ረመዳን ሲመጣ “እንኳን አላህ ለረመዳን አደረስን” በማለት ምስጋና እናቀርባለን፤ ነገር ግን ፀጋን ሳይጠቀሙና ሳይጠብቁት በአፍ ብቻ ማመስገን አጉል የሆነ ጨዋታ ቂልነትና ትልቅ ክስረት ነው።
ይህን የተከበረ የረመዳን ወር ሳንጠቀምበት እንዳያመልጠንና እንዳንከስር የሚረዱንን 100 ምክሮች እንደሚቀጥለው እናቀርባለን፡-
ኢማናዊ ምክሮች
1. ይህ ወር ራስህን የምትመረምርበት፣ ሥራህን የምትገመግምበትና ሕይዎትህን የምታስተካክልበት ወር እንዲሆን ተግተህ ተንቀሳቀስ፤
2. ከሰሐባዎችና ከደጋግ ሰለፎች በዚህ ወር ለአንተ አርዓያ የሚሆንህን ወስነህ ያዝ፤
3. የረመዳንን ጨረቃ ስታይ (ረመዳን መግባቱን ስታረጋግጥ) “ያ አላህ ይህን ጭረቃ በበረካ፣ በኢማን፣ በሰላምና በኢስላም በኛ ላይ አዝልቀው፤ የኔም የአንተም ጌታ አላህ ነው፤” (አህመድና ቲርሚዚይ ዘግበውቴል)።
4. ጌታህን በማምለክ ቀልብህ እንዲረጋጋና ጉዳይህንና ችግርህን ለፈጣሪህ ለማቅረብ እንድትችል ቀደም ብሎ ወደ መስጊድ መግባትን ራስህን አለማምድ፤
5. የመጀመሪያውን ሶፍ ለማግኘት ታገል፡- “ሰዎች በአዛንና በመጀመሪያው ሶፍ የሚገኘውን ደረጃ ቢያውቁ ኖሮ ቦታውን ለማግኘት በመካከላቸው እጣ እስከመጣል ይደርሱ ነበር፤” (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)።
6. ከሶላት በኋላና በተመረጡ ወቅቶች፤ በሱሑር ሰዓት፣ ከአስር ሶላት በኋላ፣ ከመግሪብ ሶላት በፊትና በማፍጠሪያ ጊዜ ዚክር፣ኢስቲግፋርና ዱዓ አብዛ “ፆመኛ በሚያፈጥርበት ጊዜ የማትመለስ ዱዓ አለችው፤” (ኢብኑ ማጀህ ዘግበውታል)።
7. በየቀኑ 12 ረከዓ ትርፍ (ሱና) ሶላቶችን ጠብቀህ ስገድ፡- “ማንኛውም ሙስሊም የአላህ ባሪያ በየቀኑ ከፈርድ ሶላቶች ውጭ 12 ረከዓ ትርፍ ሶላቶችን ለአላህ ብሎ አይሰግድም፤ አላህ (ሱ.ወ) በጀነት ውስጥ ቤት የሚገነባለት ቢሆን እንጂ፤”(ሙስሊም ዘግበውታል)።
8. የተራዊህን ሶላት ሙሉውን በጀመዓ ስገድ፡- “ኢማሙ አስከሚጨርስ አብሮ የሰገደ ሌሊቱን ሙሉ እንደሰገደ ይጻፍለታል።” (አቡ ዳውድና ቲርሚዚ ዘግበውታል)።
9. ከፈጅር ቀደም ብለህ በየቀኑ የምትሰግዳቸው ሁለት ረከዓዎች እንኳ ይኑሩህ፤ ከአላህ ጋር በመንሾካሾክህ (ሙናጃ) እርካታ የምታገኝበት ሰዐት ነውና በጥብቅ ለምነው።
10. ውዱእ ካደረግክ በኋላ ሁሉ ሁለት ረከዓ ስገድ፡- “ማንኛውም ሰው ውዱኡን በትክክል አድርጎ በቀልቡም በፊቱም ወደ አላህ ዞሮ ሁለት ረካአ አይሰግድም ጀነት ለሱ የተገባቸው ቢሆን እንጂ፤” (ሙስሊም ዘግበውታል)።
11 .ሁለት ረከዓ የዱሃ (የረፋድ ሰዐት) ሶላት ስገድ፡- “ማንኛችሁም በሰውነት መገጣጠሚያዎቹ ቁጥር ሰደቃ (ምፅዋት) ኖሮበት ያድራል፤ ሱብሀነላህ ማለት ሰደቃ ነው፤ አልሐምዱሊላህ ማለት ሰደቃ ነው፤ ላኢላሃኢለላህ ማለት ሰደቃ ነው፤ አላሁ አክበር ማለት ሰደቃ ነው፤ በመልካም ነገር ማዘዝ ሰደቃ ነው፤ ከመጥፎ ነገር መከልከል ሰደቃ ነው፤ ይህን ሁሉ ሁለት ረከዓ የዱሓ ሶላትን መስገድ ብቻ ይተካዋል።”(ሙስሊም ዘግበውታል)።
12. የተወሰኑ ትርፍ ሶላቶችን በቤትህ ውስጥ ስገድ፡- “ከሶላታችሁ ከፊሉን በቤታችሁ ውስጥ አድርጉ፤ ቤታችሁን እንደ መቃበር አታድርጓት።” (ቡኻሪ ዘግበውታል)።
13. ጌታህን የምትማፀንበትና በፊቱ የምታለቅስበት ጊዜ ይኑርህ! ይህ ቀልብህ እንዲስተካከል ጠቃሚ ነገር ነውና።
14. ሱጁድ አብዛ፡- “አንድ ባሪያ የበለጥ ከጌታው የሚቀርበው ሱጁድ ላይ በሚሆንበት ጊዜ ነው፤ በሱም ውስጥ ዱዓ አብዙ።” (ሙስሊም ዘግበውታል)።
15. የሱብሂ ሶላትን ከሰገድክ በኋላ በቦታህ ተቀምጠህ አላህን አውሳ፤ “ፈጅርን ሰግዶ ፀሐይ እስከምትወጣ ድረስ አላህን እያወሳ የተቀመጠና ከዚያም ሁለት ረከዓ የሰገደ ሰው ሙሉ የሐጅና ዑምራ ምንዳ ያገኛል።” ነቢያችን (ሶ.ዐ.ወ) “ሙሉ፣ ሙሉ፣ ሙሉ በማለት ሦስት ጊዜ ደጋግመው ተናግረዋል።” (ቲርሚዚይ ዘግበውታል)።
16. የሶላት ሲጠናቀቅ የሚባሉ ዚክሮችን በትኩረት አከናውን “ከሶላት በኋላ ሰላሳ ሦስት ጊዜ አላህን ያጠራ (ሱብሐነላህ ያለ)፣ ሰላሳ ሦስት ጊዜ አላህን ያመሰገነ (አልሐምዱ ሊላህ ያለ)፣ ሰላሳ ሦስት ጊዜ አላህን ያላቀ (አላሁ አክበር ያለ)፣ ይህ ዘጠና ዘጠኝ ነው፤ ከዚያ ላኢላሀ ኢለላህ ወህደሁ ላሸሪከ ለሁ ለሁል ሙልኩ ወለሁል ሐምዱ ወሁወ ዓላ ኩልሊ ሸይኢን ቀዲር (ከአላህ በስተቀር ሌላ አምላክ የለም፤ ንግስናም ምስጋናም ለሱው ብቻ ነው፤ እሱም በሁሉም ነገር ቻይ ነው)፤ ያለ ወንጀሉ የባህር ማዕበል ቢያክል እንኳ ይማርለታል።”(ሙስሊም ዘግበውታል)።
17. የአላህን ፍጡራን ለማስተዋልና ለመገንዘብ ልዩ ጊዜ ስጥ፤ ምክንያቱም ተፈኩር (ማስተንተን) ቀልብ የአላህን ታላቅነት እንዲያውቅና በአላህ ላይ ያለው እምነት እንዲጨምር ያደርጋል፤ አላህን እንዲወድና በአላህ ላይ እንዲንጠለጠል እንዲሁም ከአላህ እርዳታ ለማግኘትም ይረዳል፤
18. በመስጂድ ውስጥ የሚሰጡ የቁርኣን፣ የሀዲስ፣ የፊቅህና የሌሎችም እውቀት አይነቶችን ጠብቀህ ተከታተል።
19. በታናናሽ ወንድሞችህን እህቶችህ ክፍል ውስጥ አንዳንድ ዐረፍተ ነገሮችና ሐዲሶችን ለጥፍ፤ ለምሳሌ፡- “ረመዳንን አምኖና ምንዳውን አስቦ የፆመ ያለፈው ወንጀሉ ይማርለታል።”
20. የፍጡር ዱዓን አትዘንጋ፡- “ዘሀበ ዞመእ፣ ወብተለቲል ዑሩቅ፣ ወሰበተል አጅር ኢንሻአላህ (ጥሙ ተወገደ፣ ደም ሥሮች ረጠቡ፣ ምንዳው ተረጋገጠ ኢንሻአላህ)” (አቡ ዳውድ ዘግበውታል)።
21. ረመዳን የዱዓ ወር ነውና በአጠቃላይ ዱዓ አብዛ፡- “ባሮቼም ከእኔ በጠየቁህ ጊዜ፡- እኔ ቅርብ ነኝ። የለማኝን ጸሎት በለመነኝ ጊዜ እቀበለዋለሁ። ስለዚህ ለኔ ይታዘዙ፤ በኔም ይመኑ፤ እነሱ ሊመሩ ይከጀላልና።” (አልበቀራ 2፤ 186)
22. በነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ላይ በተለይም ጁሙዓ ቀን ሰለዋትን አብዛ፤ “በኔ ላይ አንድ ሶለዋት ያወረደ አላህ በሱ ላይ አስር ሶለዋት ያወርድበታል።” (ሙስሊም ዘግበውታል)።
23. ከአንድ ቦታ ስትንቀሳቀስ የሚደረገውን ዱዓ (ከፋረተል መጅሊስ) ጠብቀህ አድርግ “አንድ ቦታ የተቀመጠና ከመነሳቱ በፊት ሱብሐነከላሁመ ወቢሐምዲከ፣ አሽሀዱ አን ላኢላሃ ኢላ አንተ፣ አስተግፊሩከ ወአቱቡ ኢለይከ (ጌታዬ ከምስጋና ጋር ጥራት ይገባህ፣ ከአንተ በስተቀር አምላክ እንደሌለ እመሰክራለሁ ይቅርታ በመጠየቅ ወደ አንተ ተመልሻለሁ) ያለ ሰው በዚያ ቦታ ያለውን ወንጀል አላህ ይምርለታል።” (አቡ ዳውድ ዘግበውታል)።
24. አንድ ወንጀል ከሰራህ ውዱእ አድርግና ሁለት ረከዓ ስገድ፡- “ማንኛውም ሰው ወንጀል ከሰራ በኋላ በትክክል ውዱእ አድርጎ ሁለት ረከዓ ሰግዶ ከአላህ ማህርታን አይጠይቅም፤ አላህ የማረው ቢሆን እንጂ።” (አቡ ዳውድ ዘግበውታል)።
25. ከቻልክ በረመዳን ዑምራ ለማድረግ ሞክር፡- “በረመዳን ዑምራ ከሐጅ ይስተካከላል፤ ወይም ከኔ ጋር እንደተሰራ ሐጅ ይቆጠራል።”(ሙስሊም ዘግበውታል)።
ዳዕዋዊ ምክሮች
26. የአነጋገር ዘዴህን አድስ፤ ተስማሚ ጉዳዮችን ምረጥ።
27. በመሰጅድ የሚገኘውን የማስታወቂያ ሰሌዳና የሚለጠፉ መጣጥፎች፣ ፖስተሮችና ሌሎች ጠቃሚ ፅሁፎች አሻሽለህ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ አድርግ።
28. በየሳምንቱ በመስጂዱ ተጠቃሚዎች መካከል ውድድር አዘጋጅና ከቻልክ ከጁመዓ ሶላት በኋላ ሽልማት ለመስጠት ሞክር።
29. የተለያዩ ፋንፍሊቶች /በራሪ ወረቀቶች/፣ ካሴቶች በመስጅድ፣ በሥራ ቦታና በሠፈር ለተጠቃሚዎች አዳርስ፤ አለያም ይህንን በመስራት ለሚታወቁ ማህበራት በመስጠት ለፈላጊዎች እንዲደርስ አድርግ።
30. ከበጎ አድራጎት ማህበራት ጋር በመተባበር የኢፍጧር ፕሮግራሞችን በመጠቀም ወደ አላህ ጥሪ ለማድረግ ሞክር።
31. ለመስጀዱ ሰዎች አንድ ቀን እንኳ ቢሆን የኢፍጧር ፕሮግራም አዘጋጀተህ ትውውቅ በማድረግና ግንኙነታችሁን እንዲጠናከር አድርግ።
32. ጠቅላላውን የነቢያችንን (ሰ.ዐ.ወ) አዳብ ለሰዎች አስተምር፤ በተለይም የፆም ሥነ-ሥርዓቶችን ለምሳሌ ፍጡርን ማቻኮል፤ በቴምር ወይም በውሃ ማፍጠርና የመሳሰሉትን።
33. የሠፈሩን ድሃዎች ለይተህ በማወቅ በሚቻልህ መጠን በገንዘብና በማህበራዊ ጉዳዮች ተባበራቸው።
34. ሶላትን ጠብቀው ለሚሰግዱና በቁርኣን ሒፍዝ የተሻሉ ለሆኑ ታዳጊ ወጣቶች የማበረታቻ ሽልማቶችን አዘጋጅ።
35. ወንዶችና ሴቶች ጥያቄዎቻቸውን የሚያስቀምጡባቸውና መልስ የሚያገኙባቸው ሳጥኖች ለየብቻቸው አዘጋጅ።
36. ቤተሰቦችህን ለማንቃትና ደዕዋ ፕሮግራም ለማዘጋጀት ተንቀሳቀስ።
37. ወጣቶችን ከእድሚያቸውና ከልምዳቸው ጋር የሚሄዱ የበጎ ፈቃደኝነት ሥራዎች ላይ እንዲሳተፉ እድል አምቻችላቸው።
38. በረመዳን መጠቀም እንዲችሉ አንዳንድ ጠቃሚ መልዕክቶችን በባለቤትህ በኩል ለጓደኞቿና ለጎረቢቶች እንዲደርስ አድርግ።
39. በመስጂድ ሐለቃ በማቋቋም ቁርኣን ያልተማሩ ሰዎች የቁርኣን አቀራር፣ ሒፍዝና ጥናት አስተምር/ አስጀምር።
40. ለየቲም፣ ለተቸገሩ ሰዎች፣ ባጠቃላይ ዲኑን ለሚካድሙና ገቢ ለሌላቸው ሰዎች እርዳታና ድጋፍ እንዲያደርጉ አበረታታ።
41. በመጨረሻዎቹ አስር ቀናት በቅርብ የሠፈርህ መስጂድ ኢዕቲካፍ በማዘጋጀት ተሳታፊዎች ከኢዕቲካፍ የበለጠ ተቅመው እንዲወጡ የሚረዳ ፕሮግራም አዘጋጅላቸው።
42. ከአካባቢው ሰዎች በተለይም ደግ ሰዎችና ዱዓቶች ጋር ጥብቅ የሆን ትስስር መስርት።
43. በተለያዩ የቴሌቪዢን ጣቢያዎች በረመዳን ከሚተላለፉ ፕሮግራሞች መካከል ጠቃሚዎችን መርጠህ በመያዝ የአየር ጊዜያቸውን ለጓደኞችህና ጎረቢቶችህ አሳውቅ።
44. በሰዎች ላይ የመጣውን አጠቃለይ የባህሪ ለውጥ በማየት በረመዳን ከተሰጡ ትምህርቶች ምን ያክል እንደተጠቀሙ መዝግበህ ያዝ።
45. (የረመዳን ወዳጆች) ኮሚቴ አቋቁምና ታማሚዎችን በሆስፒታል፤ ድሃዎችን ደግሞ በቤታቸው በመጠየቅ ለረመዳን ወር እንኳን አደረሳችሁ መልክት እንዲያደርሱላቸው፤ ካሴቶችንና ጠቃሚ ፋንፍሌቶችን እንዲያድሏቸው እንዲሁም ስለ አላህ እንዲያስታውሷቸው በተጨማሪም ስለጦሃራና ሶላት እንዲያስተምሯቸው አድርግ።
46. በአካባቢው የተስፋፉ መጥፎ ነገሮችን ለይቶ በመያዝ ተስማሚ የሆኑ የማሰወገጃ መንገዳቸውን በማፈላለግ እንዲቀየሩ አስተባብር።
47. ሰዎች በሚሰባሰቡባቸው ሙስሊሞች በብዛት በሚያዘወትሯቸው ተቋማት ውስጥ ጠቃሚ መጽሐፍትና ፋንፍሌቶችን በትን።
48. በየቀኑ ግማሽ ገጽ የሚሆን የደዕዋ መልክት በመጻፍ ኢሜልንና ፌስ ቡክን በመጠቀም በተቻለ መጠን ብዛት ላላቸው ሰዎች በተለይም ለሠፈር ሰዎችና ዘመዶች እንዲደርስ አድርግ።
49. ከመስጂዱ ኢማም ወይም ከዱዓቶች አንዱ ጋር በመተባበር አንድ ታላቅ የአሊም ፕሮግራም በማዘጋጀት ለሰዎች በህይዎታቸው ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ነገሮች እንዲጠይቁና መልስ እንዲያገኙ መድረክ አምቻች።
50. ከጓደኞችህ ጋር በመተባበር የሚተርፉ ምግቦችን ከየቤቱ በማሰባሰብ ለድሃዎችና ችግረኞች እንዲዳረስ አድርግ፤ አጋጣሚውን በመጠቀም የተረፉ ምግቦችን ሰብስቦ የሚያከፋፍል ተቋም እንዲሆን ጣር።
መሰረታዊ ምክሮች
51. አላህ (ሱ.ወ) ለሱ ሲባል ብቻ የተሠራን እንጂ አይቀበልም እና ኒያህን ለአላህ አጥራ፤ በፆምህም ወደ አላህ ብቻ ዙር።
52. በአንድ ጊዜ ከአንድ በላይ ስራ ለመስራት ሞክር፤ ለምሳሌ እየሄድክ ዚክር ማለትና በትራንስፖርት ውስጥ ሆነህ ቁርኣን መቅራት…።
53. ሱሑር በመብላት ታገዝ፤ “ሱሑር ብሉ፤ ሱሑር መብላት በረካ አለው።” (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)።
54. ፊጥርን አቻኩል፤ “ሰዎች በኸይር ላይ ከመሆን አይወገዱም፤ ፊጥርን እስካፋጠኑ ድረስና ሱሑርን እስካዘገዩ ድረስ።” (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)።
55. ማግኘት ከቻልክ በቴምር አፍጥር፡- “ቴምርን ያገኘ በሱ ያፍጥር፤ ቴምርን ያላገኘ በውሃ ያፍጥር፤ ውሃ ንጹህ ነውና።” (አህመድ ዘግበውታል)።
56. ቁርኣንን እያስተነተንክና እየተረዳህ በብዛት አንብብው፤ በየቀኑ የምትቀራው የተወሰነ የቁርኣን ክፍል ሊኖርህ ይገባል፤ ጅብሪል (ዐ.ሰ) ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ጋር በየሌሊቱ እየተገናኘ ቁርኣንን ያጠኑ ነበር።
57. ምላስህን ከውሸት፣ ከሐሜት፣ ነገርን ከማዛመትና ከመጥፎ ንግግር ጠብቅ። ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- “ውሸት ንግግርንና በሱም መስራትን ያልተወ ሰው ምግቡንና መጠጡን መተው ለአላህ (ሱ.ወ) ጉዳዩ አይደለም።” (ቡኻሪ ዘግበውታል)።
58. አይንህን ከሐራም ከልክል፡- “(የሐራም) እይታ ሰይጣን የሚወረውረው ጦር ነው፤ እኔን ፈርቶ የተወን ሰው ጥፍጥናውን በልቡ የሚያገኘውን ኢማን እተካዋለሁ።” (ጦብራኒ ዘግበውታል)።
59. በሰዎች መካከል የሚካሄዱና አንተን የማይመለከቱህን ወሬዎችና ውይይቶች ከማዳመጥና ከመከታተል ጆሮህን ቆጥብ።
60. ራስህንና ስሜትህን እንዴት መቆጣጠር እንደምትችል ተማር፡- “ፆም ጋሻ ነው፤ አንድኛችሁ ፆመኛ በሆነ ጊዜ መጥፎ ቃል አይናገር፤ አንድ ሰው ቢሰድበው ወይም ቢጋደለው እንኳ እኔ ፆመኛ ነኝ ይበል።” (ሙስሊም ዘግበውታል)።
61. ሰደቃ አብዛ፤ ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ኸይርን በመለገስ ከሰዎች ሁሉ ቀዳሚ ነበሩ፤ በጣም የሚለገሱት ደግሞ በረመዳን ነበር።
62. በፍጡር ጊዜ ምግብ አታብዛ፤ ምግብ ማብዛት መዳከም ያመጣል፤ ሁልጊዜ ጠግቦ መመገብ ደካማነትንና ቀልብ መድረቅን ያስከትላል፤“የሰው ልጅ ወገቡን ቀጥ የሚያደርጉለት ትንሽ ጉርሻዎችን መመገብ በቂው ነው፤ ከዚህ በላይ አብዝቶ መብላት ግድ ከሆነም አንድ ሦስተኛውን ለምግብ፣ አንድ ሦስተኛውን ለመጠጥ፣ አንድ ሦስተኛውን ደግሞ ለአየር ያድርግ።” (ቲርሚዚይ ዘግበውታል)።
63. ከፍጡር በኋላ ቀልብህን በአላህ ፍራቻና ተስፋ መካከል አድርግ፤ ምክንያቱም ፆምህ ተቀባይነት አግኝቶ ከአትራፊዎች ትሆን ወይስ ፆምህ ተመልሶብህ ከከሳሪዎች መሆንህን አታውቅም።
64. ረመዳንን ግዴታነቱን አምነህና ምንዳውን አስበህ ፁም፤ “ረመዳንን አምኖና አስቦ የፆመ ሰው ያለፈው ወንጀሉ ይማርለታል።” (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)።
65. ረመዳንን አምነህና ምንዳውን አስበህ ቁም (የሌሊት ስግደት አከናውን)፡- “ረመዳንን አምኖና አስቦ የቆመ ሰው ያለፈው ወንጀሉ ይማርለታል።” (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)።
66. ለይለተል ቀድርን አምነህና ምንዳውን አስበህ ቁም፡- “ለይለተል ቀድርን አምኖና አስቦ የቆመ ሰው ያለፈው ወንጀሉ ይማርለታል።”(ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)።
67. በመጨረሻዎቹ አስር የረመዳን ቀናት በኢባዳ ታገል፡- “ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) አስሮቹ ቀናት ሲገቡ ሌሊቱን ህያው ያደርጉ ነበር፤ ቤተሰቦቻቸውንም ያነቁ ነበር፤ እርሳቸውም ታጥቀው ለኢባዳ ይነሱ ነበር።” (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)።
68. የፆምን ፍሬና ግድ የተደረገበት ውስጠ ሚስጠር አብሮህ እንዲቀጥል በነገርህ ሁሉ የአላህን ትዕዛዝ ጠብቅ፤ በድብቅም በግልጽም እርሱን ተጠባበቅ (ትዕዛዙን ከመጣስ ተጠንቀቅ) “እናንተ ያመናችሁ ሆይ ጾም በነዚያ ከናንተ በፊት በነበሩት (ሕዝቦች) ላይ እንደ ተጻፈ በናንተም ላይ ተጻፈ (ተደነባ) ልትጠነቀቁ ይከጀላልና።” (አል-በቀራ 2፤ 183)
69. በድካም፣ በረሀብና ጥም በማመካኘት የረመዳንን ቀን እየተኛህ አላህ ዘንድ እጅግ ተወዳጅ የሆነው ጀማዓ ሶላት አይለፍህ።
70. በንግድና ገንዘብ ነክ ጉዳዮችም ይሁን በምክክርንና በውይይት ጊዜ ከማታለል በእጅጉ ራቅ፡- “ያታለለን ከኛ አይደለም።” (ሙስሊም ዘግበውታል)።
71. አደራ! ጥሩ ሥነ-መግባርን ተላበስ፤ ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ሰዎችን በብዛት ጀነት የሚያስገበው ነገር ምንድን ነው ተብለው ሲጠየቁ “አላህን መፍራትና ጥሩ ሥነ-ምግባር ነው” ሲሉ መልሰዋል። (ቲርሚዚ ዘግበውታል)።
72. የታጋሽነት፣ ይቅር ባይነትና ቁጣን መዋጥ ችሎታ ይኑርህ፤ የበለጠ ለማሻሻልም ራስህን ታገል “ለእነዚያ በድሎትም ኾነ በችግር ለሚለግሱት፣ ቁጭትንም ገቺዎች ከሰዎችም ይቅርታ አድራጊዎች ለኾኑት (ተደግሳለች)። አላህም በጎ ሠሪዎችን ይወዳል።” (አሊ ዒምራን 3፤ 134)
73. ያለ አግባብ የያዝከውን ነገሮች ለባለቤቶቻቸው በመመለስ ከሰዎች ሐቅ ነፃ ሁን፡- “የወንድሙ ሐቅ ያለበት ሰው ዛሬውኑ ነጻ ይሁን፤ ነገሩ እዚያ (አኺራ) ወርቅም ይሁን ብር የለም፤ አንድ ሰው የወንድሙ ሐቅ ካለበት ከኸየር ሥራው እየተወሰደ ለወንድሙ ይከፈላል፤ ኸይር ሥራ ከሌለው ደግሞ ከወንድሙ ወንጀል እየተወሰደ እርሱ ላይ ይጣላል።” (ቡኻሪ ዘግበውታል)።
74. አገልጋዮችንና ሠረተኞችን በረመዳን ብዙ በማሰራት አታድክማቸው፤ “ከባሪያው ያቃለለ ሰው አላህ (ሱ.ወ) ወንጀሉን ይምረዋል፤ ከሳትም ነፃ ያወጣዋል።” (ኢብኑ ኹዘይማህ ዘግበውታል)።
75. ወደኸይር ነገር ጥሪ ያደረገልህን ሰው ግብዣውን ተቀበል፤ “በአላህ የተጠበቀን ጠብቁት፤ በአላህ ስም የለመነን ሥጡት፤ ጥሪ ያደረገላችሁን ተቀበሉት፤ ለናንተ ውለታ የዋለላችሁን ሰው ውለታውን መልሱለት።” (አህመድ ዘግበውታል)።
ቤተሰባዊ ምክሮች
76. ቤተሰቦችህ በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ የረመዳን ወር ሲገባ አበስራቸው።
77. ረመዳንን ምክንያት በማድረግ በቤትህ ውስጥ ለውጥ አድርግ፤ ይህም የሚሆነው ቤቱን በማጽዳት፣ እቃዎችን እንደገና በማደራጀት፣ ቁርኣን የተጻፈባቸውን ፍሬሞችና ሌሎች ጠቃሚ ምክሮች ለማስታወስና ረመዳንን ለማድመቅ በግድጊዳ ላይ ስቀል፣ ህጻናት በረመዳን መምጣት እንዲደሰቱና ደረጃውንም እንዲረዱት በክፍላቸው ውስጥ አንዳንድ ማስዋቢያዎችን ስቀልላቸው።
78. የረመዳንን ወር ጊዜያት በትክክል ለመጠቀም እቅድ አስቀምጥ፤ በየቀኑ የምትቀራውን የቁርኣን መጠንና ተራዊህ ሶላት ለመስገድ ተስማሚ የሚሆንልህን መስጅድ ከአሁኑ ውስን።
79. በረመዳን ወር መስገጃ የሚሆን ቦታ በቤት ውስጥ ለይተህ አስቀምጥ።
80. የቤተሰቦችህን ኢባዳና ሥነ-መግባር በመከታተል የተሳሳተ ሁኔታ ካለ አስተካካል።
81. ለረመዳን የሚያገለግል እለታዊ ፕሮግራም በቤትህ ውስጥ በመስቀል ሁሉም የቤተሰብ አባላት እንዲሳተፉበትና እንዲጠቀሙበት አድርግ፤ ፕሮግራሙ እንዳስፈላጊነቱ መቀያያር የሚችል መሆን አለበት።
82. ፍጡርና ሱሑር ከቤተሰብህ ጋር ተመግብ፤ ምክንያቱም አብራችሁ ስትመገቡ ቤተሰባዊ ትስስሩን ያጠብቀዋልና ነው።
83. ከልጆችህ ጋር ሆነህ ለሱብሂ ሶላት ወደ መስጊድ ሂድ፤ የመጀመሪያ ሶፍ ላይም ስገዱ፤ እናት ደሞ ከሴት ልጆች ጋር በቤት ውስጥ ትሰገድ፤ ሁኔታዎች ከተመቻቹ እናት ከባሏና ከልጆቿ ጋር መስጅድ ትሂድ።
84. ከሳምንት አንድ ቀን ከልጆችህና ሚስትህ ጋር ከፈጅር ሶላት በኋላ ተቀምጣችሁ አንድ ጁዝ ቁርኣን ቅሩ፤ እነዲዚሁም ከሲራና ከፊቅህ (በተለይም ፆምን በተመለከተ) ተፍሲርና አቂዳ የተወሰነ ተማማሩ።
85. ዋጀብና ትርፍ ኸይር ሥራዎችን የምትከታተሉበት ሠንጠረዥ ከቤተሰቡ ጋር ተስማምተህ አስቀምጥ፤ ሌሎች እንዲነቃቁ ጥሩ እንቅስቃሴ ያሳዩትን አበረታታቸው።
86. በኑሮህ መካከለኛነትን በመከተል ከገቢህ ጋር የሚመጥን የረመዳን በጀት አስቀምጥ፤ ረመዳን አስፈላጊውን የሚሟላበት ወር እንጂ የብክነት ወር አይደለም።
87. ከባለቤትህ/ሽ ጋር ሁናችሁ ለኸይር ጉዳይና ትርፍ ሰደቃ የሚውል ገንዘብ ወስናችሁ አስቀምጡ።
88. የሚዲያን ብልሹ መልክቶች ተጠንቀቅ፤ በተለይም የሴቶችን ገላ እያጋለጡ የሚያሳዩና ወደ መጥፎ ነገርና ወንድና ሴትን ለማቀላቀል ጥሪ የሚየደርጉ ጋዜጦችንና መጽሔቶችን ራቅ።
89. ልጆችህ የሙስሊሞችን ስብስብ እንዲያዩ በአንድ ታላቅ መስጊድ ለመስገድ ጥረት አድርግ።
90. ልጆችህ ቀስ በቀስ ፆም እንዲለማመዱ አድርግ፤ ሱሑር ለመብላትና ለፈጀር ሶላት እንዲነሱ አበረታታቸው።
91. ቤተሰቦችህ የጠዋትና የማታ አዝካሮችን (ውዳሴዎችን)፣ የፍጡር ዱዓና የተሀጁድ ዱዓ እንዲሐፍዙ አድርግ፤ ውድድር እያደረግክ ዱዓዎቹን በቃል ለሸመደዱና ጠብቀው ለሚጠቀሙ ሽልማት በመስጠት ልታበረታታቸው ትችላለህ።
92. በቤትህ ውስጥ ያሉትን ጥሩ ጎኖችና መጥፎ ጎኖች ለይተህ ጥሩውን ለማሳደግ መጥፎውን ደግሞ ለማስወገድ ሥራ።
93. እናት ልጆቿን ምግብ በማዘጋጀትና በማቅረብ እንዲሳተፉ በማድረግ በመካከላቸው ተባብሮ የመስራት ዋጋን እንዲረዱ ማድረግ አለባት።
94. የኸይር ከረጢት (ሻንጣ) በያንዳንዱ ቤተሰብ አለያም በጎረቤቶች ደረጃ አዘጋጅታችሁ ድሃዎችና ችግረኞች ለረመዳን እንዲጠቀሙበት በማድረግ በሙስሊሞች መካከል ሊኖር የሚገባውን ማህበራዊ ትብብር ህያው አድርጉ።
95. ከአጉል ወገንተኝነት፣ ከስሜታዊነትና ስሞታ ከማብዛት ተቆጠብ፤ በማንኛውም ሁኔታ ልበ ሰፊና የተረጋጋህ ሁን፤ አላህን ሁል ጊዜ አውሳ።
96. ዚያራ በማድረግና ስጦታ በመለዋወጥ ማህበራዊ ኑሮ ላይ ተሳተፍ፤ ከቤተሰቦችህና ከጎረቢቶች ጋር ኢባዳ የምትሠሩበትና በመካከላችሁ ያሉ አለመግባባቶችን የምታስተካክሉበት መገናኛ ጊዜያት አድርጉ።
97. በየሳምንቱ ቤተሰብህን የምትይዝበት ሳምንታዊ መልክት ምረጥ፤ ለምሳሌ “የማያዝን አይታዘንለትም” የሚለውን ሐዲስ የሳምንቱ መልክት በማድረግ የእዝነት ባህሪን አትኩሮት መስጠትና መላበስ ይቻላል። በሁለተኛው ሳምንት ደግሞ “ጌታችሁን ማህርታ ጠይቁት፤ እርሱ ማሀሪ ነውና።” የሚለውን የቁርኣን አንቀጽ በመጠቀም የኢስቲግፋርን አስፈላጊነት ታስተምራለህ። በሦስተኛው “ጌታዬ ወደ አንተ ፈጠንኩ” የወሩ ግማሽ ተገባደደ፤ ስለዚህ አላህ (ሱ.ወ) እንዲቀበለን የበለጥ በኢባዳ መጠናከር አለብን። ከዚያም በአራተኛው ሳምንት ደግሞ“ወደ አላህም ሽሹ፤ እኔ ለእናንተ ከርሱ ግልጽ አስጠንቃቂ ነኝና” (ዛሪያት 51፤ 50) ወይም “ይታዘንላችሁም ዘንድ አላህንና መልክተኛውን ታዘዙ።” (አል-ኢምራን 3፤ 132) የሚሸሸው ወደ አላህና ወደ ጀነቱ መሆን አለበት። ይህን የመሳሰሉ መልክቶች…
98. ሚስትህን የተለያዩ የምግብ አይነቶች በማዘጋጀት እንድትጠመድ አታድርግ፤ በማዕድ ቤት ውስጥ ልትጠቀምበት የሚቻል ፕሮግራም እንዲኖራት አድርግ፤ ለምሳሌ የቁርኣንና የዲን ካሴቶችን ማዳጥ…፤ ፆመኞችን ለማስፈጠር የምታደርገው ትግል ትልቅ ምንዳ የሚያስገኝላት መሆኑንም አስታውሳት።
99. በረመዳን ወር በሙሉ ለልጆችህ ሊጠቅማቸው የሚችል ማራኪ መጽሐፍ በመምረጥ፣ የንባብ ውድድር አድርግ፤ ለምሳሌ ሐያቱ ሶሐባ (አብዱረህማን ረእፈት የጻፉት)… ለዚሁም ሸልማቸው፤
100. በቤተሰብ አባላት መካከል ያለውን ልዩነት (የግል ባህሪ) አትዘንጋ፤ ለአንድኛው የሚስማማው ነገር ለሌላው ላይሆን ይችላል፤ ከዚህም አኳያ አንዱን ልጅህን በሒፍዝ ላይ ልታበረታታው ትችላለህ፤ ሌላውን ደግሞ በቂራኣ ላይ…
አላህ ከኛም ከናንተም ሶላታችንና ፆማችንን ሌላውንም ሥራችንን ይቀበለን።