ዙበይር ቢን ዓዋም – የነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሐዋርያ

0
11909

ታሪኩ ባጭሩ

ዙበይር ቢን አዋም የሰለመው የስምንት አመት ልጅ እያለ ሲሆን፣ ወደ መዲና ሲሰደድ እድሜው 18 ዓመት ነበር፡፡ በሰለመ ጊዜ አጎቱ በጣም ተቆጣ፡፡ ጠራውም፡፡ “ወደ ክህደት ተመለስ፡፡” እያለም እሳት አንድዶ በጭስ በማፈን ቀጣው፡፡ ዙበይርም፡- “በፍጹም አልከፍርም” ሲል በእምነቱ ጸና፡፡[1]

ዙበይር የሰለመው በጣም ቀድሞ ነው፡፡

ያኔ ገና ልጅ ቢሆንም አላህ ለእስልምና ልቦናውን ከፈተለት፡፡ እስልምናን በቀዳሚነት ከተቀበሉ ሙስሊሞች መካከል አንዱ ነው፡፡ በእስልምና ታሪክ መጀመሪያ የተመዘዘው ሰይፍ የዙበይር ሰይፍ ነበር፡፡

ዙበይር ቢን አል ዓዋም የነቢዩ ሐዋርያ ነው፡፡ ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፡-

“ጦልሐና ዙበይር ጀነት ውስጥ ጎረቤቶቼ ናቸው፡፡”

እነዚህ ሁለት ስብእናዎች ከነብዩ ጋር በወንድማማችነት መተሳሰራቸውን ይህ ዘገባ ያሳያል፡፡

ዙበይር የአዋም ልጅ፣ የኹወይሊድ ልጅ፣ የአሰድ ልጅ፣ የአብዱል ኢዝ ልጅ፣ የቁሰይ ልጅ፣ የኪላብ ልጅ ነው፡፡ በቁሰይ በኩል ከነቢዩነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ጋር በዝምድና ይገናኛሉ፡፡ እናቱ የነቢዩ ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም አክስት ሶፍያህ ቢንት አብዱል ሙጦሊብ ናት፡፡ በጃሂልያም በእስልምናም ዘመን ስሙ ዙበይር ሲሆን፣ አቡ አብደላህ በሚል ቅጽል ስምም ይታወቃል፡፡

እርሱና ጦልሐ በአንድ ዓመት ውስጥ ተወለዱ፣ በተመሳሳይ ዓመት ውስጥም ሸሂድ ሆነው ተገደሉ፡፡ ጦልሐ በተወሳ ቁጥር ምንጊዜም አብሮት ይወሳል፡፡ ዙበይር ሲወሳም ጦልሐ አብሮ ይወሳል፡፡

ጦልሐና ዙበይር በበርካታ ባህሪዎች ይመሳሰላሉ፡፡ ሁለቱም ባለጸጋዎች፣ የተከበሩ፣ በአላህ ላይ ጽኑ እምነት ያላቸውና በጣም ጀግኖች ነበሩ፡፡ ሁለቱም በጀነት ተበስረዋል፡፡

የዙበይር አንኳር ገድሎች

ዙበይር አንድም ቀን ለጣኦት አልሰገደም፡፡ በጃሂልያ ዘመን ጸያፍ ድርጊት አልፈጸመም፡፡ ከአላህ መልእክተኛና ከሙሐጅሮች ጋር ተሰዷል፡፡ ወደ ሁለቱም ቂብላዎች የመስገድ እድል አግኝቷል፡፡ አንድ ቀን ሙስሊሞች ዳረል አርቀም ከተባለው ቦታ በድብቅ ተሰባስበው እያለ፡- “የአላህ መልእክተኛ ተገደሉ፡፡” የሚል ወሬ ተናፈሰ፡፡ ዙበይር ወሬውን ሲሰማ እጅግ ተቆጣ፡፡ ቁጣውም እንደ ብርቱ የመሬት ነውጥ፣ ሐይለኛ እሳተ ጎመራ ወይም አስፈሪ መብረቅ ሆነ፡፡

ሰይፉን ከአፎቱ መዞ ይህን አሳዛኝ ወሬ ለማጣራት ገሰገሰ፡፡ ከመካ ከፍታ ላይም የአላህ መልእክተኛ አገኙት፡፡ ምን ሆኖ እንደሁ ሲጠይቁት የሰማውን ወሬ ነገራቸው፡፡ ያሰበውንም አጫወታቸው፡፡ የአላህ መልእክተኛ ለርሱም ለሰይፉም ድል አድራጊ ይሆኑ ዘንድ ዱዓ አደረጉላቸው፡፡

አዎ፣ ዙበይር የላቀ ክብር ሊቸረው የተገባ ሰው ነው፡፡ ለክብሩ ተከታዩ የአላህ መልእክተኛ ምስክርነት ይበቃዋል፡-

“ሁሉም ነብያት ሐዋርያት አሏቸው፡፡ የኔ ሐዋርያ ዙበይር ቢን አልዓዋም ነው፡፡”

ሰኢድ ቢን ሙሰየብን በመጥቀስ ፈዷኢሊ እንደዘገቡት ዙበይር መካ ውስጥ እያለ ነቢዩ ተገደሉ የሚል ወሬ ሰማ፡፡ ከድንጋጤው የተነሳ ሰይፉን ይዞ እርቃኑን ወጣ፡፡ መንገድ ላይ ነቢዩነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም አገኙትና “ምን ሆነህ ነው?” ሲሉ ጠየቁት፡፡ እርስዎ ተገደሉ የሚል ወሬ ሰምቼ ነው፡” አላቸው፡፡ “ታዲያ ምን ልታደርግ አሰብክ?” ሲሉ ጠየቁት፡፡ “የመካውያንን ደም አንድም ሳላስቀር እንደ ጎርፍ ላፈሰው ወሰንኩ፡፡” አላቸው፡፡ ሳቁና ኩታቸውን አውልቀው አለበሱት፡፡ ወዲያውም ጅብሪል ወረደና እንዲህ አላቸው፡-“አላህ ሰላምታ አቅርቦልሐል፡፡ ለዙበይርም ሰላምታዬን አድርስልኝ ብሎሐል፤ በአላህ መንገድ ሰይፉን የመዘዘ የመጀመሪያው ሰው በመሆኑ አንተ በነብይነት ከተላክ ጀምሮ እስከ እለተ ቂያማ ድረስ ለአላህ ሲሉ ሰይፍ የሚመዝዙ ሰዎችን ሁሉ የሚያህል ምንዳ-የነርሱ ምንዳ ሳይጓደል- አላህ እንዳዘጋጀለትም ትነግረው ዘንድ አዞሐል፡፡”

ቢን ሰእድ ጦበቃት በተሰኘ መጽሐፋቸው ውስጥ እንደዘገቡት ዙበይር እንዲህ ሲል አውግቷል፡-

“የበድር እለት መላኢኮች ከቦቃ ፈረስ ላይ ሆነው እና ቢጫ ጥምጣም ለብሰው ወረዱ’”

ዙበይር ያኔ ቢጫ ጥምጣም ለብሶ ነበር፡፡ መልእክተኛውም ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ፡- “መላኢኮች በዙበይር ሰማይ ላይ ወረዱ፡፡” ሲሉ ተናገሩ፡፡

ኢብን ኢስሐቅን በመጥቀስ ዩኑስ እንዳወሱት የበድር እለት የቁረይሾች አርማ ተሸካሚ የነበረው አቡ ጦልሐተል ዓብደሪይን ለሁለትዮሽ ግጥሚያ ሙስሊሞችን ጋበዘ፡፡ ሰዎች ከርሱ ሲሸሹ ዙበይር ሊገጥመው ወጣ፡፡ ዘሎም ከግመሉ ላይ መጣበት፡፡ ይዞትም ወደ መሬት ወረደ። በሰይፉም አረደው፡፡ የአላህ መልእክተኛም አድራጎቱን አሞገሱ፡፡ እንዲህም አሉ፡-

“ሁሉም ነብያት ሐዋሪያት አሏቸው፡፡ የኔ ሐዋርያ ዙበይር ነው፡፡ ሰዎች ከርሱ (ከቢን ጦልሐ) ሲሸሹ ሳይ ዙበይር ሊፋለመው ባይወጣ ኖሮ እኔ እፋለመው ነበር፡፡”[2]

በኡሁድ ዘመቻ እለትም የቁረይሽ ሰራዊት የጦርነቱን መስክ ለቆ ወደ መካ ካቀና በኋላ ነቢዩ ዙበይርን እና አቡበክርን የቁረይሾች ሰራዊት ያሳድዱ ዘንድ አሰማሯቸው፡፡ ይህን ያደረጉት ቁረይሾች የሙስሊሞችን ብርታት እንዲያዩና ወደ መዲና ተመልሰው ውጊያ ለመጀመር እንዳያስቡ ለማድረግ ነው፡፡ አቡበክርና ዙበይር ሰባ ሙስሊሞችን አስከትለው ቁረይሾችን ያሳድዱ ጀመር፡፡ የሚያሳድዱት ጦር ጊዜያዊ ድል ያገኘ ሰራዊት ቢሆንም እነ አቡበክር የተከተሉት የጦርነት ስልት ቁረይሾችን ማስደንገጡ አልቀረም፡፡

የሙስሊሞችን ኪሣራ በተመለከተ ስሌታቸው ስህተት እንደሆነ እንዲያስቡ አደረጉ፡፡ በተጨማሪም በአቡበክርና በዙበይር የተመራውና ሐይልና ጥበብን ያሳየው ይህ ጦር ከኋላው በነቢዩ የሚመራ ሌላ ጦር ያስከተለ እንዲመስላቸው አደረጉ፡፡ ስለሆነም ወደ መካ በፍጥነት ለማምለጥ ተገደዱ፡፡

የየርሙክ ዘመቻ እለት በርካታ የሙስሊሞች ጦር ከሮሞች ግዙፍ ሰራዊት ፊት ሲያፈገፍግ ዙበይር በተመለከተ ጊዜ ትእይንቱን መታገስ አልቻለም፡፡ አላሁ አክበር! በማለት ወደ ሮሞች ጦር ገስግሶ ክፉኛ አጠቃቸው፡፡

ዙበይር የእስልምና መሠረት

ዑርወት ቢን ዙበይር እንዲህ ሲል አውግቷል፡-

የነቢዩ ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሶሐቦች የየርሙክ ቀን ለዙበይር፡- “ካህድያንን አጥቃልን እኛም አብረንህ እናጠቃቸዋለን፡፡” አሉት፡፡ “እኔ ሳጠቃ ወደ ኋላ እንዳትቀሩ” አላቸው፡፡ “አናደርገውም” አሉት፡፡ ሮሞችን ብቻውን አጠቃ፡፡ ሰልፋቸውን ሰንጥቆም አለፈ፡፡ የተከተለው አልነበረም፡፡ ተመልሶ መጣ፡፡ የፈረሱን ልጓም ያዙና ሁለት ጊዜ ከትከሻው ላይ መቱት፡፡ አንደኛው የበድር እለት የተመታበት ቦታ ነበር፡፡ እነዚህ ምቶች ከፈጠሩት የአካሉ መሰርጎድ ውስጥ በልጅነቴ ጣቴን እያስገባሁ እጫወት ነበር፡፡

አብደላህ ቢን ዙበይር አብሮት ነበር፡፡ እድሜው 20 ዓመታት ነበር፡፡ ከፈረሱ ላይ አወጣው፡፡ አንድ ሰውም ወከለለት፡፡› (ቡኻሪ)

ዑመር ቢን አልኸጧብ እንዲህ ብለዋል፡-

“ዙበይር ከእስልምና መሠረቶች መካከል አንዱ ነው፡፡”

ዙበይር ለዲኑ ታማኝ ሆኖ በአላህ መንገድ በተደረገ ትግል መስዋእት (ሸሂድ) እስከሆነበት እለት ድረስ ለአላህ መልእክተኛ በገባው ቃል ኪዳን እንደጸና ኖሯል፡፡ ሐሳን ቢን ሳቢት የተባለ ገጣሚ ይህን በማስመልከት እንዲህ ብሏል፡-

ለነቢዩ የገባውን

ተጠባብቆ ቃል ኪዳኑን

ዝንፍ ሳይል ከቅን ፍኖት

ሆኖ የርሳቸው ሐዋርያ ረዳት

ቃሉን ከተግባሩ አዋዶ

ፍትህን ከቃሉ አዋህዶ

የርሳቸውን ጎዳና ጠብቆ

የሐቅን ወዳጅ አጥብቆ

እውቅ ፈረሰኛ ጀግና

ታዋቂ ስመ ገናና

እስልምናን በመታደግ

ያካበተ ክብር ዝና

ታላቁን ነብይ ሙስጦፋን

ከጠላት ጥቃት ተከላክሏል፡፡

ዝንብ እንኳ እንዳያርፍባቸው

ነፍሱን ሸጦ ግዳይ ጥሏል፡፡

በገፍ ይመንዳው ጌታ

መቼም አያልቅበት ስጦታ፡፡

የአላህ መልእክተኛ ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ሲሉ በጀነት አብስረውታል፡-

“ጦልሐና ዙበይር ጀነት ውስጥ ጎረቤቶቼ ናቸው፡፡”

ጀነት ውስጥ የአላህን መልእክተኛ ጉርብትና ታድሏል፡፡ ኢብን አባስ ስለ ጦልሐና ዙበይር ተጠይቀው እንዲህ ብለዋል፡-

“አላህ ይዘንላቸው፡፡ በአላህ እምላለሁ፡፡ ሙስሊሞች፣ ሙእሚኖች፣ ደጋጎች፣ አላህን የሚፈሩ፣ በጎ ሰሪዎች፣ በላጮችና ንጹሐን ነበሩ፡፡”

ቡኻሪና ሌሎችም እንደዘገቡት ዙበይር የተገደለው በ36 ዓ.ሂ በወርሃ ረጀብ ሲሆን፣ ገዳዩ አምር ቢን ጀርሙዝ ይባላል፡፡ ለዙበይር አላህ ይዘንለት።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here