ውሃ እየጠጣሁ አዛን አለ

Home የፈትዋ ገጽ ዒባዳ ጾምና ኢዕቲካፍ ውሃ እየጠጣሁ አዛን አለ

ጥያቄ፡- “እያንዳንዳችሁ የውሀ እቃ በእጃችሁ ሆኖ (እየጠጣችሁ) አዛን ቢል የፍላጎታችሁን ሳትፈጽሙ አትተዉት።” የሚል ሐዲስ እንዳለ ሰምቻለሁ። የፈጅር አዛን መሀል አንድ ሙስሊም መብላቱን ባያቆም እንዴት ይታያል? ፆሙ ይበላሽ ይሆን?


መልስ፡- ቢስሚላሂ ርራህማን አልረሂም

ነገን እንደሚፆም የሚያስብ ሰው ፈጅር (ንጋት) ከመግባቱ በፊት ከመብላትና ከመጠጣት መታቀብ አለበት። ይህ የብዝሀ (ጁምሁር) ዑለሞች እምነት ነው። የተቀሰው ሐዲስ ደግሞ አቡ ዳዉድ የዘገቡት ነው። አንዳንዶች ሶሂህ (ትክክለኛ) ሐዲስ ነው ብለውታል። ነገር ግን ሐዲሱ ንጋት (ፈጅር) መውጣቱን የሚያውቅ ሰው መብላት እና መጠጣት ይችላል የሚል ትምህርት የለውም። ይህን የምንለው ሐዲስን በሐዲስ ተርጉመን ነው። ይህ ሐዲስ በቡኻሪና ሙስሊም ዘገባ በተገኘው ተከታዩ ሐዲስ ይገደባል። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

إن بلالا يؤذن بليل فكلوا واشربوا حتى يؤذن ابن مكتوم

“ቢላል በለሊት አዛን ያደርጋል። ኢብኑ ኡሙ መክቱም አዛን እስኪያደርግ ድረስ ብሉ ጠጡ።” (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)

የለሊት አዛኖች- በሱናው- ሁለት መሆናቸው እንዳይዘነጋ። የመጀመሪያው አዛን የሱብሂ (የንጋት) መግባትን አይጠቁምም። ሁለተኛው አዛን ግን የፈጅር ወቅት ይገባበታል። ስለዚህ በሁተኛው አዛን ጊዜ መብላትና መጠጣት ሐራም ነው ማለት ነው።

ስለዚህ ሙአዚን ለሱብህ ሶላት አዛን ሲያደርግ የሰማ ሰው ገና “አላሁ አክበር!” ከማለቱ አፉ ውስጥ ያለውን መዋጥም እንኳን ይከለከላል።

ዶክተር ሒሳም ዒፋና- በአልቁድስ ዩኒቨርሲቲ የፊቅህ መመህር- እንዲህ ይላሉ፡-

“የመፆም ጊዜው የሚገባው እውነተኛው ንጋት በመውጣቱ ነው። ማለትም የፈጅር ሶላት ጊዜ በመግባቱ ነው። አላህ እንዲህ አለ፡-

وَكُلُوا وَاشْرَبُوا حَتَّىٰ يَتَبَيَّنَ لَكُمُ الْخَيْطُ الْأَبْيَضُ مِنَ الْخَيْطِ الْأَسْوَدِ مِنَ الْفَجْرِ ثُمَّ أَتِمُّوا الصِّيَامَ إِلَى اللَّيْلِ
 

“ከጎህ የኾነው ነጩ ክርም ከጥቁሩ ክር (ከሌሊት ጨለማ) ለእናንተ እስከሚገልጽላችሁ ድረስ ብሉ፤ ጠጡም፡፡ ከዚያም ጾምን እስከ ሌሊቱ ድረስ ሙሉ።” (አል-በቀራህ 2፣ 187)

ፈጅር ከወጣ በኋላ መብላት እና መጠጣት ፆመኛ ላይ እርም ሆነ ማለት ነው። መታወቅ ያለበት (ሀገራችን ላይ ብዙ አካባቢዎች ላይ ባይሰራበትም) ሱብሂ ሁለት አዛኖች አሉት። የመጀመሪያው አዛን የሶላት ወቅት መግባቱን አይጠቁምም። ስለዚህ መፆም የሚፈልግ ሰው መብላትና መጠጣት ይችላል። ሁለተኛው አዛን ሲደረግ ግን ፆመኛ መብላትና መጠጣት ይከለከላል። የሶላት ወቅቱም እዚህ ላይ ይገባል። ይህንን የሚያስረዳ ሀዲስ ከዓብዱላህ ኢብኑ ዑመር (ረ.ዐ) ተዘግቦ እናገኛለን። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

إن بلالاً يؤذن بليل فكلوا واشربوا حتى يؤذن ابن أم مكتوم وكان رجلاً أعمى لا ينادي حتى يقال له : أصبحت أصبحت.

“ቢላል አዛን ያደርጋል። ኢብኑ ኡሙ መክቱም አዛን እስኪያደርግ ድረስ ብሉ፤ ጠጡ። እርሱ ማየት የተሳነው ሰው ነበር። ነግቷል ካላሉት አዛን አያደርግም።” (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)

ከዚህ በፊት ባለፉት ነጥቦች በመንተራስ ለሶላት አዛን በመደረጉ ብቻ መብላትና መጠጣት ሐራም ይሆናል ማለት ነው። ሙአዚኑ አዛን የሚያደርገው የሶላት ወቅት መግባቱን ለማሳወቅ እንደሆነ እርግጥ ከሆነ ማለት ነው። በሐገራችን በአሁኑ ሰዓት እየተለመደ የመጣው ደግሞ ብዙ ሙአዚኖች አዛን የሚያደርጉት በጥናት በተቀመጡ ሰዓቶች ነው። የጊዜ ልውውጥ ጥናት ላይ እውቀት ያላቸው ሰዎች የሰሩት ከሆነ በእነርሱ መስራት አስፈላጊ ነው።

ኢብኑል ቀዪም እንዲህ ብለዋል፡-

وذهب الجمهور إلى امتناع السحور بطلوع الفجر , وهو قول الأئمة الأربعة , وعامة فقهاء الأمصار , وروي معناه عن عمر وابن عباس رضي الله عنهم

“ብዝሃ ዑለሞች ሰሁር መብላት ልክ ንጋት ሲገባ መቆም እንዳለበት ያምናሉ። የአራቱም መዝሀቦችና ኢማሞቻቸው አቋምም ይኸው ነው። የተለያዩ ከተሞች ኢማሞች የተጓዙትም በዚሁ ነው። ከዓብዱላህ ኢብኑ ዑመርና ከኢብኑ ዓባስም ይኸው አቋም ተዘግቧል።” (ኢብኑል ቀዪም፤ ሸርሁ ሱነን አቢ ዳዉድ፤ ቅፅ 6፤ ገፅ 341)

በጥያቄው ላይ የተጠቀሰውን ሀዲስ ኢመም አህመድ፣ አቡ ዳዉድ፣ ሀኪም፣ በይሀቂይ እና ሌሎችም የሀዲስ መዛግብት አስፍረውታል። የሐዲሱ ሰነድ ደረጃም ሐሰን (መልካም) ነው።

ነገር ግን በሐዲሱ ለመናገር የተፈለገውን ነጥብ ኢማም አል-በይሀቂይ እንዲህ ያብራሩታል፡- “ይህ ሐዲስ እንደ ብዝሀ ዑለሞች -ትክክለኛ (ሶሂህ) ከሆነ- በዟሂሩ በጥቅል ትርጓሜው መጓዝ የምንችለው አዛኑ የፈጅር (ንጋት) ሶላት ወቅት ከመግባቱ በፊት የተደረገ ከሆነ ብቻ ነው። ማለትም ውሀውን የጠጣው ከፈጅር (ንጋት) ከመቅደዱ በፊት ከሆነ…”

አንዳንድ ዑለሞች ደግሞ ሐዲሱን ፈጅር መውጣቱን ለተጠራጠረ ሰው እንደሆነ ጠቁመዋል። ንጋት (ፈጅር) መቅደዱን የተጠራጠረ ሰው እንጂ እርግጠኛ የሆነ ሰው ፈጅር ከወጣ በኋላ ከበላና ከጠጣ ፆሙ የፈርሳል። ቀዷ ማውጣትም ግዴታ ይሆናል።

ታላቁ ዓሊም ዓሊይ አልቃር-ሪይ እንዲህ ብለዋል፡- “እያንዳንዳችሁ የውሀ እቃ በእጃችሁ ሆኖ (እየጠጣችሁ) አዛን ቢል የፍላጎታችሁን ሳትፈጽሙ አትተዉት።” የሚለው የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ንግግር ንጋት (ፈጅር) አለመውጣቱን ካወቀ ወይም ከተጠራጠረ ለማለት ነው።

ኢብኑል መሊክ እንዲህ ይላሉ፡- “በዚህ ሀዲስ የሚሠራው ፈጅር መውጣቱን ያላወቀ ሰው ብቻ ነው። ፈጅር መውጣቱን ያወቀና የተጠራጠረ ሰውማ እንዲህ ቢያደርግ ፆሙ ይበላሻል።” (ሚርቃቱል መፋቲህ፤ ቅፅ 4፤ ገፅ 483)

ለማጠቃለል፡- የተጠቀሰው ሀዲስ ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ተገኝቷል። በሐሰን ደረጃ ላይ ያለ መልካም ሀዲስ ነው። ነገር ግን ፆመኛ የሱብሂ ሶላት አዛን እየተደረገ መብላት እንዲችል የሚፈቅድ ሐዲስ አይደለም።

ፆመኛ ገና የአዛን ንግግሮችን አሊፍ ብሎ ሲሰማ አፉ ውስጥ ያለውን ምግብም ሆነ መጠጥ መዋጥ ይከለከላል።

አላህ የተሻለ ያውቃል!