የረመዳን ወር አቀባበል

0
13515

ታላቁ እንግዳችን! የተከበረውን የረመዳን ወር ለመቀበል ሁሉም በየፊናው ተፍተፍ እያለ ይገኛል። ከፊሉ ቤቱን በማሰናዳት፣ ሌላው የምግብ አይነቶችን በመሸመት፣ እኩሉም የወሩን ትሩፋት ለመጠቀም እቅድ እያወጣ…ወዘተ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

ለመሆኑ ይህ አያሌ የፈጣሪ ትሩፋትን በውስጡ ይዞ የመጣውን ይህን ወር ለመቀበል ትክክለኛው መንገድ የትኛው ነው?

በወሩ ውስጥ ያሉትን እያንዳንዱን የጦዓ (አምልኮ) ወቅቶችን ሁሉ አሟጦ ለመጠቀም ምን ማድረግ ይጠበቅብናል? በነዚህ በተከበሩ ጊዜያት ውስጥ በኸይር ነገሮች መሽቀዳደም ያስፈልጋልና፤ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡-

وَفِي ذَٰلِكَ فَلْيَتَنَافَسِ الْمُتَنَافِسُونَ
“በዚህም ተሽቀዳዳሚዎች ይሽቀዳደሙ።” (አል-ሙጦፊፊን 83፤ 26)
በመሆኑም ከዚህ በመቀጠል የረመዳንን ወር በተሻለ መንገድ ለመቀበል የሚረዱ መንገዶች እንጠቁማለን፡-1. ዱዐ ማድረግ፡- በፆም፤ በሶላትና በዚክር ላይ እንድትጠነክር አላህ (ሱ.ወ) በሙሉ ጤንነትና አቅም ላይ ሆነህ ረመዳን ወር እንዲያደርስህ ከአሁኑ ዱዓ አድርግ፤ አነስ ቢን ማሊክ (ረ.ዐ) ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) የረጀብ ወር ሲገባ እንዲህ ይሉ ነበር ብለዋል፡-

اللهم بارك لنا في رجب وشعبان وبلغنا رمضان

“አላህ ሆይ! ረጀብንና ሸዕባንን ብሩክ አድርግልን፤ ረመዳንንም አድርሰን” (አህመድና ጦብራኒ ዘግበውታል)።ሰለፎች (ቀደምት ደጋግ አቦዎች) ረመዳንን እንዲያደርሳቸውና ከዚያም ሥራቸውን እንዲቀበላቸው አላህን (ሱ.ወ) ይለምኑ ነበር፤ ስለዚህ አንተም የረመዳን ጨረቃ ስትወጣ እንዲህ ብለህ ዱዓ አድርግ፡-

الله أكبر اللهم أهله علينا بالأمن والإيمان والسلامة والإسلام , والتوفيق لما تحب وترضى ربي وربك الله

“አላሁ አክበር አላህ ሆይ! ይህን ጨረቃ የአማንና የኢማን፣ የሰላምና የኢስላም፣ እንዲሁም አንተን የሚያስደስት ተግባር መስራት የምንችልበት ጊዜ አድርግልን፤ የኔም የአንተም ጌታ አላህ ነው፤” (ቲርሚዚ ዘግበውታል)።

2. ምስጋና ማቅረብ፡- ረመዳን ወር ከደረስክ ምስጋና ለአላህ አቅርብ፤ ኢማሙ ነወዊይ አል-አዝካር በተባለው ኪታባቸው ውስጥ እንዲህ ብለዋል “አንድ አዲስ ፀጋን ያገኘ ወይም አንድ ችግር የተወገደለት ሰው ለአላህን ምስጋና ለማቅረብ ሱጁድ አድረጎ አላህን በሚገባው መልኩ ማወደስ ይገባዋል።

”አላህን ማምለክና የሱን ትእዛዝ መፈጸም መቻል በራሱ አላህ (ሱ.ወ) ለአንድ ሙእሚን ከሚለግሰው ታላላቅ ፀጋዎች ነው። አንድ ሙእሚን የረመዳን ወር ሲገባ በጥሩ ጤንነት ላይ መገኘቱ ብቻ ፀጋውንና ችሮታውን ለለገሰው አላህ (ሱ.ወ) ምስጋና እንዲያቀርብ የሚያስገድደው በቂ ነገር ነው፤ ስለዚህ የረመዳንን ወር በሰላምና በጤና የደረሰ ሰው ለአላህ (ሱ.ወ) ትልቅ ምስጋና ሊያቀርብና እሱን በብዛት ሊያወድስ ይገባል፤ ለልቅናውና ለግዙፍ ስልጣኑ የሚመጥን ታላቅ ምስጋናና ውዳሴ ለአላህ (ሱ.ወ) ይሁን!!

3. መደሰት፡- ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) የረመዳን ወር ሲመጣ እንዲህ በማለት ባልደረቦቻቸውን ያበስሩ እንደነበር ተረጋግጧ፡-

جاءكم شهر رمضان شهر مبارك كتب الله عليكم صيامه فيه تفتح أبواب الجنان وتغلق فيه أبواب الجحيم

“የተባረከው የረመዳን ወር መጥቶላችኋል፤ እሱን መፆም አላህ (ሱ.ወ) በናንተ ላይ ደንግጓል፤ በረመዳን ወር የጀነት በሮች ይከፈታሉ፤ የገሀነም በሮች ደግሞ ይዘጋሉ” (አህመድ ዘግበውታል)።

ሰሐባዎችንና ታቢዒዮችን ጨምሮ ያለፉት ደጋግ አቦዎች (ሰለፎች) ለረመዳን ወር ልዩ ትኩረት ይሰጡ ነበር፤ ረመዳን ሲመጣም ይደሰቱ ነበር፤ አዎ ይህ ትልቅ ደስታ ነው! የኸይርና የአላህ እዝነት መውረጃ የሆነ ወቅት ሲመጣ ጤና ሆኖ በሂይወት ከመኖር የበለጥ የሚያስደስት ነገር አለን?!

4. ወሩን በአግባቡ ለመጠቀም መወሰንና ቀድሞ እቅድ ማውጣት፡- ብዙ ሙስሊሞች- ዲነኞችን ጨምሮ- ለዱንያ ጉዳያቸው በሚገባ እቅድ ሲያወጡ ይታያሉ፤ ነገር ግን ለአኺራቸው እቅድ በማውጣት የሚሰሩት ጥቂቶች ናቸው። ይህም የሚሆንበት ምክንያት ሙእሚን በዚች ህይወት ያለውን መልዕክት ካለመረዳትና አንድ ሙእሚን ነፍሱ በአላህ ዲን ላይ ፅናት እንዲኖራት ራሱን ለማለማመድ ከአላህ ዘንድ የሚገኙ መልካም አጋጣሚዎች ችላ ከማለት የሚመነጭ ነው።

ለአኺራ ከምናቅድባቸው ጉዳዮች መካከል የረመዳንን ወር በጧዐና ኢባዳ ለማሳለፍ የምናደርገው ዝግጅትና እቅድ አንዱ ነው፤ ስለሆነም ማንኛውም ሙስሊም የረመዳንን ወር በትክክል አላህን በመታዘዝ ማሳለፍ እንዲችል ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ፕሮግራም ማውጣት ያስልገዋል።

5. ቁርጠኛ አቋም፡- የረመዳንን ወር በመልካም ሥራዎች ለመሙላት ቁርጠኛ አቋም መያዝ። ከልቡ በእውነት ወደ አላህ የቀረበ ሰው አላህ ይቀበለዋል፤ እሱን ለመገዛትና ኸይር ለመስራትም ያግዘዋል፤ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡-

فَلَوْ صَدَقُوا اللَّهَ لَكَانَ خَيْرًا لَّهُمْ

“እውነተኞች በኾኑ ኖሮ ለእነርሱ የተሻለ በኾነ ነበር።” (ሙሐመድ 47፤ 21)

6. የረመዳን ህግጋትን መማርና መረዳት፡-ሙእሚን አላህን መገዛት ያለበት በእውቀት ላይ ተመስርቶ ነው። አላህ (ሱ.ወ) በባሮቹ ላይ ግዴታ ያደረጋቸውን ነገሮችና አፈጻጸሙን አለማወቅ ማንኛውም ሙስሊም ይቅርታ ሊደረግለት የማይችል ጉዳይ ነው። ማወቅ ግደታ ከሚሆኑት ነገሮች መካከል የረመዳን ፆም አንዱ ነው፤ ስለዚህ ማንኛውም ሙስሊም ረመዳን ከመግባቱ በፊት ፆሙ ትክክለኛና አላህ ዘንድ ተቀባይነት ያለው እንዲሆን ስለ ፆም ህግጋቶች (አህካም) መማርና ጠንቅቆ ማወቅ ይገባዋል። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡-

فَاسْأَلُوا أَهْلَ الذِّكْرِ إِن كُنتُمْ لَا تَعْلَمُونَ
“የማታውቁም ብትኾኑ የመጽሐፉን ባለቤቶች ጠይቁ።” (አል-አንቢያእ 21፤ 7)
7. ተነሳሽነትን መጨመር፡- የፆምን ትሩፋቶች (አጅር/ፈዳኢል) እና ህግጋቶች የሚያብራሩ የተለያዩ መጽሀፍትን በማንበብና ካሴቶችን በማዳመጥ ለረመዳን ፆም የሥነ-ልቦናና መንፈሳዊ ዝግጅት ማድረግ ይገባል። ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) የረመዳንን ወር በአግባቡ እንዲጠቀሙበት ባልደረቦቻቸውን ሲያዘጋጇቸው የሸዕባን ወር መጨረሻ ቀን ላይ “የረመዳን ወር መጣላችሁ…” ይሉ ነበር፤ (አህመድ ዘግበውታል)።8. ንሰሀ፡-የረመዳንን ወር ከወንጀል ሁሉ ለመራቅ፣ ለመፅዳትና ወደ ወንጅል ላለመመለስ ወስነንና እውነተኛ ተውበት በማድረግ ወደ አላህ ለመመለስ ቆርጠን ልንቀበለው ይገባል። እንደሚታቀወቀው ረመዳን የተውበት ወር ነው፤ በዚህ ወር ያልቶበተ (ወደ አላህ በንሰሀ ያልተመለሰ) ሰው መቸ ይመለሳል ተብሎ ይታሰባል?! አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡-

وَتُوبُوا إِلَى اللَّهِ جَمِيعًا أَيُّهَ الْمُؤْمِنُونَ لَعَلَّكُمْ تُفْلِحُونَ

“ምእመናኖች ሆይ! ትድኑ ዘንድ ሁላችሁም ወደ አላህ (በመመለስ) ተጸጸቱ።” (አን-ኑር 24፤ 31)

9. ዳዕዋ፡- በረመዳን ወደ አላህ (ሱ.ወ) ደዕዋ (ጥሪ) ለማድረግ በጥሩ ሁኔታ መዘጋጀት፤ ለዚህም፡-

  1. በመስጅድ ውስጥ የሚሰጡ ሙሀደራ (ስብከት) የሚሆኑ ጥሩ መልእክት ያላቸውን ፅሁፎች ከወዲሁ አዘጋጅቶ መያዝ፤
  2. የረመዳንን ወር የተመለከቱ ትንንሽ መጽሐፍትን /ፓምፍሌት/ አዘጋጅቶ ለሰጋጆችና ለአካባቢ ሰዎች ማሰራጨት፤
  3. የረመዳን ስጦታ ማዘጋጀት፤ ለምሳሌ አንድ ፖስታ ውስጥ ሁለት ካሴቶች /ሲዲ/ እና አንድ ትንሽ መጽሐፍ አሽገን ከላዩ ላይ (የረመዳን ስጦታ) ተብሎ ሊጻፍበት ይችላል፤
  4. ድሃዎቸን ማስታወስና የምስፅዋትና ዘካ ገንዘብ አሰባሰብን ከወዲሁ ማቀድ፤

10. አዲስ ምእራፍ፡- ረመዳንን አዲስና ንፁህ ምዕራፍ በመክፈት ልንቀበለው ይገባል፤ ይህም የሚሆነው

  1. ከአላህ (ሱ.ወ) ጋር ባለን ግንኙነት ትክክለኛ እውነተኛ ተውበት በማድረግ
  2. መልክተኛውም (ሰ.ዐ.ወ) ያዘዙንን በመተግበርና የከለከሉንን በመራቅ
  3. ለወላጆቻችን፤ ለቤተሰባችንና ለዘመዶች ጥሩ በመዋል ዝምድናችንን ማጠናከር
  4. ከምንኖርበት ማህበረስብ ጋር አዲስ ምዕራፍ በመክፈት መልካምና ጠቃሚ ሰው ሆንን መገኘት፤ ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡

خير الناس أنفعهم للناس

ከሰዎች በላጩ ለሰዎች የሚጠቅም ነው

አዎ! ደረቅ መሬት ዝናብን እንደሚቀበል፤ በሽተኛ ሐኪምን እንደሚቀበልና አፍቃሪ ተለይቶት የቆየ ወዳጁን ሲያገኝ በጉጉት እንደሚቀበለው ሁሉም ሙስሊምም የረመዳንን ወር በከፍተኛ ጉጉት ይቀበላል።

ያ አላህ! ረመዳን አድርሰን ከኛም ተቀበለው፤ አንተ ሰሚና አዋቂ ነህና። አሚን!

ፅሁፉን በድምፅ ለማድመጥ ተከታዩን ሊንክ ይጫኑ፡ http://bit.ly/2I5IIfz

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here