የሸዋል ወር የስድስቱን ቀን ጾም እና የረመዳንን ቀዷ በአንድ ኒያ ማስገኘት

Home የፈትዋ ገጽ ጾምና ኢዕቲካፍ የሸዋል ወር የስድስቱን ቀን ጾም እና የረመዳንን ቀዷ በአንድ ኒያ ማስገኘት

ጥያቄ፡- የረመዳን ቀዷ እንዲሆንልኝ ከሸዋል ወር ስድስት ቀናትን ብጾም እና የሸዋልን የስድስቱን ቀናት ጾም አብሬ ብነይት ይበቃኛል? የስድስቱን ቀን የሸዋል ሱና ምንዳ አገኛለሁ?


መልስ፡- የሚሻለው ሁለቱን ኒያዎች መለያየት ነው። ለቀዳእ የሚጾመው ጾም ለብቻው ይነየት። የስድስቱ የሸዋል ቀናት ጾምም ለብቻው ይነየት። አንዳንድ ዑለሞች በአንድ ላይ ሁለቱንም መነየት ይከለክላሉ። ሁለቱን በአንድ ላይ መሰብሰብ ከፈለገ -ለምሳሌ፡- ቀዳ በማውጣት ተጠምዶ ስድስቱን ቀናት መጾም የሚያስችል ጊዜ ጠበበበት ወይም ለራሱ ማቅለል ከፈለገ- ሻፊዒዮቹ ዘንድ ይፈቀድለታል። የስድስቱ ቀናትን ምንዳ ያገኛል። የቀዳእ ቀናቱም ከጫንቃው ላይ ይወርዱለታል።

ሻፊዒዮቹ እንዲህ ብለዋል፡- “በሸዋል ውስጥ የረመዳንን ወይም የሌላን ጊዜ ቀዳእ ወይም የስለት ጾም ወይም ሌላ ሱና ጾም ቢጾም የሸዋል ሱና ጾም ምንዳን ያገኛል። ምክንያቱም ዋናው መዘውር ያለው በሸዋል ወር ውስጥ በሚገኙ ስድስት ቀናቶች ውስጥ ጾም መገኘቱ ላይ ነው።”…

እንዲህም ብለዋል፡- “ይህ ተሒይ-የቱል-መስጂድ ላይ ከሚባለው ጋር ይመሳሰላል። ተሒያ መስጂድ የገባ ሰው የሚሰግዳት ሁለት ረከዓ ሶላት ነች። እርሷ በፈርድ ሶላት ወይም በሌላ ሱና ሶላት ትገኛለች። እንደውም አብራ ባትነየትም እንኳን ትገኛለች። ምክንያቱም እርሷ የተደነገገችበት ዋናው ዓላማ መስጂድ የገባ ሰው ከመቀመጡ በፊት እንዲሰግድ ነው። በተጠቀሱት ሶላቶች ደግሞ ዓላማው ተሳካ። ስለዚህ ተሒየቱል-መስጂድ እንዲሰግድ የታዘዘው ትዕዛዝ በዚያው ከጫንቃው ወረደ። እንደውም የተሻለው የዑለሞቹ ሃሳብ እንደሚያመለክተው ከነዚህ ሶላቶች ጋር አብሮ ባይነየትም ልዩ ምንዳው መገኘቱ አይቀርም።”

አላህ የበለጠ ያውቃል!