ፆምና ጥበባቱ

1
5337

ኢስላም አንድን ነገር ለጥበብ ቢሆን እንጂ አይደነግግም፡፡ አንዳንዱ ቢረዳውና ሌላው ባይረዳውም፡፡ አላህ ሱብሃነሁ ወተአላ የድንጋጌው ጥበባት ድንቅ ነው፡፡ በአፈጣጠሩም በትእዛዛቱም ጥበበኛ ነው፡፡ ምንም ነገር ለከንቱ አልፈጠረም፤ ምንም ነገር ለቀልድ አላዘዘም፡፡

አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ከዓለማት የተብቃቃ ነው፡፡ ፍጡራኑና ባሪያዎቹ ግን ወደርሱ ከጃዮች ናቸው፡፡

ባሪያዎች የሚፈፅሙት ወንጀል እንደማየጎዳው ሁሉ ትእዛዛቱ ስለተፈፀሙለትም ጥቅምን አያገኝም፡፡ ምክንያቱም የአላህን ትእዛዛት የመፈፀም ጥቅም ወደታዛዦች ተመላሽ ነውና፡፡

የሀይማኖቱ ድንጋጌ ሰነዶች ባመለከቱት መሰረት ፆም ብዙ ጥበባትና ጥቅሞች አሉት፡፡ ከነሱም ውስጥ፡-

1. የአላህን ትእዛዛት በመፈፀም ራስን ማጥራት፤ ከእቀባዎቹ ራስን በመግታት ሙሉ ታዛዥነት ላይ ነፍስን ማለማመድ፤ ነፍስን ከስሜቷ በማገት ዙሪያዋን ከተበተቧት ማነቆዎች ነፃ ማውጣት ነው፡፡ ሰውዬው የአላህን ውዴታ ከጃይ ባይሆንማ(በረመዳን ቀን ክፍለ ጊዜ) ከፈለገ ይበላል፣ ይጠጣል ከባለቤቱም ጋር ግንኙነት የፈፅማል፡፡ ይህን ሁሉ ቢያደርግ ከአላህ በስተቀር ማንም አያውቅበትም፡፡ ይህን አስመልክቶ አቡሁረይራ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና በዘገቡት ሀዲስ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ይላሉ፦

“ነፍሴ በጁ በሆነችው ጌታ እምላለሁ የፆመኛ ሰው የአፍ ጠረን አላህ ዘነድ ከሚስክ ሽቶ በላይ ጣፋጭ ነው‘ምግብ መጠጥና ስሜቱን ለእኔ ብሎ ነው የተወው። የአደም ልጅ ስራ በሙሉ ለራሱ ነው። ፆም ሲቀር እርሱ ለእኔ ነው። እርሱን እኔ ነኝ የምመነዳው።” (ቡኻሪና ሙስሊም) 

2. ዶክተሮችና የጤና ባለሙያዎች እንዳረጋገጡት ፆም የሰውነትን ጤና ለመጠበቅ ይጠቅማል፡፡ ከዚህም ባሻገር የሰው ልጅን መንፈሳዊ ማንነቱ በቁሳዊ ክጃሎቱ ላይ ድልን ይጎናጸፍ ዘንድ ያግዘዋል። የሰው ልጅ  ወደ ጥሩም ወደ መጥፎም የማዘንበል ተፈጥሯዊ አቅም ተሰጥቶታል። ብሎም የአፈጣጠሩ መዋቅር የተቦካ ጭቃ እንዲሁም ከአላህ የሆነ መለኮታዊ እስትንፋስ(ሩህ) ውህድ ነው፡፡ አንዱ ለውርደቱ ምክንያት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ማዕረጉን ይጨምርለታል። ጭቃዊ አፈጣጠሩ በማንነቱ ላይ የበላይ ከሆነ ውርደትን ከመላበስ በተጨማሪ ወደ እንስሳ ደረጃ ያዘቅጠዋል፤ አልያም መንገዱን የሳተ ያደርገዋል። ግና መንፈሳዊ ማንነቱ የበላይ ከሆነ ወደ መላእክት አድማስ ከፍ ይላል። ልዕልናንም ይጎናፀፋል፡፡ ስለዚህ በፆም ወቅት መንፈሳዊ ማንነት ቁስን፤ ህሊና ስሜትን ያሸንፋሉ፡፡ ጿሚ የሆነ ሰው በየቀኑ እስኪያፈጥር ድረስ የሚያጣጥመው ደስታ ሚስጥሩ ይህ ነው። በሃዲስ እንዲህ ተብሏል፦

“ለፆመኛ ሁለት ደስታዎች አሉት፡፡ ሲያፈጥር በማፍጠሩ ይደሰታል። ከጌታው ጋር ሲገናኝም በጾሙ ይደሰታል፡፡” ((ቡኻሪና ሙስሊም) 

3. ፆም ፍላጎትን የመግሪያ፣ ነፍስን (ከመጥፎ ጎዳና) ታግሎ የመጣያ፣ ብሎም ትዕግስትን መለማመጃ የሆነ ታላቅ የንቅናቄ አውድማ ነው። የሰው ልጅ በፍላጎት የተከበበ አይደለምን? መልካም ነገርስ በፍላጎት እንጂ ይገኛልን? (ዲን) እምነትስ ታዛዥ በመሆን ላይ መጽናትና ከወንጀል መራቅ ላይ ብርቱ መሆን አይደለምን? በዚም ጾም በራሱ ሁለት የትዕግስት ምህዳሮችን ያመላክተናል።

አንደኛ: የአላህ መልእክተኛ ሰለለሁ ዓለይሂ ወሰለም የረመዳንን ወር የትዕግስት ወር ብለው ሲጠሩት እንዲሁ አልነበረም። በሀዲስ ከኢብን ዐባስ እና አሊይ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንደተጠቀሰው “የትዕግስት ወር (የሆነውን ረመዳን) መጾም፤ እንዲሁም ከእያንዳንዱ ወር ሶስት ቀን መጾም የደረትን ዝገት ያስወግዳሉ።” በዚህ ሀዲስ የደረት ዝገት  ሲባል የነፍስን ውስወሳና አባይነት ነው። እንዲሁም ተንኮልንና ንዴት(ብስጭት) ነውም ተብሏል። 

ሁለትኛ: የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንደገለጹት “ጾም ጋሻ ነው”። ይህንንም በተለያዩ ዘገባዎች ብዛት ባላቸው ሰሃቦች ተነግረው በሀዲስ እናገኛቸዋለን። ለአብነት ያህል ከአቡ ሁረይራ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና  የተዘገበው ሀዲስ “ጾም በዚህች ዓለም ከወንጀል መጠበቂያ፤ በመጨረሻይቱ ቀንም ከእሳት መዳኛ ነው።” ዑስማን ቢን ዐስ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና በዘገቡት ሌላ ሀዲስ “አንዳቹ በጦርነት እንደሚከላከልበት ጋሻ ጾምም ከእሳት መከላከያ (ጋሻ) ነው።” (አህመድና ነሳኢ) እንዲሁም አቢ ኡማማ በጠቀሱት ሌላ ሀዲስ ደግሞ “ጾም ጋሻ ነው። እሱም ከሙእሚን ምሽጎች ውስጥ አንዱ ነው።” (ጦበራኒ)

4.ወሲባዊ ስሜት ሸይጣን የሰውን ልጅ ለማጥመም ከሚጠቀምባቸው አደገኛ መሳሪያዎች ውስጥ ዋነኛው መሆኑ ልዩነት የሌለበት ቁም ነገር  ነው። አንዳንድ የስነ_ልቦና ባለሞያዎች ወሲባዊ ስሜት ለሰው ልጅ የእለት ተእለት ክንውኖች ዋና አንቀሳቃሽ ሀይል ነው እስከማለት ደርሰዋል:: የዛሬዋን የአውሮፓ ስልጣኔ ያስተዋለ ልቅ የወሲባዊ ግንኙነቶችና ያልተገራ ስሜት  ያስከተሉትን የሞራል ልሽቀትና በሽታ ለብዙ ጥፋቶችና ውድመቶች ሰበብ እንደሆነ ይረዳል::

ጾም በተለይም ምንዳን ከአላህ ተፈልጎበት የተፈጸመ ከሆነ ይህን ስሜት በማረቅና ደረጃውንም ከፍ በማድረግ ረገድ ዓይነተኛ አስተዋጽኦ አለው። ለዚህም ኢብኑ መስዑድ በጠቀሱት ሀዲስ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም አላህ ከችሮታው እስኪያብቃቃቸው ድረሰ የትዳርን ወጪ መሸፈን ለማይችሉ ወጣቶች ሲያብራሩ እንዲህ በለዋል፦

“ወጣቶች ሆይ! ከናንተ የትዳርን ጣጣ የቻለ ያግባ። እሱ እይታን ይሰበራል ብልትንም ይጠብቃል። ይህን ማድረግ ያልቻለ ግን በጾም አደራውን። እሱ(ጾም) ከልካይ ይሆንለታል።” (ቡኻሪ)

5. ሌላኛው የፆም ጥበብ ደግሞ ፆመኛው አላህ በርሱ ላይ የዋለለትን ፀጋ ምን ያህል እንደሆነ እንዲገነዘብ ያግዘዋል። የሰው ልጅ ትኩረት ሳይሰጣቸው በመቅረቱ የተነሳ አእላፍ ችሮታዎች ያመልጡታል። የፀጋዎች ምንነት የሚታወቀው ሲወገዱ መሆኑ እሙን ነው። የነዚህ ጸጋዎች ተቃራኒ ሲከሰት ትርጉማቸው ይበልጥ ግልጽ ይሆናል። ይህም ሰው ሲራብና ሲጠማ በልቶ የመጥገብንና ጠጥቶ የመርካተን ፀጋ ይረዳል፡፡ ከርሀቡ በኋላ በልቶ ሲጠግብ ከጥማቱ በኋላ ጠጥቶ ሲረካ ከውስጡ በሚመነጭ ስሜት “አልሃምዱሊላህ” በማለት መስጋናውን ለጌታው ያደርሳል። ይህ ሂደትም አላህ የዋለለትን ችሮታ በማስተዋል አመስጋኝ እንዲሆን ይገፋፋዋል፡፡ ይህንኑ እውነታ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሀዲስ ይጠቁመናል። እንዲህ ይላሉ፦ “ጌታዬ የመካን ሸለቆዎች በሙሉ ወርቅ ላድርግልህ አለኝ። (ይቅርብኝ) ጌታዬ ሆይ! ግና አንድ ቀን ጠግቤ አንድ ቀን መራብን (እመርጣለሁ)። የተራብኩ ጊዜ ወዳንተ እተናነሳለሁ፤ አስታውስሃለሁም፡፡ የጠገብኩ ጊዜ ደግሞ አመሰግንሃለሁ፡፡ (አህመድና ትርሚዚ)

6. ፆም በተለይ የረመዳን ወር ጎላ ያለ ማህበራዊ ፋይዳ አለው፡፡ የሚበላ ያለውም የሌለውም ቀኑን (በጾም)እንዲራብ ያደርጋል፡፡ ይህም እቀባ የግዴታ እኩልነትን ያሳያል፡፡ በዚህም ፆም በባለፀጋዎችና ሀብታሞች ልቦና ውስጥ የድሆችንና ነዳውያንን የርሃብ ሰቆቃ ይዘራል። ኢብኑል ቀዪም እንዳሉትም “የሚስኪኖችን ከባድ የረሃብ ስሜት ያስታውሳቸዋል።”

ታላቁ ዓሊም ኢብኑ ሐማም እንዲህ ይላሉ፦ “ውስን ለሆኑ ሰዓታት የረሀብን ስቃይ ይቀምሳል። በዚህም ሁኔታ በሁሉም ጊዜያት ከረሀብ ጋር ለሚኖሩ ሰዎች ለመድረስ ይቻኮላል።

በዚህም ለወር ያህል የሚቆይ ተግባራዊ ማስታወሻ እውን ይሆናል። ይህ ማስታወሻ እርስ በርስ መተዛዘንን፣ አንዱ አንዱን እንዲንከባከብ፤ ብሎም በግለሰቦች መሃከል ያለውን የመተዛዘን ስሜት ይጎለብት ዘንድ ጥሪውን ያስተላልፋል። ለዚህም ረመዳንን “የመተባበሪያ ወር” የሚል ስያሜ የሰጡ የሀዲስ ዘገባዎች ተወስተዋል። ከነዚህም ውስጥ ከሰልማን የተወራው ሀዲስ ይገኝበታል። ቡኻሪና ሙስሊም በዘገቡት ሀዲስ ደግሞ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም በረመዳን በመልካም በመለገስ ከአውሎ (ንፋስ) ይበልጣሉ መባሉም ግልጽ ነው።

ከዚህም የተነሳ ታላቅ ምንዳ ከሚገኝባቸው ተግባሮች ተርታ ጾመኛን ማስፈጠርን እናገኛለን። በሀዲስ እንደተዘገበው“ጾመኛን ያስፈጠረ ከጾመኛው ምንም ዓይነት ምንዳ ሳይቀነስ የጾመኛውን ይህል ምንዳ ያገኛል።” (አህመድና ቲርሚዚ)

7. ከዚህ በፊት የተጠቀሱትን ጥበባት በሙሉ ጠቅልሎ የሚይዘው ደግሞ ጾም የሰው ልጅን ወደ ተቅዋ ደረጃ በማድረስ የሙተቆችን ማዕረግ እንዲጎናጸፍ ያግዘዋል። ኢማም ኢብኑል ቀዪም እንዲህ ይላሉ፦ “ጾም ለውጫዊ የሰውነት ክፍሎች ደህንነት ብሎም ለውስጣዊ ጥንካሬው የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ያበረክታል። … ጾም የቀልብን እና የሰውነት አካላትን ጤንነት ይጠብቃል። በሸህዋ (መጥፎ ስሜት) ምክንያት የተነጠቁትን መልካም ማንነትና ስብእና ይመልስላቸዋል። ጾም ወደ ተቅዋ ለሚደረገው ጎዞ የአጋዥነት ሚናው ከፍተኛ ነው። ይህንንም በማስመልከት አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ ብሏል፦


يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا كُتِبَ عَلَيْكُمُ الصِّيَامُ كَمَا كُتِبَ عَلَى الَّذِينَ مِن قَبْلِكُمْ لَعَلَّكُمْ تَتَّقُونَ

እናንተ ያመናችሁ ሆይ ጾም በነዚያ ከናንተ በፊት በነበሩት (ሕዝቦች) ላይ እንደ ተጻፈ በናንተም ላይ ተጻፈ (ተደነባ) ልትጠነቀቁ ይከጀላልና፡፡ አልበቀራ 183

የረመዳን ጾም ልዩ የሆነ ትምህርት ቤት የመሆኑ እውነታ ግልጽ ነው። ኢስላም ተማሪዎቹን ታላቅ በሆነ እሴት ብሎም ደረጃው በላቀ መርህ ተግባራዊ በሆነ መልኩ ለማነጽ በየአመቱ የሚከፈተው ትምህርት ቤት ነው። ይህን እድል በመጠቀም በውስጡም ለጌታው ልግስና እራሱን ያዘጋጀ ድኗል። አላህ እንዳዘዘው አድርጎ አሳምሮ የጾመ ብሎም የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ስርዓት ባስያዙት(በደነገጉት) መሰረት ሰላትን በአግባቡ ያቆመ በእርግጥም ፈተናውን አልፏል። ከዚህ ታላቅ ወቅትም(ረመዳን) ንግዱ እጅጉን አትራፊ ሆኖለት ይወጣል።

የአላህን ምህረት ማግኘት ብሎም ከእሳት ቅጣት መዳንን የሚያህል ታላቅ ትርፍና ስኬት እንዴትስ ይኖራል?

አቡሁረይራ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ከአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ይዘው እንዳወሩት እንዲህ ብለዋል፦ “ረመዳንን ከውስጡ አምኖና አስቦ የፆመ ያለፈው ወንጀሉ ይማርለታል።” (ቡኻሪና ሙስሊም)

1 COMMENT

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here