የድህረ ወሊድ ደም አለመቋረጥ

Home የፈትዋ ገጽ ጣሃራ የድህረ ወሊድ ደም አለመቋረጥ

ጥያቄ፡- ባለቤቴ ከአንድ ወር ከግማሽ በፊት በተፈጥሯዊው መንገድ ወልዳ ነበር። ከወለደች በኋላ ግን ለሦስት ወራት ያህል የሚያገለግል የእርግዝና መከላከያ መርፌ ወስዳለች። ችግሩ ግን የኒፋስ ደም ላይ ነበረችና ደሙ መፍሰሱን አላቋረጠም። ከዚህ በፊት ሁለት ጊዜ መውለዷ ታሳቢ ይደረግ። ያኔ ደም ወዲያው ነበር የቆመላት። ጥያቄዬ ምንድን መሰላችሁ፡ በወሰደችው መርፌ ምክንያት ነው ደሙ ያላቋረጠው? አርባ ቀኗ አልፏልና ምንድን ነው ማድረግ ያለባት? አሁን እየፈሰሳት ያለው ደም የበሽታ ደም ነው የሚባለው፤ ስለዚህ ትስገድ ትፁም? ለእያንዳንዱ ወቅት ሶላትስ ዉዱእ ታድርግ?


መልስ፡- ከወሊድ በኋላ የሚፈሰው ደም (ኒፋስ) አርባ ቀን ድረስ ከፈሰሰ- በአርባ ቀን ውስጥ የመቆራረጥ ባህሪ ቢኖረውም እንኳን- በሸሪዓው ኒፋስ ነው። ስለዚህ እንደ የወር አበባ ደም አንዳንድ የአምልኮ ተግባራትን ክልክል ያደርጋል። ሻፊዒዮቹ ዘንድ የኒፋስ ደም ስድሳ ቀን ሊደርስ ይችላል የሚል እምነት አለ። ይህ እንደሴቲቱ እና እንደየወሊዱ ሊለያይ ይችላል። በመኖሪያ አካባቢና በዝርያም ሊለያይ ይችላል። ለምሳሌ በአንድ ወሊድ ላይ የኒፋስ ደም አንድ ወር ሊዘልቅ ይችላል። በሌላ ወሊድ ላይ ግን ሊጨምር ወይም ሊቀንስ ይችላል። ደሙን ሉፕ እና የመሳሰሉት የወሊድ መቆጣጠሪያዎች ሊያዛቡትም ይችላል። በዚህ መሰረት ሴትየዋ -እንደብዙዎቹ ዑለሞች ሃሳብ- አርባ ቀን ከአምልኮ ተግባራት ታቅባ ልትቆይ ትችላለች። ወይም እንደ ሻፊዒዮቹ ሃሳብ ከሆነ ደግሞ ስድሳ ቀን ትቆያለች። ከዚህ የጊዜ ገደብ በኋላም ደሙ ካልቆመ ግን ገላዋን ትታጠባለች፤ ደሙ የበሽታ ደም (ኢስቲሓዷ) ነው ማለት ነው። ለየሶላቱ ዉዱእ ታደርጋለች። ወቅቱ ሲያበቃም ዉዱእዋ ይበላሻል። የሌላ ሶላት ወቅት ሲገባ ደግሞ ሌላ ዉዱእ ታደርጋለች። የፈለገችውን ፈርድም ሆነ ሱና ሶላት መስገድ ትችላለች። ቁርኣን ታነባለች። መስጂድ ትገባለች። ባሏም ሊቀርባት ይችላል። ልክ ንጹህ እንደሆነች ሴት ማለት ነው።

አላሁ አዕለም!