በረመዳን የሚከሰቱ ብክነቶች

0
9470

አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ በተከበረው ቁርኣኑ ካወገዛቸውና በግልጽና ቀጥተኛ በሆነ መልእክት ከከለከለን ወንጀሎችና ጥፋቶች መካከል አንዱ ማባከን ነው፡፡ ማባከን የአላህን ሱብሃነሁ ወተዓላ ፀጋ ከግምት ውስጥ አለማስገባት፣ ስጦታውንና ልግስናውን አለማክበር እንዲሁም የእስልምናን ድንጋጌ በሚፃረር መልኩም ገንዘብን ከአላህ ትእዛዛት ውጭ ለሆነ ነገር መለገስ ነው፡፡ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ ብሏል፡-

وَكُلُوا وَاشْرَبُوا وَلَا تُسْرِفُوا ۚ إِنَّهُ لَا يُحِبُّ الْمُسْرِفِينَ

“ብሉም፤ ጠጡም፤ አታባክኑም፡፡ እርሱ አባካኞችን አይወድምና፡፡” (አል-አዕራፍ፡31)

በሌላ የቁርኣን አንቀጽም

كُلُوا مِن ثَمَرِهِ إِذَا أَثْمَرَ وَآتُوا حَقَّهُ يَوْمَ حَصَادِهِ ۖ وَلَا تُسْرِفُوا ۚ إِنَّهُ لَا يُحِبُّ الْمُسْرِفِينَ

ባፈራ ጊዜ ከፍሬው ብሉ፡፡ በአጨዳውም ቀን ተገቢውን (ዘካ) ስጡ፡፡ አታባክኑም፡፡ እርሱ አባካኞችን አይወድምና፡፡ (አል-አንዓም፡ 141) ብሏል፡፡

ሙስሊሞች እንዳያባክኑ ሲያስስጠነቅቅም እንዲህ ብሏል

وَآتِ ذَا الْقُرْبَىٰ حَقَّهُ وَالْمِسْكِينَ وَابْنَ السَّبِيلِ وَلَا تُبَذِّرْ تَبْذِيرًا

إِنَّ الْمُبَذِّرِينَ كَانُوا إِخْوَانَ الشَّيَاطِينِ ۖ وَكَانَ الشَّيْطَانُ لِرَبِّهِ كَفُورًا

ለዝምድና ባለቤትም መብቱን ስጥ፡፡ ለምስኪንና ለመንገደኛም (ስጥ)፡፡ ማባከንንም አታባክን፡፡ አባካኞች የሰይጣናት ወንድሞችናቸውና፡፡ ሰይጣንም ለጌታው ብርቱ ከሓዲ ነው፡፡ (አል-ኢስራእ፡26-27) ፡፡

የተከበረው የረመዳን ወር አላህን አብዝተን የምንፈራበት፣ በብዛት የምንለግስበት፣ ደግ የምንውልበት፣ የእዝነት፣ የምህረትና የአላህ ውዴታ ወር ነው፡፡ ሆኖም ግን ከሌላው ወር በተለየ መልኩ በዚህ ወር ውስጥ አንዳንድ ሙስሊሞች በእጅጉ ሲያባክኑና ሲያጠፉ እናስተውላለን፡፡ ከምግብ፣ ከመጠጥ፣ ከጣፋጭ ነገርም ይሁን ከሌላ እጅግ ምርጥና ውድ የሆኑትን ነገሮች ሲገዙና ሲጠቀሙ እናያለን። ይህም ረመዳንን የምግብና በምግብ ዙሪያ በሚደረጉ ነገሮች የመፎካከሪያ መድረክ አስመስሎታል፡፡ የሚገርመው አብዛኞቹ ሰዎች ከሚገዙትም ሆነ ከሚሰሩት የሚጠቀሙት ጥቂቱን ብቻ ነው፡፡ በላጩ እጅ ግን ይበላሻል፣ ተርፎና ባክኖ በቆሻሻ ገንዳዎች ውስጥ ይጣላል፡፡ በሌላ በኩል ግን ብዙ የሙስሊም ቤተሰቦች የእለት ጉርሳቸውን እንኳን የሚሸፍንላቸው አጥተው በርሃብና በችግር ይሰቃያሉ፡፡

በረመዳን ውስጥ ማባከን ዱንያ አላቸው በሚባሉ ሀብታም ቤተሰቦች ዘንድ ብቻ የሚታይ አይደለም፡፡ አብዛኛው ሀብታሙም ሆነ ድሃው የማህበረሰብ ክፍል የዚህ ችግር ተጠቂ ነው፡፡ ይህም በረመዳን ወቅት በሚደረጉ የግብዣናኢፍጣር ዝግጅቶች ላይ ጎልቶ ይታያል፡፡ በብዙ ቦታዎች ላይ ለዝግጅቱ ለተጋበዙ ሰዎች ከሚያስፈልገው በላይ ምግብም ሆነ መጠጥ እየቀረበ ብክነት ይፈጠራል፡፡ በረመዳን ውስጥ የሚስተዋለውን የማባከን ሁኔታ ለመቀነስ አንዳንድ ነጥቦችን እንጠቁማለን፡፡

ሁላችንም የረመዳን ጾም የተደነገገለትን ዓላማ በደንብ ልናውቅ ይገባል፡፡ ይህም ነፍስን፣ ገንዘብንና ማህበረሰብን ማንፃት ነው፡፡ ትልቅ የአምልኮ ተግባርም ሲሆን ነፍስ ትእግስትን፣ ብርታትን፣ መስዋእትነትን፣ መከራንና ሌሎች ፈተናዎችን ሁሉ ትላመድ ዘንድ ጉልህ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ረመዳን የተለያዩ ዝግጅቶችን በማዘጋጀት በመብላት በመጠጣትና በመቀናጣት የምናሳልፈው የመፎካከሪያና የጉራ ወር አይደለም፡፡

ከመጠን በላይ ከመለገስ በፊትም ሆነ ሲለግሱና ወጭ ሲያወጡ ተከትሎት የሚመጣውን የብክነት መዘዝ ውጤት አርቆ ማሰብና ማስተንተን ያስፈልጋል፡፡ ዛሬ ራሱን መርምሮ የተጠነቀቀ ሰው የነገ የአኺራ ምርመራ ቀላል ይሆንለታል፡፡ በዚሁ ዙሪያ ዑመር ኢብኑ አልኸጧብ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ሲናገሩ “ከመመርመራችሁ በፊት ነፍሳችሁን መርምሩ፡፡ ነገ ከመመዘኗ በፊት ዛሬውኑ ስራዎቻችሁን መዝኑ፡፡ ለታላቁ ትእይንትም(ቂያማ) ተዘጋጁ፡፡” ብለዋል፡፡ ስለሆነም አንድ ሙስሊም ነገ በመጨረሻው ዓለም አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ፊት ለምርመራ ከመቆሙ በፊት በረመዳን ወር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሌላውም ጊዜ ድሆችን፣ ችግረኞችንና ታጋዮችን እንዲሁም ሌሎችን ማስታወስ ይኖርበታል፡፡ ዘወትር በተከታታይ ራስን መመርመርና ያሉበትን ሁኔታ ማወቅ አንድ ሙስሊም በተለይም ጾመኛ የሆነ ሰው ከነፍሱ ጋር ቆራጥ ሆኖ በሷ እንዳይሸነፍ፤ ስሜቷንና ፍላጎቷንም እንዲቆጣጠር የሚያስችለው ከመሆኑም በላይ በኢስላም ትክክለኛ መንገድ ላይ እንድትጓዝ ያደርጋታል፡፡

በረመዳን ውስጥ በሚያሳዩት ስነምግባርና በልግስናቸው የአላህን መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እና ከርሳቸው በኋላ የተተኩትን የሰሃቦቻቸውን ፈለግ ልንከተል ይገባል፡፡ እነርሱ በነገሮቻቸው ወስጥ መካከለኞች ነበሩ፡፡ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፡-

“የአደም ልጅ ከያዘው ሁሉ ከሆዱ የበለጠ መጥፎ ነገር የለም፡፡ ጀርባውን ሊያቆምበት የሚችል የተወሰኑ ጉርሻዎች ይበቁታል፡፡ የግድ መሆን ካለበት ደግሞ አንድ ሶስተኛውን ለምግቡ፣ አንድ ሶስተኛውን ለመጠጡ፣ አንድ ሶስተኛውን ለትንፋሹ ያድርግ፡፡” ብለዋል፡፡

በሌላም ሐዲሳቸው “ያለ ኩራትና መቀናጣት ብሉ፣ ጠጡ፣ ለግሱ፡፡” ብለዋል፡፡

ከሚያባክኑ እና ከሚቀናጡ ሰዎች መራቅ ይኖርብናል፡፡ እነርሱን ወዳጅ አድርገን መያዝ የለብንም፡፡ ጓደኞቻችን ጠዋት ማታ የአላህን ፊት ፈላጊዎች የሆኑ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም

“አንድ ሰው በወዳጁ ሃይማኖት ላይ ነው የሚሆነው ማንን እንደተወዳጃችሁ ልብ በሉ፡፡” ብለዋል፡፡

በሌላም ሐዲሳቸው አማኝን እንጂ ወዳጅ አድርገህ አትያዝ፡፡ አላህን የሚፈራ ሰው እንጂ ምግብህን አይብላ፡፡ ብለዋል፡፡

በረመዳን ውስጥ እያንዳንዱ የሙስሊም ቤተሰብ ከልግስናና ከወጭ አንፃር የእስልምናን አስተምህሮ ቢተገብርና ለብክነት ችግሮችም የእስልምናን መፍትሄዎች በመድሃኒትነት ቢጠቀም ውጤቱ መልካም በሆነ ነበር፡፡ ከውጤቶቹም የተወሰኑትን ለመጠቀስ፡-

በዚህችም ሆነ በመጨረሻው ዓለም የአላህን ውዴታ መጎናፀፍ ያስችላል፡፡ ጾምም ሆነ ሌሎች አንድ ሰው በረመዳን ውስጥ የሚያከናውናቸው የአምልኮ ተግባራት ተቀባይነት ያገኛሉ፡፡በማይጠቅም ነገር ላይ አንዳንድ ጊዜም የአላህን ሸሪዓ የሚፃረሩ ጉዳዮች ላይ የሚወጣውን ወጭ ቢያንስ በግማሽ ያህል ለመቀነስ ያስችላል፡፡ ቤተሰብ በእዳ ከመዘፈቅ ይተርፋል፡፡ በዚህም የተነሳ ከሸይጣን ተንኮል ሐራም ሰርቶ ከመገኘት ይጠበቃል፡፡ ስለሆነም ጿሚዎች ሆነን በምንለግስበት ጊዜ መካከለኞች መሆን እና ራሳችንን የሸይጣንና የአጥፊዎች ባህሪ ከሆነው ማባከን መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ የመመገብና የመጠጣት ዋና ዓላማው በአላህ መንገድ ላይ ለመበርታትና በዚህም ሆነ በመጨረሻው ዓለም ውዴታውን ለማግኘት መሆኑን ልናውቅ ይገባል፡፡ የምግብ ዓላማው ሆድ መሙላት፣ አጉል ጉራና ፉክክር፣ እንዲሁም በኛ ላይ ሐቅ ያላቸውን ድሆችና ችግረኞች የሆኑ ወንድሞችን መርሳት መሆን የለበትም፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here