ጤናማ ረመዳን ለማሳለፍ የሚረዱ ጥቆማዎች

1
11200

ይህ ጽሁፍ በረመዳን ጾም ወቅት ከሚፈጠሩ የተለመዱ የጤና መታወኮች ለመጠበቅ የሚረዱ ምክሮችን ያዘለ ነው፡፡ እነኚህን ምክሮች በትክክል ከተከተሉ በአላህ ፍቃድ የረመዳንን በርካታ መንፈሳዊ ጥቅሞች በመልካም ጤንነት ላይ ሆነው ለመቋደስ ይችላሉ፡፡

በተከበረው የረመዳን ወር የምንመገበው ምግብ በመደበኛ ጊዜ ከምንመገበው ምግብ እጅግ የተለየ መሆን የለበትም፡፡ ይልቁንም በተቻለ መጠን ቀላል ያለ ሊሆን ይገባል፡፡

የምንመገበው ምግብ ያለንን የክብደት መጠን ጠብቆ ለማቆየት የሚያስችል እንጂ ከመጠን በላይ ሊያወፍረን ወይም በተቃራኒው ከመጠን በላይ ሊያከሳን አይገባም፡፡ ነገር ግን እጅግ ወፍራም የሆኑ ሰዎች ክብደት መጠናቸውን ለማስተካከል ረመዳን የተመቻቸ እድል ይፈጥራል፡፡

የምንጾመው ለረጅም ሰዓት በመሆኑ የምንመገባቸው ምግቦች በዝግታ የሚፈጩ የምግብ አይነቶች ቢሆኑ ይመረጣል። ፋይበር ያላቸው ምግቦች ለመፈጨት እስከ ስምንት ሰዓታት የሚወስድባቸው ሲሆን ፋይበር የሌላቸው ምግቦች ግን ከ3-4 ሰዓታት ውስጥ ተፈጭተው ያልቃሉ። ይህም በስሁር ወቅት ፋይበር ያላቸው የምግብ አየነቶች ከተመገብን ጨጓራችን ከቀትር በፊት ባዶ ሆኖ ከሚያደርስብን ከፍተኛ ርሀብና ድካም ይታደገናል፡፡ ይህም ኢባዳችንን እና ስራችንን በአግባቡ እንድንሰራ በከፍተኛ ሁኔታ ያግዘናል፡፡

እንደ በቆሎ፣ ስንዴ፣ አጃ፣ ማሽላ፣ ሩዝ፣ ባቄላ እና አተር የመሳሰሉ ያሉ ጥራጥሬ እህሎች በውስጣቸው ከፍተኛ የፋይበር መጠን ያላቸው በመሆኑ በጨጓራችን ውስጥ ለመፈጨት ረዘም ያለ ጊዜ ይወስዳሉ፡፡በአንፃሩ ደግሞ በውስጣቸው የስኳር ንጥረ ነገርን የያዙ እንደ ፉርኖ ዱቄት ያሉ ምግቦች ደግሞ በጨጓራችን ውስጥ በፍጥነት ተፈጭተው ያልቃሉ፡፡

ገለባ ያላቸው ጥራጥሬ ምግቦች በውስጣቸው ፋይበር ያላቸው የምግብ አይነቶች ናቸው፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት ጥራጥሬዎች በተጨማሪ ከነልጣጫቸው የሚበሉ የፍራፍሬ አይነቶችን ከዚህ ምድብ ይመደባሉ፡፡

በተጨማሪም የምንመገበው ምግብ የተመጣጠነ ሊሆን ይገባል፡፡ፍራፍሬና አትክልት፣ ስጋ፣ የእንስሳት ተዋፅዖ እና ከሌሎችም የምግብ አይነቶች አመጣጥኖ መመገብ ያስፈልጋል፡፡የተጠበሱ የምግብ አይነቶች ጤናችንን የሚጎዱ በመሆናቸው በተቻለን መጠን ከምግባችን ልናስወግዳቸው ይገባል፡፡

ከሚከተሉት ይቆጠቡ!

  1. የተጠበሱና ጮማ ነክ ምግቦችን
  2. እጅግ ጣፋጭ የሆኑ ምግቦችን
  3. ከልክ በላይ መመገብ በተለይ ስሁር ላይ
  4. በስሁር ወቅት ብዙ ሻይ መጠጣት፣ ብዙ ሻይ መጠጣት ብዙ እንድንሸና ያደረገንል፡፡ በምንሸናበት ወቅት ከሽንታችን ጋር በቀኑ ክፍለ ጊዜ ሰውነታችን ሚፈልጋቸውን የጨው ንጥረ ነገሮች አብረው ይወገዳሉ፡፡
  5. ሲጋራ ማጨስ

የሚከተሉትን ይመገቡ!

  1. ጨጓራችን ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ መቆየት የሚችሉ ምግቦችን መመገብ የርሀብ መጠናችንን ይቀንስልናል፡፡
  2. ለውዝ፣ ፕሮቲን፣ ፋይበርና አነስተኛ የፋት መጠን ያለው የምግብ አይነት በመሆናቸው ይመከራሉ፡፡
  3. ብርቱካን የፖታሲየም፣ የማግኒዝየምና የካርቦሃይድሬት ምንጭ በመሆኑ መመገቡ ይመከራል፡፡

መጠጥ

የተቻለንን ያህል ውሀ ወይም የፍራፍሬ ጭማቂ ከፍጡር በኋላና ከመተኛታችን በፊት መጠጣት ይመከራል፡፡ ይህም ሰውነታችን የፈሳሽ መጠኑን በጊዜ እንዲያስተካክል ይረዳናል፡፡

የሆድ ድርቀት

የሆድ ድርቀት ኪንታሮትን፣ የፊንጢጣ መሰንጠቅን እንዲሁም የምግብ አለመፈጨት ችግርን ያስከትላል።

መንስኤው ፋይበር የሌላቸው ምግቦችን ከመጠን በላይ መመገብ፣ በቂ ውሀ አለመጠጣት፣ ምግቦች ውስጥ በቂ ፋይበር አለማካተት።

መፍትሄ ፋይበር የሌላቸውን ምግቦች መቀነስ፣ ውሀን በብዛት መጠጣት፣ ከነ ገለባቸው የተፈጩ ምግቦችን መመገብ።

የምግብ አለምፈጨት (Indipestic) እና በምግብ መፈጨት ሂደት ሊፈጠር የሚችል ጋዝ (Wind)

መንስኤ ከመጠን በላይ መመገብ፣ የተጠበሱና ጮማ ነክ ምግቦችን ማብዛት፣ ቅመም የበዛባቸው ምግቦችና (Wind)ን የሚፈጥሩ እንደ እንቁላል፣ ጎመን፣ ለስላሳ መጠጥ ያሉ ምግብና መጠጦች አብዝቶ መጠቀም፡፡

መፍትሄ በመጠኑ መመገብ፣ የፍራፍሬ ጭማቂ ወይም ንፁህ ውሃ መጠጣት፣ የተጠበሱ ምግቦችን ቢቻል አለመጠቀም ካልሆነ  መቀነስ፡፡

መልፈስፈስ (የደም ማነስ)

ከመጠን ያለፈ ላብ ማላብ፣ የድካም ስሜት፣ ጉልበት ማጣት፣ መደበር፣ ከተቀመጡበት ለመነሳት መቸገር “የደም ማነስ” ምልክቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ምልክቶች ብዙውን ጊዜ ከቀትር በኋላ የሚታዩ ናቸው፡፡

መንስኤ በቂ ፈሳሽ አለመውሰድ፣ የጨው እጥረት

መፍትሄ ቀዝቀዝ ያለ ቦታ መሆን፣ በቂ ፈሳሽና ጨው መውሰድ

ይጠንቀቁ! የደም ማነስ መረጋገጥ ያለበት ምልክቶቹ ሲታዩ የደም ግፊትን በመለካት መሆን ይኖርበታል፡፡ ደም ብዛት ያለባቸው ሰዎች በረመዳን ፆም ወቅት ህክምናቸው ላይ ማሻሻያ ሊያስፈልጋቸው ስለሚችል ሀኪም ማማከር አስፈላጊ ነው፡፡

ራስ ምታት

መንስኤ አንደቡናና ሲጋራ ያሉ ሱሶች መውሰድ፣ እንቅልፍ ማጣት፣ ርሀብና ከአቅም በላይ መስራት፡፡ ራስ ምታት ከደም ማነስ ጋር አብሮ ከመጣ ከፍጡር በፊት ወደ ማቅለሽለሽ ስሜት ሊያመራ ይችላል፡፡

መፍትሄ እንደቡናና ሲጋራ ያሉ ሱሶችን ከረመዳን ቀደም ብሎ ቀስ በቀስ መተው፣ በቂ እንቅልፍ ለማግኘት የሚያስችል የረመዳን እቅድ ማውጣት፡፡

በደም ውስጥ የስኳር መጠን መቀነስ (Low Blood Sugar)

የድካም ስሜት፣ የአእምሮ መታወክ፣ ያለማስተዋል ችግር፣ የሰውነት መንቀጥቀጥ፣ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ አለመቻል፣ ራስ ምታትና ፈጣን የልብ ምት የደም ውስጥ የስኳር መጠን መቀነስ ምልክቶች ናቸው፡፡

መንስኤ ስኳር በሽተኛ ላልሆኑ ሰዎች ከመጠን በላይ የስኳር ንጥረ ነገር መጠቀም (Refined Carbohydrates) በተለይ በስሁር ወቅት፡፡

መፍትሄ ስሁር መመገብና የስኳር ንጥረ ነገር የበዛባችው ምግቦች ወይም መጠጦችን መቀነስ፡፡

ይጠንቀቁ! የስኳር በሽተኞች በረመዳን ፆም ወቅት የመድሀኒት አወሳሰድ ላይ ማሻሻያ ሊያስፈልጋቸው ስለሚችል ሀኪሞቻቸውን ማማከር ይኖርባቸዋል፡፡

የጡንቻ መሸማቀቅ (Muscle Cramps)

መንስኤበምግባችን ውስጥ በቂ ካልሲየም፣ ማገኒዝየምና ፖታሲየም ያላቸው ምግቦች አለማካተት

መፍትሄእንደ ቅጠላ ቅጠል፣ ፍራፍሬ፣ የእንስሳት ተዋፅኦ፣ ስጋና ቴምር የመሳሰሉ ምግቦችን መጠቀም፡፡

ይጠንቀቁ!  የደም ግፊትና የኩላሊት ጠጠር ያለባቸው ሰዎች ሀኪሞቻቸውን ማማከር ይኖርባቸዋል፡፡

የጨጓራ ማቃጠል ስሜት (Peptic Ulcer)

በፆም ጊዜ በባዶ የአሲድ መጠን መጨመር እነዚህን በሽታዎች ያባብሳቸዋል፡፡ ጨጓራችን የማቃጠል ስሜት የሚፈጥሩ ሲሆን የማቃጠል ስሜቱ እስከ ጉሮሮ ከፍ ሊል ይችላል፡፡ ቅመም የበዛባቸው ምግቦች፣ ቡናና ለስላሳ መጠጦች እነዚህን ችግሮች ያባብሳሉ፡፡

በጨጓራችን ውስጥ ያለውን የአሲድ መጠን መቆጣጠር የሚያስችል ህክምና በመኖሩ የዚህ አይነት ችግር ያለባቸው ሰዎች ቀደም ብለው ሀኪሞቻቸውን ሊያማክሩ ይገባል፡፡

የኩላሊት ጠጠር

በቂ ፈሳሽ በማይወስዱ ሰዎች ላይ የመከሰት እድል አለው፡፡የጠጠሩን መፈጠር ለመከላከል በቂ ፈሳሽ ቢወስዱ ይመከራል፡፡

1 COMMENT

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here