ታላቁ ጌታ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንድንኖረው የፈለገውን የደስታ ህይወት መንገድ ተወዳጁ ነብይ ሙሀመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም አብራርተው ነግረውናል። ይህችን የደስታ ህይዎት ከቤተሰቦቻቸን፣ ከጎረቤቶቻችን፣ ከጓደኞቻችን፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች ከምናገኛቸውና ተጽዕኖ ከምንፈጥርባቸውም ይሁን ከሚፈጥሩብን ሰዎች ሁሉ ጋር እንኖራለን። ከሰዎች በላጩ በተለያዩ የህይወት ዘርፎች ሰዎችን ለማገልገል አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ የህይወት ግቡን ተረድቶ፣ የጌታን ይሁንታ (ተውፊቅ) ታድሎ
ራሱን ከህብረተሰቡ ሳያገልና እኔ ለኔ ብቻ ነው የምኖረው ሳይል ሐሳቡንና ጭንቀቱን ለነፍሱ ብቻ ከማድረግ ይልቅ ለሌላው የሚያስበውን ሰው አላህ ይዘንለት። አዎ! እኔ የምኖረው ለራሴ ነው፤ ማዳን ያለብኝም ራሴን ብቻ ነው ብሎ ማስብ የተሳሳተ አመለካከት ነው፤ ወደ አላህ ቁጣም ይወሰዳል። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ በአንድ ወቅት መላኢኮችን አንድን አገር (አካባቢ) እነዲያጠፉ ባዘዛቸው ጊዜ “ጌታችን ሆይ በዚች መንደር አንድ ጥሩ ያንተ ባሪያ አለና እንዴት እናድርግ” ሲሉት፤ ታለቁ ጌታም “በሱ ጀምሩ” ነበር ያላቸው፤ ይህ ሰው በራሱ ጥሩ ቢሆንም ጥሩነቱ ግን አልጠቀመውም ነበር፤ ምክንያቱም ጥሩ ሆኖ የኖረው ለራሱ ብቻ ስለነበር ነው፤ “ለራሱ ብቻ የኖረ ሰው መወለድ አይገባውም ነበር።” ትክክለኛ ሙእሚን ግን ራሱን አግልሎ በመስጅድ ወይም በኸልዋ ለመኖር ነፍሱ አትቀበልም፤ ይልቁንም ወደ ህይዎት መስኮች በመውረድ ይሰጣል፤ ይቀበላል፤ ይጠቅማል፤ ይጠቀማል፤ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ ይላል፡-
እያንዳንዳችን በየንጋቱ ጠዋት በሦስት መቶ ስድሳ የሰዉነት መገጣጠሚያችን ልክ ሦስት መቶ ስድሳ ሶደቃ ይጠበቅበታል። ነቢያችን ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ይላሉ“ማንኛም ሰው ፀሐይ በወጣችበት ቀን (በያንዳንዱ ቀን) ከራሱ ሰደቃ መስጠት አለበት” አቡዘር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እኔ ገንዘብ የለኝም ከየት ሰደቃ ልስጥ አላቸው፤ ነቢያችንም ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ አሉ “ከሰደቃ በሮች መካከል አላሁ አክበር፣ ሱብሀነላህ፣ አልሐምዱሊላህ፣ ላኢላሀኢለላህ ማለትና ኢስቲግፋር ማድረግ ይገኙበታል፤ በጥሩ ነገር ማዘዝህና ከመጥፎ ነገር መከልከልህ፣ እሾህ አጥንትና ድንጋይን ከሰዎች መንገድ ላይ ማስወገድህ፣ አይነ ሥውርን መምራትህ፣ መስማት የተሳነውንና ዱዳን እስኪገባው ድረስ ማስረዳትህ፣ አንድ ባለ ጉዳይ የሚፈልገውንና የምታውቀውን ነገር ማሳየትህ፤ ያለህን አቅም ሁሉ ተጠቅመህ የተጨነቀንና የሚማፀንን ሰው ለማዳን መሞከርህ፣ ባለህ አቅምና ሐይል ከደካሞች ጎን መቆምህ… ይህ ሁሉ አንተ በራስህ ላይ የምታደርገው ሰደቃ ነው፤ ከሚስትህ ጋር ፆታዊ ግንኙነት ስትፈጽም እንኳ አጅር (ምንዳ) አለህ።”
ዘይኑል ዓቢዲን ዓሊይ ቢን ሑሰይን አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ዳቦ እየተሸከሙ በጨለማ ወደ ሚስኪኖች ቤት ይወስዱ ነበር (ይህን ምግብ ለነዚህ ሚስኪኖች ማን እንደሚያመጣላቸው እርሳቸው እስከሚሞቱ ድረስ አልታወቀም ነበር)። ሰዎች ለመጥቀም መንቀሳቀስ ሠናይ ተግባር መሆኑን ለመረዳት የነቢያችን ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ባህሪ መሆኑ ብቻ ይበቃል። ነቢያችን ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም በሒራ ዋሻ ውስጥ እያሉ መላአኩ ጅብሪል በድንገት ሲመጣቸው በሁኔታው በተደናገጡ ጊዜ እናታችን ኸድጃ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ሲያረጋጓቸው በጎ ተግባራቸውን እያወሱ እንዲህ ነበር ያሉት“ወላሂ አንተን አላህ መቸም ለክፉ አይሰጥህም፤ ወላሂ አንተ ዝምድናን ትቀጥላለህ፤ ደካማን ትሸከማለህ (ታህሚሉ ከል)፤ ያጣን ታሸምታለህ (ቱክሲቡል ማዕዱም)፤ እንግዳን ትቀበላለህ እውነት ላይም ታግዛለህ።”
ለዘመዶች መልካም መዋል “ደካማን ትሸከማለህ” (ታህሚሉ ከል) በሚል ተገልጧል። “ከል’’ የሚለው ሸክም እንደ ማለት ሲሆን ወላጅ አልባ ህፃናት፣ ችግረኞች ወዘተ መርዳትን ያጠቃልላል። “ያጣን ታሸምታለህ” (ቱክሲቡል ማዕዱም)፤ ማለት ሌሎች እንዲያገኙ ትለግሳለህ እንደማለት ነው።
የአላህ ወዳጆች ሆይ…
ይኸው እኛ የአላህን ትዕዛዛትና የረሱልን ፈለግ በመከተል ልንኖረው በምንፈልገው ህይዎት ውስጥ የአላህን ውዴታ እናገኝ ዘንድ ልንጠቀምባቸው የሚገቡን የተከበረው የረመዳን ቀናት ወደኛ እየመጡ ነው
1ኛ. አላማን መወሰን
i. ወደ አላህ መመለስ:- አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ ይላል፡-
إن الله تعالى يبسط يده بالليل ليتوب مسيء النهار، ويبسط يده بالنهار ليتوب مسيء الليل حتى تطلع الشمس من مغربها
“አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ በቀን ያጠፋ ተፀፅተው ይመለሱ ዘንድ እጁን በሌሊት ይዘረጋል፤ በሌሊት ያጠፋ ተፀፅተው ይመለሱ ዘንድ እጁን በቀን ይዘረጋል፤ ይህም የሚሆነው ፀሐይ በመግቢያዋ እስከምትወጣ (እስከ አለም ፍፃሜ) ድረስ ነው።” (ሙስሊም ዘግበውታል)
ii. መዋብ (በመልካም ስራ)ና መላቀቅ (ከመጥፍ ተግባራት) /ተሀሊ ወ ተኸሊ/:- አንዳንድ በረመዳን ልንላበሳውና ልንዋብባቸው የሚገቡ መልካም ሥነ መግባራትን ቀድመን መለየት፤ ለምሳሌ እውነተኛነት፣ ታማኝነት፣ ቃልን ማክበር ወዘተ። እንደዚሁም በአንጻሩ ደግሞ ልንርቃቸው የሚገባንን አንዳንድ መጥፎ ባህሪያትን መለየትና ከነሱም መጥራት። ለምሳሌ ውሸት፣ሐሜት፣ በሀሰት መመስከር ወዘተ።
iii. ለቁርኣን ትኩረት መስጠት፡- ረመዳን የቁርኣን ወር ነው፤ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ ይላል፡-
ቁርኣን ጋር መኖር ስንል በየቀኑ አንድ ወይም ሁለት ወይም ሦስት ጁዝእ ሁሉም እንደየ አቅሙና ችሎታው መቅራት ማለት ነው። አቡ ሙሳ አል ዓሽዐሪይ እንዳስተላለፉት ነቢያችንሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ይህን ተናግረዋል፡-
تعاهدوا هذا القرآن، فوالذي نفس محمد بيده لهو أشدُّتفلتًا من الإبل في عقلها
“ይህን ቁርኣን ጠብቃችሁ ያዙ፤ የሙሐመድ ነፍስ በእጁ በሆነቸው ጌታ እምላለሁ እሱ (ቁርኣን) የታሰረች ግመል በጥሳ ለማምለጥ ከምትፈጥነው የበለጥ ለመረሳት የፈጠነ ነው።” (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል) በመሆኑም በቃል የሸመደድናቸውን (የሀፈዝነውን) የቁርኣን ክፍሎች መከለስ ያስፈልጋል።
iv. የተሰራ በደልን ማስተካክል፡- የረመዳን ወር ከመግባቱ በፊት ከሰዎች ያለ አግባብ የወሰድናቸው ንብረቶች ካሉ ለባለቤታቸው እንመልስ። ሰዎችን አምተንና ክብራቸውን ነክተን ከሆነም ይቅርታ በመጠየቅ ከሐቃቸው እንጥራ። አቡ ሁረይራ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንደዘገቡት ነቢያችንሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፡-
من كانت عنده مظلمة لأخيه فليتحلله منها، فإنه ليس ثم دينار ولادرهم، من قبل أن يؤخذ لأخيه من حسناته، فإن لم يكن له حسنات أخذ من سيئات أخيهفطرحت عليه
“ወንድሙን የበደለ ከወዲሁ (ከተበዳዩ ዘንድ በመሄድ) ራሱን ነፃ ያስደርግ፤ እዚያ (አኺራ) ወርቅም ብርም የለምና፤ ከሱ የስራ ምንዳው እየተወሰደ ለወንድሙ(ለተበዳዩ) ሳይሠጥና ኸይር ሥራው ካለቀ ወይም ከሌለው ደግሞ የወንድሙ ወንጀል እየተወሰደ በሱ ላይ ሳይጣል በፊት ዛሬ ከበደል ነፃ ይሁን።” (ቡኻሪ ዘግበውታል)
v. ዱዓን ማዘውተርና ወቅቶቹን መከታተል፡- (በፊጡር ሰዓት፣ በሱሁር ሰዓት፣ ቁርኣን ሲኸተም፣ በአዛንና ኢቃም መሀከል፣ ከግዴታ ሶላቶች በኋላ፤ ጁምዐ ከአስር ሰላት በኋላ ወዘተ..)
የአላህ ባሪያዎች ሆይ…
በዱዓ ላይ ብርቱ ጥረት አድርጉ፤ የአላህን ውዳሴ አብዙ፤ ተስፋችሁን አሳድጉ፤ የዱዓ አዳቦችን ጠብቁ፤ የአላህ ካዝና ሙሉ ነው፤ እጆቹም በሌሊትም በቀንም ለጋስ ናቸው፤ ካዝናው በመስጠት አይጎድልም። እሰኪ ተመልከቱ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ሰማያትንና መሬትን ከፈጠረ ጊዜ ጀምሮ እየሰጠ እየለገሰ ቢሆንም እርሱ ጋር ያለው ድልብ ካዝና ግን መርፌ በባህር ውስጥ ገብታ እንደምታጎድለው አንጂ አለመጉደሉን አስተውላችኋልን? በሐዲሰል ቁድስ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ ይላል፡-
يا عبادي، لو أن أولكم وآخركم، وإنسكم وجنكم، اجتمعوا في صعيد واحدفسألوني، فأعطيت كل واحد منهم مسألته، ما نقص ذلك مما عندي شيئًا
“ባሮቼ ሆይ! መጀመሪያችሁም መጨረሻችሁም፤ ሰዋችሁም ጅናችሁም፣ በአንድ ቦታ ተሰባስበው ቢጠይቁኝና ለያንዳንዳቸው የጠየቀኝን ብሰጥ፣ይህ እኔ ጋር ካለው ምንም አያጎድልም።” (ሙስሊም ዘግበውታል)
vi. አላህ ብቻ የሚያውቃቸው በሚስጥር የሚሰሩ በጎ ስራዎች ላይ መበርታት፡- እናታችን ዘይነብ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና በእጃቸው እየሰሩ ሰደቃ ይሰጡ ነበር። ነቢያችንሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ከመሞታቸው በፊት እንዲህ ብለው ነበር“ከናንት መካከል ቀድማ እኔን የምትከተለኝ ከመካከላችሁ እጀ ረጅሟ ነች።” እናታችን ዘይነብ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ከነቢያችን ሞት በኋላ ከሌሎች ሚስቶቻቸው ቀድማ ነበር የሞተችው። ዘይኑል አቢዲን የተቸገሩ ሰዎች ቤት ጨለማን ተገን አድርገው በመሄድ በራፉ ላይ ምግቦችን ያስቀምጡ የነበረ። ይህ ድርጊታቸው የታወቀው ከሞቱ በኃላ እርዳታው ሲቋረጥ ነበር።
vii. ኢዕቲካፍ መቀመጥ፡- ቡኻሪና ሙስሊም አብደላህ ኢብኑ ዑመርን ጠቅሰው እንደዘገቡት ነቢያችንሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ከረመዳን ወር የመጨረሻዎችን አስር ቀናት ኢዕቲካፍ ይገቡ ነበር (በመስጅድ ያሳልፉ ነበር)። ስለዚህ ከመጨረሻዎቹ አስር ቀናት ውስጥ ቢቻል ሁሉንም ካልሆን ከሶስት ቀናት ላላነሰ ጊዜ ኢዕቲካፍ መግባት ያስፈልጋል፤ ኢዕቲካፍ ለመቀመጥ አስበን መስጅድ በምንገባበት ጊዜ መነየት ያስፈልጋል።
viii. ዝምድናን መቀጠል፡- አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንህ ይላል፡-
ነቢያችንሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲሁ ይህን ተናግረዋል፡-
من أحب أن يُبسط له في رزقه، ويُنسأ له في أثره، فليصلرحمه
“ሲሳዩ እንዲሰፋለትና ፋናው እንዲቀርለት የፈለገ ሰው ዝምድናውን ይቀጥል።” (ቡኻሪና ሙስሊም ተስማምተውበታል)።
ix. ሁሉንም ሶላቶች በጀመዓ መስገድ፡- አቡ ደርዳእ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ነቢያችንሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ሲሉ ሰምቻለሁ በማለት አስተላልፈዋል፡-
ما من ثلاثة في قرية ولا بدو لا تقام فيهم صلاة إلا قد استحوذ عليهمالشيطان فعليك بالجماعة، فإنما يأكل الذئب من الغنم القاصية
“በመንደርም ይሁን በዱር ሦስት ሰዎች ሶላተል-ጀመዓ ሳያቋቁሙ አንድ ላይ አይኖሩም ሰይጣን የተቆጣጠራቸው ቢሆን እንጂ፤ ጀመዓን (ህብረትን) አደራህን፤ ከፍየሎች መካከል ተኩላ የሚበላው ለብቻዋ ተነጥላ ያለችውን ነውና።” (አቡ ዳውድ ዘግበውታል)።
x. የጠዋትና የማታ እንዲሁም በየሁኔታው የሚባሉ ዚክሮችን ጠብቆ ማለት፡- አብደላህ ቢን ቡስር እንደዘገቡት አንድ ሰው ወደ ነቢያችንሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም መጣና“የአላህ መልክተኛ ሆይ የኢስላም ህግጋቶች በዙብኝና አጥብቄ የምይዘው አንድ ነገር ይንገሩኝ አላቸው። ነቢያችንምሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ አሉት “ምላስህ በአላህ ዚክር ከመርጠብ አትቦዝን።” (ቲርሚዚ ዘግበውታል)።
xi. ግዴታ የሆነውን ዘካ ለማውጣት መፋጠን ፡-
“እነዚያ ያመኑ። መልካም ሥራዎችንም የሠሩ። ሶላትንም ያስተካከሉ። ዘካንም የሰጡ ለነርሱ በጌታቸው ዘንድ ምንዳቸው አላቸው። በእነርሱም ላይ ፍርሃት የለባቸውም እነርሱም አያዝኑም።” (አል-በቀራ 2፤ 277)
አቡ ሁረይራ እንዳስተላለፉት ነቢያችንሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋልለ፡-“አላህ ገንዘብ ሰጥቶት ዘካውን ያላወጣ ሰው ሁለት ጡቋቁር አይኖች ያለው ተናዳፊ እባብ ሆኖ የቂያማ ቀን ይመጣበታል፤ ከዚያም ጉንጭና ጉንጩን ይዞ ያጣብቀዋል፤ይነድፈዋል። እኔ ያከማቸኸኝ ገንዘብህ ነኝ ይለዋል፤ ነቢያችንሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ይህን ተናግረው የሚቀጥለውን አንቀጽ አነበቡ፡
“እነዚያም አላህ ከችሮታው በሰጣቸው ገንዘብ የሚነፍጉ እርሱ ለእነሱ ደግ አይምሰላቸው። ይልቁንም፤ እርሱ ለነሱ መጥፎ ነው። ያንን በርሱ የነፈጉበትን በትንሣኤ ቀን (እባብ ኾኖ) ይጠለቃሉ። የሰማያትና የምድርም ውርስ ለአላህ ብቻ ነው። አላህም በሚሠሩት ሁሉ ውስጥ ዐዋቂ ነው።” (ኣሊ ዒምራን 3፤ 180) (ቡኻሪ ዘግበውታል)።
ከዚህ በተጨማሪ ዘካተል ፊጥርን ከዒድ ሶላት በፊት ማውጣት።
xii. የኢድ ሶላት፡- የኢድ ሰላትን በሰፊ ሜዳ ለመስገድ ቤተሰቡን በሙሉ ይዞ መውጣት።
2ኛ. በረመዳን ወር ከራሴ፣ ከቤተሰቤ፣ ከሥራ ባለደረቦቼ፣ ከሚስቴ/ከባሌ፣ ከልጆቼና በትራንስፖረት ላይ የሚኖረኝን ፕሮግራም ማስቀመጥ።
ከራስ ጋር
- ለተውበትና ኢስቲግፋር መፍጠን፤
- በሳምንት አንድ ቀን አንድ ድሃ ሚስኪን ማብላት፤
- በሳምንት አንድ ቀን አላህ ብቻ የሚያውቀው የሚስጥር ሰደቃ ማውጣት፤
- በየቀኑ ከአንድ ጁዝ ያላነሰ ቁርኣን መቅራት፤
- ኢማንን የሚያጠናክሩ ፕሮግራሞችን መከታታል፤
- አላህን ለመታዘዝ ያወጣሁትን ፕሮግራም የሚያጠናክሩልኝ ፕሮግራሞችን ብቻ በመከታተል ቴሌቪዥኔን መቆጣጠር
- የወሩ መፈክሬ “ተስፋዬ አላህ እንዲቀበለኝ ነው’’ የሚል ማድረግ፤
- ዝምድናየን መቀጥል (ዘመዶቼን የምዘይርበትን ጊዘያት ማስቀመጥ)፤
- በወሩ አንድ ጊዜ ለመገሰጥና ለመመከር መቃብሮችንና ሆስፒታሎችን መጎብኘት
- የበደሉኝን ሰዎች ሁሉ ይቅር ማለትና በሌሉበት ለነሱ ዱዓ ማድረግ፤
- መንገደኛን ወይም አላፊን በቴምር እንኳ ቢሆን ለማስፈጥር መጣጣር፤
- ቤተሰቦቼን ለኸይር ሥራ ላይ ማሰማራት ወደ አላህ ትዕዛዝ መገፋፋት
- በሥራዬ ሁሉ አዎንታዊ (ኢጃቢይ/positive) መሆንና ለጓደኞቼ ቅርብና አርአያ መሆን፤
- ጓደኞቼን ለፍጡር ወደ ቤቴ መጥራትና አንዳንድ ስጦታዎችን ማቅረብ፤
- የጠዋትና የማታ እንዲሁም የተለያዩ ገዜያት አዝካሮችን ዘወትር ማለት፤
- ከአዛን በፊት መስጊድ መግባትና ቢያንስ በየቀኑ 12 ረከዓ ሱና ሶላቶችን መስገድ፤
- በተለይም የፈጅር፣ የኢሻና የተራዊህ ሶላቶችን በጀመዓ ጠብቄ መስገድ።
ከቤተሰብ ጋር
- ከፍጡር በፊት የማታ ዚክርን ለማለት መሰባሰብ፤
- ከአስር ሶላት በኋላ እለታዊ ቁርአን (ዊርድን) ለመቅራትና አንዳንድ ጠቃሚ ምክሮችን መለዋወጥ፤
- በአንድ የተመረጡ ዲናዊ ፕሮግራም ዙሪያ መሰባሰብና መወያያት፤
- በአንድ ሰሐቢይ ወይም የቁርኣን ምዕራፍ ዙሪያ እለታዊ ውድድር ማካሄድ፤
- በረመዳን ውስጥ አንድ ሱራ (ምዕራፍ) ለመሐፈዝ መስማማት፤ (ለምሳሌ ሱረት ኑር፣ አል-ሑጁራት፣ አል-ሙእሚኑን..) ላሸናፊዎችም ሽልማት ማዘጋጀት፤
- በየሳምንቱ አንድ ጊዜ ለችግረኛ ሰደቃ ለመስጠት መስማማት (ለአላህ ብሎ መሥራትን ሁሉም የቤተሰቡ አካል እንዲወድና እንዲለማመድ ሰደቃውን በተለያየ ጊዜ የተለያየ ሰው ቢሰጥ ይመረጣል)፤
- በየሳመንቱ ቢያንስ አንድ ፆመኛ ለማስፈጠር ከረመዳን በፊት ፕረግራም ማውጣት፤
- አንድ ቅርብ ዘመዳችንን ወደ ቤታችን መጥራት (ለዚህ ፕሮግራም የሚያስፈልጉ ዝግጅቶችን በዝርዝር አስቀምጥ)፤
- በየዕለቱ ከምንሰራው ኢባዳዎች (ሶላት፣ ዚክር፣ ቁርኣን፣ ተስቢህ..) አኳያ ራሳችንን የምንገመግምበት መንገድ ላይ ተስማምተን ማስቀመጥ፤
- በፍጡር ሰዓት ተሰባስበን ዱዓ ማድረግ፤ በዱዓችን ቤተሰቦቻችንን፣ ዘመዶቻችንን፣ ወንድሞቻችንንና ባጠቃላይ ሙስሊሙን ኡማ ማስታወስ፤ በተለይ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ሙስሊሞች ላይ ያጋጠመን ታላቅ ፊትና አላህ እንዲያከሽፈውና የሙስሊሙ አንድነት እንዲጠናከር ወደ አላህ መማጸን፤
- ከቤተሰቦቻችን ጋር ሆነን በየቀኑ ጁዝ የሚቀራበት መስጅድ መሄድ (የራሳችንን ቁርኣንን ይዘን መሄድ፤ ለሰጋጆች ደግሞ ሐዲያ ይዘን መሄድ)፤
- በሳምንት አንድ ጊዜ ለጎረቢቶቻችን ሐዲያ መስጥት (ይህንንም በሰንጠራዥ ሠርተን ከእቅዳችን እናካተው)፤
- ለዒድ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ቢበዛ በመጀመሪያውና በሁለተኛው ሳምንታት ውስጥ ገዝተን እንጨርስ፤
- አዋቂ ወንዶችና ወንድ ህጻናት በመስጅድ ውስጥ አዋቂ ሴቶችና ሴት ህጻናት ደግሞ በቤት ውስጥ ኢዕቲካፍ የሚቀመጡበትን ሁኔታ በፕሮግራም ማስቀመጥ፤
- ለቤተሰቡ መፈክር ማስቀመጥ፤ (ለምሳሌ “ወደ አላህ ማንም አይቀድመኝም!”፣ “ረመዳን የደስታ በር!”፣ “በከዕባ ጌታ እምላለሁ ፍላጎቴን አገኘሁ!”፤ “የጀነት ሺታ ከረመዳን ጋር ይሸተኛል!”፤ “የተሰናባችን ፆም ፁሙ!”…)፤
ከሚስት ጋር
- በሁለታችሁ መካከል አላህ ብቻ የሚያውቀው የሚስጥር ኢባዳ ለመስራት መስማማት (ሰደቃ፣ ዚክር፣ ቂያም..)፤
- ያስቀምጥነውን ፕሮግራምና ልጆችን በየጊዜው መከታተል፤
- ባል ሚስቱን/ ሚስት ባሏን ለሌሊት ሶላት ማስነሳትና ማገዝ፤
- ሚስት ፍጡር ስታዘጋጅ መርዳት፤ የፍጡር ምግብ አይነቶችን በማብዛት የሚስትህን ሂይወት አታባክን፤
- ሚስትህን ጥያቄ በማብዛት አለማድከም፤
- የሁለቱንም ቤተሰቦች ለኢፍጧር መጥራት፤ ፍጡሩን ቀለል ማድረግ፤ ረመዳን የምግብ ኤግዚቢሽን አይደለም!
- በየዕለቱ ቁርኣን መቅራትና እስቲግፋርን በጋራ ማድረግ፤
- በበጎ ስራዎች መተባበር (የረመዳን ስጦታ፣ ፆመኛን ማስፈጠር፤ ድሆችን መርዳት…)
- ለሚስትህ በሌለችበት ዱዓ አደርግላት፤ ለስህተቶቿም ምክንያት ፈልግላት፤ ሚስትም ለባሏ እንደዚያው፤
ከልጆች ጋር
- ከልጆችህ ጋር ሆነህ ቴምርና ውሃ በማዘጋጀት በፉጡር ሰዓት በመንገድ ላይ ቆማችሁ/በመስጊድ ፆመኞችን አስፈጥሩ፤
- ለልጆች ሐዲያ በመስጠት ለጎሮቤቶችና ለጓደኞቻቸው እንዲሰጡ አድርግ፤
- ልጆች ሶላተል ጀመዓ እንዲሄዱ ማበረታታት በተለይም ሱብሂና ኢሻ ሶላቶች፤
- ልጆች ከግል ወጭያቸው ሰደቃ እንዲሰጡ ማበረታታት፤
- ከልጆች እድሜ ጋር የሚመጥን ልዩ ውድድር ማዘጋጀት፤
- ከልጆች ጋር በመወያየት የሚመጥናቸውን ፕሮግራም መምረጥ፤
- ሁሉም ልጆች የሙሃሰባ (ራሳቸውን የሚገመግሙበት ፕሮግራም) ማድረግ፤
- ሁሉም ልጆች እንደየአቅማቸው እለታዊ የቁርኣን ዊርድ (መጠን) እዲኖራቸውና መቅራታቸውን መከታተል፤ በጣም ህፃን የሆነና መቅራት የማይችል ልጅ ሌላው ሲቀራ ያዳምጥ፤
- በመመካከሪያ ፕሮግራም ልጆች (የሚሰማቸውን) ኻጢራ (ምክራዊ ሀሳብ/ ውልብታ) እንዲናገሩ እድሉን መስጠት፤
- የሰሐባ ልጆች የረመዳን ውሎን መማማር።
ከጎረቤት ጋር
- የኢሻ፣ የተራዊህና የፈጅር ሶላት በጀመዓ ለመስገድ በአንድነት ወደ መስጊድ መሄድ፤
- በረመዳን ወር ከአንድ ጊዜ በላይ ቁርኣን ለሚያኸትሙ ሽልማት ማዘጋጀት፤
- የረመዳንን ፕሮግራም በተሻለ መልኩ ለሚፈጽሙ ቤተሰቦች ሽልማት ማዘጋጀት፤
- በረመዳን ልንላበሳቸው የሚገባ አንዳንድ መልካም ባህሪያትን ለይቶ ማስቀመጥ (እውነተኝነት፣ አማና፣ ዝምታ፣ መቻቻል፣ይቅር ማለት፣ ቃል ኪዳንን መጠበቅ፣ ወላጆችን መንከባከብ…)፤
- በቤት ውስጥ የቁርኣንና የጠቅላላ እውቀት ውድድር ለማድረግ መስማማት
- በሳምንት አንድ ቀን የረመዳን ምሽት ፕሮግራም መያዝ
- ረመዳንን ለመቀበል ቤቶችን ማስዋብ
- ለራስና ለጎረቢት ቤቶች መፈክር (መልእክት) ማስቀመጥ፤ (ለምሳሌ “ኑእሚኑ ሰዓ”- ኑ አንድ ሰዓት እንመን /ለኢማን እንቀማመጥ!/)
- የማፍጠሪያ ምግብ አሰባስቦ የአካባቢውን ድሃዎች በጋራ መጋበዝ
ከጓደኞች ጋር
- ረመዳንን ለመቀበል የሥራ ቦታዎችን ማዘጋጀትና ማስዋብና (የንግድ ቦታ፣ ካምፓኒ፣ ፋብሪካ..)፤
- ጓደኞች ለሩብ ሰዓት ያህል ቁርኣን አብሮ የመቅሪያ ጊዜ ማዘጋጀት፤
- ጓደኛሞች ከዙህር ሶላት በኋላ ኻጢራ (ውልብታቸውን) መነጋገር፤
- በጓደኛሞች መካከል የጠቅላላ እውቀት ውድድር ማዘጋጀት፤
- አንድ የቁርኣን ምዕራፍ ለመሐፈዝ መስማማት፤
- ከኢስላም ታላላቅ ስብዕናዎች አንዱን መርጦ በዙሪያው ጥናት ማድረግ (ለምሳሌ ኡመር ኢበን አብዱል አዚዝ)
- አንድን ፕሮግራም መከታተልና በሱ ዙሪያ ውይይት ማድረግ፤
- ማህበራዊ ኤግዚቢሽን ማዘጋጀት (አልባሳት፣ የትምህርት መሣሪያዎች….)
- ገቢያቸው ውስን ከሆኑ የቅጥር ሠራተኞች ጋር የማህበራዊ ትብብር ፕሮግራም ማድረግ፤
- ለሠራተኞች ለማከፋፈል የረመዳን ሻንጣ (ስጦታ) ማዘጋጀት (በወሩ ውስጥ ሁለት ወይም ሦስት ጊዜ ሊሆን ይችላል፣ ስጦታው ላይ “የረመዳን ስጦታ” ብሎ መጻፍ)፤
- ዘካተል ፊጥርን ሰብስቦ ለድሃ ለሠራተኞች ማከፋፈል፤
- ጓደኛሞች ጠቃሚ መጣጥፎች፣ ካሴቶችንና ሲዲዎችን መለዋወጥ፤
- ጓደኛን ቤተሰቦች በአንዱ ጓደኛ ቤት ውስጥ ለፍጡር መጋበዝ፤ ፍጡሩን ቀለል ማድረግ፤
- ጓደኛሞችን በጠቅላላ በምግብ ቤት ወይም በመስጅድ ክበብ ውስጥ በፊጡር ላይ ማሳተፍ (ኢፍጣር ጀማኢ)
- በካምፓኒ ወይም በፋብሪካ ውስጥ ሁሉም በዙሪያው የሚሰባሰቡበት አንድ መፈክር (መልዕክት) ማስቀመጥ፤
- አንዳንድ ጓደኞችን በረመዳን ወር ዑምራ እንዲሰሩ ማበረታታትና ለሐጅ ዝግጅት ማድረግ።
በመኪና ውስጥ
- ቁርኣንን በካሴት ማዳመጥ፣ የጠዋትና የማታ አዝካሮች ካሴት መከታተል፤
- ከጓደኞችና ከተሳፋሪዎች ጋር ልዩ የረመዳን ስጦታ መለዋወጥ፤
- ወደ ቤታችን ስንመለስ ማፍጠሪያ ማዘጋጀት (የታሸገ ቴምር)፤ ፀሐይ በምትጠልቅበት ጊዜ ዱዓ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ማስታወስ፤
- በየቀኑ ኸዋጢርን መነጋገር አስፈላጊ ስለመሆኑ መወያየት፤
- በመንገድ ላይ ውድድር ማድረግና አስቸኳይ ሽልማቶችን ማዘጋጀት፤
- በመንገድ ላይ ኢስቲግፋርና ተሲቢህ ማድረግ፣ ቁርዐን በኪስ ይዞ መዞርና መቅራት።
ጥሩውን ሰምተው ከሚተገብሩት ያድርገን፤ የተከበረውን ወር ይቀበለን ዘንድ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንለምን!
jezakumullah ethiomuslim betam arif masgenzebya new
በጣም ጠቃሚ እና በበሳል እይታ የተቃኘ ሆኖ አንኝቼዋለሁ ማሻአላህ በርቱ። ተደራሽነቱን ከማስፋት አንጻር ቢታሰብበት መልካም ነው እላለሁ።