የሐጅ መጓጓዣ እና የእንግልቱ ምንዳ

Home የፈትዋ ገጽ ሐጅና ዑምራ የሐጅ መጓጓዣ እና የእንግልቱ ምንዳ

ጥያቄ፡- ወደ ሐጅ በአውሮፕላን መሄድ ይሻላል ወይስ በመኪና ወይም በእግር? በእግራችን ስለመጣን የሚከፈለን ምንዳ ከሌላው ይበልጣል ብለው የሚያስቡ ከፓኪስታን በእግራቸው የመጡ ሰዎች አጋጥመውኝ ነው። ሃሳባቸው ትክክል ነው?


መልስ፡- በዒባዳ የሚገኝ ምንዳ በእንግልት ላይ ብቻ የተመሠተ አይደለም። ታሳቢ መሆን ያለባቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ቀደምት መስፈርቶች ተደርገው የሚታዩ ብዙ ነገሮች አሉ። ዋናው ኢኽላስ ነው፤ ስራን ጥርት አድርጎ ለአላህ መስራት። ዒባዳውን በሚገባ በጥንቃቄ መከወን፤ ስርዐቱን መጠበቅ፤ ማሳመር… ሌላው ታሳቢ ነገር ነው። ኢኽላስ ባማረ ቁጥር፣ ስራው በጥንቃቄና በትኩረት በተከወነ ቁጥር፣ ተግባሩ በሱና ስርዐት የተሞላ ሲሆን… ዒባዳው ምንዳው ከፍ ያለ ይሆናል። ከዚያ በኋላ ነው ዒባዳውን ለመከወን የተደረገ ጥረትና እንግልት ከግምት ውስጥ የሚገቡት። አምልኮን ለመተግበር ብዙ ዋጋ የከፈለ ሰው ትጋቱ በከንቱ ይባክናል ተብሎ አይጠበቅም። አላህ ዘንድ ምንዳውን አያጣም። ነገርግን ችግሩ ሰውየው ራሱን ለማስጨነቅ ብሎ የፈጠረው አለመሆኑ እዚህ ጋር ታሳቢ ይሆናል።

ለምሳሌ፡- ሰውየው የሚሰግድበት መስጂዱ ቅርብ ነው። ነገርግን ሰውየው ወደሩቅ ቦታ ሂዶ፣ ዞሮ ተጠማዞ እርምጃውን በማብዛት ብዙ ርቀት ተጉዞ እዚያው መስጂድ መስገዱ ምንዳውን ይጨምርለታል?! አይጨምርለትም!

ነገርግን ቤቱ ከሚሰግድበት መስጂድ በመራቁ ምክንያት ወደ መስጂድ የሚራመደው ርምጃ ሲበዛ ምንዳውን ከፍ ያደርግለታል። በእያንዳንዱ ርምጃው ሐሰና ያገኛል። በሌላኛው ርምጃው ኃጢያቱ ይራገፋል።

በኑ ሰሊማ የሚባሉት ጎሳዎች መዲና ድንበር ላይ የነበረውን መንደራቸውን ትተው ወደ ነብዩ መስጂድ መቅረብ ፈልገው ነበር። ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ግን አልፈቀዱላቸውም። ወደ ሶላት የሚራመዱት እርምጃቸው- እያንዳንዱ- ምንዳቸውን እንደሚጨምርላቸው ነገሯቸው። እነዚህ ሐሰናዎች አላህ ዘንድ ይካማችላቸዋል፤ ኢንሻ አላህ። ነገርግን ሰውየው ሐሰናውን ለማብዛት አላስፈላጊ ርምጃ ያብዛ፣ ርቆ ይሂድና ተመልሶ ወደ መስጂዱ ይምጣ ማለት አይደለም።

ሰውየው የአውሮፕላን የቲኬት ወጪን የሚሸፍንበት ገንዘብ ከሌለው በከብት ተጭኖ ወይም በእግሩ ተራምዶ ወይም በመኪና ተሳፍሮ ሐጅ ሊያደርግ ይችላል። ይህ ሰው ያለጥርጥር ምንም እንግልት ሳይነካው በአንድ ወይም በሁለት ሰዐታት ወደ መካ ከሚመጣው ሰው የበለጠ ምንዳ አለው።

ዋናው ነገር ሰውየው እንግልቱን ሆን ብሎ ፈጥሮት እንዳይሆን። አላህ የሚጋልበው የተሻለ ነገር ሰጥቶት እያለ ራሱን ለማስጨነቅ በእግሩ ተጉዞ እንዳይሆን። አውሮፕላን መጠቀም እየቻለ መኪና፣ መኪና መጠቀም እየቻለ ከብት፣ ከብት መጠቀም እየቻለ በእግሩ መጥቶ እንዳይሆን።

የተሻለውን መጠቀም ሳይችል በመቅረቱ ምክንያት ሰውየው የሚገጥመው እንግልት ምንዳውን ከፍ ያደርግለታል። ከርሱ በታች የሆነ እንግልት የደረሰበት ሰው ምንዳው ከርሱ ጋር አይመጣጠንም። ነገርግን ችግሩን ፈልጎ እየፈጠረው የሚንገላታ ሰው በምቾት ከሚጓጓዘው ጋር ምንም ልዩነት የለውም።

ወላሁ አዕለም!