የእስረኛ ጾም


ጥያቄ፡- ምርኮ ወይም በምርመራ ላይ ያለ እስረኛ ጾም ግዴታ ይሆንባቸዋል?


መልስ፡- ጾም ከስሜት መታቀብ ነው። ጾም ወደ አላህ ለመቃረብ ብሎ አስቦ ከሚያስፈጥሩ ነገሮች- ከምግብ፣ ከመጠጥና ከስሜት ንከኪ መከልከል ነው። ሙስሊም በማንኛውም ሁኔታው ላይ ሆኖ ጾም ሊነይት ይችላል። ምርኮ መሆን ወይም እስር ከዚህ ተግባር አያግደውም። ሁለቱን  የጾም ማዕዘናት- ኒያንና መታቀብን- እስካሟላ ድረስ መጾም ይችላል።

ነገርግን እስረኛ ወይም ምርኮ በቀን ካልሆነ ምግብ የማያገኝ ሊሆን እና ሊቸገር ይችላል። ምግቡን ለሊት አቆይቶ እንዳይበላ ሊታገድም ይችላል። በዚህ ጊዜ የማፍጠር ፍቃድ ይሰጠዋል። አላህ ነፍስን ከችሎታዋ በላይ አያስገድዳትም። አላህ በዲን ውስጥ ችግርን አላደረገም።

የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) አንድ መንገደኛን አዩ። እጅግ የመጨነቅ እና የችጋር ምልክት ይታይበት ነበር። ሰዎችም ዙርያውን ከበውት ቀለል እንዲለው ውሃ ይረጩበታል። ከዚያም የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ምንሆኖ እንደሆነ ጠየቁ። “ጾመኛ ነው” አሏቸው። እርሳቸውም እንዲህ አሉ፡-

ليس من البر الصيام في السفر

በጉዞ ወቅት መጾም መልካም ነገር አይደለም።”

በዚህ አይነት አስቸጋሪ ሆኔታ ላይ ሆኖ መጾም በጎ አይደለም ማለታቸው ነው። መንገደኛ በዚህ ሁኔታው ላይ መጾሙ ከአላህ መልእክተኛ ተቃውሞ ከገጠመው ከርሱ በላይ የሆነው ምርኮ ወይም እስረኛም- ምግብ በፈለገው ሰዐት የማያገኝ እስከሆነ ድረስ መጾሙ የተወገዘ ነው ማለት ነው። እጾማለሁ ብሎ ራሱን አስጨንቆ አደጋ ላይ መውደቅም የለበትም። በበደል ያሰሩት ሰዎች ወይም ጠላቶቹ የሚፈልጉት ነገር ይህን ነው።

ስለዚህ በእንዲህ ዓይነቱ ተጨባጭ ላይ ያለ ሙስሊም ማፍጠር ይገባዋል። አላህ ከእስር ሲለቀው ወይም ያለበት ሁኔታ ሲለወጥ ያፈጠረበትን ቀን የሚያክል በሌላ ቀን በመጾም ቀዳውን መክፈል አለበት። አላህ እንዲህ ይላል፡-

يُرِيدُ اللَّهُ بِكُمُ الْيُسْرَ وَلَا يُرِيدُ بِكُمُ الْعُسْرَ

“አላህ በእናንተ ገሩን (ነገር) ይሻል። በእናንተም ችግሩን አይሻም።” (አል-በቀራ 2፤ 185)