የጀመዐን ምንዳ ለማግኘት ፈርድ ሶላትን ደግሞ መስገድ

Home የፈትዋ ገጽ ሰላት የጀመዐን ምንዳ ለማግኘት ፈርድ ሶላትን ደግሞ መስገድ

ጥያቄ፡- የመግሪብን ሶላት ለብቻዬ ከሰገድኩኝ በኋላ በጀመዐ ሲሰገድ አገኘሁኝ። አብሬያቸው ደግሜ መስገድ እችላለሁ? ስሰግድስ ሦስት ረከዐ ነው የምሰግደው ወይስ አራት አድርጌ ልስገደው?


መልስ፡- ሶላትን በህብረት (በጀመዐ) መስገድ ብቻውን ከመስገድ በሃያ ሰባት ደረጃ ይበልጣል። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-

صَلَاةُ الْجَمَاعَةِ تَفْضُلُ صَلَاةَ الْفَذِّ بِسَبْعِ وَعِشْرِينَ دَرَجَةً موطأ مالك، وفي رواية بِخَمْسٍ وَعِشْرِينَ

“የጀመዐ ሶላት ለብቻ ከሚሰገድ ሶላት በሃያ ሰባት ደረጃ ይበልጣል።” የኢማም ማሊክ አል-ሙወጧእ የተሰኘው መፅሀፍ ላይ ተዘግቧል። በሌላ ዘገባ፡- “…በሃያ አምስት ደረጃ…” የሚል ተገኝቷል።

የአላህ መልእለክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ፈርድ ሶላትን ለብቻው ከሰገደ በኋላ በህብር የሚሰግዱ ሌሎች ሰዎችን ያገኘ ሰው በድጋሚ ከጀመዐዎቹ ጋር እንዲሰግድ አበረታተዋል። ከአቡ ዘር እንደተዘገበው የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-

صَلِّ الصَّلَاةَ لِوَقْتِهَا، فَإِنْ أَدْرَكْتَهَا مَعَهُمْ فَصَلِّهَا فَإِنَّهَا لَكَ نَافِلَةٌ

“ፈርዱን በወቅቱ ስገድ፤ ከዚያም እየሰገዱ ካገኘሃቸው በድጋሚ ስገድ። ይችኛዋ ላንተ ትርፍ ትሆንልሃለች።” አቡዳዉድ ዘግውታል።

“ይችኛዋ (فَإِنَّهَا)” የሚለው ቃል የመጀመሪያዋን ወይም ሁለተኛዋን ለማለት ሊሆን ይችላል። በዚህ መሰረት ዑለሞቹ በሁለቱ ሃሳቦች መሀል ተለያይተዋል። ዋናው ነገር ከሁለቱ ሶላቶች አንዱ ሱና ነው። ምክንያቱም በአንድ ሰው ላይ በአንድ ቀን ውስጥ ሁለት ተመሳሳይ ሶላቶች ግዴታ አይሆኑም። አንድ ጊዜ በመስገድ ጫንቃውን ንፁህ ማድረግ እና ራሱን ከጥያቄ ማዳን ይቻላል። ሌላኛዋ ሶላት በአላህ ችሮታና በቱሩፋቱ ከምንዳ አትራቆትም። ነገርግን አንዱ ፈርድ ነው ከተባለ ሌላኛው ፈርድ አይሆንም።

ይች ሱና ናት ያልናት ሦስት ወይም ሁለት ወይም አራት ረከዐ ከመሆን የሚያግዳት ምንም ነገር የለም። ሙዐዝ (ረ.ዐ) ከአላህ ነብይ ጋር የዒሻእን ሶላት ይሰግዱና ወደ ቤተሰቦቹ ሲሄድ ኢማም ሆኖ በድጋሚ ያሰግዳቸዋል። ለነርሱ ፈርድ ይሆንላቸዋል። ለርሱ ደግሞ ናፊላ (ትርፍ) ይሆንለታል።

ከላይ ያስቀደምነው የአቡዳዉድ ሐዲስ ሶላቱ ባለ ሦስት ረከዐም ሆነ ባለ አራት ወይም ባለ ሁለት ሳይለይ ነው የቀረበው። ስለዚህ መግሪብን በድጋሚ የሰገደ ሰው አንድ ረከዐ ይጨምር ለማለት የሚያስችል ምንም መሰረት አይኖርም። ስለዚህ እንደነበረው ሦስት ረከዐ ብቻ መስገድ ይበቃል።

አላሁ አዕለም!