ግዴታ ፆም እያለበት ለሞተ ሠው ምን ይደረግ

Home የፈትዋ ገጽ ዒባዳ ጾምና ኢዕቲካፍ ግዴታ ፆም እያለበት ለሞተ ሠው ምን ይደረግ

ጥያቄ፡- አስሰላሙ ዓለይኩም ወራህመቱላህ ወበረካቱሁ። ባለቤቴ ባለፈው ዓመት በረመዷን ውስጥ ታሞ ነበር። ከዚያም ሞተ። ከረመዷን ያፈጠረባቸው (ያልፆመባቸው) ቀናትን ምን ላድርግለት?


መልስ፡- ወዓለይኩሙስ-ሰላም ወረሕመቱሏሒ ወበረካቱሁ። ቢስሚላሂር ራህማኒር ረሂም

የአላህ ድንጋጌዎች ከሠው ችሎታ (አቅም) ጋር የተመጣጠኑ ናቸው። አላህ እንዲህ ይላል፡-

لَا يُكَلِّفُ اللَّهُ نَفْسًا إِلَّا وُسْعَهَا 

“አላህ ነፍስን ከችሎታዋ በላይ አያስገድዳትም፡፡” (አል-በቀራህ 2፣ 286)

ፆም ከምግብና ከመጠጥ ታቅበን መቆየት በመቻል ላይ የሚመሰረት አምልኮ ነው። በቀን በመደበኛ ሁኔታ መድሀኒቶችን መውሰድ የሚያሻው ህመምተኛ ወይም ከህመሙ ጋር ረሀብን መቋቋም የማይችል ሰው የረመዷንን ቀናት ማፍጠር (መብላት) ይፈቀድለታል። በመሆኑም ባለቤትሽ ህመም ላይ ሆኖ ባለመፆሙ አይጠየቅም። አላህ እንዲህ አለ፡-

وَمَن كَانَ مَرِيضًا أَوْ عَلَىٰ سَفَرٍ فَعِدَّةٌ مِّنْ أَيَّامٍ أُخَرَ يُرِيدُ اللَّهُ بِكُمُ الْيُسْرَ وَلَا يُرِيدُ بِكُمُ الْعُسْرَ
 

“በሽተኛ ወይም በጉዞ ላይ የኾነም ሰው ከሌሎች ቀኖች ቁጥሮችን (በልኩ) መጾም አለበት፡፡ አላህ በእናንተ ገሩን (ነገር) ይሻል፡፡ በእናንተም ችግሩን አይሻም፡፡” (አል-በቀራህ 2፣ 185)

ለሞተ ሰው መፆም እንዴት ይታያል? ብዙ ሀዲሶች ይህን ጥያቄ ያብራሩታል። የተወሰኑትን እንመልከት፡፡

ሙስሊም ዓኢሻን (ረ.ዐ) ዋቢ በማድረግ እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

مَن مات وعليه صيام صامَ عنه وليُّه

“ፆም እያለበት የሞተ ሰው ወልዩ (ቤተሰቡ) ይፆምለታል።” (ሙስሊም)

ቤተሰቡ (ወልዩ) ሲባል ዘመዶቹንም ያካትታል (ወራሽም የማይወርስም)። በወልዩ ፍቃድ ባዕድ ቢፆምለት ይሆናል። ያለ ወልይ ፍቃድ ቢፆምለት ግን አያብቃቃውም።

ከዓብዱላህ ኢብኑ ዓባስ (ረ.ዐ) እንተዘገበው አንዲት ሴት ወደ መልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) መጣችና እንዲህ አለቻቸው፡-

إن أمي ماتتْ وعليها صوم شهر، وفي رواية صوم نَذْر، أفأصوم عنها؟ فقال ـ عليه الصلاة والسلام: أرأيتِ لو كان على أمكِ دَيْن أكنتِ تقضينه؟ قالت: نعم، قال: فدَيْن الله أحق بالقضاء، وفي رواية قال: فصومي عن أمك”.

“እናቴ የአንድ ወር ፆም እያለባት (በሌላ ዘገባ “የስለት ፆም አያለባት”) ሞታለች። ልፁምላት?” የአላህ መልእክተኛም (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሏት፡- “እናትሽ ላይ እዳ ቢኖር ትከፍዪላት ነበር?” ሴትየዋ “አዎን!” አለች። እርሳቸውም እንዲህ አሉ፡- “የአላህ እዳ በዋናነት መከፈል የሚገባው ነው። (በሌላ ዘገባ፡- “ለእናትሽ ፁሚላት”) አሏት።”

ስለዚህ በህመም ምክንያት ያፈጠረው ባልሽ ከህመሙ አገግሞ ቀዷ ለማውጣት የሚያስችል ጤንነት ላይ ሳይገኝ ከሞተ ምንም ኃጢያት የለበትም። በመሆኑም ሚስቱ ባፈጠራቸው የረመዷን ቀናት ቁጥር ልክ ልትፆምለት ትችላለች። በፆሙ ፈንታ ለየአንዳንዱ ቀን አንድ እፍኝ (ግማሽ ኪሎ) እህል ልትሰጥ ትችላለች። ወይም እህሉን በገንዘብ ተምና መክፈል ትችላለች።

አላህ የተሻለ ያውቃል!