ዳዕዋ ማድረግ ግዴታ ነው ወይስ ሱና?

Home የፈትዋ ገጽ ዳዕዋ ዳዕዋ ማድረግ ግዴታ ነው ወይስ ሱና?

ጥያቄ፡- ከጓደኞቼ ጋር በዳዕዋ ጉዳይ ላይ ተወያይተን ነበር። አንዳንዶቻችን ግዴታ (ፈርድ) ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደረስን። ሌሎች ደግሞ የሚወደድ (ሙስተሀብ) ወይም ሱና እንደሆነ አስተያየት ሰጥተዋል። በቁርአን እና በሀዲስ እይታ ዳዕዋ ያለው ሥፍራ የትኛው ይሆን? ግዴታ (ፈርድ) ወይስ ሱና?


kTKBee9jcመልስ፡- ይህ ጥሩ ጥያቄ ነው። በጣም ደስ ያለን ደግሞ ከጓደኞችህ ጋር በዚህ ታላቅ ጉዳይ ላይ መወያየታችሁ ነው። ብዙ ሙስሊሞች ስለ ዳዕዋ ደንታ የላቸውም። ወሬዎቻቸው ላይም አይቀላቅሉትም። ብዙዎቹ ጊዜያቸውን የሚያቃጥሉት በማይጠቅሙ ነገሮች ላይ ነው። የእናንተ ውይይት ግን በዚህ መሰል ጉዳዮች ላይ መሆኑ እኛን አስደስቷል። አላህ (ሱ.ወ) ሥራችሁን እንዲቀበላችሁ እንለምናለን!

በቅድሚያ ዳዕዋ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ማወቅ ይገባል። ዳዕዋ ማለት ሰዎችን ወደ አላህ (ሱ.ወ) መንገድ መጣራት ማለት ነው። ሀቅን እንዲያውቁ እና እንዲከተሉ መጣራት ማለት ነው።

ዳዕዋ በሁለት መንገድ ሊፈጸም ይችላል። መልካም አርአያ (ቁድዋ ሀሰና) በመሆን ሰዎችን ወደ አላህ (ሱ.ወ) መንገድ ማመላከት ሊገኝ ይችላል። ይህ እንደ ቁርአን አገላለጽ እንዲህ ተጠቁሟል፡-

شُهَدَاءَ عَلَى النَّاسِ

 “በሰዎች ላይ መስካሪዎች” (አል-በቀራ 2፤143)

ይህኛው የዳዕዋ ዘርፍ በሁሉም ሙስሊም ላይ ግዴታ ነው። ሁሉም ሙስሊም ወንድ ይሁን ሴት፣ ወጣትም ይሁን አዛውንት ከሰዎች መሀል የአላህ ምስክር መሆን አለበት። ሰዎች ሙስሊምን ሲያዩ እውነተኛ፣ ታማኝ፣ ታታሪ፣ አዋቂ፣ ትሁት… ስብዕና ያለውን ሰው ሊመለከቱ ይገባል። የሙስሊም ህይወት የኢስላምን ውበት የሚያሳይ ክፍትና ዘውታሪ ዐውደ-ርእይ (ኤግዚቢሽን) መሆን አለበት። ሰዎች ወደ ኢስላም እንዲሳቡ የሚገፋ ሀይል ሊኖረው ይገባል። አላህ (ሱ.ወ) ቁርአን ውስጥ እንህ ይላል፡-

وَكَذَٰلِكَ جَعَلْنَاكُمْ أُمَّةً وَسَطًا لِّتَكُونُوا شُهَدَاءَ عَلَى النَّاسِ وَيَكُونَ الرَّسُولُ عَلَيْكُمْ شَهِيدًا
 

“እንደዚሁም (እንደመራናችሁ) በሰዎች ላይ መስካሪዎች ልትሆኑና መልክተኛውም በናንተ ላይ መስካሪ ይሆን ዘንድ ምርጥ ሕዝቦች አደረግናችሁ።” (አል-በቀራ 2፤143)

ሙስሊሞች ሁሉ እንደ ግለሰብ፣ እንደ ቤተሰብ እና እንደ ማህበረሰብ የኢስላም ውበትና ፋይዳ ማሳያ መሆን አለባቸው። ከነርሱ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ሁሉ በተግባር መሬት ላይ የሚንቀሳቀስ እስልምናን መመልከት ይኖርባቸዋል። ደጋግ ሰዎች የፈጠረውን እስልምናን መመልከት ይኖርባቸዋል።

ሌሎች ዳዕዋ የሚሰራባቸው መንገዶች ማስተማር፣ መስበክ፣ መወያየት፣ ክርክር፣ መጽሐፍትን መጻፍ፣ ሲዲዎች እና ሌሎችም ናቸው። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡-

ادْعُ إِلَىٰ سَبِيلِ رَبِّكَ بِالْحِكْمَةِ وَالْمَوْعِظَةِ الْحَسَنَةِ وَجَادِلْهُم بِالَّتِي هِيَ أَحْسَنُ
 

“ወደ ጌታህ መንገድ በብልሃትና በመልካም ግሳጼ (በለዘብታ ቃል) ጥራ። በዚያችም እርሷ መልካም በኾነችው (ዘዴ) ተከራከራቸው።” (አን-ነህል 16፤125)

በርግጥም ይህ የዳዕዋ ዘርፍ እውቀትና ትምህርት ያሻዋል። ዝግጅት፣ ጥናትና ስልጠና ያስፈልጋል። ሙስሊሞች በማንኛውም ጊዜ ቢሆን የተለያዩ የዳዕዋ መንገዶችን ሁሉ መጠቀም አለባቸው። ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት ዳዕዋ ራዲዮ፣ ቴሌቪዥን፣ ጋዜጣ፣ የኢንተርኔት ድረገጾችን መጠቀም ያስፈልገዋል። ሁሉም ሰው ደግሞ ለትምህርትና ስልጠና በቂ ጊዜና አቅም ላይኖረው ይችላል። ስለዚህ በዚህ መልኩ የሚደረጉ ዳዕዋዎች የሁሉም ሙስሊም ግዴታ አይደሉም። ነገር ግን የተወሰኑ የሙስሊሙ ማህበረሰብ አካላት ይህን የዳዕዋ ክፍተት የመሙላት ግዴታ አለባቸው። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡-

 

وَمَا كَانَ الْمُؤْمِنُونَ لِيَنفِرُوا كَافَّةً فَلَوْلَا نَفَرَ مِن كُلِّ فِرْقَةٍ مِّنْهُمْ طَائِفَةٌ لِّيَتَفَقَّهُوا فِي الدِّينِ وَلِيُنذِرُوا قَوْمَهُمْ إِذَا رَجَعُوا إِلَيْهِمْ لَعَلَّهُمْ يَحْذَرُونَ 

“ምእምናንም በሙሉ ሊወጡ አይገባም። ከእነሱ ውስጥ ከየክፍሉ አንዲት ጭፍራ ለምን አትወጣም። (ሌሎቹ) ሃይማኖትን እንዲማሩና ወገኖቻቸው ወደነርሱ በተመለሱ ጊዜ እንዲጠነቀቁ ይገስጹዋቸው ዘንድ (ለምን አይቀሩም)።” (አት-ተውባ 9፤122)

በልዩ ስልጠናና ትምህርት የሚሰሩ ዳዕዋዎች ላይ የተወሰኑ ሰዎች መሰማራታቸው “ፈርዱልኪፋያ” ነው። ማለትም የተወሰኑ የሙስሊሙ ማህበረሰብ አባላት በቂ ስልጠናና ትምህርት በመውሰድ ሌላውን ማህበረሰብ በመወከል፣ ጊዜ በመስጠት፣ በተቀናጀ ሁኔታ ዳዕዋ በመስራት ይህን ኃላፊነት መወጣት አለባቸው። ይህ ስራ በበቂ ሁኔታ በነዚህ ሰዎች ከተሰራ መላው ማህበረሰብ አይወቀስም። በዚህ መልኩ የሚሠሩ የዳዕዋ ሰራተኞች ከሌሉ ግን ሁሉም የማህበረሰብ አባል ተጠያቂ ይሆናል። ይህ ሥራ በአግባቡ እንዲሰራ በቁሳቁስና በገንዘብ ማገዝም የሁሉም ሙስሊም ኃፊነት ነው።

የእኛን ሀገር የዳዕዋ ተጨባጭ ብንመለከት ግን ሁለቱም የዳዕዋ ዘርፎች ላይ ሰፊ ክፍተት ይታያል። በህዝቦች ላይ የአላህ ምስክሮች የሆኑ ሙስሊሞች የሉንም። እስልምናን በህይወታቸው ላይ የሚተገብሩ ግለሰቦች፣ ቤተሰቦችና ማህበረሰብ የለንም ከማለት አይተናነስም። በሚገባ የሰለጠኑ የዳዕዋ ሰዎችም የሉንም። በጣም ጥቂትና ጥቃቅን የዳዕዋ ሥራን የሚሰሩ ድርጅቶች ብቻ ናቸው፤ የሙስሊሙ ህዝብ ንብረቶች። እነሱም በሰፊው ሙስሊም ማህበረሰብ በቂ ድጋፍ ያላቸው አይደሉም። ነገርግን ሌሎች ኃይማኖቶችን ብንመለከት ይህ ተጨባጭ ፍፁም የተጋነነ ልዩነት ያሳያል። ሁሉም ኃይማኖቶች በግዙፍ ባጀቶች የሚንቀሳቀሱ፣ ራዕያቸው አለምን የሚሸፍን፣ ፍፁም የተደራጁ ብዙ ድርጅቶች አሏቸው።

ከዚህ እና ኢስላም ላይ ከሚቃጡ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻዎች ጋር የሚመጣጠን የዳዕዋ እንቅስቃሴ መመስረት የሁሉም ሙስሊም ኃፊነት መሆኑንም በዚሁ አጋጣሚ እናሳስባለን።