ምስጋና ለአለማት ጌታ ለአላህ ይሁን፤ ሰላትና ሰላም በመልክተኛውና በወደዳቸው ላይ ሁሉ ይውረድ።
የተከበረና የተባረከ ወር መምጫው ቀርቧል፤ በውስጣችን የኢማንና የሂዳያ (ቅናቻ) ስሜቶችን አነቃቅቷል፤ የኢባዳና የኸይር ስራ ፍላጎትን ቀስቅሷል፤ የሸዕባን ወር የረመዷን መሸጋገሪያና መግቢያ ወር ሲሆን ኡማው ወደ አላህ የመቃረብን ጣፍጭነትን የሚቀምስበትና የኢማንን ጣዕም በማጣጣም ለፆም፣ ለቂያምና ለበጎ ስራዎች ልምምድና ዝግጂት የሚያደርግበት ነው።
በዚህ ዝግጅት ታንፆ ወደ ረመዷን የገባ ወሩን በከፍተኛ ወኔና በጉጉት ይቀበላል፤ በኢባዳና በጣዓ (አላህን መታዘዝ) ላይም ይበረታል።
ለዚሁም ቀጥሎ የተዘረዘሩትን ነጥቦች በአንክሮ ማየት ያሻል፡-
- የሸዕባን ወር ትሩፋቶች
- ነብያችን (ሰ.ዐ.ወ) በሸዕባን ወር ፆም የማብዛታቸው ሚስጠር
- በተከበረው ወር (ረመዷን) መግቢያ ላይ ሆነን ልንመካከርባቸው የሚገቡ ነገሮች
የሸዕባን ወር ትሩፋቶች
ኢማም አህመድና ኢሚም አን-ነሳኢይ ከኡሳማ ቢን ዘይድ (ረ.ዐ) ጠቅሰው እንደዘገቡት “ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ምንም ሳያቋርጡ አከታትለው ይፆሙ ነበር፤ በአንጻሩም አይፆሙም እስከምንል ድረስ ከሳምንቱ ሁለት ቀናትን እንጂ ሌላውን አይፆሙም ነበር፤ከወሮች ሁሉ (ከረመዷን ውጭ) በብዛት የሚፆሙት የሸዕባንን ወር ነበር፤ እኔም ‘የአላህ መልክተኛ ሆይ ምንግዜም አያፈጥሩም እሰከምንል ይፆማሉ፤ እንደዚሁም አይፆሙም እስከምንል ሁለት ቀናት ሲቀሩ ያፈጥራሉ፤ ሁለቱ ቀናት ፆመዎ ውስጥ ካልተጠቃለሉ ነጥለው ይፆሟቸዋል’ አልኳቸው፡፡ የአላህ መልክተኛም (ሰ.ዐ.ወ) ‘ሁለቱ ቀኖች የትኞቹ ናቸው?’ ሲሉ ጠየቁኝ፤ ‘ሰኞና ሐሙስ’ አልኩኝ፣ የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ‘እነዚህ ሁለት ቀናት ሥራዎች ሁሉ ወደ አለህ የሚቀርቡባቸው ስለሆኑ እኔ ፆመኛ ሆኜ ስራዬ ወደ አላህ እንዲቀርብ ስለምፈልግ ነው’ ብለዋል።”
ከላይ በተጠቀሰው ሐዲስ ታለቁ ሰሐቢይ ኡሳማ ቢን ዘይድ (ረ.ዐ) የነቢያችንን (ሰ.ዐ.ወ) የአመቱን እንቅስቃሴ ምን ይመስል እነደነበር ይገልፅልናል። ባልደረቦቻቸው አያፈጥሩም ብለው እስኪያስቡ ድረስ በተከታታይ መፆምና አይፆሙም ብለው እስኪያስቡ ድረስ በተከታተይ ማፍጥር የነብያችን (ሰ.ዐ.ወ) መንገድ ነበር። ይህንን እናታችን ዓኢሻ (ረ.ዐ) እንዲህ በማለት ገልጸውታል “የአላህ መልክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ምንግዜም አያፈጥሩም እስከምንል ድረስ ይፆሙ ነበር፤ አይፆሙም እስከምንል ድረስ ያፈጥሩ ነበር።” አነስ ቢን ማሊክ (ረ.ዐ) እነደተናገሩት ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ሲፆሙ ፆም ጀመሩ ተብሎ ይነገር ነበር፤ ሲያፈጥሩም አፈጠሩ ተብሎ ይነገር ነበር።
ይህ የሚያሳየው የነቢያችንን (ሰ.ዐ.ወ) ፆም ብዙሃኑ ባልደረባ ያውቀው እንደነበርና በሚጾሙባቸው ቀናት ያዩዋቸው ከፆማቸው ብዛት የተነሳ ሁል ጊዜ ይፆማሉ ይሉ እንደነበር፤ በአንፃሩ ደግሞ በፊጥራቸው ጊዜ (ሳይጾሙ) ያዩዋቸው በተከታታይ በዚህ ሁኔታ ሳይፆሙ ስለሚቆዩ አይፆሙም ይሉ ነበር። ይህ ሁኔታ የነቢያችን መንገድና መመሪያ ስለነበረ ነው።
ሰኞና ሐሙስ መጾም ከነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ሱና ነው
ሰሐቢዩ ኡሳማ ቢን ዘይድ እና እናታችን አዒሻ (ረ.ዐ) እንደተናገሩት ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ሰኞና ሐሙስ ቀናትን ጠብቀው ይፆሟቸው ነበር፤ የነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ሰሐባዎች ይህንን የነቢያችንን (ሰ.ዐ.ወ) ሁኔታ ሲያዩ “አንቱ የአላህ መልክተኛ ሆይ ሰኞና ሐሙስን ጠብቀው የሚፆሙበት ምክንያት ምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቋቸው እርሳቸውም እንዲህ ሲሉ መለሱ “በሰኞና ሐሙስ ቀናት አላህ (ሱ.ወ) ለሁሉም ሙስሊሞች ምህረቱን ይለግሳል፤ የተኳረፉ ሰዎች ሲቀሩ።”
ኢማም ሙስሊም ከአቡ ሁረይራ ይዘው በዘገቡት ሐዲስ እንደተነገረው ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) አንዲህ ብለዋል፡- “ሰኞና ሐሙስ የጀነት በሮች ይከፈታሉ፤ በአላህ (ሱ.ወ) በርሱ ምንም ለማያጋራ ሰው ሁሉ ምህረት ያደርጋል፤ በርሱና በሙስሊም ወንድሙ መካከል ኩርፊያ ያለ ሰው ሲቀር፤ እነዚህን ሁለት ሰዎች እሰከሚታረቁ ድረስ አቆዩዋቸወ ይላል።”
ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ሰኞና ሐሙስ የመፆማቸው ሚስጥር ምን እንደሆነ ሲጠየቁ “እነዚህ ሁለት ቀናት ሥራዎች ሁሉ ወደ አለህ የሚቀርቡባቸው ናቸው፤ እኔ ደግሞ ፆመኛ ሆኜ ስራዬ ወደ አላህ እንዲቀርብ እፈልጋለሁ” ብለዋል።
ሰኞና ሐሙስ ሥራዎች ወደ አላህ (ሱ.ወ) በተለይ የሚቀርቡባቸው ቀናት ናቸው ለማለት እንጂ ስራዎች በየቀኑ ማለትም የሌሊት ሥራዎች ከመንጋቱ ቢፊት የቀን ሥራዎች ደግሞ ከመመሸቱ በፊት በየእለቱ ወደ አላህ (ሱ.ወ) እንደሚቀርቡ ኢማም ሙስሊምና ኢብኑ ማጀህ በዘገቡት ሐዲስ ተረጋግጧል።
ባጠቃላይ እነዚህ ዘገባዎች ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) በሰኞና ሐሙስ ፆም የማዘውተራቸውን ምስጢር በግልፅ ያስቀምጡልናል፤ ስራቸው ወደ ጌታቸው ጾመኛ ሆነው እንዲቀርብላቸው ይፈልጋሉ፤ ምክንያቱም የበለጥ ተቀባይነት ስለሚኖረው።
ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) በሸዕባን ወር ፆም ያበዙ ነበር
ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) በሸዕባን ወር ፆም ማብዛታቸው የታወቀ ጉዳይ ነው። ከሌላው ጊዜ በበለጠ በሸዕባን ወር ይፆሙ ነበር፤ እናታችን ዓኢሻ (ረ.ዐ) እንዲህ ብለዋል፡- “ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ከረመዷን ውጭ ማንንም ወር ሙሉ በሙሉ ሲፆሙ አላየኋቸውም፤ ከሸዕባን ወር የበለጥ በብዛት የሚፆሙት ወር አልነበረም።”
በነቢያችን ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ሱና ለሚሰሩና የሳቸውን ፈለግ ተከትለው መልክተኛው አርአያቸው መሆናቸውን ለዓለም ላወጁ ሁሉ፤ ከወዳጃችሁ ዘንደ ተወዳጅ የሆነ ወር መጥቶላችኋል ስንል እናስገነዝባለን፤ የዚህን ወር መለያዎችና ደረጃው ተገልጾላችኋል፤ትሩፋቶቹንም አውቃችኋል፤ ይህን ወር ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) በምን መልኩ ያሳልፉት እንደነበር ተረድታችኋል፤ በዚህ ወር ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ፆም ያበዙ እንደደነበር በግልጽ ታውቋል፤ ታዲያ እናንተስ ይህንን ወር በምን መልኩ ልታሳልፉት ተዘጋጅታችኋል?
ከላይ የጠቀስናቸው ሐዲሶች እንድምታ “እናንተ የሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ተከታዮች ሆይ! እርሳቸው እሰከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ በጉጉት ይሰሩት የነበረን ኸይር ለመስራት ተነሱ!” ሲሉ ጥሪያቸውን ወደኛ ያስተላልፋሉ።
ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) በሸዕባን ወር የነበራችውን ሁኔታና ፆም ያበዙ እንደነበር በሰሐባዎች (ረ.ዐ) መካከል ሙሉ ስምምነት አለ፤ ታዲያ የዚህ ጉዳይ ሚስጥሩ ምን ይሆን?
ኢማም አሽሸውካኒ (አላህ ይዘንላቸው) ይህን አስመልክተው የሚከተለውን ተናግረዋል፡-
ولعل الحكمة في صوم شهر شعبان أنه يعقُبه رمضان، وصومه مفروض، وكان النبي- صلى الله عليه وسلم- يُكثر من الصوم في شعبان قدر ما يصوم في شهرين غيره لما يفوته من التطوع الذي يعتاده بسبب صوم رمضان
“ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) በሸዕባን ወር ፆም የማብዛታቸው ሚስጥር ምናልባትም ቀጥሎ መፆሙ ግድ የሆነው የረመዷን ወር ስለሚገባ ሊሆን ይችላል፤ ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) በሸዕባን ወር በሌላ ሁለት ወራት የሚፆሙትን ያህል ትርፍ (ግዴታ ያልሆነ) ፆምን ይፆሙ ነበር፤ ይህንንም የሚያደርጉት በየወሩ ይፆሙት የነበረው ትርፍ ፆም (ተጠዉዕ) በረመዷን ወር ምክንያት ስለሚያልፋቸው ይህንን ለማተካካት ነው።”
ሐፊዝ ኢብኑ ረጀብ አል ሐንበሊይ ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) በሸዕባን ወር ፆም የማብዛታቸውን ሚስጥር አስመልክተው እንዲህ ብለዋል “የሸዕባን ወር በረጀብና ረመዷን ወራት መካከል ስለሆነ ሰዎች ይዘነጉታል፤ እነዚህ ታላላቅ ወራት ከተከበሩ ወራት (አሽሁሩል ሑሩም) የሆነው ረጀብና የጾም ወር የሆነው ረመዷን የሸዕባንን ወር ስለሚከቡት ሰዎች ለነዚህ ወራት ትኩረት በመስጠት የሸዕባንን ወር ችላ ይሉታል፤ ብዙ ሰዎች የረጀብን ወር መፆም የሸዕባንን ወር ከመፆም የሚበልጥ ይመስላቸዋል፣ ይህ ትክክል አይደለም፤ እናታችን ዓኢሻ (ረ.ዐ) የሚከተለውን ዘግበዋል ‘ሰዎች የረጀብን ወር ይፆማሉ ተብሎ ለነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ተነገራቸው፤ ‘ሸዕባንን ለምን አይፆሙም’ አሉ’።”
ኢማም ኢብኑ ረጀብ “ሰዎች የሸዕባንን ወር በረጀብና ረመዷን ወር መካከል በመሆኑ ይዘነጉታል” ማለታቸው ሰዎች የሚዘናጉባቸውን ወቅቶች በዒባዳ ማነጽ ተወዳጅ መሆኑን ያስረዳል። ከሰለፎች አንዳንዶቹ በመግሪብና ኢሻ ሶላቶች መካከል ያለውን ጊዜ ህያው ማድረግ ይወዱ ነበር፤ ምክንያታቸውን ሲያስረዱም ይህ ጊዜ የገፍላ (መዘንጊያ ወቅት) ነው ይሉ ነበር። እንደዚሁም እኩለ ሌሊት ላይ ለሶላት መቆም ብልጫ አለው፤ ምክንያቱም በዚህ ሰዓት ብዙ ሰዎች በመኝታ ላይ ስለሚሆኑ ከአላህ ዚክር ስለሚዘነጉ ነው፤ ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡- “በዚህ ሰዓት አላህን ከሚያወሱት ለመሆን ከቻልክ አድርግ።” ይህ ሰዎች አላህን በብዛት የማያወሱባቸው ጊዜያትን መርጦ እሱን ማውሳት ብልጫ እንዳለው ያመለክታል።
የተከበሩት ነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ማለታቸው ተረጋግጧል “በፈተና ጊዜያት አላህን መገዛት ወደ እኔ ስደት (ሂጅራ) የማድረግ ያህል ነው።” (ኢማም አህመድ ዘግበውታል)
የዚህ ምክንያቱ በፈተና ጊዜያት ሰዎች ዲንን መከተል ትተው ወደ ስሜታቸው ይዞራሉ፤ ሁኔታቸውም የጃሂሊያ ዘመን (ከነቢያችን መላክ በፊት) ሁኔታን ይመስላል፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ከሰዎች በተለየ ዲኑን አጥብቆ የሚይዝና አላህን በመገዛት አላህ የሚወደውን የሚሰራ የሚጠላውን የሚከለከል ሰው ከጃሂሊያ ዘመን ሰዎች መካከል ወጥቶ ወደ ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) የተሰደደን ሰው ደረጃ ያገኛል ማለት ነው።
ሌላው በሸዕባን ወር ፆም ማብዛት የሚፈለግበት ምክንያትና ሚስጥር ኡሳማ ቢን ዘይድ (ረ.ዐ) ባስተላለፉት ሐዲስ ላይ ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) የገለጹት ጉዳይ ነው፤ እሱም “የሸዕባን ወር ስራዎች ወደ ዓለማት ጌታ አላህ (ሱ.ወ) የሚወጡበት ወር ነው፤ እኔ ፆመኛ ሆኜ ስራዬ ወደ አላህ እንዲወጣልኝ እፈልጋለሁ” ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) የአመቱ ስራዎቻቸው በጥሩ የኢባዳ ደረጃ ላይ ሆነው ወደ አላህ እንዲወጡላቸው (እንዲቀርቡላቸው) ይወዳሉ ማለት ነው፤ ለዚህም ነው “ፆመኛ ሆኜ ስራዬ ወደ አላህ እንዲወጣልኝ እወዳለሁ” ያሉት።
በሸዕባን ወር መጾም ለምን እንዳስፈለገ ሌላ ምክንያትም ተጠቅሷል፤ እሱም ሸዕባንን መፆም ለረመዷን ፆም ልምምድ ይሆናል የሚለው ሲሆን፤ ይህም የረመዷንን ወር እየከበደው እንዳይጀምር ይረዳዋል ማለት ነው፤ ይልቁንም በሸዕባን ወር ፆም ስለተለማመደና የፆምን ለዛ ስለቀመሰ የረመዷንን ፆም በንቃትና በብቃት ይጀምራል።
የሸዕባን ወር ለረመዷን ወር እንደ መግቢያ ስለሆነ በረመዷን የተደነገጉት እንደ ፆምና ቁርአን መቅራት ያሉ ኢባዳዎች በሸዕባንም ይበረታታሉ፤ በዚህም ሰዎች ለረመዷን ጾም የሥነ-ልቦና ዝግጀት ያደርጋሉ፤ ራሳቸውንም በአላህ ጧዓ ላይ ያለማምዳሉ። አንዳንዶች የሸዕባን ወር የቂራኣ ወር ነው ይሉ ነበር።
ሰለማ ቢን ኩሀይል አል-ኩፍይ የተባሉት ታቢዒይ (አላህ ይዘንላቸው) ይህን አስመልክተው እንዲህ ብለዋል፡- “ሸዕባን በሚገባ ጊዜ ሰዎች ወደ ቁርኣንን ይዞሩ ነበር፤ ስለዚህም ነው ሸዕባንን የቁርዐን ወር ያሉት።”
በሸዕባን ወር ልንመካከርባቸውና ትኩረት ልንሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች
ይህ ወር የታላቁ የረመዷን ወር መንደርደሪያና መለማመጃ የአላህ ጣዓን ማብዣ ጊዜ ነው፤ ጀነትን ለሚያፈቅሩና ከመልክተኛው ጋር በጀነት ውስጥ ለመጎራበት ለሚሹ ሁሉ የተቸረ ወርቃማ እድል ነው!
ከዚህ አንፃር በዚህ ወር ትኩረት ልንቸራቸው የሚገቡ አንዳንድ ነጥቦች እንመልከት
- ለተከበረው ለረመዷን ወር አላህ ኢማናችንና ጤናችንን ጠብቆ በሰላም እንዲያደርሰን፤ ወሩንም በአግባቡ ከሚጠቀሙ እንዲያደርግን አጥብቀንና ደጋግመን መለመን (ዱዐ ማድረግ)፤
- በአምልኮታችን የነቢያችንን (ሰ.ዐ.ወ) ፈለግ መከተልና በዚህ ወር ፆም ማብዛት፤
- ሴቶች እህቶቻቸን ካለፈው ረመዷን ያለባቸውን “ቀዷ” ፆም ለማውጣት መፍጠን፤
- የተከበረውና ቁርኣን የወረደበት የረመዷን ወር መግቢያው የተቃረበ ከመሆኑ አንፃር ከአሁኑ በአላህ ፍራቻ ቁርዐንን ማንበብና ማስተንተን፤
- አንደበታችንና አይናችንን ካልተፈቀዱ ነገሮች ለመቆጠብ ልምምድ ማድረግ፤
- በረመዷን ወር ሙስሊሞችን በሰላተ-ተራዊህ የሚመሩ ሀፊዝ ወንድሞች በዚህ በሸዕባን ወር የሐፈዙትን ቁርዐንን ደጋግመው በመቅራትና ሂፍዛቸውን በመከለስ በረመዷን ወር በጥሩ አቋም ላይ መገኘት፤
ጥሩ ስራዎቻችንን ሁሉ አላህ (ሱ.ወ) ይቀበለን፤ የአላህ እዝነት፣ ሠላምና በረከቱ ለሰዎች መልካም ነገርን አስተማሪ በሆኑት ነቢይ ሙሐመድ ላይ ይውረድ።