የጀናዛ ሶላትን ለማስገድ ይበልጥ ተገቢው ሰው

Home የፈትዋ ገጽ ጀናኢዝ የጀናዛ ሶላትን ለማስገድ ይበልጥ ተገቢው ሰው

ጥያቄ:- የጀናዛ ሶላትን ለማሰገድ ይበልጥ ተገቢው ሰው ማነው? የመስጂዱ ኢማም ወይስ የሟቹ የቅርብ ዘመድ?


መልስ፡- ዑለሞች በሟች ላይ ሶላት ለማሰገድ እጅግ ተገቢው ሰው የትኛው ነው በሚለው ቅደም ተከተል ላይ ወጥ አቋም መያዝ አልቻሉም። ከፊሎቹ ጭቅጭቅና ዉዝግብን ለማስወገድ ሲባል ሥልጣኑ ያለው- ማለትም የሥልጣን ባለቤት የሆነው ክፍል እንዲያሰግድ፣ ኹጥባ እንዲያደርግና ለሌላም ነገር የወከለው መደነኛ ኢማም ነው ተገቢው ሰው ያሉ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ለዚህ ቦታ ይበልጥ ተገቢው ሰው የሟቹ የሥጋ ዘመዶች ናቸው ብለዋል።

የሻፊዒ መዝሀብ ተከታይ የሆኑት ኢማም አን-ነወዊ “አል-መጅሙዕ” ዉስጥ እንዲህ በማለት አስፍረዋል፡- የሥልጣን ባለቤት (ዋሊ) እና የቅርብ ዘመድ (ወሊይ) በዚህ ጉዳይ ላይ ከተወዛገቡ ሁለት ነገር ተብሏል። በፊት መዝሃብ (ቀዲም) ላይ ባለሥልጣን ይቀድማል ሲባል ነበር። በአዲሱ (ጀዲድ) አቋም ግን የቅርብ ዘመድ ይበልጥ ተገቢው ሰው ነው ተብሏል። ለምን ከተባለ ከውርስ ዉጭ የሆነ አካል በመምጣቱ ምክንያት በጋብቻ ጊዜ እንደሚደረገው ሁሉ ከባለሥልጣኑ ይልቅ የቅርብ የሥጋ ዘመዱ እንዲቀደም ሆነ ብለዋል።

ስለሆነም በጀናዛ ሶላት ጊዜ የሶላቱን ሁኔታ በሚገባ የሚያውቅ፣ በዕውቀትም፣ በበጎነትም ጥሩ የሆነ የሟቹ የቅርብ ሥጋ ዘመድ ቢሰግድበት ይበልጥ ተገቢው ነው። ካልሆነ መደበኛው የመስጂዱ ኢማም ያሰግድ። አላህ ከሁሉም በላይ አዋቂ ነው።