የሻዕባንን ወር በረመዳን ስሜት

1
6995

“ጌታችሁ በዘመናችሁ ውስጥ ችሮታውን የሚለግስባቸው ቀናት አሉትና ችሮታውን ለማግኘት የተመቻችሁ ሆናችሁ ቅረቡ..” የሚል መልዕክት ከቀደምት አባቶች ተላልፏል። አዎ ወራት ያልፋሉ፤ ቀናትም ይለዋወጣሉ፤ የዓለማት ጌታ አላህ (ሱ.ወ) እዝነቶችና ልግስናዎችም እንደዚሁ ተከታትለው ይመጣሉ::

በነዚህ አሁን ባለንባቸው ቀናትም ግዙፍ የሆኑ መለኮታዊ ልግስናዎች በኛ ላይ አንዣበዋልና እንጠቀምባቸው። የሸዕባን ወር የኸይርና የትሩፋቶች ወር ነው፤ እነደዚሁም የኢባዳና የደግ ስራዎች ወቅት መጀመሪያ ነው፤ ከዚህ ወር ቀጥሎ የሚገባው የረመዳን ወር የታላላቅ የአላህ ልግስናዎች መገኛ ጊዜ ነውና ይህኑ ለማግኘት የምንዘጋጅበት ጊዜ ዘሁን ነው።

የሸዕባን ወር ብልጫ

ታላቁ ሰሐቢይ ኡሳማ ቢን ዘይድ (ረ.ዐ) ለአላህ መከልክተኛ እንዲህ አልኳቸው አሉ፡- የአላህ መልክተኛ ሆይ! በሸዕባን ወር የሚፆሙትን ያህል በሌላ ወር ሲፆሙ አላየኾትም! ይህ ምክንያቱ ምንድን ነው? እርሳቸውም፡-

ذَلِكَ شَهْرٌ يَغْفُلُ النّاسُ عَنْهُ بَــيْنَ رَجَبَ وَرَمَضَانَ، وَهُوَ شَهْرٌ تُرْفَعُ فِيهِ الأَعْمَالُ إلَى رَبِّ الْعَالَمِينَ، فَأُحِبُّ أَنْ يُرْفَعَ عَمَلِي وَأَنَا صَائِمٌ

“ይህ ወር በረጀብና ረመዳን መካከል ስለሆነ ሰዎች ይዘነጉታል፤ በዚህ ወር ስራዎች ወደ አለማት ጌታ አላህ (ሱ.ወ) ይወጣሉ፤ እኔ ፆመኛ ሆኜ ስራዬ ወደ አላህ እንዲነሳ እፈልጋለሁ።” (ኢማሙ ነሳኢይ ዘግበውታል።)

ከላይ ከተጠቀሰው ሐዲስ ብዙ ቁምነገሮችን እንረዳለን፡-

  1. ሶሐባዎች (ረ.ዐም) መልካም ተግባራትን ለማወቅ የነበራቸውን ጉጉት በግልፅ ያሳያል:: በሐዲሱ እንደተጠቀሰው ሰሐባዎች የነቢያችንን (ሰ.ዐ.ወ) ተግባራትና እንቅስቀሴዎች ሌት ከቀን በንቃት ይከታተሉ ነበር፤ ይህንንም የሚያደርጉት የነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ሱና (ፈለግ) ተረድተው የሳቸውን አርአያነት ለመከተል ካላቸው ታላቅ ጉጉት የተነሳ ነበር። ታለቁ ሰሀቢይ ኡሳማ ቢን ዘይድም ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) በሸዕባን ወር ፆም ያበዙ እንደነበር አስተውሏል፤ በመሆኑም ከዚህ ተግባራቸው በስተጀርባ ኸይር ነገር እንዳለ ስላሰበ ይህንን መልካም ነገር ለማወቅ ጉጉት አደረበት፤ ስለሆነም ኸይርን ለማወቅ ነውና ያለምንም ሐፍረትና ፍራቻ ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ስለዚህ ጉዳይ በሸዕባን ወር ፆም የሚያበዙበት ምክንያት ምን እንደሆነ እንዲያብራሩለት ጠየቀ።
  2. ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) “ይህ ወር (ሸዕባን) በረጀብና ረመዳን መካከል ስለሆነ ሰዎች ይዘነጉታል” ማለታቸው የሸዕባን ወር ከተከበሩ ወሮቸ አንዱ የሆነው የረጀብ ወር ስለሚቀድመውና ከዚህም በተጨማሪ የፆም፤ የቁርኣና የበረከት ወር የሆነው የረመዳን ወር ስለሚከተለው ሰዎች ትኩረታቸውን ለነዚህ ታላላቅ ወራት በመስጠት የሸዕባንን ወር እንደሚዘነጉት ማመላከታቸው ነው። ለዚህም ነው ብዙ ሰዎቸ ሸዕባንን ከመፆም ሸህረል ሐራም (የተከበረ ወር) የሆነውን ረጀብን መፆም በላጭ የሚመስላቸው፤ ነገሩ ግን እንዲህ አይደለም።
  3. ሌላው ሐዲሱ የሚያመለክተው ጉዳይ ሰዎች የሚዘነጉባቸውን ጊዚያት በኢባዳ ማነጽ እንደሚገባ ነው። ለዚህም ነው አንዳንድ ሰለፎች በመግሪብና ዒሻ ሶላቶች መካከል ያለውን ጊዜ በኢባዳ ህያው ማድረግ ይወዱ የነበረው፤ ይህች የዝንጋቴ ሰዓት ነች፤ ይሉም ነበር። በተመሳሳይ መልኩ በገበያ ቦታ ላይ አላህን ማውሳትም የተወደደ ነው፤ ምክንያቱም የገባያ ቦታ ሰዎች ጭልጥ ብለው ወደ ዱንያ ጉዳያቸው የሚገቡበትና አላህን ማውሳትና ማስታወስን የሚዘናጉበት ስፍራ በመሆኑ ነው። በዝንጋታ ጊዜያተ የሚደረግ ኢባዳ ምንዳው ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ቀጣዩ ሀዲስ ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል። አሚሩል ሙእሚኒን ዑመር ኢብኑል ኸጧብ (ረ.ዐ) እንዳስተላለፉት ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

مَنْ دَخَلَ السُّوقَ فقالَ: لا إِلهَ إِلاَّ اللَّهُ وَحْدَهُ لا شَريكَ لَهُ، لَهُ المُلْكُ وَلَهُ الحَمْدُ، يُحْيِي ويُمِيتُ وَهُوَ حَيٌّ لا يَمُوتُ، بِيَدِهِ الخَيْرُ وَهُوَ على كُلّ شَيْءٍ قَدِيرٌ: كَتبَ اللَّهُ لَهُ ألْفَ ألْفِ حَسَنَةٍ، وَمَحَا عَنْهُ ألْفَ ألْفِ سَيِّئْةٍ، وَرَفَعَ لَهُ ألْفَ ألْفِ دَرَجَة

“ገበያ ቦታ ሲገባ፡- ‘ላኢላሃ ኢለላህ ወህደሁ ላሸሪከ ለህ፤ ለሁል ሙልኩ ወለሁል ሐምዱ፤ ዩህይ ወዩሚት፤ ወሁወ ሐዩን ላየሙት፤ ቢየዲሂል ኸይር ወሁወ ዓላ ኩሊ ሸይኢን ቀዲር’ (ከአላህ በስተቀር ሌላ አምላክ የለም ንግስናም ምስጋናም ለሱ ብቻ ነው፤ ህያው የሚያደርግ የሚገድል እሱ ግን ህያውና የማይሞት የሆነው፤ መልካም ነገሮች በሞላ በእጁ የሆኑ፤ በሁሉም ነገር ቻይ የሆነ ነው።) ያለ ሰው አላህ (ሱ.ወ) አንድ ሚሊዮን ምንዳ (ሐሰናት) ይጽፍለታል፤ አንድ ሚሊዮን ታናናሽ ወንጀሎችን (ሰይይኣት) ያብስለታል፤ አንድ ሚሊዮን ደረጃ ከፍ የይደረግለታል።” (ሐኪም ዘግበውታል፤ ቡኻሪና ሙስሊምም በተለያዩ መንገዶች ዘግበዎታል። “በጀነት ውስጥ ቤት ይገነባለታል” የሚል ዘገባም ጨምረውበታል።)

የዝንጋታ ጊዜን በኢባዳ ህያው ማድረግ የተለያዩ ጥቅሞች አሉት፤ ከነሱም መካከል፡-

  • ኸይር ስራን መደበቅ ያስችላል፤ ዋጅብ ያልሆኑ ስራዎችን በተለይም ፆምን ከሰው እይታ ደብቆ መስራቱ ደግሞ ተመራጭ ነው። ፆም በባሪያና (ሰው) በጌታው (አላህ) መካከል የሚደረግ ሚስጥር ነውና፤ ለዚህም ነው ፆም ሪያእ (ይዩልኝ) አይገባውም የተባለው። ከሰለፎች ከፊሎቹ ማንም ሳያውቅባቸው ለብዙ አመታት ይፆሙ ነበር፤ ከቤታቸው ወደ ስራ ቦታ ሲወጡ የሚበሉ አስመስለው ዳቦ ይዘው ይወጡና ሰደቃ ሰጥተውት እነሱ ፆመው ይውላሉ፤ ቤተሰቦቻቸው በስራ ቦታ የሚበሉ ሲመስላቸው የስራ ባልደረቦቻቸው ደግሞ በቤታቸው የበሉ ይመስላቸዋል:: ሰለፎች (ቀደምት ደጋግ አበው) ፆመኛ መሆናቸውን የሚያመላክቱ ነገሮች እንዳይታዩ ይጥሩ ነበር:: ታላቁ ሰሐቢይ አብደላህ ቢን መስዑድ (ረ.ዐ) እንዲህ ይላሉ፡-“ፆመኛ ሆኖ ያደረ ሰው ጠዋት ሲወጣ ተቀባብቶ ይውጣ” ሲሉ ቀታዳ የተባሉት ታበዒይም “ፆመኛ ሰው የፆም ምልክት እንዲጠፋ መቀባባት ይወደድለታል” ብለዋል።
  • እንደዚሁም በዝንጋታ ጊዜያት የሚሠሩ ስራዎች ለነፍሰ ይከብዳሉ። አንድ እየከበደን ነፍሳችንን አሸንፈን የምንሰራው ነገር ደግሞ ምንዳው ከፍተኛ ይሆናል። ምክንያቱም አንድ ስራ ብዙሃኑ ሲሳተፍበት ይቀላል፤ ብዙሃኑ ሲተወው ደግሞ ለብቻ ተነጥሎ መስራቱ ይከብዳል። ከሙዐቂል ቢን የሳር ይዘው ኢማሙ ሙስሊም ባስተላለፉት ሐዲስ ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል:-

الْعِبَادَةُ فِي الْهَرْجِ، كَهِجْرَةٍ إِلَيّ

“በፈተና ጊዘያት የሚሠራ ስራ (ኢባዳ) ወደኔ ስደት እንደማድረግ ይቆጠራል።”

የዚህ ምክንያቱ በፈተና ጊዜያት ሰዎች ስሜታቸውን ተከትለው ከዲንና ከኢባዳ ስለሚርቁ፤ በዚያን ወቅት ዲንን አጥብቆ መያዝ ትልቅ ፅናትን ስለሚጠይቅ ነው። ኢማሙ አንነወዊይ (ረሂመሁላሁ) ይህን ሐዲስ ሲያብራሩ እንዲህ ብለዋል፡- “በሐዲሱ ውስጥ የተጠቀሰው ሀረጅ (ችግር ጊዜ) የሚለው ቃል የፈተና ጊዜያት ማለት ሲሆን በዚህ ጊዜ ነገሮች ሁሉ ይቀላቀላሉ፤ በዚህ ወቅት የሚሰራ ኢባዳ ምንዳው የበዛበት ምክንያትም ሰዎች በግርግር ውስጥ ስለሚሆኑ ከኢባዳ ይዘናጋሉ፤ አንዳንድ ሰዎች ብቻ ናቸው ኢባዳ ላይ ጠንክረው የሚገኙት። በመሆኑም ምንዳቸው ከፍተኛ ይሆናል።”

በሸዕባን ወር የሚበረታቱ መልካም ስራዎች

1. ፆም፡- ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ለመፆም ከሚጓጉላቸው ወሮች አንዱ የሸዕባን ወር ነበር። ይህን በተመለከተ አቡ ዳውድ በዘገቡት ሐዲስ እናታችን አዒሻ (ረ.ዐ) “ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) የሸዕባንን ወር መፆም ይወዱ ነበር፤ ከረመዳን ወር ጋርም በፆም ያያይዙታል” ሲሉ ተናግረዋል። ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) የሚወዱትን ነገር መውደድ ደግሞ እሳቸውን መከተል ማለት ነው። በሌላ ዘገባ ኢማሙ ሙስሊም እንዳስቀመጡት ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) የሸዕባንን ወር በሙሉ ወይም ትንሽ ቀናት ብቻ ሲቀር ይፆሙ ነበር፤ ይህን አስመልክቶ ኡለማኦች በሰጡት ማብራሪያ ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ሸዕባንን ወር ሙሉ በሙሉ አልፆሙም፤ ይልቁንም አብዛኛውን የወሩን ክፍል ነበር የሚፆሙት።

ይህን የኡለማኦች ማብራሪያ ቀጥሎ የተጠቀሰውና ኢማም ሙስሊም ከናታችን አዒሻ ይዘው የዘገቡት ሐዲስ ያጠናክረዋል:- “ከረመዳን ወር ውጭ ማንንም ወር ሙሉ በሙሉ ሲፆሙ አላየኋቸውም።” በሌላ ዘገባም “መዲና ከመጡ በኋላ ከረመዳን ውጭ ሌላ ወር ሙሉ በሙሉ አልፆሙም” ሲሉ እናታችን አዒሻ (ረ.ዐ.) ተናግረዋል።

ቡኻሪና ሙስሊም ከአብደላህ ቢን ዓባስ እንደዘገቡት ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ከረመዳን ውጭ የትኛውንም ወር ሙሉ በሙሉ አይፆሙም ነበር፤ ኢብኑ አባስ (ረ.ዐ) ከረመዳን ወር ውጭ ሌላ ወር ሙሉ በሙሉ እንዲፆም አይወዱም ነበር። ታላቁ የሐዲስ ሊቅ ኢብኑ ሐጀር አል ዐስቀላኒ እንደዘገቡት ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) በሸዕባን ወር ሌላ ጊዜ ከሚፆሙት የበዛ ትርፍ ፆም ይፆሙ ነበር፤ አብዛኛውን የሸዕባን ወር ይፆሙት ነበር። በጠቅላላው ፆም ከፍተኛ ምንዳ ከአላህ የሚከፈልበት ኢባዳ ነው፤ አቡ ሰዒድ አል ኹድሪ እንዳስተላለፉት ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- “በአላህ መንገድ አንድ ቀን የፆመ ሰው አላህ (ሱ.ወ) ሰባ አመት ያህል ከእሳት ያርቀዋል።” (ሁለቱ ሸይኾች ተስማምተውበታል።)

ኢማሙ አህመድ ከአብደላህ ቢን ዐምር (ረ.ዐ) ይዘው እንደዘገቡት ነብያችን (ሰ.ዐ.ወ) የሚከተለውን ተናግረዋል፡- “ፆምና ቁርኣን አላህ ዘንድ የቂያማ ቀን ያማልዳሉ። ፆም ጌታዬ ሆይ ይህን ሰው በዱንያ አለም እያለ ቀን ሙሉ ከምግብና መጠጥ ከልክየዋለሁና ለሱ አማላጅነቴን ተቀበለኝ፤ ይላል። ቁርኣን ደግሞ ጌታዬ ሆይ! ይህን ሰው በዱንያ አለም እያለ ሌሊት ከመኝታ ከልክየዋለሁና ለሱ አማልጅነቴን ተቀበለኝ፤ ይላል። ከዚያም አላህ ይቀበላቸውና ሰውየው ይማራል።”

2. አምስት ወቅት ሶላቶችን ጠብቆ በጀመዓ መስገድ፡- ሶላትን ጠብቆ በጀመዓ መስገድ ያለውን ጥሩፋትና ደረጃ እንዲሁም እየቻሉ በችልትኝነት ጀመዓን (የህብረትን ሰላት) ማሳለፍ ያለውን ጉዳት በተመለከተ በብዙ ሐዲሶች ተብራርቷል። ከነዚህም ውስጥ አብደላህ ቢን ኡመር (ረ.ዐ) ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ያስተላለፉት ሀዲስ ይጠቀሳል “በህብረት (በጀመዓ) መስገድ በተናጠል ከመስገድ በሃያ ሰባት ደረጃ ይበልጣል።” (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)

በሌላ ሐዲስ ኢማሙ ሙስሊም እንደዘገቡት ታላቁ ሰሐቢይ አብደላህ ቢን መስዑድ (ረ.ዐ) እንዲህ ብለዋል፡- “ነገ በአኺራ አላህን ሙስሊም ሆኖ መገናኘት የፈለገ ሰው እነዚህን ሶላቶች ተጠባብቆ በጀመዓ ይስገድ። አላህ (ሱ.ወ) ለነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ቅን መንገዶችን ደንግጓል። እነዚህ ሶላቶች ደግሞ ከቅን መንገዶች ናቸው። እናንተም ይህ አፈንጋጭ እንደሚያደርገው ጀመዐ ትታችሁ በቤታችሁ ብትሰግዱ የነቢያችሁን ሱና (መንገድ) ተዋችሁ ማለት ነው፤ የነቢያችሁን መንገድ ከተዋችሁ ደግሞ ጠመማችሁ ማለት ነው። ማንኛውም ሰው በአግባቡ ተፀዳድቶ (ሰውነቱን ታጥቦ አለያም ውዱእ አድርጎ) ወደ አንድ መስጊድ አያመራም፤ አላህ (ሱ.ወ) በእያንዳንዷ እርምጃ አንድ ምንዳ (ሐሰና) የጻፈለት፤ አንድ ወንጀል (ሰይኣ) ያበሰለት፤ አንድ ደረጃ ከፍ ያደረገው ቢሆን እንጂ። ንፍቅናው ግልጽ የወጣ ሰው እንጂ ማንም ከሶላተል ጀመዓ የማይቀርበትን ጊዜ አሳልፈናል፤ አንድን የታመመ ሰው በሁለት ሰዎች መካከል ደግፈው ሶላት ሶፍ ላይ ሲያቆሙትም አይተናል።”

ከላይ የተጠቀሱት ሐዲሶች የሚያስረዱት የሶላተል ጀመዓ ጉዳይ ጥብቅ መሆኑንና የታመሙ ሰዎች እንኳ ጀመዓ ላይ ለመገኘት የሚያስችላቸው ሁኔታ ካለ መገኘት እንዳለባቸው ነው። ሶለተል ጀመዐን በተመለከተ ሌላም ብዙ ሐዲሶች ተዘግበዋል።

3. በሸዕባን ወር ቁርኣንን መቅራት፤ መሐፈዝ (መሸምደድ) እና ማጥናት፡- አላህ ዘንድ ከፍተኛ ምንዳ ከሚያስገኙ ታላላቅ የኸይር በሮች አንዱ ነው። አብደላህ ቢን መስዑድ (ረ.ዐ) ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል ሲሉ አስተላልፈዋል፡- “ከአላህ መጽሐፍ (ቁርአን) አንድን ፊደል ያነበበ ሰው ለሱ ኸይር ሥራ ይጻፍለታል፤ አንዱ ኸይር ሥራ ደግሞ በአስር ይባዛል፤ አሊፍ-ላም-ሚም የሚለው አንድ ፊደል ነው አልልም፤ ነገር ግን አሊፍ ብቻውን አንድ ፊደል ነው፤ ላም ብቻውን አንድ ፊደል ነው፤ ሚም ብቻውን አንድ ፊደል ነው።” (ቲርሚዚይ ዘግበውታል።)

የሸዕባን ወር የረመዳን ወር መግቢያ እንደመሆኑ መጠን በረመዳን ወር የሚበረታቱ እንደ ፆም፤ ቁርኣንና ሰደቃ ያሉ መልካም ተግባራት ማብዛት ተገቢ ይሆናል። ሰለማ ቢን ሱሐይል እንዳሉት የሸዕባን ወር የቃሪኦች ወር እየተባለ ይታወቅ ነበር። ሐቢብ ቢን አቡ ሳቢት የሸዕባን ወር ሲገባ “ይህ የቃሪኦች (የቁርዐን ወዳጆች) ወር” ነው ይሉ ነበር። ዐምር ቢን ቀይስ አል ሙላኢይ የሸዕባን ወር ሲገባ ሁሉን ነገር ትተው ቁርኣንን ወደ መቅራት ይዞሩ ነበር።

4. ለመጀመሪያው የሙስሊሞ ቂብላ ዱዓ ማድረግ፡- ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ወደ መዲና ከሄዱ በኋላ ለአስራ ሰድስት ወራት ያህል ፍልስጤም ወደሚገኘው መስጅደል አቅሷ አቅጣጫ ዞረው ነበር የሚሰግዱት። ቂብላ (የሶላት አቅጣጫ) ከመስጅደል አቅሷ ወደ መስጅደል ሐራም የዞረው በሸዕባን ወር ነበር።

قَدْ نَرَىٰ تَقَلُّبَ وَجْهِكَ فِي السَّمَاءِ ۖ فَلَنُوَلِّيَنَّكَ قِبْلَةً تَرْضَاهَا ۚ فَوَلِّ وَجْهَكَ شَطْرَ الْمَسْجِدِ الْحَرَامِ ۚ وَحَيْثُ مَا كُنتُمْ فَوَلُّوا وُجُوهَكُمْ شَطْرَهُ ۗ وَإِنَّ الَّذِينَ أُوتُوا الْكِتَابَ لَيَعْلَمُونَ أَنَّهُ الْحَقُّ مِن رَّبِّهِمْ ۗ وَمَا اللَّهُ بِغَافِلٍ عَمَّا يَعْمَلُونَ

“የፊትህን ወደ ሰማይ መገላበጥ በእርግጥ እናያለን። ወደምትወዳትም ቂብላ እናዞርሃለን። ስለዚህ ፊትህን ወደ ተከበረው መስጊድ (ወደ ካዕባ) አግጣጫ አዙር። የትም ስፍራ ብትኾኑም (ስትሰግዱ) ፊቶቻችሁን ወደርሱ አግጣጫ አዙሩ።” (አል-በቀራ 2፤ 144)

ታዲያ በዚህ አጋጣሚ የመጀመሪያው ቂብላችን በአሁኑ ሰዓት በቀማኛ አይሁዳዊያን የሚፈጸምበትን ሴራ እያየን አላህ (ሱ.ወ) ከአይሁድ እጅ ነጻ አውጥቶት ወደ ሙስሊሞች እንዲመልሰው በዱዓ እንኳን ልናስታውሰው ይገባል።

5. የሌሊት ሶላትን መለማመድ፡- ብዙ ሙስሊሞች የሌሊት ሶላት (ቂያም አል-ለይል) ትዝ የሚላቸው በረመዳን ወር ብቻ ነው። በረመዳን ወርም ቢሆን ሌሊት ለመቆም በጣም ይከብዳቸዋል፤ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ከረመዳን ውጭ ሌሊት መቆም ባለመለማመዳቸው ነው። በረመዳን ወር የቂያም ሶላት (ተራዊህ) በድንገት ሲመጣብን ሁልጊዜ ጠብቀን ለመስገድ ከፍተኛ ችግር ያጋጥመናል። ሰውነታችን ከረመዳን ውጭ ባሉ ጊዜያት አመቱን ሙሉ ሌሊት መቆም ተለማምዶ በነበር ግን በረመዳን ወር የሌሊት ሶላት ባልከበደን ነበር። ስለዚህ የረመዳን ወር ከመግባቱ በፊት በሸዕባን ወር ቢያንስ ሁለት ረከዓ እንኳ ሌሊት ተነስቶ አለያም ማታ ከዒሻ ሶላት በኋላ በመስገድ ለረመዳን ቂያም መዘጋጀት ያስፈልጋል። ኢማም ሙስሊም ከእናታን አዒሻ (ረ.ዐ) በዘገቡት ሐዲስ እንደተጠቀሰው ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- “ወደ አላህ (ሱ.ወ) ተወዳጅ የሚሆነው ሥራ ትንሽ እንኳ ቢሆን ዘውታሪ የሆነው ነው።” እናታችን አዒሻ አንድን ሥራ ከሠሩ ሁል ጊዜ ይዘወትሩበት ነበር።

6. በሙስሊሞች መካከል ያለን ግንኙነት ማስተካከል፡- ሥራዎች ወደ አላህ (ሱ.ወ) የሚቀርቡት በሸዕባን ወር መሆኑን ባሳለፍናቸው ሐዲሶች ጠቅሰናል። ስለዚህ ነው ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ሥራቸው ወደ አላህ በሚቀርብ ጊዜ እሱን በመታዘዝ ላይ መሆን የፈለጉት። ይህም አንድ ሙስሊም ሥራው ወደ አላህ (ሱ.ወ) በሚቀርቡበት የተከበረው የሸዕባን ወር በሙሉ ታዛዥነት (ጦዓ) ላይ ሆኖ እንዲገኝ የሚችለውን ሁሉ ማድረግ እንዳለበት ጠቋሚ ነው። ይህ ሁኔታ አንድ ሙስሊም ሥራው ወደ አላህ ሲቀርብ በዚህ ሁኔታ ላይ ከተገኘ አንዳንድ ጉድለቶች ቢገኙበት እንኳ አላህ (ሱ.ወ) በእዝነትና በማርታ አይኑ ተመልክቶት እንዲቀበለው መክንያት ሊሆነው ስለሚችል ነው። በሰዎች መካከል ያሉ ሁኔታዎችን ማስተካከልና ለችግሮች መፍትሄ መስጠት በተለይም በዚህ የተከበረ ወር ትልቅ ኢባዳ ነው። አቡ ደርዳእ እንዳስተላለፉት ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ለሰዎች እንዲህ አሏቸው፡-

‏قَالَ رَسُولُ اللَّهِ- ‏صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ-:”‏أَلا أُخْبِرُكُمْ بِأَفْضَلَ مِنْ دَرَجَةِ الصِّيَامِ وَالصَّلاةِ وَالصَّدَقَةِ”؟. قَالُوا: بَلَى. قَالَ: “صَلاحُ ‏‏ذَاتِ الْبَيْنِ؛ ‏فَإِنَّ فَسَادَ ‏ذَاتِ الْبَيْنِ ‏هِيَ الْحَالِقَةُ

“ከፆም፤ ከሶላትና ከሰደቃ የበለጠ ደረጃ ያለውን ነገር ልንገራችሁን?” ሰዎቹም አዎ አሉ፤ ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) አሉ፡- “በመካከላችሁ ያለው ሁኔት (ግንኙነት) መስተካከል ነው፤ በሰዎች መካከል ያለው ሁኔታ መበላሸት ላጭ (አጥፊ) ነው” (ቲርሚዚ ዘግበውታል።) በሌላ ዘገባም ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) “እሷ ላጭ ነች፤ ፀጉርን ትላጫለች አልልም፤ ነገር ግን ዲንን ትላጫለች- ታጠፋለች” ብለዋል።

በቱህፈቱል አህወዚ (የቲርሙዚ ሸርህ/ማብራሪያ) እንደተጠቀሰው “ሃሊቃ (ላጭ) ማለት ልክ ምላጭ ፀጉርን ከመባቀያው ሙልጭ አድርጎ እንደሚያስወግድ ሁሉ ዲንን ከመሠረቱ ሙልጭ አድርጎ የሚያጠፋ ነገር ማለት ነው። ዲንን የሚላጭ ማለት ዝምድናን መቁረጥና ሰዎችን መበደል ማለት ነው ተብሎም ተተርጉሟል። ጢቢይ የተባሉት አሊም እንዳሉት ይህ ሐዲስ በሰዎች መካከል ያለውን ግንኙነት ማስተካካል አስፈላጊ እንደሆነ ያበረታታል፤ ምክንያቱም በሰዎች መካከል ያለው ግንኙነት ያማረ ሲሆን በሙስሊሞች መካከል አንድነት ይፈጣራል፤ በሙስሊሞች መካካል ያለው ግንኙነት ሲበላሽ ደግሞ ዲናቸው ላይ ጠባሳ ይጥላል፤ በመሆኑም የሙስሊሞችን ግንኙነት እንደይበሽ የተንቀሳሰ ሰው ቀን እየፆመ ሌት እየቆመ የግል ኢባዳ ከሚሠራ ሰው የበለጠ ደረጃ ያገኛል።”

ስለዚህ ክቡር ሙስሊም ሆይ! የሸዕባንን ወር በኢባዳ ካነፅክ በኋላ ከዘመዶችህ ወይም ከጠቅላላው ሙስሊም ወንድሞችህ ጋር ያለህ ግንኙነት በመበላሸቱ ምክንያት ምንዳህ ሊጎድልብህ አይገባም።

ውድ ወንድሜ ሆይ! በሙስሊሞች መካከል የሚኖር ጥላቻና ጭቅጭቅ ምን ያህል ጉዳት እንዳለው ቀጥሎ የሚጠቀሰው ሐዲስ ያስረዳናል፤ አቡ ሁረይራ (ረ.ዐ) እንደዘገቡት ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

تُفْتَحُ أَبْوَابُ الْجَنَّةِ يَوْمَ ‏الاثْنَيْنِ وَيَوْمَ الْخَمِيسِ فَيُغْفَرُ لِكُلِّ عَبْدٍ لا يُشْرِكُ بِاللَّهِ شَيْئًا إِلاَّ رَجُلاً كَانَتْ بَيْنَهُ وَبَيْنَ أَخِيهِ شَحْنَاءُ ‏فَيُقَالُ: أَنْظِرُوا ‏‏هَذَيْنِ حَتَّى يَصْطَلِحَا، ‏أَنْظِرُوا ‏هَذَيْنِ حَتَّى يَصْطَلِحَا، أَنْظِرُوا هَذَيْنِ حَتَّى يَصْطَلِحَا

“የጀነት በሮች በሰኞና ሐሙስ ቀኖች ይከፈታሉ፤ በሱና በወንድሙ መካከል ጥል ያለው ሰው ሲቀር ማንኛውም በአላህ የማያጋራ ሰው ሁሉ ምህረት ያገኛል፤ እነዚህን እርቅ እስከሚያወርዱ ድረስ አዘግይዋቸው፤ እነዚህን እርቅ እስከሚያወርዱ ድረስ አዘግይዋቸው፤ እነዚህን እርቅ እስከሚያወርዱ ድረስ አዘግይዋቸው ይባላል::”

ከሐዲሱ እንደምንረዳው በሙስሊሞች መካከል የሚፈጠረው አለመግባባትና ንትርክ ሥራዎች ወደ አላህ በሚቀርቡበት ጊዜ ተቀባይነታቸው እንደሚያዘገይ ነው። የሸዕባን ወር ደግሞ ሥራዎች ወደ አላህ (ሱ.ወ) የሚወጡበት ጊዜ ነው፤ ስለዚህ በዚህ የተከበረ ወር ወንጀላችንን እንዳይማር ምክንያት የሚሆንን ነገር ሁሉ መራቅ አለብን።

የተከበረው የረመዳን ወር ወደኛ ሊደርስ ጥቂት ቀናት በቀሩበት በአሁኑ ወቅት ከጥላቻና ከቅሬታ የፀዳና በፍቅርና በደግነት የተሞላ ንጹህ ልቦና ይዘን ልንቀበለው ይገባል። በመካከላችን የተበላሸ ነገር ካለም ይህን የሸዕባንን ወር ተጠቅመን ማስተካከል ይገባል።

ወደ መልካም ሥራዎች እንሽቀዳደም

አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡-

۞ وَسَارِعُوا إِلَىٰ مَغْفِرَةٍ مِّن رَّبِّكُمْ وَجَنَّةٍ عَرْضُهَا السَّمَاوَاتُ وَالْأَرْضُ أُعِدَّتْ لِلْمُتَّقِينَ

“ከጌታችሁ ወደ ኾነችም ምሕረትና ስፋትዋ እንደ ሰማያትና ምድር ወደ ኾነች ገነት አላህን ለሚፈሩ የተዘጋጀች ስትኾን ተቻኮሉ።” (አሊ ዒምራን 3፤ 133)

እንዲህም ይላል፡-

سَابِقُوا إِلَىٰ مَغْفِرَةٍ مِّن رَّبِّكُمْ وَجَنَّةٍ عَرْضُهَا كَعَرْضِ السَّمَاءِ وَالْأَرْضِ أُعِدَّتْ لِلَّذِينَ آمَنُوا بِاللَّهِ وَرُسُلِهِ ۚ ذَٰلِكَ فَضْلُ اللَّهِ يُؤْتِيهِ مَن يَشَاءُ ۚ وَاللَّهُ ذُو الْفَضْلِ الْعَظِيمِ

“ከጌታችሁ ወደ ኾነች ምሕረት፣ ወርዷ እደ ሰማይና ምድር ወርድ ወደ ሆነችም ገነት ተሽቀዳደሙ። ለእነዚያ በአላህና በመልክተኞቹ ላመኑት ተዘጋጅታለች። ይህ የአላህ ችሮታ ነው። ለሚሻው ሰው ይሰጠዋል። አላህም የታላቅ ችሮታ ባለቤት ነው።” (አል-ሐዲድ 57፤ 21)

فَاسْتَبِقُوا الْخَيْرَاتِ

“ወደ መልካም ሥራዎችም ተሽቀዳደሙ።” (አል-በቀራ 2፤ 148)

አዎ በዚህ በተከበረው የሸዕባን ወር ሁሉም የአላህ ምህረትና እዝነት ለማግኘት ይሽቀዳደማል። ሁሉም አዲስ ምዕራፍ በመክፈት መልካም ነገሮችን በመስራት የአለማት ጌታ አላህ (ሱ.ወ) ትዕዛዛት ይፈጽማል። ይህ አዲስ ምዕራፍ በሸዕባን ወር ይጀምርና በረመዳን ወር ከፍ ይበል፤ ከዚያም አመቱን ሁሉ ይቀጥል። ሙስሊም ሆይ ታለቅ ኸይርና ትርፍ ሊያመልጣችሁ አይገባም፤ ስለሆነም ወደዚህ መለኮታዊ ስጦታና የኢማን ምጥቀት ፈጠን ብለህ ጉዞ እንጀምር።

1 COMMENT

  1. Hulum neger be Allah feqad nwu yemiho nwu!!! Web sayitu ke agenyehung jemero bexam bedesta, b niyah iyanebeb kung nwu gn …beyibelx degmo temhertun kenate gar face to face bageng felagote nbr… Allah Alimochachenen edmena xena yisxeln!!! Amen Allahuma Amen Ya Rabal Alamen <3

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here