ኢስራእና ሚዕራጅ – አስተምህሮትና ተግሳፅ

2
17902

ሙስሊሞች በየዓመቱ አንድ ታላቅ ነቢያዊ ክስተት ያሳልፋሉ። አሏህ (ሱ.ወ) በተከበረዉ ቁርዓን ዉስጥ ታሪካዊነቱን ዘግቧል። ከዛም አልፎ ክስተቱን የቁርዓን ምዕራፍ መሰየሚያ አድርጎታል። ያ ክስተት “የኢስራእና የሚዕራጅ” ሌሊት በመባል ይታወቃል። ሀያ ሰባተኛው የረጀብ ሌሊት ላይ ነበር ይህ ተዓምራዊ ጉዞ የተደረገው። “ኢስራእ” ማለት በየብስ የተደረገ የየብስ ጉዞ ነው።

አላህ (ሱ.ወ) ታላቁን ነቢይ (ሰ.ዐ.ወ) በአንድ ሌሊት ከመካ ወደ በይተል-መቅደስ (ከመስጅደል-ሃረም ወደ መስጅደል-አቅሷ) እነዲጓዙ ያስቻለበት ነዉ።

“ሚዕራጅ” ማለት ከምድር ወደ ሰማይ የተደረገ የህዋ ጉዞ ነዉ። የጉዞው መነሻ በይተል-መቅደስ ሆኖ ወደ ሰማየ-ሰማያት የተደረገ እርግታ ነዉ። ይህንን መዳረሻ የሰው ልጅ ኮቴ ረግጦት አያቅም። “ሲደረተል-ሙንታሃ” ይሰኛል- የጉዞዉ መዳረሻ። ምንነቱን አላህ (ሱ.ወ) ብቻ ነዉ የሚያዉቀዉ።

እነኝህ ሁለት ጉዞዎች በነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ህይዎትና በመካ ዳዕዋቸው ላይ ወሳኝ እርከኖች ናቸዉ። ከመካ ቁረይሾች ዓይነቱ የበዛ መከራን ካሳለፉ በኋላ ምናልባት “ሠቂይፍ” የተባሉ የጧኢፍ ጎሳዎች ዘንድ ተቀባይነትን የማግኘት ተስፋን ሰንቀው ወደ ጧኢፍ አመሩ። ዳሩ ግን አስከፊ መልስ ነበር የጠበቃቸው። ቂላቂሎቻቸዉን ሰባሰቡባቸዉ፤ ባሮቻቸዉን አዘዙባቸዉ፤ በህፃናቶቻቻዉ ድንጋይ አስወረወሩባቸዉ። የረሱል (ሰ.ዐ.ወ) እግር በደም ተጠመቀ። አግልጋያቸዉ ዘይድ ብን ሃሪሣህ (ረ.ዐ) የሚወረወሩ ድንጋዮች እርሱ ላይ እንዲዘንቡ ይጥራል። የረሱልን (ሰ.ዐ.ወ) ስቃይ ይቀንስ ዘንድ ይረባረባል። የራስ ቅሉ በርካታ ቦታ ላይ ተፈነከተ። በሰውነቱ ላይ የሚፈሰው ደም ጫማውንም አራሰ።

ረሱሉ (ሰ.ዐ.ወ) እግራቸዉ በደም ተጠምቆ ከጧኢፍ ወጡ። ከሚዘንብባቸው የድንጋይ ናዳ የበለጠ ልባቸዉን ያደማው ይሰነዘሩባቸው የነበሩ የንቀትና የስድብ ቃላት ነበር። ለዚህም ነበር እንዲህ ብለዉ ዱዓእ ማድረጋቸዉ

اللهم إني أشكوا إليك ضعف قوتي وقلة حيلتي وهواني على الناس ياأرحم الراحمين, أنت رب المستضعفين وأنت ربي إلى من تكلني, إلى بعيد يتجهمني, أم إلى عدو ملكته أمري إن لم يكن بك غضب علي فلا أبالي, ولكن عافيتك أسع لي, أعوذ بنور وجهك الذي أشرقت به الظلمات, وصلح عليه أمر الدنيا والآخرة, أن ينزل بي غضبك أويحل بي سخطك

“ጌታዬ ሆይ! የሀይሌን መድከም፤ የመላዬን ማነስና ሰዎች ዘንድ የደረሰብኝን ንቀት ለአንተ አቤት እላለሁ። አንተ የአዛኞች ሁሉ አዛኝ! አንተ የደካሞች ጌታ- አንተ የኔ ጌታ! ለማን ትተወኛለህ? ለሩቅ አጥቂ ትሰጠኝ ወይንም በጠላት እጅ ላይ ትጥለኝ? በኔ ላይ ተቆጥተህብኝ ካልሆነ በሚደርስብኝ ሁሉ ግድ የለኝም። ነገር ግን እኔን ደህና ማድረገህ ለኔ የሰፋ ነዉ። ጨለማዎችን ባበራዉ በአንተ ብርሃን፤ የቅርቢቱም ይሁን የመጭዉን አለም ያሳመረ በሆነዉ የአንተ ብርሃን እጠበቃለሁ – ቁጣህ እንዳይወርድብኝ ወይም ጥላቻህ እንዳይሰፍርብኝ።”

ይህኔ አላህ (ሱ.ወ.) የተራራን መላኢካ ወደ ረሱሉ (ሰ.ዐ.ወ) ላከ።

“አንተ ሙሀመድ ሆይ! ሁለቱን ተራራዎች በነርሱ ላይ እንዳላትም ፍላጎትህ ከሆነ አደርገዋለሁ።” አላቸዉ።

አዛኙ ነቢይ (ሰ.ዐ.ወ) ይህንን ተቃወሙ። እንዲህም አሉ:-

“ከአብራካቸዉ እርሱን በብቸኝነት ያለማጋራት የሚያመልኩ ልጆችን አላህ (ሱ.ወ) እንደሚያወጣ ተስፋ አደርጋለሁ” አሉና ይህንን ዱዓ አስከተሉ:-

اللهم اهدي قومي فإنهم لايعلمون.

“ጌታዮ ሆይ! የሚሰሩትን አያዉቁምና ወደ ትክክልኛዉ ጎዳና ምራቸዉ።”

ከዚህ ክስተት በኋላ ነበር የኢስራእና ሚዕራጅ ጉዞ እዉን የሆነዉ። የደረሰባቸውን መከራ ይረሱ፤ ስቃያቸዉን ያስታገሱ ዘንድ ይህ ታአምራዊ ጉዞ ሆነ። “የምድር ቤት ሰዎች እንደማይቀበሉህ ሊነግሩህ በድንጋይ ቢወግሩህ የሰማዩ ቤት አቀባበል ከፍ ያለ ነዉ” እንደማለት ነዉ።

“እነኝ ሰዎች ሀገራቸዉን ቢከለክሉህ ታለቁ አላህ (ሱ.ወ) ያስተናግድሀል። አንቢያዎች ይከተሉሃል- ኢማማቸዉም ትሆናለህ።” የሚል መልዕክት ነበረዉ። ይህ በርግጥም ለደረሰባቸዉ መከራ ማካካሻና አሏህ ዘንድ ያላቸዉን ልቅናምም መጨመሪያ ነበር። በተጨማሪም ከሂጅራ በኋላ ላለው ወሳኝ እርከን እያዘጋጃቸዉ ነበር። ከሂጅራ በኋላ የዳዕዋ ህይዎት ከባድ የትጥቅ ትግልንም ያካተተ ነበርና። ዐረቦቹ በሙሉ በረሱሉ (ሰ.ዐ.ወ) ላይ አንድ ግንባር የሚፈጥሩበት ጊዜ ነው። የተለያዩ ተቀናቃኝ ግንባሮች አንድነት ፈጥረው የረሱሉን ዳዕዋ ሊያጠፉ የሚነሱበት ወቅት ነዉ። ዐረቢያ ደሴት ያለው ባዕድ አምላኪዎች በአንድ በኩል፤ እሳት አምላኪ መጁሳዎች በሌላ በኩል፤ አላህ (ሱ.ወ) ያወረደዉን መፅሀፍ በመለወጥና ቃል ኪዳን በማፍረስ የሚታወቁት ሸፍጠኛ አይሁዶችም በአንድ ግንባር ተሰልፈዋል። ኢንጅልን የለወጡና ተዉሂድን ከጣዖታዊነት ጋር የቀላቀሉ ክርስቲያኖችም በሮማ ቤዛንታይን አዝማችነት አንድ ግንባር ናቸዉ።

ታዲያ ለዚህ ትልቅ ትግል ረሱሉ (ሰ.ዐ.ወ.) መዘጋጀት ነበረባቸዉ። ዝግጅቱ እነኝህን ሁሉ ኃይላት በፅናት መጋፈጥ የሚያስችል መሆን ነበረበት። ረሱሉ (ሰ.ዐ.ወ) እነኝህን ኀይላት በአናሳ ቁጥርና እዚህ ግባ በማይባል የሎጅስቲክ ዝግጅት መጋፈጥ አይቀራቸዉም። እናም አላህ (ሱ.ወ) የምድርንም የሰማያትንም ተዓምራት ያሳያቸዉ ዘንድ ፈለገ።

سُبْحَانَ الَّذِي أَسْرَىٰ بِعَبْدِهِ لَيْلًا مِنَ الْمَسْجِدِ الْحَرَامِ إِلَى الْمَسْجِدِ الْأَقْصَى الَّذِي بَارَكْنَا حَوْلَهُ لِنُرِيَهُ مِنْ آيَاتِنَا إِنَّهُ هُوَ السَّمِيعُ الْبَصِيرُ
 

“ያ ባሪያውን ከተከበረው መስጊድ ወደዚያ ዙሪያውን ወደ ባረክነው ወደ ሩቁ መስጊድ በሌሊት ውስጥ ያስኼደው (ጌታ) ጥራት ይገባው። ከተዓምራቶቻችን ልናሳየው (አስኼድነው)። እነሆ እርሱ (አላህ) ሰሚው ተመልካቺው ነው።” (አል-ኢስራእ 17፤ 1)

በዚህ ፍጥረተ-ዓለም ውስጥ ያለን ተአምር ይመለከቱ ዘንድ- ረሱሉ (ሱ.ዐ.ወ)። በምድርም ብቻ ሳይገታ በሰማያትም ያለን አስደናቂ ተዓምራት ይመለከቱ ዘንድ! የ“ነጅም” ምእራፍ ላይም ይህንን የሰማይ ተዓአምራትን አስመልክቶ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል:-

مَا زَاغَ الْبَصَرُ وَمَا طَغَىٰ لَقَدْ رَأَىٰ مِنْ آيَاتِ رَبِّهِ الْكُبْرَىٰ

“ዓይኑ (ካየው) አልተዘነበለም። ወሰንም አላለፈም። ከጌታው ታምራቶች ታላላቆቹን በእርግጥ አየ።” (አን-ነጅም 53፤ 17-18)

የረሱሉ (ሰ.ዐ.ወ) ልብ ይጠነክር፣ ጥንካሬያችዉ ይታደስ፣ ሞራላቸዉ ይገንባና የክህደትን ማዕበል ከሁሉም አቅጣጫ መመከት ይችሉ ዘንድ ከታላላቅ ተዓምራቶች አሳያቸው።

የሶላት ግዴታ መሆን

ኢስራእና ሚዕራጅ ለረሱሉ (ሰ.ዐ.ወ) ልቅና የተዘጋጀ ጉዞ ነበር። በመካም ሆን በጧኢፍ ህዝባችዉ ያደረሰባቸዉን ስቃይ ማስረሻና መንፈሳቸውን ማደሻም ነበር። ከዚህ ሁሉ በተጨማሪ አንድ ትልቅ ሀላፊነትም የተረከቡበት ጉዞ ነበር። ያ ሃላፊነትም ለወደፊት በራሳቸዉም ይሁን በተከታይ ሙስሊሞች ህይዎት ላይ ከባድ ተፅእኖ የሚኖረዉ ግዙፍ ሃላፊነት ነበር- ሶላት። በዚህች ታላቅ ሌሊት አላህ (ሱ.ወ) ሶላትን ግዴታ አደረገ። የአላህ ፍላጎቱ ነበር- ወደ ሰዎች አምባሳደር የሆነዉን ታላቅ ሰዉ መጥራት። ሙሀመድ (ሱ.ዐ.ወ)። በሌሊት ጉዞ ከተከበረው ከአላህ (ሱ.ወ) ቤት መስጅደል-ሃረም ወደ መስጅድል-አቅሷ – ከዛም ሰማይ ሰማያትን አቋርጠው “ሲደርተል -ሙንታሃ”ን ረገጡ። ይህ ጉዞ የኃላፊነቱን ክብደት ያሳያል። ሶላት ግዴታ ተደረገ። ሶላት በሙስሊም ግለሰብና ማህበረሰብ ዘንድ ሊኖረዉ የሚገባዉን ትኩረትና ክብደት አመልካች ነበር። ይህች ሰግደት (ሶላት) አንድ ባርያ ከጌታው ጋር የሚገናኝበት ቀጠሮ ነች። ሶላት የተደነገገዉ ሀምሳ የሶላት ወቅቶች ሁኖ ነዉ። በወንድማቸዉ ነቢዩላህ ሙሳ (ዐ.ሰ) ምክር እተመላለሱ ወደ አምስት ወቅት አስቀነሱ። የአሏህ እዝነቱ ሰፊ ነውና በተግባር አምስት በአጅር ግን ሃምሳ ሶላት ያክል ሆኑ- የተደነገጉት አምስት ወቅት ሶላቶች። በሌላ መልኩ አንድ ሰዉ ከአንድ ጉዞ መልስ ስጦታ (ሀድያ) ይዞ እንደሚመለሰዉ አዛኙ ነብይም (ሰ.ዐ.ወ) ከዚህ ተዓምራዊ ጉዞ መልስ ለዑመታቸዉ ሶላትን ሀድያ ይዘዉ መጡ። ሶላት ለሁሉም ሙስሊም ከረሱሉ (ሱ.ዐ.ወ) የተበረከተ ሀድያ እንደማለት ነዉ። ይህች ታላቅ ሀድያ አንድ ሙስሊም የተላቀዉን ጌታውን ይገዛበታል። የመንፈስ እርካታንም ይጎናፀፍበታል። ዉስጡን ያፀዳበታል። የዱንያ ጭንቀቱን ያስወግድለታል። በርግጥም ከርሷ ረፍትን ያገኛል። ስክነት ዉሰጥ ይሆናል።

ሶላትን ስናስብ ምንግዜም መስጅደል-አቅሷን እናስታዉሳለን። ያ የመጀመሪያዉ የሙስሊሞች ቂብላ ነው። ረሱሉ (ሰ.ዐ.ወ) ከተላኩ ጀምሮ ለሦስት አመታት ወደሱ ዙረዉ ሰግደዋል። ከዛም ፊታቸዉን ወደ ካዕባ ያዞሩ ዘንድ አላህ አዘዛቸዉ።

فَوَلِّ وَجْهَكَ شَطْرَ الْمَسْجِدِ الْحَرَامِ وَحَيْثُ مَا كُنتُمْ فَوَلُّوا وُجُوهَكُمْ شَطْرَهُ
 

“ስለዚህ ፊትህን ወደ ተከበረው መስጊድ (ወደ ካዕባ) አግጣጫ አዙር። የትም ስፍራ ብትኾኑም (ስትሰግዱ) ፊቶቻችሁን ወደርሱ አግጣጫ አዙሩ።” (አል-በቀራ 2፤ 144)

መዲና ያሉ አይሁዶች በዚህ አምላካዊ ትዕዛዝ ላይ አሉባልታችዉን እና ዉዝግቦችን አንሱ።

سَيَقُولُ السُّفَهَاءُ مِنَ النَّاسِ مَا وَلَّاهُمْ عَن قِبْلَتِهِمُ الَّتِي كَانُوا عَلَيْهَا

“ከሰዎቹ ቂሎቹ ‘ከዚያች በርሷ ላይ ከነበሩባት ቂብላቸው ምን አዞራቸው?’ ይላሉ፤” (አል-በቀራ 2፤ 142)

“ከአሁን በፊት ይሰግዱት የነበረዉ ሶላት ውድቅ ሆነ” ሲሉም ወሬ ነዙ። አላህም ለዚህ አሉባልታቸዉ መልስ ሰጠ።

وَمَا جَعَلْنَا الْقِبْلَةَ الَّتِي كُنتَ عَلَيْهَا إِلَّا لِنَعْلَمَ مَن يَتَّبِعُ الرَّسُولَ مِمَّن يَنقَلِبُ عَلَىٰ عَقِبَيْهِ وَإِن كَانَتْ لَكَبِيرَةً إِلَّا عَلَى الَّذِينَ هَدَى اللَّهُ وَمَا كَانَ اللَّهُ لِيُضِيعَ إِيمَانَكُمْ إِنَّ اللَّهَ بِالنَّاسِ لَرَءُوفٌ رَّحِيمٌ

“ያችንም በርሷ ላይ የነበርክባትን አቅጣጫ መልክተኛውን የሚከተለውን ሰው ወደ ክህደት ከሚመለሰው ሰው ልናውቅ (ልንገልጽ) እንጅ ቂብላ አላደረግናትም። እርሷም በነዚያ አላህ በመራቸው ሰዎች ላይ በስተቀር በእርግጥ ከባድ ናት። አላህም እምነታችሁን (ስግደታችሁን) የሚያጠፋ አይደለም፤ አላህ ለሰዎች በጣም ርኅሩኅ አዛኝ ነውና።” (አል-በቀራ 2፤ 143)

“ዕምነታችሁን” ማለት ሶላታችሁን ማለት ነዉ። ሶላትን ዕምነት ብሎ ገለጸ። ምክንያቱም እምነት የሚገለፅበት ተግባር ነችና። ሶላት ያችን የተባረከች ሌሊት ዘላለም እንድናስታዉስ ታደርገናለች።

የኢስራአና ሚእራጅ ጉዞ አሰተምህሮቶች

ኢስራእና ሚዕራጅን ስናስብ ሁለት ዋና ዋና ቁም-ነገሮች ላይ በጽኑ እናተኩራለን።

የመጀመሪያው የአቅሷ መስጂድ ነው። አላህ (ሱ.ወ) በመስጂደል-ሃረምና በመስጂደል-አቅሷ መካከል እንዴት ትስስር እንደፈጠረ እናሰተዉላለን። ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ከመካ ቀጥታ ወደ ሲደርተል-ሙንተሃ አላረጉም። በሌሊት ጉዞ (ኢስራእ) ከመካ ወደ በይተል-መቅዲስ ተጉዘዋል። ይህ ትኩረት የሚሻ፣ አስተዉሎ የሚጠይቅ ነጥብ ነው። ለምን ይሆን አላህ (ሱ.ወ) ይህንን ማድረጉ? ለምን ይሆን ሀረምን ከአቅሷ ማስተሳሰሩ? ይህ ክስተት አንድ ነገር ይጠቁመናል። ረሱሉ (ሰ.ዐ.ወ) በዚህ በተቀደሰዉ በይተል-መቅዲስ ማለፋቸዉ ድንገተኛ አልነበርም። በይተል-መቅዲስና ዙሪያዋ የተባረከች ምድር ነች። በበይተል-መቅዲስ ቆይታቸዉ ነብያትን ኢማም ሆነዉ አሰግደዋል። ይህ ከባድ መልእዕክትን ያዘለ ሁነት ነው። ነብያቶችን በጠቅላላ ኢማም ሆነዉ ረሱሉ (ሰ.ዐ.ወ) የማሰገዳቸው ትርጉም እንዲህ ነዉ፡-

“የሠዉን ልጅ የመምራቱ ኅላፊነት ወደ አዲሱ የረሱሉ (ሰ.ዐ.ወ) ዑማ ተሸጋግሯል። ነቢይነትም ወደ መጨረሻው ነቢይ ተጠቅልሏል። በርሱም በቅቷል። የመጨረሻዉ ነቢይ ነውና ነቢይነቱ እንደአለፉት ነቢያት አይደለም። እኒያ ነቢያት ለተወሰነ ህዝብና ለተወሰነ ጊዜ ነበር የተላኩት። የመጨረሻው ነቢይ ግን ለዓለማት ሁሉና ለዘለዓለሙ ነዉ የተላከው። ለዓለማት በሙሉ እዝነት ይሆን ዘንድ ነው ተልዕኮው። የመልዕክቱ ሁሉን አቀፍ መሆንና ዘለዓለማዊ መሆን የግድ ነበር። ይህ ነቢያትን ያስከተለ ሶላት እንድምታ ይህ ነበር። የጥንት ነቢያት እነ ኢብራሂም፣ ኢስሃቅ፣ ሙሳ፣ ዒሳ፣ … ወደ ነበሩባት ሀገር መጓዙ የአመራር ሽግግሩን ለማብሰር ነው። ኢስላማዊው አመራር ወደ አዲሱ ዑማ ተሸጋግሯል። መልዕክቱ ወደ ዓለማቀፋዊነትና ዘለዓለማዊነት ሰፍቷል።”

መስጅድ-አል ሀረምና መስጅድ-አል አቅሷ

በመስጅድ-አል ሀረምና በመስጅድ-አል አቅሷ መካከል የተፈጠረው ትስስር የሁለቱንም መስጂዶች ቅዱስነት በአጽንኦት ለማመልከት ነው። አንዱ የኢስራእ መነሻ ሌላኛው መዳረሻ ነው። በተጨማሪም አንዱ የሚዕራጅ መነሻ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ከሚዕራጅ መመለሻ ሆኖ እናገናገኘዋለን። ይህ ክስተት አንድ ነገር ያስገነዝበናል፡- “በተከበረው በይተል-መቅዲስ ላይ ቸልተኛ መሆን በመስጅድ-አል ሀረም ላይ ቸልተኛ ከመሆን ያልተናነሰ ነው።” አላህ (ሱ.ወ) ሁለቱንም መስጅዶች በኢስራእ ማስተሳሰሩ በሙስሊሞች ልቦና ውስጥ የሁለቱንም መስጂዶች ክብር ከፍ ለማድረግ ነው። መስጅድ-አል አቅሷን በበረካ ገለጸው፡-

الَّذِي بَارَكْنَا حَوْلَهُ
 

“ዙሪያውን ወደ ባረክነው” (አል-ኢስራእ 17፤ 1)

ይህ መስጂድ በዚህ ክብር የተሰየመው ከመስጂደል-ነበዊ (የመዲናው) በፊት ነው። ምክኒያቱም ኢስራእና ሚዕራጅ ከሂጅራ በፊት ነውና። አላህ (ሱ.ወ) ሁለቱን የተቀደሱ መስጅዶች በዚህ ተዓምራዊ ክስተት ማስተሳሰሩ በሁለቱም በተከበሩ መስጅዶች ላይ ሙስሊሞች በሁለቱም መስጅዶች “ሀቅ” ላይ ችላ እንዳይሉ ለማሳሰብ ነው። የመስጅድ-አል አቅሷን “ሀቅ” ያጓደለ የመስጅድ-አል ሀረምንም “ሀቅ” ሊያጓድል የሚችል ሠው ነው። መስጅድ-አል አቅሷ የሙስሊሞች የመጀመሪያው ቂብላ ነበር። ሦስት ዓመታት በመካ እና አስራ ስድስት ወራት በመዲና ወደ መስጅድ-አል አቅሷ አቅጣጫ ተሰግዷል። ያ የተቀደሰ መስጅድ ለክብሩ ከሩቅ ሀገር ተጉዞ ሊዘየር (ሸዱ ሪኃል)የሚገባው መስጂድ እንደሆነ ኢስላም ያስተምራል። በርግጥም ከሩቅ ሀገር ለክብራቸውና ለቅዱስነታቸው ሊዘየሩ የሚገባቸው መስጅዶች መስጅድ-አል አቅሷን ጨምሮ መስጅድ-አል ሀረምና መስጅድ አነ-በዊይ ናቸው።

አላህ (ሱ.ወ) የመስጅድ-አል አቅሷን ጉዳይ ዘለዓለማዊና በየዓመቱ ከረጀብ መጨረሻ ቀናት ጋር ተያይዞ ከሚታወሰው ኢስራእና ሚዕራጅ ጋር አስተሳስሮታል። የጉዳዩን ክብደት እንረዳ፣ የቦታውን ቅዱስነት እንገነዘብ ዘንድ ነው። እናም በሙስሊሞች ልብ ውስጥ ለዘለዓለም ይኖራል።

ሶላት

ሶላት የተደነገገችው በተዓምረኛዋ የኢስራእና ሚዕራጅ ሌሊት መሆኑ የሶላትን ክብደት ያስተምረናል። በዘመናችን ያሉ መንግስታት ከሌላ መንግስታት ጋር ከበድ ያለ ጉዳይ ሲኖራቸው ለአምባሳደሮቻቸው መልዕክት ከመላክ ይልቅ አምባሳደሮቻቸውን በአካል ይጠራሉ። ይህ የጉዳዩን ከባድነት ለማስገንዘብ የሚደረግ ነው። ከፍ ያለ ምሳሌ ለአላህ (ሱ.ወ) የተገባው ነው። ረሱሉ (ሱ.ዐ.ወ) ወደ ሰው ልጆች የተላኩ የአላህ (ሱ.ወ) አምባሳደር ናቸው። አላህ (ሱ.ወ) አምባሰደሩን በሌሊት ወደ በይት-አል መቅዲስ አስጉዞ ወደ ሰማየ-ሰማያት በማሳረግ ሲድረተል ሙንተሀ አደረሳቸው። እዚያ የተላቀ ስፍራ ላይ አምስቱ ወቅት ሶላቶች ተደነገጉ።

ሁሉም ድንጋጌዎች መሬት ላይ ነው የተደነገጉት። ሶላት ሰማይ ላይ ነው የተደነገገው። ይህ የሶላትን ቦታ ከፍ ያደረገ ክስተት ነው። ሶላት በረሱሉ (ሰ.ዐ.ወ) “ሚዕራጅ” (እርገት) ጊዜ መደንገጓ ከዚህ ተዓምራዊ ጉዞ እስከ ምጽዓት ቀን ቀሪ የሆነ ፋና ይታያል። ረሱሉ (ሰ.ዐ.ወ) በአካል ያደረጉትን እርገት እያንዳንዱ ሙስሊም በመንፈሳዊ እርገት ይገልጸዋል። ያ መንፈሳዊ ጉዞ ሶላት ነው። ሶላት ኢማናዊ እርገት ነው። እያንዳንዱ ሙዕሚን በሶላት አማካኝነት መንፈሣዊ እርገት ይፈጽማል። ከፈጣሪው ጋር ይገናኛል። ለዚህም ነው አላህ (ሱ.ወ) በሀዲስ-አልቁድስ ይህንኑ እውነታ ያስቀመጠልን፡-

قسمت الصلاة بيني و بين عبدي قسمين, ولعبدي ماسأل, فإذا قال عبدي: الحمد لله رب العالمين, قال الله تعالى: حمدني عبدي, فإذا قال: الرحمن الرحيم, قال تعالى: أثنى علي عبدي, فإذا قال: ماللك يوم الدين, قال الله تعالى: مجدني عبدي, فإذا قال: إياك نعبد وإياك نستعين, قال الله تعالى: هذا بيني وبين عبدي, ولعبدي ماسأل, فإذا قال: اهدنا الصراط المستقيم إلى آخر الفاتحة, قال الله تعالى: هذا لعبدي, ولعبدي ماسأل.

“ሶላትን በእኔና በባሪያዬ መካከል ከሁለት ከፍያታለሁ። ባሪያዬ የለመነውን ያገኛል። ባሪያው: ‘አልሀምዱ ሊላሂ ረቢልዓለሚን’ ሲል፣ አላህ (ሱ.ወ) ‘ባሪያዬ አመሰገነኝ’ ይላል። ‘አር-ረህማኒ አር-ረሂም’ ሲል፣ አላህ (ሱ.ወ) ‘ባሪያዬ አወደሰኝ’ ይለዋል። ‘ማሊኪየውሚዲን’ ሲል፣ አላህ (ሱ.ወ) ‘ባሪያዬ አላቀኝ’ ይላል። ‘ኢያከነዕቡዱ ወኢያከነስተዒን’ ሲል፣ አላህ (ሱ.ወ) ‘ይህ በኔና በባሪያዬ መካከል ያለ ጉዳይ ነው። ባሪያዬ የለመነውን ያገኛል’ ይላል። ‘ኢህዲነሲራጠል ሙስተቂም’ እስከመጨረሻው የፋቲሃ ምዕራፍ ሲያነብ፣ አላህ (ሱ.ወ) ‘ይህ የባሪያዬ ጉዳይ ነው። ባሪያዬ የለመነውን ሁሉ ያገኛል።’ ይለዋል።”

ይህን ያክል ክብር የተቸረው ሶላት ከመስጅድ-አል አቅሷ ጋር ያለውን ትስስርም ማስተዋል የግድ ይላል። ሶላት ከተደነገገ በኋላ የመጀመሪያው ቂብላ መስጅድ-አል አቅሷ ነውና።

እናም ከኢስራእና ሚዕራጅ ሁለት ዋና ዋና አስተምህሮቶችን እንወስዳለን። መስጅድ-አል አቅሷን በሚመለከት የሙስሊሙ ዑማ ኃላፊነት አንዱ ሲሆን፣ የሶላትን ክብርና ከመስጅድ-አል አቅሷ ጋር ያለውን ትስስር በውሉ መገንዘብና አቅሷን ሁሌም ከልባችን ማስተዋስ ሌላኛው ነው።

2 COMMENTS

  1. The first paragraph DUA is very interesting but because it is not possible to read it (at least for me), I can’t use this wonderful DUA. Or, is this DUA restricted only for prophet Mohammed(SWW)?

  2. ﺍﻟﻠﻬﻢ ﺻﻠﻲ ﻭﺳﻠﻢ ﻭﺑﺎﺭﻙ ﻋﻠﻰ ﺳﻴﺪﻧﺎ ﻣﺤﻤﺪ ﻭﻋﻠﻰ ﺁﻟﻪ ﻭﺻﺤﺒﻪ
    ﺃﺟﻤﻌﻴﻦ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here