ጥርስን ስለማስተካከል

Home የፈትዋ ገጽ ጤናና ህክምና ጥርስን ስለማስተካከል

ጥያቄ:- ወጣት ነኝ። ጥርሴ ወደፊት ወጣ ወጣ ያለ ነው። በተለይ በምስቅበት ጊዜ ተቸግሬያለሁ። በዚህም የሥነልቦና ጉዳት እየደረሰብኝ ነው። በዚሁ የተነሳ አንዳንዴም ከመሳቅ የምቆጠብበት ሁኔታ አለ። ስለሆነም ጥርስን ማስተካከል በሸሪዓ እንዴት ይታያል? ክልክል ነው ወይንስ ይፈቀዳል?


መልስ:- ለተመሳሳይ ጥያቄ የግብፁ ዳሩል-ኢፍታእ የሚከተለውን መልስ አስፍሯል፡-

አላህ (ሱ.ወ) የሰው ልጆችን ከሌሎች ፍጥረታት በተለየ መልኩ አስዉቦ ነው የፈጠረው። እሱ ከፈጠረበት አፈጣጠሩም እንዳይቀይርና ሥሪቱን እንዳይለውጥም አዞታል። ሸይጣን የሰውን ልጅ ጥፋት ላይ የሚጥልበትን ሁነታ ሲገልጽም እንዲህ ማለቱን ይጠቅሳል-

وَلَآمُرَنَّهُمْ فَلَيُغَيِّرُنَّ خَلْقَ اللَّهِ وَمَن يَتَّخِذِ الشَّيْطَانَ وَلِيًّا مِّن دُونِ اللَّهِ فَقَدْ خَسِرَ خُسْرَانًا مُّبِينًا

“አዛቸውና የአላህን ፍጥረት ይለውጣሉ፤ (ያለውን ይከተላሉ)። ከአላህም ሌላ ሰይጣንን ረዳት አድርጎ የሚይዝ ሰው ግልጽ ክስረትን በእርግጥ ከሰረ።” (አን-ኒሳእ 4፤119)

የአላህ መልዕክተኛም (ሰ.ዐ.ወ)፡-

لعن الله الواشمات والمستوشمات والمتنمصات والمتفلجات للحسن المغيرات خلق الله

“አላህ ነቃሽን ተነቃሽን፣ ቅንድብ ላጭዋንና አስላጭዋን፣ ጥርስ አስዘርዛሪዋንና የአላህን አፈጣጠር የምትቀይረዋን ረግሟል።” ብለዋል። (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል።) እርግማን ማለት ከአላህ እዝነት መባረር ነው።

ነገርግን በሸሪዓው እንደሚታወቀው ጉዳት መወገድ አለበት (አዶረሩ ዩዛል)።

لا ضرر ولا ضرارመጉዳትም መጎዳትም የለም።” የሚለው ሐዲሥ እዚህም ላይ ይሠራል። ራስም ሆነ ሌላውን መጉዳት የተከለከለ ነው።

በመሆኑም ጥርስን ማስተካከል በታማኝ ሐኪም ኃላፊነትና እገዛ እስከሆነ ድረስ የአላህን አፈጣጠር ከመቀየር አይመደብም። ስለሆነም ይፈቀዳል ማለት ነው። አላህ እጀግ አዋቂ ነው።