የህመምተኛ ጾም፤ ብይኑ እና ጥበቡ

Home የፈትዋ ገጽ ዒባዳ ጾምና ኢዕቲካፍ የህመምተኛ ጾም፤ ብይኑ እና ጥበቡ

ጥያቄ፡- ባለቤቴ የደም ግፊት በሽታ ተጠቂ ናት። ቋሚ የሆነ የኩላሊት በሽታም አለባት። ሐኪሞች እንዳትጾም ቢመክሩም እርሷ ግን እምቢ ብላለች። በጾም ምክንያት አንዳንዴ ራሷን ትስታለች። ዲን በዚህ ጉዳይ ላይ ያለው እይታ ምንድን እንደሆነ ማወቅ እሻለሁ። ጀዛኩሙላሁ ኸይር።


መልስ፡- አላህ ህመምተኛ በረመዷን እንዲያፈጥር ፈቅዷል። አላህ ያዘዛቸው ግዴታዎቹ ሲፈፀሙ እንደሚደሰተው ሁሉ ፍቃዶቹና ማግራራቶቹ ሲከወኑለትም ይወዳል። ሊያገራልን እንጂ ሊያጠብቅብን አይሻም። ስለዚህ ክብርት ባለቤትህ ሐኪሞች- አደጋ ላይ እንዳትወድቅ ብለው እስከከለከሏት ድረስ- ማፍጠር ነው ያለባት።

በአዝሃር ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር ሙሐመድ ሰይድ አል-ሙሰዪር እንዲህ ይላሉ፡-

የአላህ ዲን ገር ነው። የአላህ ሸሪዓ ለሰው ልጅ ጥቅም የተደነገገ ነው። የአላህ ትዕዛዛት በሰው አቅም ላይ የተመሰረተ ነው። አላህ እንዲህ ይላል፡-

لَا يُكَلِّفُ اللَّهُ نَفْسًا إِلَّا وُسْعَهَا

አላህ ነፍስን ከችሎታዋ በላይ አያስገድዳትም፡፡ (አል-በቀራ 2፤ 286)

የአላህ መልእክተኛም (ሰ.ዐ.ወ.) እንዲህ ይላሉ፡-

ما نهيتكم عنه فاجتنبوه وما أمرتُكم به فأتوا منه ما استطعتم

“ያዘዝኳችሁን ነገር -የቻላችሁትን ያህል- ስሩ። የከለከልኳችሁን ነገር ራቁ።”

ጾም የተደነገገበት ሰበብ እና ጥበብ ሰዎችን ማስጨነቅ እና ማስቸገር አይደለም። የቁርኣንን አንቀጾች- ስለጾም በሚያወሩበት ስፍራ ላይ ካነበብናቸው ይህንን እውነታ ቁልጭ ብሎ እናገኘዋለን።

يُرِيدُ اللَّهُ بِكُمُ الْيُسْرَ وَلَا يُرِيدُ بِكُمُ الْعُسْرَ

“አላህ በእናንተ ገሩን (ነገር) ይሻል። በእናንተም ችግሩን አይሻም። (አል-በቀራ 2፤ 185)

ባለቤትህን ሙስሊም እና ባለሙያ የሆነ ታማኝ ሐኪም እንድታፈጥር እስከመከራት ድረስ፣ ጠያቂው እንደጠቀሰውም በጾም ተዳክማ ራሷን እስከመሳት የምትደርስ ከሆነች እንድታፈጥር እንመክራታለን። ማፍጠር እና ከጾም መታቀብ ግዴታዋም ነው። አላህ እንዲህ ይላል፡-

وَلَا تُلْقُوا بِأَيْدِيكُمْ إِلَى التَّهْلُكَةِ

“በእጆቻችሁም (ነፍሶቻችሁን) ወደ ጥፋት አትጣሉ።” (አል-በቀራ 2፤ 195)

ሁለት ምርጫ ብቻ ነው ያላት፡-

የሚቀጥለው ረመዷን ከመግባቱ በፊት ትድናለች ተብሎ የሚጠበቅ ህመም ከሆነ ያመለጧትን ቀናት አስባ ስትድን ቀዷ ትክፈለው። ህመሙ የማይድን ቋሚ ህመም ከሆነ ግን ለየቀኑ አንድ ሚስኪን በማብላት ቤዛ ትክፈል። የምታበላው መጠን አምስት መቶ ዘጠኝ (509) ግራም ነው። ወይም ይህንን በገንዘብ ተምና ትክፈል።

ሴትየዋ የሰው ኒያ ከሥራው እንደሚበልጥ ማወቅ አለባት። የኒያዋም ምንዳ አላህ ዘንድ ይቀመጥላታል። አላህ እንዲያሽራትም እንለምንላታለን።

አላሁ አዕለም!