የቁንጅና ውድድር እና የሴቶች መብት

Home የፈትዋ ገጽ ማህበራዊ ጉዳዮች ቤተሰብ የቁንጅና ውድድር እና የሴቶች መብት

ጥያቄ፡- በየትምህርት ቤቱ፣ በየከተማው በሀገር ዐቀፍ ብሎም በኢንተርናሽናል ደረጃ ሳይቀር የሚሰናዱ የቁንጅና ውድድሮች በኢስላም እንዴት ይታያሉ?


መልስ፡- እነዚህ ውድድሮች የመቆሸሽ እና የመበከል ምልክቶች ናቸው፡፡ የሃያ አንደኛው ምዕተ ዓመት መሀይምነት መገለጫዎች ናቸው፡፡ የሴቶችን ክብር ዝቅ የሚያደርጉ ወራዳ ነገሮች ናቸው፡፡ በእንዲህ ዓይነት ውድድሮች ላይ የተሳተፈ ማንኛውም ሰው ኃጢያተኛ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ውድድሮች ላይ በመካፈል ነፍሷን ማዋረድ የመረጠች ሴትም ወንጀለኛ ናት፡፡ ለልጁ፣ ለሚስቱ፣ ለእህቱ መቅናት ያቃተው “ደዩስ” ቤተሰቧም ኃጢያተኛ ነው፡፡ የሀገር አስተዳዳሪ የሆኑ የሚመለከታቸው አካላትም -የህዝቦቻቸውን ባህል፣ ወግና ማንነት ለማስጠበቅ የገቡትን ቃል በማፍረሳቸው- ኃጢያተኞች እና ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ውድድር ያስተዋወቀ፣ የደገፈ እና ያስተባበረ ሰው ሁሉ ወንጀለኛ ነው፡፡

በጉዳዩ ላይ የዓለም ዑለማኦች ህብረት አባል የሆኑት ሸይኽ አክረም ከሳብ እንዲህ ሲሉ ፈትዋ ሰጥተዋል፡-

በሙስሊም ሀገሮች ላይ ሳይቀር እንዲህ ዓይነት ውድድሮች መከናወናቸው ያሳዝናል፡፡ ጉዳዩ ተከታዩን የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሐዲስም ያስታውሰናል፡-

إن ما أدرك الناس من كلام النبوة الأولى , إذا لم تستح فاصنع ما شئت

“ሰዎች የደረሳቸው የመጀመሪያው የነብያት ንግግር ‘ካላፈርክ የፈለከውን ሥራ፡፡’ የሚለው ንግግር ነው፡፡” ቡኻሪይ ዘግበውታል፡፡

እንዲህ ዓይነት ውድድሮች ላይ በማንኛውም መልኩ መሳተፍ ከታላላቅ ኃጢያቶች ይመደባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ኃጢያቱም ለተካፋዮቹ እንደተሳትፏቸው ደረጃ ይከፋፈላል፡፡ እንደዚህ እናብራራዋለን፡-

  1. ተወዳዳሪት፡- ይች የነጃሳ ገበያ ላይ ነፍሷን ሸቀጥ ሆና መቅረብ የመረጠች ሴት ናት፡፡ ፈታኝ አካሏን እያሳየች፣ ጌጧን እያጋለጠች፣ የሰዎችን ክብር የሚነግዱት ወራዶች እንዲመርጧት ራሷን አዘጋጅታለች፡፡ ተከታዩን የአላህ ንግግር ችላ ብላለች፡-

وَقُل لِّلْمُؤْمِنَاتِ يَغْضُضْنَ مِنْ أَبْصَارِهِنَّ وَيَحْفَظْنَ فُرُوجَهُنَّ وَلَا يُبْدِينَ زِينَتَهُنَّ إِلَّا مَا ظَهَرَ مِنْهَا وَلْيَضْرِبْنَ بِخُمُرِهِنَّ عَلَىٰ جُيُوبِهِنَّ …وَلَا يَضْرِبْنَ بِأَرْجُلِهِنَّ لِيُعْلَمَ مَا يُخْفِينَ مِن زِينَتِهِنَّ وَتُوبُوا إِلَى اللَّهِ جَمِيعًا أَيُّهَ الْمُؤْمِنُونَ لَعَلَّكُمْ تُفْلِحُونَ

“ለምእምናትም ንገራቸው፡- ዓይኖቻቸውን ይከልክሉ፡፡ ብልቶቻቸውንም ይጠብቁ፡፡ ጌጣቸውንም ከእርሷ ግልጽ ከኾነው በስተቀር አይግለጡ፡፡ ጉፍታዎቻቸውንም በአንገትጌዎቻቸው ላይ ያጣፉ፡፡ …ከጌጣቸውም የሚሸፍኑት ይታወቅ ዘንድ በእግሮቻቸው አይምቱ፡፡ ምእመናኖች ሆይ! ትድኑ ዘንድ ሁላችሁም ወደ አላህ (በመመለስ) ተጸጸቱ፡፡” (24፤31)

በሌላም አንቀፅ እንዲህ ብሏል፡-

يَا أَيُّهَا النَّبِيُّ قُل لِّأَزْوَاجِكَ وَبَنَاتِكَ وَنِسَاءِ الْمُؤْمِنِينَ يُدْنِينَ عَلَيْهِنَّ مِن جَلَابِيبِهِنَّ ذَٰلِكَ أَدْنَىٰ أَن يُعْرَفْنَ فَلَا يُؤْذَيْنَ وَكَانَ اللَّهُ غَفُورًا رَّحِيمًا 

“አንተ ነቢዩ ሆይ! ለሚስቶቸህ፣ ለሴቶች ልጆችህም፣ ለምእምናን ሚስቶችም ከመከናነቢያዎቻቸው በላያቸው ላይ እንዲለቁ ንገራቸው፡፡ ይህ እንዲታወቁና (በባለጌዎች) እንዳይደፈሩ ለመኾን በጣም የቀረበ ነው፡፡ አላህም መሓሪ አዛኝ ነው፡፡” (33፤59)

የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ሴት ከቤቷ ውጪ ልብሷን እንዳታወልቅ አስጠንቅቀዋል፡፡ እንዲህ ብለዋል፡-

أيما امرأة نزعت ثيابها في غير بيتها خرق الله عنها سترا

“ማንኛዋም ሴት ከቤቷ ውጪ ልብሷን ካወለቀች አላህ ሽፋኑን ይገልጥባታል፡፡ (ያዋርዳታል ወይም ጥበቃውን ያነሳባትና ይቀጣታል፡፡)” አሕመድ ዘግበውታል፡፡

  1. ወልይዋ፡- እርሷን በተመለከተ ተጠያቂነት ያለበት ሰው በሙሉ በዚህ ጉዳይ ላይ ኃጢያተኛ ነው፡፡ አባትም ይሁን ወንድም ወይም ባል በድርጊቷ ደስተኛ ከሆኑና በጀ ብለው ከተቀበሉ ደዩሶች ናቸው፡፡ ለሴቶቻቸው የማይቀኑ ደንታ ቢሶች፡፡ ለሴቶቻቸው ራቁትን የወደዱ ሴቶቻቸው የዝሙት ማጋጋያ የስሜት ገንዳዎች መሆናቸውን የመረጡ ወንዶች በሙሉ ይጠየቃሉ፡፡ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

لا يدخل الجنة ديوث

“ደዩስ ጀነት አይገባም፡፡” ጦበራኒይ ዘግበውታል፡፡

በሌላ ሐዲስ እንዲህ ይላሉ፡-

ثلاثة قد حرم الله تبارك وتعالى عليهم الجنة: مدمن الخمر ، والعاق ، والديوث الذي يقر في أهله الخبث

“አላህ በሦስት ሰዎች ጀነትን እርም አድርጓል፡- አልክሆል የሚያዘወትር ሰው፣ ወላጆቹን የበደለ እና ለሚስቱ ቆሻሻን የመረጠ ደዩስ፡፡” አሕመድ እና ሌሎችም ዘግበውታል፡፡

ይህ ቸላተኝነት ከባድ ኃጢያት ነው፡፡ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-

كفى بالمرء إثما ان يضيع من يقوت

“(ለአጥፊ) ኃጢያትነት ሰውየው የሚቀልባቸውን ሰዎች ችላ ማለቱ ይበቃዋል፡፡” አሕመድ ዘግበውታል፡፡

  1. መንግስት፡- እንዲህ ዓይነት ውድድሮች እንዲከናወኑ የሚፈቅድ መንግስት ኃላፊነት አለበት፡፡ መንግስት የህዝቡን ማንነትና ባህል የመጠበቅ ግዴታ አለበት፡፡ መንግስት ለህዝቡ የሚጠቅመውን መልካም ነገርን ብቻ ማበረታታት ለህዝቡ የሚጎዳን ክፉን ነገር መከላከል ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ኃላፊነቱን አልተወጣም፡፡ አደራውን በልቷል፡፡ የአላህንም የህዝቡንም አደራ ጥሏል፡፡ በሐዲስ ውስጥ እንዲህ የሚል ዘገባ አለ፡-

كلكم راع ومسؤول عن رعيته فالإمام راع وهو مسؤول عن رعيته

“ሁላችሁም እረኞች ናችሁ ስለጠበቃችሁትም ነገር ትጠየቃላችሁ፡፡” ቡኻሪይና ሙስሊም ዘግበውታል፡፡

ለህዝቡ በጎን ነገር ከመምረጥ የሚቦዝን መሪን አስመልክቶ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

ما من عبد يسترعيه الله رعية يموت يوم يموت وهو غاش لرعيته إلا حرم الله عليه الجنة

“አላህ መሪ አድርጎ ሾሞት በሚሞትበት ቀን ህዝቡን እንዳጭበረበረ የሚሞት ማንም ባርያ የለም አላህ ጀነትን እርም ያደረገበት ቢሆን እንጂ!” ሙስሊም ዘግበውታል፡፡

  1. እነዚህን ውድድሮች የሚደግፉ አካላት፡- የውድድሮቹ ደጋፊዎች መንገድ የሳቱ ክፉ ሰዎች ናቸው፡፡ አላህ የሰጣቸውን መልካም ፀጋ የካዱ፣ ለፀጋው ምላሽ የክህደትና የድርቅና አፀፋ የሰጡ ሰዎች ናቸው፡፡ ገንዘባቸውን አላህን ለመዋጋት ያዋሉ፣ ብክለትን ለማስፋፋት የተጠቀሙ ሰዎች ናቸው፡፡
  2. አጋናኞች፡- እንዲህ ዓይነቱን ውድድር የሚያጋንኑት የሚዲያ ሰዎች ናቸው፡፡ ይህ ቆሻሻ ተግባር ያለበትን ቦታ ያነፈንፋሉ፡፡ ካሜራቸውን አንግተው ብክለትን ለማሰራጨት ይተማሉ፡፡ በብዕራቸውም ይህንኑ አመፅ ለማጋነን ይተጋል፡፡ ካሜራቸው ርክሰትን ለመቀደስ ይጣጣራል፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹን አስመልክቶ አላህ እንዲህ ብሏል፡-

إِنَّ الَّذِينَ يُحِبُّونَ أَن تَشِيعَ الْفَاحِشَةُ فِي الَّذِينَ آمَنُوا لَهُمْ عَذَابٌ أَلِيمٌ فِي الدُّنْيَا وَالْآخِرَةِ وَاللَّهُ يَعْلَمُ وَأَنتُمْ لَا تَعْلَمُونَ

“እነዚያ በእነዚያ ባመኑት ሰዎች ውስጥ መጥፎ ነገር እንዲስፋፋ የሚወዱ ለእነሱ በቅርቢቱም በመጨረሻይቱም ዓለም አሳማሚ ቅጣት አላቸው፡፡ አላህም ያውቃል እናንተ ግን አታውቁም፡፡” (24፤19)

በጉዳዩ ላይ ሦስት ነጥቦችን እናንሳ፡-

  1. የቀድሞውና የአሁኑ ዘመን ጃሂሊያ፡-

የዘመናችን ጃሂሊያና የቀድሞውን ጃሂሊያ የሚያመሳስል ነገር አለ፡፡ የነጃሳው ገበያ ያመሳስላቸዋል፡፡ የቀድሞውና የአሁኑ የነጃሳ ገበያ ቢለያይም ቅሉ በዋናው ነጥብ ላይ አንድ ናቸው፡፡ የድሮው ጃሂሊያ የሴት ባሮችን ስጋ ለገበያ ያቀርብ ነበር፡፡ የአሁኑ ጃሂሊያ ግን የሁሉንም ሴቶች ስጋ ለገበያ ያቀርባል፡፡ ነገርግን አዲሱ ጃሂሊያ ለነጃሳው ገበያ መልካም ሥም ያወጣል፡፡ የቁንጅና ውድድር፣ ጥበብ… እያለ ቆሻሻውን ይደብቃል፡፡ ነገርግን ጥበብ እብደት ሆነ፡፡ ትልቁ የአላህ ስጦታ የነበረው ፈን/ጥበብ በክፉ ሰዎች እጅ ታሸና አደፈ፡፡ የሰዎችን ስብዕና ሻረና በቦታው እንስሳነትን አሰረፀ፡፡

  1. ኢስላም ለሴቶች ያለው እይታ፡-

ሴት በኢስላም የሚሸጥ ሸቀጥ አይደለችም፡፡ የምትሸተት ፅጌሬዳም አይደለችም፡፡ እቃ ማሻሻጫ ቅርፅም አይደለችም፡፡ በክብካቤ የምትጠበቅ እንቁ ናት፡፡ የምታሳሳ ሉል ናት፡፡ ኢስላም ህፃን ሆና ይጠብቃታል፡፡ ይንከባከባታል፡፡ ትልቅም ሆና ይጠብቃታል፡፡ በዚህና በዚያ መሀልም በክብካቤ ትልቅ ደረጃ እንድትደርስ በመልካም አስተዳደግ ውስጥ የምታልፍ ልጅ፣ እገዛ የሚያሻት እህት፣ ባለ መብት ሚስት፣ የምትመሰገን እናት፣ ጀብዷ የሚወሳላት አያት ናት!…

  1. ከዋናው አጀንዳችን ማዘናጊያ፡-

እነዚህ ውድድሮች ከባህላችን የራቁ፣ ማንነታችንን የማያንፀባርቁ፣ ከማንኛችንም ኃይማኖት -ከክርስትናም ሆነ ከኢስላም ያፈነገጡ ከመሆናቸው ጋር የህልውናችን መሰረት፣ የዘመናዊነት ማሳያ፣ የተራማጅነት ምልክት ተደርገው እንዲታዩ የተደረጉት ለምንድን ነው?! ለኢትዮጲያዊያን ትልቁ ጉዳይ ዳቦ ነው ወይስ የሴት ገላ? ለሴቶቻችንስ የሚያሻቸው ትምህርት ነው ወይስ ዝሙት? ርክሰት?

እኛማ ጉዳዩ ማንነታችንን በማሳጣት ለራሳችን ክብር እንዳይኖረን፣ በዋና ዋና ችግሮቻችን ላይ እንዳናተኩር የሚያደርግ የቅኝ ገዢዎች ዘዴ ይመስለናል!

አላህ የበለጠ ያውቃል!