የሴቶች ኢሕራም ፊትን መግለጥ የሆነበት ብይን እና ጥበብ

Home የፈትዋ ገጽ ሐጅና ዑምራ የሴቶች ኢሕራም ፊትን መግለጥ የሆነበት ብይን እና ጥበብ

ጥያቄ፡- ኢሕራም ላይ ያለች ሴት ፊቷን መሸፈን ወይም ኒቃብ መልበስ እርም ይሆንባታል? ፊቷን ብትሸፍን ኃጢያተኛ ትሆናለች ማለት ነው? ነገሩ እንዲህ ከሆነስ ሴት ኢሕራም ላይ ፊቷን እንድትገልጥ የታዘዘበት ጥበብ ምንድን ነው?


መልስ፡- አብዝሃኞቹ ዑለሞች በኢሕራም ወቅት ሴት ፊቷን መሸፈን እርም እንደሚሆንባት ያምናሉ። ስለዚህ ኒቃብም ሆነ ጓንት አትለብስም። ምክንያቱም የሴት የኢሕራም መገለጫ ፊቷን መክፈቷ ነው። የሐዲስ ኢማሞቹ ቡኻሪይ፣ አቡዳዉድ እና ነሳኢይ ናፊዕን ዋቢ አድርገው እንደዘገቡት እንዲህ ብለዋል፡-

ولا تنتقب المرأة المحرمة ولا تلبس القفازين

“ኢሕራም ላይ ያለች ሴት ኒቃብ አትለብስም። ጓንትም አትለብስም።”

ኢብኑል-ሙንዚር እንዲህ ይላሉ፡- “በኢሕራም ውስጥ ኒቃብን የፈቀደ አንድ ሶሐባ አናውቅም።”

ኢብኑ ዐብዲል-በር ደግሞ እንዲህ ይላሉ፡- “ለሙሕሪም ሴት ኒቃብ እርም መሆኑን አብዝሃኞቹ ሶሓቦች፣ ተከታዮቻቸው እና ከነርሱ በኋላ የመጡት የየሃገሩ የፊቅህ ልሂቃን ባጠቃላይ ያምናሉ። በጥቂቱ ግን ‘ኢሕራም ላይ ሆነው ፊታቸውን ሸፍነዋል የሚል’ ከአስማእ ቢንት አቢበክር የተዘገበ ዘገባ አለ።”

ኢማም ኢብኑ ቁዳማ ግን “አስማእ ፊታቸውን ይሸፍኑ የበነበረው አስፈላጊ በሆነባቸው ቦታዎች ላይ ብቻ” በመሆኑ ጉዳዩ ያለ ልዩነት የተረጋገጠ ነው ማለት ያስችለናል ብለው የኢብኑ ዐብዲል-በርን ጥርጣሬ መልሰዋል። ስለዚህ ጉዳዩ የዑለሞች ስምምነት አለበት ማለት ነው።

አቡ ዳዉድ እና አል-አስረም ዓኢሻ እንዲህ ማለታቸውን ዘግበዋል፡-

كان الركبان يمرون بنا , ونحن محرمات مع رسول الله صلى الله عليه وسلم فإذا حاذونا , سدلت إحدانا جلبابها من رأسها على وجهها , فإذا جاوزونا كشفناه

“እኛ ከአላህ መልእክተኛ ጋር ኢሕራም ላይ ሆነን ሰዎች ባጠገባችን ያልፋሉ። ከነርሱ ጋር ስንቀራረብ ጂልባባችንን ፊታችን ላይ እንለቀዋለን። ስንተላለፍ ግን እንገልጠዋለን።”
ይህም ፊታቸውን የሚሸፍኑት በኒቃብ እንዳልሆነ ያሳየናል።

በዚህ መሰረት ሴት ኢሕራም ላይ ሆና ኒቃብ መልበስ አትችልም። ነገርግን እንድትሸፍን የሚያደርግ ምክንያት ካላት ያለኒቃብ በሌላ ነገር ፊቷን ትሸፍነዋለች። ነገርግን መሸፈኛው ፊቷ ላይ መለጠፍ የለበትም። ይህ አብዝሃኞቹ ዑለሞች የሄዱበት መንገድ ነው።

እንደውም አንዳንዶቹ የፊቅህ ሰዎች ሴትየዋ ኢሕራም ላይ ሆና ኒቃብ ከለበሰች ቤዛ የሚሆን መቀጫ ግዴታ ይሆንባታል ባይ ናቸው።
ኢብኑ ዐብዲል-በር እንዲህ ይላሉ፡- “እኔ ትክክል ነው ብዬ የማምነው አንዲት ሴት ኢሕራም ላይ ሆና ሳለ ፊቷን መሸፈን እርም መሆኑን ነው። ይህንን ካደረገችም የመቀጫ ቤዛ (ፊድያ) ግዴታ ይሆንባታል።”

ብዙ ዑለሞች ግን ይህንን ሃሳብ ይቃወማሉ። “ፊድያ ግዴታ አይሆንባትም።” ይላሉ። በተለይም አስማእ ቢንት አቢበክር ሙሕሪም ሆነው ኒቃብ መልበሳቸው መዘገቡ ይህንን ያጠናክራል። ከዓኢሻም “ሴት- ከፈለገች- ፊቷን መሸፈን ትችላለች” የሚል ተዘግቧል።

በኢሕራም ወቅት ሴት ፊቷን መግለጧ ጥበቡ ምንድን ነው? ስለሚለው ጥያቄ እንዲህ እንላለን፡-

በመሰረቱ አምልኮ ለአላህ ብቻ ነው። አላህ ደግሞ ሴቶችንም ሆነ ወንዶችን በፈለገው መልኩ አምልኮ እንዲፈፅሙ ያዛቸዋል። አላህ እንዲህ ይላል፡-

وَمَا كَانَ لِمُؤْمِنٍ وَلَا مُؤْمِنَةٍ إِذَا قَضَى اللَّهُ وَرَسُولُهُ أَمْرًا أَن يَكُونَ لَهُمُ الْخِيَرَةُ مِنْ أَمْرِهِمْ

“አላህና መልክተኛውም ነገርን በፈረዱ ጊዜ ለምእምናንና ለምእምናት ከነገራቸው ለእነርሱ ምርጫ ሊኖራቸው አይገባም!” (አል-አህዛብ 33፤ 36)

ነገርግን አላህ አምልኮን ትርጉም አልባ አላደረገውም። ሰዎች እንዲመራመሩበት እና ሚስጥራቱን ነቅሰው እንዲያወጡ እድሉን ሰጥቷል። ይህም አምልኮውን ለመፈፀም እንዲችሉ እና እንዲያሳምሩት ያግዛቸዋል።

በዚህ መሰረት ሴቶች በኢሕራም ወቅት ፊታቸውን እንዲገልጡ የታዘዘበት ምክንያት የሚከተሉት ሊሆን ይችላል፡-

አንደኛ፡- ነፍስ ምንም አይነት ተቃውሞም ሆነ ማቅማማት ለአላህ ትእዛዝ ተገዥ እንድትሆን ማሰልጠን። ይህ ሃሳብ የባርነትን ፅንስ ያሰርፃል። ኒቃብ በሴቶች ላይ የተወሰነ ቢሆንም እንኳን የአላህ ፍላጎት ወደ ምንም ሳይዞር የባርነትን ፅንሰ ሃሳብ በሰዎች ነፍስ ውስጥ ማጠናከር ነው።

ሁለተኛ፡- ነፍስን ከተለምዶዋ ማላቀቅ ነው። ይህም ሐጅን እና ዑምራን የሚፈፅም ሰው በሙሉ ልቡ ወደ ተግባራቱ እንዲዞር ያስችላል። የቀልብን ንፅህና ያረጋግጣል። ከተለምዶ እስር ያላቃል። የተፈቀደ ከነበረ ነገር የተላቀቀችውኮ አላህን ለመታዘዝ ነው። ስለዚህ ነፍስ ክልክል ከሆኑ ነገሮች መላቀቅ አያቅታትም ማለት ነው።

ሦስተኛ፡- የሐጅና የዑምራ ስርዐት የቂያማን ቀን ይመስላል። ሰዎች ያንቀን ራቁት ሆነው ነው የሚመጡት። የሚያዩት ነገር አያስደንቃቸውም። ሰው ፍፃሜውን በመጠበቅ በሚንከራተትበት ቀን በመመሰል እና እለቱን ለማታወስ ልብን ከአላህ ውጪ ካሉ ነገሮች ማላቀቅ ታስቦ ነው። ስለዚህ ሰዎች በሐጅ ወይም በዑምራ ስራዎች ተጠምደው አላህን እንጂ ሌላን እንደማይመለከቱ ለመጠቆም።

አራተኛ፡- የወንድ ኢሕራም ራሱ (አናቱ) ላይ ስለሆነ ጭንቅላቱን መሸፈን አይችልም። ስለዚህ በጉዳዩ ላይ ሁለቱንም ጾታ ለማጣጣም ሴትም የሚመጥናት የኢሕራም ምልክት ተደረገላት። ኢሕራሟን- ሸሪዐው- ፊቷ ላይ አደረገው። ስለዚህ ፊቷን መሸፈን አትችልም።

ወላሁ አዕለም!