهُ ، وَلَوْ شَاءَ أَنْ يُمْضِيَهُ أَمْضَاهُ ، مَلأَ اللَّهُ قَلْبَهُ يَوْمَ الْقِيَامَةِ رِضًا ، وَمَنْ مَشَى مَعَ أَخِيهِ
فِي حَاجَةٍ حَتَّى يُثْبِتَهَا ، أَثْبَتَ اللَّهُ قَدَمَيْهِ يَوْمَ تَزُولُ الأَقْدَامُ 
ከሰዎች አላህ ዘንድ በጣም ተወዳጁ ለሰዎች በጣም ጠቃሚ የሆነዉ ነዉ፤ አላህ ዘንድ በጣም ተወዳጁ ስራ ሙስሊምን ማስደሰት፣ ጭንቀቱን ማስወገድ፣ እዳዉን መክፈልና አብለቶ ረሀቡን ማስወገድ ናቸዉ፡፡ በመዲና መስጂድ ወር ኢዕቲካፍ ከማድረግ ወዴ አንድ ችግር ካጋጠመዉ ወንድም ዘንድ መሄድ ለእኔ በላጭና የተወደደ ነዉ፡፡ ቁጣዉን የተቆጣጠረ ሰዉ አላህ ነዉሩን ይሸፍንለታል፡፡ መፈፀም እየቻለ ቁጭቱን ዉጦ ዝም ያለ የቂያማ ቀን አላህ ቀልቡን በተስፋ (ረጃዕ) ይሞላለታል፤ ሀጃ (ችግር) ወዳለበት ወንድሙ ሄዶ ያፅናና ሰዉ ድልጫ በበዛበት ትንሳዔ ዕለት  አላህ እግሩን ያፀናለታል።”(ጦበራኒ)

ለእስልምና ለመስራት የዕቅድ አስፈላጊነት

ለአለማዊ ህይወታችን፣ ለንግዳችንና ለነገሮቻችን በሙሉ ዕቅድ ማዉጣት ሰዉ የመሆን ግዴታችን እንደሆነ ሁሉ ወደአላህ ጥሪ ለማድረግና ለሰዎች መልካም ነገርን ለማድረስ ሸሪዓዊ ግዴታ እናደለብን መገንዘብ ይገባናል፡፡  ሸሪዓዊ መርሁም እንዲህ ይላል፡- “ግዴታ የሆነ ነገር የሚሟላዉ በእርሱ ብቻ የሆነ ነገር ሁሉ ግዴታ ነዉ፡፡” የአላህን ዲን (እስልምናን) በምድር ላይ የበላይ ላመድረግና መልካም ነገሮችን ሁሉ ለሰዉ ልጆች ለማድረስ ቅሮት የሌለዉ ግዴታ ስለሆነ ለእስልምና ሊሰራ በሚነሳ ላይ ሁሉ በዕቅድ መመራት የግድ ይሆንበታል፡፡

ስለዚህ ለእስልምና እሰራለሁ በሚል ሰዉ ላይ ከረመዳን ወር ታላቅ ፋይዳ ይዞ ለመዉጣት ቁጭ ብሎ ዕቅድ ማዉጣት  ግዴታ ይሆንበታል፡፡ ዕቅዱን በሚያወጣበት ጊዜ መጀመሪያ ግለፅ ግብ ማስቀመጥ አለበት፡፡ ግቡን እዉን የሚያደርግባቸዉን ስልቶች፣ እያንዳንዱ ስልት ተግባራዊ መሆኑን ማረጋገጫና መለኪያ፣ ስራዎቹ የሚፈፀሙበት ግልፅ የሆነ የጊዜ ሰሌዳ፣ ሀላፊነቱን የወሰደዉ አካል፣ የጠቅላላ ዉጤት መለኪያና የመከታተያ ዘዴዉ በትክክል የተቀመጠ መሆን ይገባዋል፡፡ ዕቅዱ መወጣት ያለበት የረመዳን ወር ከመድረሱ ረዥም ጊዜ በፊት መሆን አለበት፡፡ ለአንድ ነገር ጊዜዉ ከመድረሱ በፊት ከታቀደ በርካታና ሁሉን አቀፍ ጥቅም ያስገኛል፡፡

ዝምድናን መቀጠል

1. የተከበረዉ የረመዳን ወር ሲገባ ዘመዶችህን ቀድመህ የእንኳ አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፍላቸዉ፡፡ መልዕክቱ በአንድ አይነት መንገድ ብቻ መሆን የለበትም፡፡

  • ለወላጆችህ ከሆነ በአካል ቢሆን ጥሩ ነዉ ካልሆነ ግን በቀጥታ በስልክ ደዉለህ እነሱን እንኳን አደረሳችሁ ማለት፡፡ መልዕክት አድራሽ ባትጠቀም ይመረጣል፡፡
  • ለወንድምና ለእህቶች (ሸቂቆች) እና አማቾች በስልክ ደዉሎ እንኳን አደረሳችሁ ማለት አማራጭ የሌለዉ ስልት ነዉ፡፡
  • ለቅርብ የስጋ ዘመዶች፣ ጓደኞችና ሌሎች ሁሉ ምንም እንኳን በአካል የተመረጠ ቢሆንም በስልክ ሚሴጅ፣ ኢሜል፣ ፌስቡክ እና ዘመኑ ምቹ ባደረጋቸዉ የመልዕክት ማስተላለፊያ ሁሉ የእነኳን አደረሳችሁ መልዕት ማስተላለፍ እዳትረሳ።

2. ከቤተሰቦችህ ጋር የምታፈጥርበት ቀጠሮ ይኑርህ። በዚህ ኢፍጣር ፕሮግራም ወላጆችህ፣ ወንደምና እህቶችህ እስከ ቤተሰቦቻቸዉ ታዳሚ ብታደርጋቸዉ መልካም ነዉ፡፡

3. ከሚስትህ ቤተሰቦች ጋር የምታፈጥርበትም ቀጠሮ ይኑርህ። በዚህ ኢፍጣር ልክ ከቤተሰቦችህ ጋር ስታፈጥር እንደነበረዉ ደስ ይበልህ፡፡ ቦታዉ እዳመችነቱ ካነተ ወይም ከነሱ ጋር ሊሆን ይችላል፡፡

4. (ስለ ፆም) ትንንሽ ኪታቦች፣ ፓፕሌቶችና መጣጥፎች ለወዳጅ ዘመዶችህ በስጦታ መልክ አበርክትላቸዉ፡፡

5. የምተችለዉን ያክል ሰዉ ሰብስበህ ስለ ረመዳን ፆም ህግጋት እና ስነስርዓት አስተምራቸዉ፡፡

6. ልጆችህ ከእኩዮቻቸዉ የዘመድ ልጆች ጋር ግንኙነት እንዲኖራቸዉ አድርግ ምክንያቱም የዝምድናን አስፈላጊነት ከለጋ እድሜያቸዉ ጀምሮ እንዲያቁት ያስፈልጋልና፡፡

7. ከወላጆችህ፣ ከሚስትህና ከልጆችህ ቀጥሎ በሰደቃህና በዘካህ ድሃ የቅርብ ዘመዶችህን እንዳትረሳቸዉ፡፡

8. ድሃ ዘመድህ ለኢፍጣር ከጠራህ በስጦታ መልክ የምትችለዉን ይዘህ ጥሪዉን አክብረህ ሂድ፡፡

9. በኢፍጣር ወቅት መዘንጋት የሌለባቸዉን ስነስርዓት ጠብቅ። አላስፈላጊ የተቃራኒ ፆታ ቅልቅል፣ ከተራዊህ ሶላት መሳነፍ፣ አዝካር መሳዕ(የማታ ዚክር) መርሳት እና መግሪብና ኢሻ ሰላትን በመስጂድ ጀምዓ አለመስገድ መጠንቀቅ አለብህ፡፡

10. ረመዳን ከመግባቱ ከስምንት እና አስር ቀን በፊት ስለ ፆም ይዘት ያላቸዉ ብሮሸሮችና መፅሀፍት ለጎሮቤትህ ከቻልክም ከስጦታ ካርድ ጋር አበርክተለት፡፡

11. ልጆችህ ከጎረቤት ልጆች ጋር ሆነዉ ጊቢያችሁንና አካበቢያችሁን የረመዳንን መመምጣት በሚስታዉሱ ፖስተሮች በመለጣጠፍ እንዲያሳምሩት አድርግ፡፡

12. የረመዳንን መምጣት ምክንያት በማድረግ የምትኖረዉ አፓርታማ ላይ ከሆነ የበረንዳ መብራት ወይም  ቪላ ከሆነ የመንገድ መብራት ከሌለ መብራት በመዘርጋት ለሁሉም አገልግሎት መስጠት መልካም ነገር እንዳስታዉሱ አድርግ፡፡

13. ቢያንስ በረመዳን አንድ ጊዜ ከጎረቤቶች (ሙስሊም ያልሆኑ ቢሆንም) ጋር የአፍጠር ፕሮግራም እንድኖርህ ዕቅድ ይኑርህ የዚህ አይነት ተግባር እንዲለመድና ሌሎችም እንዲተገብሩት ጥረት አድርግ፡፡

14. ሚስትህ ሴት ጎረቤቶቿን ሰብስባ ቁርዓን መቅራት፣ ተጅዊድ እና የተለያዩ ፆምን የሚመለከቱና ሌሎችም ዲናዊ (ሀይማኖታዊ) ትምህርቶችን የሚማማሩበት ሁኔታን እንድታመቻች አድርጋት፡፡

15. የጎረቤት ልጆችን ወላጆቻቸዉን አሳዉቀህ ቁርዓን እንዲቀሩና እንዲሀፍዙ አድርገህ መጨረሻ ላይ ቀላል ሽልማት አዘጋጅላቸዉ፡፡

16. ጎረቤቶችህን አስተባብረህ “ሻንጣ ረመዳን” የረመዳን ስጦታ ለሚስኪኖችና ለድሆች አከፋፍል፡፡

17. ረመዳንን ምክንያት በማድረግ የተለያዩ ስጦታዎች ለጎረቤት በማበርከት የመሰጣጠትን ባህል ለጎረቤቶችህ አስተምር፡፡

18. ለፈጅር ሰላት ወደ መስጂድ ስትሄድ ጎረቤትህ ጀምዓ እንዳያመልጠዉ ቀስቅሰዉ፤ ምንአልባት ስሁር በልቶ እንቅልፍሊያሸንፈዉ ይችል ይሆናልና፡፡

19. ረመዳንን ምክንያት በማድረግ ከጎረቤቶችህ ጋር ሆነህ በአካባቢያችሁ ያለን የፅዳት እና ተመሳሳይ ችግር ካለ በጋራ ሆነህ መፈትሄ ለማበጀት ጥረት አድርግ፡፡

20. በረመዳን ብቻ ለሚሰገደዉ የተራዊህ ሰላት ተልቅ ትኩረት መስጠት፤ በአንድ መስጂድ ለጀምዓ የሚሰባሰበዉን ሰዉ ሁሉ የተራዊህ ሰላትን በንቃትና በብርታት መስገድ እንዲችል የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ማበረታት ያስፈልጋል፡፡ በተርዊህ ሰላት ወቅት የሚቀራዉን የቁርዓን መጠን በተመለከተ ጀመዓዉን (የአካባቢውን ሰጋጆች) በማማከር ስምምነት ላይ መደረስ አለበት፡፡

21. ከሰላት ተራዊህ ጋር በማያያዝ ፆሞ ዉሎ ለሰላት መስጅድ ለሚመጣዉ ሰዉ ያለበትን ሁኔታ ያገናዘበ፤ ኢማኑን የሚጨምርለት እና ከአላህ ጋር ያለዉን ግንኙነት የሚያጠናክርለት የተመረጡ ፕሮግረሞችን በማቀድና ቀድሞ ለሰዉ በማሳዎቅ ሁሉንም ቀን መጠቀም፡፡

22. የመስጂድ ኸጢብ ከሆንክ ከሻዕባን ወር ጀምሮ የምታድረገዉ ኹጥባ የረመዳን ወር ለመድረስ ሰዎችን የሚያጓጓ መሆን ይኖርበታል፡፡ የአላህ መልካም ባሮች ረመዳንን ለመቀበል ያደርጉት የነበረዉን ዝግጅት፣ በረመዳን ከቁርዓን ጋር ሊኖር ስለሚገባ ባህሪና በረመዳን ይዧቸዉ ስለሚመጣዉ መልካም ነገር ሁሉ እንዲያገኝ አላህን መማፀን እንዳለበት የሚያስገነዝብ መሆን ይጠበቅበታል።

23. አንተ ራስህ ኸጢብ ካልሆንክ የመስጂዱ ኢማም ረመዳንን በተመለከተ ኹጥባ እንዲያዘጋጁና ህዝቡ በሚገባዉ ቋንቋ  እንዲተረጎም አድርግ፡፡

24. መስጂዱን ማፅዳትና የተለያዩ ችግሮች ካሉ ለመፍታተት መሞከር። ረመዳን ከመግባቱ ቀድሞ የመስጂዱን ዉስጥና ጊቢዉን ማፅዳት፣ የመብራት ችግር ካለ ማስተካካል፣ የዉሃ እጥረት ካለ ዉሃ ማቅረብ እና ሌሎችም ችግሮች ተቀርፈዉ መስጂዱ ለሰጋጆች አመቺ እንዲሆን ማድረግ፡፡ በመሰረቱ እነዚህን ነገሮች መስራት በሌላም ጊዜ ግዴታችን ቢሆኑም በረመዳን በጣም ግዴታነቱ የበረታ መሆኑን መገንዘብ አለብን፡፡

25. ዉጫዊ የመስጅዱን ክፍል ማስዋብ። አላስፈላጊ የገንዘብ ብክነት በሌለበት ሁኔታ የመስጅዱን ዉጫዊ ክፍል በተለይ ሚናራዉን በኤሌክትሪክ መብራትና በመሳሰሉት ዉብ ማድረግ አስፈላጊ ነዉ፡፡

26. ወደ መስጂዱ በሚያመሩ መንገዶች ላይ የመንገድ መብራት ከሌለ ለሰላት በምሽት ጀምዓ የሚመጣ ሰዉ እንዳይቸገር መብራት ማድረግ፡፡

27. ረመዳንን የሚያስታዉሱና አስተማሪ የሆኑ በመስጂድ ግድግዳና አጥርላይ የሚለጠፉ ፖስተሮችን አዘጋጅቶ መለጠፍ፡፡

28. ስለረመዳን ልዩ እትም ይዘት ያለዉ መፅሄት ማዘጋጀትና በየቢሮዉና በየሰዉ ቤት እንዲበተን ማድረግ፡፡

29. በመስጂዱ የጋራ የኢፍጣር ፕሮግራም ማዘጋጀት። የኢፍጣሩን ፕሮግራም ቀድሞ ለመስጂዱ ጀመዓዉ ማሳወቅ፡፡ የፕሮግራሙ አላማ መብላትና መጠጣት ሳይሆን በጋራ በሚያፈጥሩበት ጊዜ በመካከላቸዉ ዉዴታንና ኢስላማዊ ወንድማማችነት ለማምጣት መሆኑ ግምት ወስጥ እንዲገባ ማድረግ፡፡

30. በመስጂድ አካባቢ ለሚገኙ ሚስኪንና ድሆች ሰዎችን አስተባብሮ እንዲረዱ ማድረግ፡፡ በሚከተለዉ መልኩ ሊሰራ ይችላል::

ከጎረቤት ጋር

መስጂድ መሰረት አድርጎ ሊሰሩ የሚችሉ ስራዎች

  • በገንዘብም ሆነ በአይነት አስተዋፅዖ ሊያደርጉ የሚችሉ ሰዎችን ማስተባበር
  • ወጣቶች አስፈላጊ ነገሮችን በመሰብሰብና ለሚገባቸዉ ድሃና ሚስኪኖች እንዲያከፋፍሉ ማድረግ
  • በሀላፊነት ሰዎችን የሚያስተባብር አንድ ልምድ ያለው ሰዉ መኖር አለበት
  • አንዳንድ በክፍያ መሰራት ያለባቸዉን ስራዎች ለሚሰሩት ተገቢ ክፍያ መፈፀም አለበት

31. በመስጂድ ዉስጥ ፆመኞችን በምናስፈጥርበት ጊዜ መስጂዱ ዉስጥ የምግብ ማብሰያ ከሌለ ምግብ ቤት አስርቶ እንዲመጣ ማድረግ፡፡

32. በመስጂድ ዉስጥ ፆመኞች የሚያፈጥሩበት በቂ ቴምር ማዘጋጀት

33. በአንድ መስጂድ የሚሰግዱትን የጀምዓ አባለት ሁሉ “ሻንጣ ረመዳን” (የረመዳን ስጦታዎች) መሽሩዕ አዘጋጅቶ እንዲሳተፉ ማድረግ፡፡ ይህ መሽሩዕ (ፕሮግራም) በመስጂዱ አካባቢ ለሚኖሩ ችግረኞች በወርሀ ረመዳን በፍፁም ስለ መሰረታዊ አስፈልጎታቸዉ (ምግብ) እዳያስቡ ማድረግ እንደሚቻል ሰርቶ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ እንደ አስፈላጊነቱ ሻንጣዉ (ስጦታው) ዘይት፣ ሩዝ፣ ጤፍ፣ ዱቄት… ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ፕሮግራም ረመዳን ከመድረሱ በፊት በአካባቢዉ ያሉ ድጋፍ የሚስፈልጋቸዉን ሰዎች ስም ዝርዝር፣ ሰዎችን አስተባብሮ ሻንጣዉን ማዘጋጀትን የመሳሰሉት ነገሮች መታቀድ ይኖርባዋቸል፡፡

34. የመስጂዱን አስተዳደር በማስፈቀድ የረመዳን ጥያቄና መልስ ዉድድር አዘጋጅቶ መጨረሻ ሽልማት መስጠት፡፡

ሁሉንም በመስጂድ የሚሰግዱትን የጀምዓ አባላት ሊያሳትፍ በሚችል መልኩ ከቁርዓን፣ ከሀዲስ፣ ከፊቅህ፣ ከሲራ እና ሌሎችንም እስልምናን እና ሙስሊሞችን የሚመለከት ቀለል ያለ ጥያቄ ማዘጋጀት፡፡

  • ጥያቄዉ በቦርድ ላይ ከተለጠፈ ወይም ከተበተነ በኋላ የመልስ መስጫ ቦታ ጊዜ በግልፅ ማስቀመጥ፡፡
  • ለአሸናፊዎች የሚሰጠዉን የሽልማቱን አይነት ማሳወቅ፡፡ ተሳታፊዎችን የሚያበረታታ ጥሩ የሚባል ሽልማት ማዘጋጀትና ሽልማቱ የሚሰጥበት ቀን ሞቅ ባለ መልኩ ቢዘጋጅ ጥሩ ነዉ፡፡

35. ረመዳን ሊጀመር አንድ ሳምንት ሲቀረዉ በመስጂዱ ኢማም ወይም በሌላ ሰዉ ስለ ፆም መሰረታዊ ህግጋቶችና ስነስርዓቶች በተከታታይ መቅረብ አለበት፡፡ ተሳታፊዎችም ጥያቄ እንዲጠይቁ መደረግ ይኖርበታል፡፡

36. የመስጂዱን አስተዳደር በመጠየቅ ቁርዓን (ሙስሀፍ) በትልቁ፣ በመካከለኛዉ፣ በአነስተኛዉ መጠን እና የቁርዓንማንበቢያ (አትሮንስ) በበቂ ሁኔታ መኖሩን አረጋግጠህ እጥረት ካለ ለማሟላት ጥረት አድርግ፡፡ በተጨማሪም ቆመዉ መስገድ ለማይችሉ ታማሚዎችና የዕድሜ ባለፀጋ አባቶች ቁጭ ተብሎ ሊሰገድባቸዉ የሚችሉ ወንበሮችን ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡

37. መስጂዱ ለሴቶች መስገጃ ከሌለዉ ቀድሞ በበቂ ሁኔታ ማዘጋጀት እና ልክ እንደወንዶቹ የመስጊዱ ክፍል የሚያስፈልገዉን ሁሉ ማሟላት፡፡

38. በርካታ ሰዉ ተሳታፊ እንዲሆን በተለይ ወጣቶች ከቁርዓን ጋር ያላቸዉን ግንኙነት እንዲያጠናክሩ ስለሚያበረታታ ለሁሉም የዉድድር አይነቶች ጥሩ ሽልማት ማዘጋጀት፡፡

መጀመሪያ ደረጃ– ረዥም ሚባሉት ሱራዎች እንዴ ከ4-6 ሱራዎች- ተዉባ፣ ዩኑስ፣ ሁድ፣ ዩሱፍና ወዘተ

ሁለተኛ ደረጃ–  ከመካከለኛ ርዝመት ካላቸዉ ከ3-4 ሱራዎች- ሹራ፣ ዙኽሩፍ፣ ዙመር፣ ሷድ ወዘተ

ሶስተኛ ደረጃ – ሱረት ሙሀመድ፣ ፈትህ፣ ሁጁራት፣ ዛሪያት፣ ሀዲድ፣ ሙጃደላ ወዘተ

39. ግቢ ማዘጋጀት ምክንያቱም የአማኞችን ከመፅሃፍ እና ከንባብ ጋር ያላቸዉን ግንኙነት ለማሻሻል ስለሚረዳ ነዉ፡፡

40. የመስጂዱ ጀመዓ ረመዳን ከመግባቱ በፊት ተውበት (መፀፀት) ማድረግ እደሚገባዉ በተደጋጋሚና የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ማስታወስ በጣም አስፈላጊ ነዉ፡፡ የአላህ መልካም ባሮች ረመዳን ስድስት ወር ሲቀረዉ ጀምሮ ዝግጅት ያደርጉ እንደነበር በማዉሳት ሁሉም ሰዉ ከሌላ ሰዉ ጋር የተቀያየመበት ምክንያት ካለ ለአላህ ብሎ ይቅርታ ተደራርጎና ተፀፀቶ በንጹህ ቀልብ ረመዳንን እንዲፆም ማስቻል፡፡

41. የረመዳን ጨረቃ የታየችበት የመጀመሪያዉ ፆም የሚያዝበት ቀን በመስጂድ ተገኝተህ ለመስጂዱ ጀመዓ አባላትየእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትህን በማስተላለፍ የደስታ ተካፋይ ሁን፡፡

42. የሻዕባንን የመጨረሻ ቀን ጠብቀህ ለመስጂድ ጀመዓዎች በሙሉ ምርጥ የሞባይል የፅሁፍ መልዕት አዘጋጅተህ ላክላቸዉ፡፡

43. የፈጅር ሰላት ከተሰገደ በኋላ ከ5-7 ደቂቃ የሚፈጅ እጥር ምጥን ያለ የሰጋጆችን ቀልብ የሚለዝብና ኢማን የሚጨምር ፕሮግራም እንዲኖር ዕቅድ ማዉጣት፡፡

44. የሌሊት (ተሀጁድ) ሰላትን በተመለከተ በሰንተኛዉ ቀን እንደሚጀመር፣ ተጀምሮ የሚያልቅበት ሰዓት፣ ኢማም፣ በስንት ጁዝ እንደሚሰገድ ከመስጂዱ ጀመዓ ጋር ሹራ ተደርጎ በስምምነት በግልፅ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

45. ከመስጂዱ አስተዳደር ጋር በመስማማት ኢዕቲካፍ ረመዳን ማቀድ። በተለይ የመስጂዱ መዕተኪፎች በቁጥር ብዙ ከሆኑ መሪ (አሚር) እንዲኖራቸዉ ማድረግ፣ የኢዕቲካፍ ፕሮግራም ማዉጣትና ፕሮግራሙ በአግባቡ እንዲተገበር ጥረት መደረግ አለበት ምክንያቱም የረመዳን ኢዕቲካፍ በአመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚገኝ አጋጣሚ ስለሆነ ኢዕቲካፍ ያደረጉ ሁሉ ሙሉ ጊዜያቸዉን በዒባዳ በማሳለፍ ከአላህ ጋር ያላቸዉ ቅርበት ጨምሮ የሚፈልጉትን አግኝተዉ መዉጣት አለባቸዉ፡፡

46. በጀመዓ ዑምራ ረመዳን ላይ ማቀድ። በአንድ መስጂድ የሚሰግዱ የጀመዓ አባለት አብረዉ ሆነዉ ረመዳን ከመድረሱ በፊት ለዑምራ የሚያስፈልገዉን ወጪ አዘጋጅተዉ በጀመዓ ዑምራ ረመዳን መፈፀም፡፡

47. መሽሩዕ ቁርዓን- አብዛኛዉ ሰዉ በረመዳን መስጊድ ሲገባ ቁርዓን ይቀራል፡፡ ይህንን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ቁርዓን ማንበብ የሚችሉ ሁሉ ቁርዓን አስተካክለዉ መቅራት እንዲችሉ አመቺ የሆነ ፕሮግራም በማዉጣት በረመዳን በርካታ ሰዎች ቁርዓን አስተካክለዉ እንዲቀሩ ማመቻቸት ትኩረት ሊሰጠዉ የሚገባ ስራ መሆኑን ቢታሰብበት መልካም ነዉ፡፡

48. በተራዊህ ሰላት ቁርዓን የሚከተምበትን ቀን ለመስጂዱ ጀመዓ ቀድሞ በማሳዉቅ በዕለቱን ቁርዓን (ኺትማ) ኪትማ ዱዓ ተካፋይ እንዲሆኑና በዕለቱ ለየት ያለ ፕሮግራም በማዘጋጀት ለታዳሚዎች ስለ ቁርዓን እንዲያዉቁ የሚያስችል ፕሮግራም መስራት፡፡

49. ሰላተል ጀመዓ አዘዉትረዉ በመስጂድ ከሚሰግዱት የጀምዓዉ አባላት መካከል በረመዳን የፈጅርን ሰላት ከሰገዱ በኋላ ፀሀይ እስከምትወጣ (ኢሽራቅ) ድረስ በመስጂድ የተለያዩ ዒባዳዎችን እየሰሩ ቆይተዉ ሁለት ረከዓ ዱሃ ሰላት ሰግደዉ በሀዲስ እንደተነገረዉ የሀጅና የዑምራ ምንዳን ማግኘት እንደሚችሉ ከማስታወስ በዘለለ በተግባር እንዲሰራ መመከር፡፡ የአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፡-

 من صلى الغداة في جماعة، ثم قعد يذكر الله حتى تطلع الشمس، ثم صلى ركعتين كانت له كأجر حجة وعمرة تامة تامة تامة

የማለዳን (ፈጅርን) ሰላት በጀምዓ የሰገደና ፀሀይ እስከምትወጣ ድረስ አላህን እያስታወሰ (እየዘከረ) የተቀመጠና ከዚያ ሁለት ረከዓ ሰላት የሰገደ ሙሉ የሆነ ሐጅና ዑምራ እዳደረገ ይቆጠርለታል፡፡” (ቲርሚዚይ ዘግበዉታል)

50. የረመዳን ወር ግማሽ ከሆነ ጀምሮ የዒድ አልፈጥር በዓልና የዒድ ሰላት በደንብ መታቀድ ይኖርበታል፡፡ የዒድ ሰላት አላማዉ በአንድ ከተማ ወይም አካባቢ የሚኖሩ ሙስሊሞች አንድ ላይ ተሰብስበዉ የሚሰግዱት ሰላት ስለሆነ የዒድ ሰላት የሚሰገድበትን ቦታ፣ ኹጥባና የመሳሰሉት አስፈላጊ ነገሮች ቀድሞ መዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡ በተጨማሪም የዒድ በዓል ዕለት ሁሉም ሙስሊሞች ተደስተዉ እንዲዉሉ የሚያስፈልጉ ነገሮች ሁሉ እነዲሟሉ በቅድሚያ ዕቅድ ዉጥቶ መሰራት አለበት፡፡

 

ፅሁፉን በድምፅ ለማድመጥ ሊንኩን ይጫኑ፡፡ ለሌሎችም ያስተላልፉ!

http://bit.ly/2I0q5d9


 

1 COMMENT

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here