አስር (10) የሱብሂ ሰላት ጥቅሞች

4
28270

በእስልምና ህግጋት ውስጥ በዋነኝነት የሚጠቀሰው ሰላት ነው። ሰላት አንድ ባሪያ ወደ ጌታው የሚቃረብበት መንገድ ነው። በ24 ሰዓት ክፍለ ጊዜ 5 (አምስት) የተለያዩ ወቅቶችን ወደጌታው የሚሰግድበት ሶስቱ በጨለማው ጊዜ የሚሰገዱ ሲሆን የተቀሩት ሁለት ሰላቶች በቀኑ ክፍለ ጊዜ ይሰገዳሉ። የቀኑ የመጀመሪያው ሰላት በቀኑ የንጋት ክፍለጊዜ ላይ የሚገኘው የሱብሂ ሰላት ሲሆን ስለሱብሂ ሰላት ጠቀሜታዎች እንዳስስ። የሱብሂ ሰላት ሌላኛው መጠሪያው ፈጅር በመባል ይታወቃል።

በርካታ ኡለሞች ከሀዲስና ከቁርአን በመነሳት አስር ጠቀሜታዎችን ያስቀምጣሉ። የሱብሂ ሰላትን በጀመአ መስገድ ለአንድ ሰው በህይወቱ ላይ የሚፈጥረውን ጠቀሜታ እንመልከታለን።

1. ቀኑን በሙሉ በአላህ ጥበቃ ስር ይውላል

ጁንዱብ ቢን አብደላህ ቢን ሱፍያን በጅሊ አላህ መልካም ስራዎቻቸውን ይውደድላቸው አሉ ነብያችን ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም አሉ “ሱብሂን ሰላት በጀምአ የሰገደ በአላህ ጥበቃ ስር ይውላል …….”

“የሱብሂን ሰላት በጀመአ መስገድ በቀኑ ክፍለጊዜ በአላህ ጥበቃ ስር ይውላል ፣የሰው ልጆች ከሰዎች ጠባቂ ተላቀው በጌታቸው እንዲብቃቁና እንዲጠበቁ የሚደርግ ሰላት ነው፣……..” ሙስሊም ወአህመድ

2. አጅሩ(ምንዳው) ለሊቱን እንደቆመ ይቆጠርለታል

አቢሁረይራ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ባስተላለፉት ሀዲስ ነብዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ አሉ“የኢሻን ሰላት በጀመአ የሰገደ ግማሹን ለሊት እንደቆመ ሲሆን ሱብሂን በጀመአ የሰገደ ሙሉውን ለሊት እንደቆመ ይቆጠራል።” ሙስሊም

3. ከሙናፊቅነት ነጃ ይባላል

አቢሁረይራ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ባስተላለፉት ሀዲስ ነብዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ አሉ“በመናፍቃን ላይ ከባድ ሰላቶች የሱብሂና የኢሻ ሰላቶች ናቸው የእነዚህን ሰላቶች ጥቅም ቢያውቁ ኖሮ በዳዴም ቢሆን ወደሰላቱ ይመጡ ነበር።”  አህመድ፣ቡኻሪ እና ሙስሊም

4. ሙሉ የሆነን ኑር (ብርሃንን) ይለብሳል፤ በቂያም ቀን (በትንሳኤ ቀን)

ከቡረይዳ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ተይዞ ነብዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም “በጨለማ መስጂዶችን የሚጓዙ በየውመል ቂያማ (በትንሳኤ ቀን ) በሙሉ ኑር (ብርሃን) ይሆናሉ።” አቡ ዳውድ እና ቲርሚዚ

5. መልአክቶች ይመሰክሩለታል፤ ያወድሱታልም

አቢሁረይራ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ባስተላለፉት ሀዲስ ነብዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ አሉ  “በሰው ልጆች ላይ የተመደቡት መልአክቶች ይቀያየራሉ። በቀኑና በምሽቱ ክፍለ ጊዜ የሚቀያየሩበት ሰአት የሱብሂ ወቅት ላይ እና የአስር ወቅት ላይ ሲሆን ከዛም የ24 ሰአት ውሎአቸውን አላህ እያወቀ ለመልእክተኞቹ ይጠይቃቸዋል። ባሮቼን እንዴት ትታችኃቸው መጣችሁ ብሎ ሲጠይቃቸው፤ እነሱም እንዲህ ይመልሳሉ። እየሰገዱ ትተናቸው መጣን። ስንመጣም እየሰገዱ አገኘናቸው።” ቡኻሪ ወሙስሊም

6. አጅራቸውን ልክ ሀጅ እና ኡምራ አድርገው እንደመጡ ማስመዝገብ ይችላሉ

አነስ ቢን ማሊክ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ባስተላለፉት ነብዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ አሉ“የሱብሂን ሰላት በጀመአ የሰገደ ከዛም ፀሀይ እስክትወጣ በዚክር ቁርአን በመቅራት እና መሰል ኢባዳዎች ሲሰራ ቆይቶ ሁለት ረካአን የሰገደ ከሀጅ እና ከኡምራ ጋር የሚስተካከል አጅርን አገኘ ሙሉ መሉ አጅርን ሸመተ ቲርሚዚ

7. ዱንያ ላይ አከፋፍሎ የማይጨርሰውን ምርኮ ያገኛል

ኡመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና በስተላለፉት ሀዲስ ላይ “ከነብዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ይዞ በዘገበው ስለምርኮ እና ውርስ እያወሩ በነሩበት አጋጣሚ ብዙዎቹ በዚህ ምርኮ ላይ ፈጥነው ውሳኔን የሚወስኑ ፈጣኖች ሲሆኑ አንድ ምንም የለሌለው ሰው እንዲህ አላቸው ምን አይነት ነገር ላይ እንፍጠን ውሳኔያችንስ ምን ላይ ይሁን ስለበላጩ ምርኮ ከዚህ በሚበልጠው ሲላቸው ነብዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ አሉ “ልምከራችሁን? (ልጠቁማችሁን) ከህዝቦች በላይ ስለተደረጉት በምርኮ ላይ ፈጥነው ከሚሽቀዳደሙት?ህዝቦች ናቸው የሰላተ ሱብሂን ሰላት በጀምአ የተካፈሉት ናቸው ከዚያም ፀሀይ እስኪወጣ  አላህን የሚዘክሩ የሆኑት እነዚህ ናቸው ወደእውነተኛው ምርኮ በፍጥነት የሚሽቀዳደሙት።” ቲርሚዚ

8. ከሱብሂ ሰላት በፊት የሚገኘውን  ትልቅ እድል ይገጥማቸዋል

አኢሻ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ባስተላለፈችው ሀዲስ ላይ  ነብዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ አሉ“ከሱብሂ በፊት የምትሰገደው ሁለት ረከአ ሰላት ዱንያና ዱንያ ከያዘቻቸው ነገሮች በሙሉ ትበልጥለታለች” ሙስሊም

9. ከእሳት ነፃ ይባላል በጀነትም ይበሰራል

ኡማራህ ቢን ሩወይባ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ባስተላለፉት ሀዲስ ነብዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ አሉ “ፀሀይ ከመግባቷ በፊት እና ፀሀይ ከመግባቷ በፊት ሰላትን የሰገደ ሰው እሳት አያገኘውም” ይህም ማለት  “የሱብሂ እና የአስር ሰላቶች ናቸው።” ሙስሊም

10. በቂያማ ቀን (በትንሳኤ ቀን)ጌታውን ለማየት ይታደላል

ጀሪር ቢን አብድላህ በጀሊይ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንዲህ ይላል “ከነብዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ተቀምጠን የለይለተ በድርን (ከረመዳን ለሊት) ጨረቃ በተመለክትን ጊዜ እንዲህ አሉ “ልክ ይችን ጨረቃ እንደምታዩት ጌታችሁን ማይት ትሻላችሁ እንግዲያውስ ፀሃይ ከመውጣቷ በፊት እና ከመግባቷ በፊት ያሉትን ሰላቶች እራሳችሁን አሸንፉ” ቡኻሪ እና ሙስሊም

ሙእሚን አላህን እውነት ብሎ ላመነ አንዱም ሀዲስ በቂ ነበር። የሰው ልጆች ግን ዝንጉና ረሺ በመሆናቸው በርካታ አስታዋሽ ሀዲሶች ሊቀርብ ችሏልና የሱብሂን ሰላት በጀምአ ለመስገድ ከምንግዜው በላይ መጠናከር ይኖርብናል።

መቼስ በቂያማ ቀን የአላህ ፊት ማየት የማይሻ የለም እና ይህን ለማግኘት በእነዚህ ሰላቶች መበራታት አለብን  እስቲ ይህን የቁርአን አንቀፅ አንብበው

وُجُوهٌ يَوْمَئِذٍ نَّاضِرَةٌ
﴿٢٢﴾
إِلَىٰ رَبِّهَا نَاظِرَةٌ
﴿٢٣﴾

“ፊቶች በዚያ ቀን አብሪዎች ናቸው። ወደ ጌታቸው ተመልካቾች ናቸው።”

ይህን ከባድ ቀን እንደዋዛ ልታሳልፈው ነው ወንድሜ? ይህን ታላቅ ብስራት እንደቀልድ ልታባክነው አሰብክን? የተጫነብንን አብዋራ አራግፈን ከቸልተኝነት እና ከአላዋቂነት ለመንቃት ይህች ቁርአን። ይህች አለም ደሞ ጠፊ መሆኗን ባወቅን ጊዜ ምነኛ በባነንን ነበር!

ነፍስህ በዚያ በውድቅት ለሊት ተኛ ብላ በትወሰውስህ ሙአዚኑ እንዲህ ሲል ንቃ! “አሰላቱ ኸይሩን ሚነ ነውም” “ሰላት ከእንቅልፍ ትበልጣለች” ብሎ ሲጠራክ ጌታክን ለማየት እንደምትቻኮል አትጠራጠር! ያን ጊዜ የሰላተ ሱብሂን ጥፍጥና ታገኝና ዱንያ አሉ በሚባሉ ማናቸውም ነገሮች የማትተካውን ደስታ እና ከአላህ ጋር ከባድ ፍቅርን ትላበሳለክ።

4 COMMENTS

  1. “ፊቶች በዚያ ቀን አብሪዎች ናቸው። ወደ ጌታቸው ተመልካቾች ናቸው።” what Aya & Sura is this?

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here