የወርሀ ሻዕባን ታላላቅ ክስተቶች

1
6631

ሻዕባን ኢስላም ውስጥ ታላቅ ክብር ከሚሰጣቸው ወራቶች ውስጥ ነው። የአመቱ መልካም ሥራዎች ወደ አላህ የሚነሱበት ወር ነው። ሻዕባን “ሙኽታሩ ሲሓሕ” የተሠኘው መጽሐፍ ላይ እንደተገለጸው ህዝቦች ማለት ነው።

ከጎሳ በላይ የሆነ ብዛት ያለው የህዝቦች ብዛትን እንደሚወክል ቋንቋው ይጠቁማል። ይህን ወር መልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ብዙውን ይጾሙት ነበር። ስለዚህ የረመዳን መግቢያ እንደመሆኑ ሙስሊሞች ለረመዳናቸው ይበልጥ የሚዘጋጁበት ወር ነው። በዚህ ወር የተከሠቱትን ታሪካዊና ኃይማኖታዊ ክስተቶች እነሆ።

ዘመቻዎችና የጦር ውሎዎች

 • ሻዕባን 9፣ 932 (ሒጅራ) ወይም ሜይ 21፣ 1526 (እ.አ.አ.) ሙስሊሙ ሱልጣን ባበር ሻህ የሂንዱን ሰራዊት አሸንፏል። የሂንዱው ሠራዊት ቁጥሩ እጅግ ከፍተኛ ነበር። መቶ ሺህ ወታደሮች እና አንድ ሺህ ዝሆኖችን ያካተተ ነበር። ውጊያው ለሠባት ሠዓት ያህል ብቻ ነበር የቆየው። ሱልጣን ባበር የዘር ሀረጉ ወደ ቲሞር የሚደርስ ቤተሰብ ተወላጅ ነው። እነዚህ ጎሳዎች ለሦስት ምእተ አመታት ያህል የቆየውን ኢስላማዊ መንግስት በህንድ የመሠረቱ ናቸው።
 • የሑሰይድ ጦርነት፡- ይህ ጦርነት በ“አል-ቀዕቃዕ ኢብኑ ዐምር” በሚመሩ ሙስሊሞችና በ“ሩዘበህ” በሚመሩት ፋርሶች መሀል የተካሄደ ጦርነት ነበር። ውጊያው ሻዕባን 10፣ 12 (ሒጅራ) ወይም ኦክቶበር 20፣ 633 (እ.አ.አ.) ተካሄደ። ሙስሊሞችም አሸነፉ። ፋርሶቹም መሪያቸው ከተገደለ በኋላ ሸሹ።
 • ሻዕባን 15፣ 1294 (ሒጅራ) ወይም ኦገስት 25፣ 1877 (እ.አ.አ.) የዑስማኒያው የጦር መሪ አሕመድ ሙኽታር ባሻ የሩሲያውን ጦር “ኩድክለር” በተሠኘው የጦር አውድማ አሸንፎታል። በዚህ ድል የተነሳ “ጋዚ” ወይም “ዘማቹ” የሚል ማእረግ ከዑስማኒያው ሱልጣን “ዐብዱልሐሚድ ሁለተኛው” ተበርክቶለታል። አሕመድ ሙኽታር ባሻ ሩሲያዎችን ከዚህ ውጭም በተለያዩ የጦር አውድማዎች ላይ ተደጋጋሚ ድሎችን ተጎናጽፏል።
 • ሻዕባን 18፣ 967 (ሒጅራ) ወይም ሜይ 14፣ 1560 (እ.አ.አ.) ባለልዩ ተልእኮ፣ በጠርገድ ባሻ የሚመራው የዑስማኒያዎች ሠራዊት ልዩ ወታደራዊ ተልእኮ ያለው መስቀለኛው የእስፔን ሠራዊት ላይ ቱኒዚያ አካባቢ በምትገኘው “ጂርባ” በምትሠኘው ሥፍራ ላይ ድል ተቀዳጅቷል። በዓለማችን ልዩና በታላቅነቱ የመጀመሪያውን ደረጃ የሚይዝ የባህር ጦርነት ነበር። በጦርነቱ ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑ የእስፔን የባህር ተዋጊዎች ተገድለዋል። ከዑስማኒዮች በኩል ግን አንድ ሺህ የሚሆኑ ሸሂዶች ብቻ ነበር የተገኙት።
 • ሻዕባን 20፣ 852 (ሒጅራ) ወይም ኦክቶበር 19፣ 1448 (እ.አ.አ.) የዑስማኒያው ሱልጣን ሙራድ ሁለተኛው ክርስቲያናዊውን የአውሮፓ ሠራዊት አሸንፏል። አውሮፓዎቹ መቶ ሺህ የሚሆኑ ወታደሮችን በዚህ ጦርነት ላይ አሰልፈዋል። ውጊያው የተካሄደውም ኮሶቮ ውስጥ ነበር። ሦስት ቀን ከፈጀ ውጊያ በኋላ 17 ሺህ የሚሆኑ አውሮፓዊያን ተገድለውበት ጦርነቱ ተጠናቋል። ይህ ውጊያ አውሮፓዎች ዑስማኒዮችን ከአውሮፓ ለማስወጣት ካደረጓቸው ዘመቻዎች መካከል ስድስተኛው ነበር። ነገር ግን አልተሳካም።
 • ሻዕባን 23፣ 13 እንደ ሒጅራ ወይም ኦክቶበር 22፣ 634 እንደ አውሮፓዊያን በሙስሊሞችና በፋርሶች መሀል የጂስር ጦርነት ተካሄደ። ሙስሊሞች በአቡ-ዑበይድ ሲመሩ ፋርሶች ደግሞ በበህመን ጃዙዊየህ ይመሩ ነበር። ጦርነቱ ከባድ ነበር። አቡ-ዑበይድ ተገድሏል። ከዚያም ሙስሊሞችን ሙስና ቢን ሐሪሳ ሙስሊሞችን መምራት ጀምረ። ጦርነቱ ላይ ሙስሊሞች በጥሩ ሁኔታ ቢታገሉም ድል መቀዳጀት ግን ተስኗቸዋል።
 • በሙስንና ቢን ሓሪሳህ የሚመሩት ሙስሊሞች እና በፋርሶች መሀል የተደረገው ጦርነት ሻዕባን 24፣ 13 ሒጅሪያ ወይም ኦክቶበር 23፣ 634 እ.አ.አ. ተካሄደ። ይህ ጦርነት ላይ ሙስሊሞች እድለኞች ነበሩ።

ልደቶች

 • ሻዕባን ታላቁ ሶሐቢይ ዓብዱላህ ቢን ዙበይር የተወለዱበት ጊዜ ነው። እኚህ ሶሐቢይ ቢኢስላም ውስጥ የተወለዱ የመጀመሪያው ህጻን ናቸው። የልደት ቀናቸውም ሻዕባን 02፣ 02 እንደ ሒጅራ ሲሆን ይህም እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከጃንዋሪ 29፣ 624 ጋር ይገጥማል። ሶሐባው የተከበረ ቤት፣ ዕውቀትና ጥበብ በበዛበት ቤተሰብ ውስጥ አድገዋል። አባታቸው ታላቁ ሶሐባ ዙበይር ቢን አል-ዓዋም ናቸው። እናታቸውም አስማእ ቢንት አቢበክር አስ-ሲዲቅ ናቸው። አክስታቸው የሙእሚኖች እናት አዒሻ ናቸው። እራሳቸውም ሶሐባ ናቸው። በጀግንነታቸው ይታወቃሉ። በ64 ሒጅሪያ ከሙዓዊያ ቢን የዚድ ሞት በኋላ እራሳቸውን ለኸሊፋነት አቅርበው ነበር።
 • ሻዕባን 3፣ 4 እንደ ሒጅራ ወይም እ.አ.አ. ጃንዋሪ 9፣ 626 ኢማሙል ሑሰይን ቢን ዓሊይ (ረ.ዐ) በመዲና አልሙነውወራህ ተወለዱ። እርሳቸውንና ወንድማቸውን -ሐሰንን- ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በጣም ይወዷቸው ነበር። ሙዓዊያ ቢን አቢ-ሱፍያን ከሞተና ልጃቸው የዚድ ከተሾመ በኋላ ኸሊፋ ለመሆን እራሳቸውን አቅርበው ነበር። ሑሰይን የዚድ ለሙስሊሞች ኸሊፋ ለመሆን ብቁ አይደለም በማለት ሞግተዋል። ኋላም በከርበላእ ጦርነት ላይ በጠላቶቻቸው ተገድለዋል።
 • ሻዕባን 15፣ 476 ሒጅሪያ ወይም እ.አ.አ. ዲሴምበር 28፣ 1083 ላይ ታላቁ ዓሊም አቢል ፈድል ዒያድ ኢብኑ ሙሳ አል-የሕሶቢይ አል-ሲብቲይ ተወለዱ። ቃዲ ዒያድ የሚታወቁበት ሥማቸው ነው። የምዕራቡ (ሞሮኮ) ሐፊዝ ናቸው። ከአምስተኛውና ስድስተኛው ምእተአመት (እንደ ሒጅራ) ታላላቅ የዒልም ሠዎች ይመደባሉ። ፊቅህ፣ ሐዲስ፣ ታሪክ እና ሌሎችም የእውቀት ዘርፎች ላይ የፃፏቸው መጽሐፍት ታላቅነታቸውን ይመሰክራሉ። ከእነዚህ መሐል “መሻሪቁል አንዋር” እና “ኢልማዕ” ምርጦቹና የታወቁት ናቸው።
 • ሻዕባን 15፣ 1217 እንደ ሒጅራ ወይም እ.አ.አ. ዲሴምበር 11፣ 1803 ታላቁ ኢማም አቢስ-ሰናእ ሺሀቡድ-ዲን መሕሙድ አል-አሉሲይ ተወለዱ። አስራ ሶስተኛው ምእተአመት ሒጅሪያ ላይ ከነበሩት ታላላቅ ኢማሞች ይቆጠራሉ። “ሩሑልመዓኒ” የተሰኘው የቁርአን ማብራሪያ (ተፍሲር) ከመጽሐፍቶቻቸው መሀል የአሉሲይን ታላቅነት ይጠቁማል።
 • የዑስማኒያው ሱልጣን ዓብዱልሐሚድ ሁለተኛው ሻዕባን 16፣ 1258 ላይ ተወለዱ። ይህ ቀን ከሴፕቴምበር 22፣ 1842 ጋር ይጋጠማል። ኸሊፋነታቸው ሳይወድም እና ፀሐያቸው ከመጥለቋ በፊት ካለፉት የዑስማኒያ ነገስታት ዝርዝር ውስጥ ከታላላቆቹ ጋር የሚመደቡ ሰው ናቸው። ለሠላሳ አንድ አመታት የቆየው ስልጣናቸው በታላላቅ ክስተቶችና ድሎች የተሞላ ነበር። ኢምፓየሩን ከመበታተን በማዳናቸው ይታወቃሉ።
 • ሻዕባን 25፣ 625 ሒጅሪያ ወይም ጁላይ 31፣ 1227 ታላቁ ዓሊም እና የሻፊዒያ መዝሀብ የፊቅህ ሊቅ ተቂዩድዲን ሙሐመድ ኢብኑ ዓሊይ ቢን ወህብ (ኢብኑ ደቂቅ አል-ዒድ በመባል የሚታወቁት) ተወለዱ። የሰባተኛው ዓመተ ሂጅራ ዕውቅ ሰው ነበሩ። ብዙ ድርሳናት ያሏቸው ሲሆን ባለ ትልቅ ጀብድም ነበሩ።
 • ታላቁ ሙጀዲድና የሙስሊም ወንድማቾች ጀመዓ (ኢኽዋኑል ሙስሊሚን) መሪና መስራች ኢማም ሐሠኑል-በንና በዚህ ወር ሻዕባን 14፤ 1324 ወይም ኦክቶበር 14፤ 1906 በግብፅ ተወለዱ። በነዲድ የማስተካከል ጭንቀቶች፣ በሚዛናዊ አመለካከት እና ለኢስላማዊ አንድነት ባላቸው ልዩ ትኩረት እኚህ ኢማም ይታወቃሉ። የመሠረቱት ጀመዓም በዚህ ዘመን ካሉት የዳዕዋ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ሰፊውን የማንቃት ድርሻ ይወስዳል።

ሞቶች

 • ሻዕባን 1፣ 1409 ወይም ማርች 9፣ 1989 ታላቁ የዘመናችን ዓሊም እና የሶሪያው የኢኽዋኑል-ሙስሊሙን መሪ ሼኽ ሰዒድ ሐውዋ አረፉ። እኚህ ሰው ታላላቅ መጽሐፍቶችን፣ ነፍስን በማጥራት፣ በተፍሲር፣ በፊቅህ፣ በሐዲስና በዘመናዊው ኢስላማዊ አስተሳሰብ ዙሪያ በሰሯቸው ሥራዎች ይታወቃሉ። “አል-አሳስ ፊተፍሲር” እና “አል-አሳስ ፊሲራ” ዝናን ካተረፉ መጽሐፍቶቻቸው ይቆጠራሉ።
 • ኸሊፋው አቢ-ዓብዲላህ ሙዕተዝ ቢን አልሙተወክኪል ቢን አልሙዕተሲም ሻዕባን 2፣ 255 ሒጅሪያ ወይም ጁላይ 16፣ 868 ላይ አረፉ። ስልጣን ላይ የወጡት 252 ሐጅሪያ ላይ ነበር። ሦስት አመት ከግማሽ ድረስ በስልጣን ቆይተዋል። ከእርፈታቸው በኋላ አል-ሙህተዲ ቢላህ ተክተዋቸዋል።
 • ልክ ሻዕባን 6፣ 1398 ወይም ጁላይ 7፣ 1978 ትልቁ የፊቅህ ሠው ሼኽ ዓሊይ አል-ኸፊፍ አረፉ። በአስራ አራተኛው የሂጅራ ምእተ-አመት ከታዩ ታላላቅ የፊቅህ ሰዎች መሀል አንዱ ናቸው። ጥልቅ የሆኑ ትልልቅ የፊቅህ ድርሰቶች አሏቸው። ከ “አል-ቀዷኡሽ-ሸርዒይ” ትምህርት ቤት ነበር የተመረቁት። የተወሰኑ አመታትን በዳኝነት አገልግለዋል። ከዚያም በካይሮ ዩኒቨርሲቲ የህግ የትምህርት በህግ ትምህርት ቤት ውስጥ የሸሪዓ መምህር ሆነው ሠርተዋል።
 • ሻዕባን 19፣ 1413 እንደ ሒጅራ ወይም እ.አ.አ ፌብራሪ 12፣ 1993 ታላቁ የሐዲስ ምሁር ዐብዱላህ ቢን ሙሐመድ አል-ጉማሪይ አረፉ። እኚህ ሰው የዘመናቸው ትልቅ የሐዲስ ሐፊዝና የብዙ መፅሐፍት ባለቤት ናቸው።
 • ሻዕባን 21፣ 1208 እንደ ሒጅራ ወይም እ.አ.አ. ጁላይ 25፣ 1793 ታላቁ የአዝሐር ሼኽ ኢማም አሕመድ አልዓሩሲ አረፉ። ሰውየው በአዝሀር ሸይኾች ዝርዝር ውስጥ አስራአንደኛው ሼኽ ናቸው። ሼኹ ጀግንነታቸውን ባንጸባረቁ አጋጣሚዎቻቸው ይታወቃሉ። በአንዳንድ ንጉሶች በደል ያረረውን ህዝብ በመርዳት ይታወቃሉ። የዒልም መድረክ ላይም ጎልተው የሚታዩባቸው መጽሐፍትም አሏቸው። ከነዚህም መሀል “ሙኽተሰሩል-ዓሩሲ ፊል ፊቅህ” የታወቀ ነው።
 • ሻዕባን 28፣ 456 እንደ ሒጅራ ወይም ጁላይ 15፣ 1064 እ.አ.አ. ታላቁ ኢማም ሙሐመድ ቢን ዓሊይ ቢን አሕመድ ቢን ሰዒድ ቢን ሐዝም- ኢብኑ ሐዝም በመባል የሚታወቁት- ኢማም አረፉ። የአምስተኛው ምእተ አመት ሂጅሪያ ታላቅ ሰው ነበሩ። በተለያዩ የፊቅህ፣ የታሪክ እና የሐይማኖት ንጽጽር መጽሐፍቶቻቸው ይታወቃሉ። ከነዚህ መሀል “አል-ሙሐላ”፣ “አል-ፈስሉ ፊል-ሚለል ወል-አህዋኢ ወን-ኒሐል”፣ “ኢሕካሙል-አሕካም” እና “ጀምሀረቱ አንሳቢል ዓረብ” የተሰኙት መጽሐፍት የታወቁ ናቸው።
 • ሻዕባን 30፣ 415 ወይም ኖቬምበር 10፣ 1024 የታላቁ የሱና ኢማም አቢልቃሲም ዑበይዲላህ ቢን ዐብዱላህ ቢን አል-ሑሠይን አልኸፋፍ- ኢብኑን-ነቂብ በመባል የሚታወቁት- የእርፈት ቀን ነበር። የተወለዱት ከሒጅራ በኋላ 305 ላይ ነበር። ከብዙ ዓባሲያ ስርወ መንግስት ነገስታት ጋር አብረው ኖረዋል። ከነ አል-ሙቅተዲር፣ አል-ቃሂር፣ አር-ራዲ፣ አል-ሙትተቂ፣ አል-ሙስተክፊ፣ አል-ሙጢዕ፣ አጧዒዕ፣ አል-ቃዲር፣ አል-ጋሊብ ቢላህ ጋር ማለት ነው። በመቶ አስር አመት እድሜያቸው አቅራቢያ አርፈዋል።

የተለያዩ ክስተቶች

 • ሻዕባን 3፣ 646 እንደ ሒጅራ ወይም ኖቬምበር 21፣ 1248 እ.አ.አ. የኢሽቢሊያ ትልቁ የአንደሉስ (ስፔን) ከተማ በስፔኑ የካስቲላ ስርወ መንግስቱ በፈርናንዶ ሦስተኛው እጅ ሥር ወድቃለች። የዚች ከተማ መወረር ሌሎች በሙስሊሞች ቁጥጥር ስር የነበሩ የአንደሉስ ከተሞች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተከትሎ የተከሰተ ነው። ኮርዶቫ (ቁርጡባ)፣ ቫሌንሺያ (በለንሲያ)፣ ጂያን ወ.ዘ.ተ. የመሰሉ ከተሞችን ማለታችን ነው። ስለዚህም የእስልምና ሚና በደቡባዊው የአንደሉስ (የአሁኗ ስፔን) መንግስት ግራናዳ ውስጥ ተወስኖ ቀርቷል።
 • ሻዕባን 4፣ 1367 ወይም ጁን 11፣ 1948 በዓረብ ሠራዊት እና በአይሁድ ወንበዴ ቡድኖች መሀል በፊሊስጢን የመጀመሪያው የቶክስ አቁም ስምምነት ተካሄደ። የመንግስታቱ ድርጅት አደራዳሪ የነበረው ፎልክ በርናዶት የሚባል ሠው ነበር። ወደ ፊሊስጢን የሚሰደዱት አይሁዶች መጠን መገደብ እንዳለበትና አል-ቁድስ በፊሊስጢኖች ሙሉ ትድድር ውስጥ መቆየት እንዳለበት የሚገልጽ አቋም በመያዙ አይሁዶቹ ገደሉት!!
 • ልክ ሻዕባን 7፣ 12 እንደ ሒጅራ ወይም 17፣ 633 እ.አ.አ. አቢዑበይደተ ኢብኑልጀርራሕ (ረ.ዐ) አቡበክር ሱድዲቅ (ረ.ዐ) ከላኳቸው አራት ሰራዊቶች መሀል የአንዱ ጦር መሪ ሆኖ ተላከ። የአራቱ ጦሮች ተልእኮ ሻምን (ሶሪያና አካባቢዋን) መክፈት ነበር። አቡዑበይዳ ከማለዳው ወደ እስልምና ከገቡት መሀል ነው። በነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ዘመቻዎች እና ልዑኮቻቸው ላይ ተሳትፈዋል። በአቡበክር እና በዑመር ዘመን የነበሩት ታላላቅ ኢስላማዊ ሀገራትን የማቅናት ዘመቻዎች (ፉቱሃት አል-ኢስላሚያህ) ላይ ታላቅ ገድሎች ነበሯቸው።
 • ሻዕባን 13፣ 1339 እንደ ሒጅራ ወይም ማርች 24፣ 1920 ላይ ፊሊስጢን በብሪታኒያ ሞግዚትነት ስር ውላለች። ይህም የሆነው ከመጀመሪያው የአለም ጦርነት መባቻ በኋላ ነበር። ይህ ሁኔታም አይሁዶች ወደ ፊሊስጢን የሚያደርጉትን ስደት አፋጥኖታል። ምክንያቱም የማመቻቸቱ እና ዓረቦቹን የማፈናቀሉ ስራ በብሪታኒያዊያኑ ስለተፋጠነ ነው። ይህ አሳዛኝ ክስተት የመንግስታቱ ድርጅት ፊሊስጢንን ለሁለት በመክፈል ተጠናቋል። ማለትም ልክ በ1947።
 • ሻዕባን 13፣ 1425 ወይም ሴፕቴምበር 27፣ 2004 የዘር ሀረጋቸው ከሞሮኮ የሆኑ ሁለት ሙስሊም ሴቶች ምርጫ በማሸነፍ የፈረንሳይ የኮንግሬስ አባል ሆኑ። ለፈረንሳይ ሙስሊሞች የመጀመሪያው ትልቅ የፖለቲካ ተሳትፎ መሆኑ ነው እንግዲህ። ሁለቱ ሙስሊሞች የግራ ክንፉን ፓርቲ በመወከል ነበር የተወዳደሩት።
 • ልክ ሻዕባን 14፣ 1402 ወይም ጁን 6፣ 1982 የኢስራኤል ሀይሎች በመከላከያ ሚኒስትራቸው ኤሪያል ሻሮን መሪነት ወደ ሊባኖስ ምድር ዘመቱ። ከዚያም መጠነ ሰፊ የዘር ጭፍጨፋ በሊባኖስ ምድር ሰብራና ሻቲላ የተሰኙ ስፍራዎች ላይ አደረጉ። ፊሊስጤማዊያን ነበር በግፍ የታረዱት። የጭፍጨፋው አጸፋም ሒዝቡላህ በሙሐመድ ሐሠን ፈድሉላህ እጅ ተመሠረተ። ትግሉንም ጀመረ። ከዚያም ብዙውን የደቡብ ሊባኖስ ምድር አስለቀቀ። በተደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል ኢስራኤል ከፍተኛ ኪሳራ ገጥሟታል። ዘጠኝ መቶ ወታደሮቿን አጥታለች። ደም አይለቅም እና ደም ለማፍሰስ እንደወጡ ቀሩ።
 • ሻዕባን 21፣ 489 እንደ ሒጅራ ወይም ኦገስት 15፣ 1096 የአውሮፓው ጳጳስ የመስቀል ጦረኞች ቆስጠንጢኒያ ላይ እንዲሰበሰቡ ቀጠሩ። ጥሪው ምስራቁን የሙስሊሙን ሀገር (ሶሪያ፣ ዒራቅ፣ ፊሊስጢን፣ ሊባኖስ) ለመውረርና አልቁድስን ከሙስሊሞች እጅ ለመመንጠቅ የሚደረግ ዝግጅት ለማድረግ ያቀደ ነበር።
 • ሻዕባን 21፣ 559 ወይም ጁላይ 19፣ 1164 ሰላሁድ-ዲን አል-አዩቢይ ሑምስን ከመስቀለኞች እጅ የመነጠቀበት ቀን ነበር። ይች ቦታ እስትራቴጂካዊ ሚና ስለነበራትም ሌሎች የአካባቢው ቦታዎች ከእጁ ወድቀዋል።
 • ሻዕባን 22፣ 588 ወይም ሴፕቴምበር 2፣ 1192 በሰላሁድ-ዲን አል-አዩቢይና በሪቻርድ ቀልቡል-አሰድ መሀል “ሱልሁል-ረምላህ” (የአሸዋዋ ስምምነት) ተካሄደ። ይህ የሆነውም ሦስተኛው የመስቀለኞች ወረራ አላዋጣ ሲል ነበር። የስምምነቱ ውጤት ክርስቲያኖች ወደ አል-ቁድስ የሚያደርጉት ኃይማኖታዊ ጉዞ በሠላም ማከናወን እንዲችሉና ከሱር እስከ ያፋ የተሰኙት የሻም ሀገርን መስቀለኞቹ እዲያስተዳድሩ መፍቀድ አስችሏል።
 • ሻዕባን 23፣ 492 እንደ ሒጅራ ወይም ጁላይ 15፣ 1099 እ.አ.አ. አል-ቁድስ (አላህ ይመልሳትና) በመስቀል ጦረኞች ሥር ወደቀች። ይህም የሆነው ምስራቁን የኢስላም ሀገር በወረሩበት መጀመሪያው ዘመቻቸው ላይ ነበር። ወደ ቁድስ የዘለቁት ከአርባ ቀናት በላይ የቆየ ከበባ ካደረጉ በኋላ ነበር። ወደ ከተማዋ ሲገቡ ጭፍጨፋ ፈጸሙ። ንጹሀንን፣ ሴቶችን እና ህጻናትን አረዱ።

1 COMMENT

 1. በጣም ምርጥ ፔጀ ነዉ ።በመልካም ሰራችሁ አሏህ ምንዳችሁን ያብዛላችሁ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here