ዐቂቃ ጥቅሙ አስፈላጊነቱና አደራረጉ እንዴት ነው?

Home የፈትዋ ገጽ ቤተሰብ ዐቂቃ ጥቅሙ አስፈላጊነቱና አደራረጉ እንዴት ነው?

ጥያቄ፡- የዐቂቃ ጥቅሙ ምንድነው? የዝግጅቱ አስፈላጊነትስ ምን ያህል ነው? ትክክለኛ አደራረጉስ በምን መልኩ ነው?


መልስ፡- “ዐቂቃ” ማለት ጥሬ ትርጉሙ “እራስ ላይ የሚገኝ የፊት ፀጉር” ማለት ነው። ልጅ ከተወለደ በኋላ የሚታረድ እንሠሣም ዐቂቃ ይባላል። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ “ኑሱኪያ” ወይንም “ዘቢሃ” (እርድ) ይሉታል። የዐቂቃ ዓላማው ለአላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ምስጋና ለማድረስ ነው። ይህም አንድ ሰው ልጅ ስለተወለደለት ደስታውን ለመግለፅ እና ይህንንም ልደት ሰዎች እንዲያውቁት ለማድረግ እና የተወለደውም ልጅ የማን እንደሆነ ለማሣወቅ ነው።

በዐረቢኛ “ዐቂቅ” የሚለው ቃል ለውድ ድንጋይ የተሠጠ ስያሜ እንደሆነም ይነገራል። በዚሁ መነሻነት ዐቂቃ ማለት የልጆችን ውድነት የሚያስገነዝበን ዝግጅት (በዓል) ነው ማለትም እንችላለን።

በአብዛኞቹ ሙስሊም ምሁራን እንዳሉት ዐቂቃ መደረግ ያለበት ትልቅ ሱና (ሱና ሙአከዳ) ነው። እንደ አንዳንድ ምሁራን ደግሞ ዐቂቃ ማድረግ ዋጅብ (ግዴታ) ነው። በላጩና የተመረጠው የዐቂቃ ማውጫ ጊዜም ልጅ በተወለደ በሰባተኛው ቀን ነው የሚሆነው። ወላጆች (እናትና አባት) አሊያም አያቶች ማለትም የወላጅ አባት እና እናት ለልጃቸው አሊያም ለልጅ ልጃቸው ዐቂቃ ማውጣት አለባቸው። በአንዳንድ ሀዲሦች ለወንድ ልጅ ሁለት በግ ለሴት ልጅ ደግሞ አንድ በግ መታረድ እንዳለበት የሚጠቅስ መጥቷል። ነገርግን ይህ እጅግ አስፈላጊ ላይሆን ይችላል። ምክኒያቱም አንድ ሰው ወንድ ልጅ ከተወለደለት አንድ በግ ማረድም ይችላል። ነቢያችን ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ለሀሰን እና ለሁሴን አንድ አንድ በግ ነው ያረዱት።

የታረደው እንሠሣ ሥጋው በዒድ አል-አድሃ በዓል እንደሚደረገው ሁሉ ሦስት ቦታ መከፈል አለበት። አንድ ሦስተኛው- ለድሃ፣ አንድ ሦስተኛው- ለጓደኞች እና አንድ ሦስተኛው ደግሞ ለቤተሰብ ይሠጣል። አንድ ሰው የታረደውን ሥጋ ሁሉንም ለድሆችና ችግረኛ ሰዎች መስጠት ይችላል።

ልጆች የአላህ ስጦታ ናቸው። እናም ይህን ታላቅ ፀጋ የሠጠንን አላህን ማመስገን ይኖርብናል። ልጆችንም ገና ከህፃንነታቸው ጀምሮ ልንንከባከባቸውና በኢስላማዊ አስተዳደግ እና ትምህርት ያድጉ ዘንድ ከፍተኛ ትኩረት ልናደርግላቸው ይገባል። ወላጆች ለልጆቻቸው ዓይነተኛ ምሣሌ መሆን ይኖርባቸዋል። ልጆቻቸው ትክክለኛ ነገር እየተማሩ ስለመሆናቸውና ትክክለኛ አስተማሪ እና ጓደኞች ይዘው እንደሆነም መከታተል ይኖርባቸዋል። ህፃናት እንደ ስፖንጅ ናቸው። የተሠጣቸውን ሁሉ ይቀበላሉ። ስለዚህም ትክክለኛውን ነገር ልንሠጣቸው ያስፈልጋል። ልጆች በቴሌቭዥን ስለሚያዩትና ስለሚከታተሉት ፊልምም መጠንቀቅ ይገባናል።

አላሁ አዕለም!