የስኳር በሽተኛን ማግባት

Home የፈትዋ ገጽ ቤተሰብ ጤናና ህክምና የስኳር በሽተኛን ማግባት

 


ጥያቄ፡- በጠባይ፣ በዲናዊም ሆነ በማህበረሰባዊ መመዘኛዎች ብቁ የሆነ ሰው አጭቶኝ ነበር። ነገርግን ቤተሰቦቼ የስኳር በሽተኛ ስለሆነ ጋብቻውን ማገድ ይችላሉ? ሁለታችንም እንዋደዳለን፤ እንፈላለጋለን። ቤተሰብ በዚህ ዓይነት ምክንያት ጋብቻችንን ማገድ ይችላል? ቤተሰቦቼ እንዲስማሙስ እንዴት ላሳምን እችላለሁ? ምክራችሁን እሻለሁ።


መልስ፡- የህክምና ባለሙያዎች የስኳር በሽታ የጋብቻ ህይወት ላይ እክል እንደማይፈጥር አስረድተዋል። ለጋብቻ ህይወት የሚያዳግት ለእይታ የሚያስጠላ በሽታ አይደለም። በንክኪና በግብረስጋ ግንኙነት የሚጋባ በሽታም አይደለም።

በዚህ መሠረት ቤተሰቦችሽ ያጨሽን ሰው ከጋብቻ ማገድ አይችሉም። ዲንና መልካም ጠባይ እስካለውና ታማኝ እስከሆነ ድረስ ጋብቻውን ሊከለክሉ አይገባም።

በአል-አዝሃር ዩኒቨርሲቲ የሸሪዐ ጥናት መምህር የሆኑት ዶክተር ዐብዱል-ፈታሕ ኢድሪስ እንዲህ ይላሉ፡-

“ህመም የአላህ ፈተና ነው። ሰውየው በራሱ የሚያመጣው ነገር አይደለም። ህመም ደግሞ ጋብቻን አያግድም። በምድር ላይ አነሰም በዛም ህመም የሌለበትን ሰው ማግኘት ይቸግራል። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

إذا جاءكم من ترضون خلقه ودينه فزوجوه إلا تفعلوا تكن فتنة في الأرض وفساد كبير

“ዲኑን እና ጠባዩን የምትወዱለት ሰው ከመጣላችሁ ዳሩት። ይህንን ካላደረጋችሁ በምድር ላይ ፈተናና ትልቅ ብክለት ይፈጠራል።”

በዚህ መሠረት ይህ ሰው በዚህ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ንግግር የተጠቀሰውን መስፈርት እስካሟላ ድረስ ከጋብቻ መከልከል አይገባም። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ለኃይማኖቱ ታማኝ እና ጠባየ መልካም ከመሆኑ በዘለቀ ከበሽታ ነጻ የሆነ ሰው ከመጣ አላሉም። ስለዚህ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንድናስተውላቸው ከመከሩን ነገሮች ውጪ መሥፈርቶች በማብዛት ልጃገረዶችን ከጋብቻ ማገድ ተገቢ አይደለም። አላህ በቁርኣኑም ይህንን መሠል እገዳዎችን አውግዟል፤ ከልክሏል። ይህንን ድርጊት የሚፈፅም ሰውም ኃጢያተኛ ነው። አላህ እንዲህ ብሏል፡-

فَلَا تَعْضُلُوهُنَّ أَن يَنكِحْنَ أَزْوَاجَهُنَّ إِذَا تَرَاضَوْا بَيْنَهُم بِالْمَعْرُوفِ ذَٰلِكَ يُوعَظُ بِهِ مَن كَانَ مِنكُمْ يُؤْمِنُ بِاللَّهِ وَالْيَوْمِ الْآخِرِ

“በመካከላቸው በሕግ በተዋደዱ ጊዜ ባሎቻቸውን ከማግባት አታስተጓጉሏቸው። ይህ (መከልከል) ከእናንተ በአላህና በመጨረሻው ቀን የሚያምን ሰው በርሱ ይገሰጽበታል።” (2: 232)

አላህ የበለጠ ያውቃል!