ጾም ላይ ሳይነይት ንጋት ከቀደደ?

Home የፈትዋ ገጽ ዒባዳ ጾምና ኢዕቲካፍ ጾም ላይ ሳይነይት ንጋት ከቀደደ?

ጥያቄ፡- በለሊት ከሱብሒ በፊት ረስቼ አልነየትኩም። ከዚያም ከፈጅር በኋላ እንዳልነየትኩኝ ትዝ አለኝ። ጾሜ ትክክል ይሆንልኛል?


መልስ፡- ጾም ያለኒያ አይሆንም። ተቀባይነት የለውም። አብዝሃኞቹ ዑለሞች ለየዕለቱ መነየት ግዴታ እንደሆነ ያምናሉ። አንዳንዶቹ የመጀመሪያው የረመዷን ለሊት ላይ የወሩን መነየት ይበቃል ብለው ያምናሉ። የኒያው ጊዜ ፀሀይ ከጠለቀች በኋላ ንጋት ከመቅደዱ በፊት ነው። በዚህ የጊዜ ገደቡ ውስጥ በማንኛውም ወቅት ሰውየው ኒያ ካደረገ በቂው ነው። ከኒያው በኋላ ከፈጅር በፊት ቢበላና ቢጠጣም ችግር የለውም። አሕመድ፣ አቡዳዉድ፣ ነሳኢይ፣ ኢብኑማጀህ እና ቲርሙዚይ ከአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ማለታቸውን ዘግበዋል፡-

مَنْ لم يجمع الصّيام قبل الفجر فلا صِيام له

“ለሊት ጾምን ነይቶ ያላደረ ጾም የለውም።”

ኒያን በንግግር መግለፅ ግዴታ አይደለም። የኒያ ቦታው ልብ ነው። በልቡ ነገ እንደሚጾም ከወሰነ በቂው ነው። እንደውም ነገን በመጾም ሃሳብ ሱሑር ከበላ በቂው ነው። ነገ ሲጾም ጥም እንዳያስቸግረው ውሃ ቢጠጣ እንኳን በቂ ነው። በለሊት ወቅት ከነዚህ አማራጮች አንዱንም ካልከወነ ጾሙ ተቀባይነት አይኖረውም። ቀዷ ማውጣትም ግዴታ ይሆንበታል። ይህ ጾሙ ፈርድ ጾም ከሆነ ነው። ጾሙ ሱና ከሆነ ግን በቀን ከዙሁር በፊት መነየት ይቻላል።