ዉዱእ የማይቋጠርለት በሽተኛ ሶላት

Home የፈትዋ ገጽ ጣሃራ ዉዱእ የማይቋጠርለት በሽተኛ ሶላት

ጥያቄ፡- ሆዴ በጋዝ የተሞላ ነው። ከሆዴ የሚወጡ ጋዞች አይቋረጡም። በዚህ ችግር እጅግ በጣም እየተሰቃየሁ ነው። ሶላት መስገድም ያስቸግረኛል። ፈሴ ያለማቋረጥ ከሆዴ ስለሚወጣ ዉዱእ አይቆይልኝም። ፈፅሞ ዉዱእ ማቆየት አልችልም። ስለዚህ ምን ማድረግ አለብኝ?


መልስ፡- በቅድሚያ አላህ ጤና እንዲሰጥህ እንለምናለን።

ሶላት ያለዉዱእ ውድቅ እንደሆነ የታወቀ ነው። አካልን ከነጃሳ ንፁህ ማድረግና ዉዱእ ማድረግ የሶላት መስፈርት ነው። ከሁለቱ የተለመዱ መንገዶች በአንዱ የሚወጣ- ሽንት፣ ዓይነምድር፣ ፈስ ወይም ማንኛውም ነገር ዉዱእ ያፈርሳል።

ፈስ ያለማቋረጥ መውጣት እና በፈርድ ሶላት ወቅት በሙሉ በዚህ ሁኔታ ማሳለፍ ሰውየውን ያለዉዱእ ያቆየዋል። ይህ ደግሞ ሰውየውን ባለዑዝር (ባለሰበብ) ያደርገዋል።

ይህ ሰበብ ሰውየው ሶላቱን እና ዉዱኡን በድጋሚ ማድረግ ግዴታ እንዲሆንበት አያደርግም። ምክንያቱም በዚህ ሁኔታ ላይ ያለ ሰው ደጋግሞ ዉዱእ ያድርግ ማለት አስቸጋሪ ነው። አላህ ጉዳዩን አቅልሎልናል። እንዲህ ብሏል፡-

يُرِيدُ اللَّهُ بِكُمُ الْيُسْرَ وَلَا يُرِيدُ بِكُمُ الْعُسْرَ

“አላህ በእናንተ ገሩን (ነገር) ይሻል፡፡ በእናንተም ችግሩን አይሻም፡፡” (አል-በቀራ 2፤ 185)
አላህ በሌላ አንቀፅ ላይ እንዲህ ይላል፡-

فَاتَّقُوا اللَّهَ مَا اسْتَطَعْتُمْ

“አላህንም የቻላችሁትን የክል ፍሩት” (አት-ተጋቡን 64፤ 16)
የፊቅህ ሰዎች ከሚመረኮዙባቸው የፊቅህ መርሆች መሀል እንዲህ የሚል እናገኛለን፡-
(المشقة تجلب التيسير) – “ችግር ማግራራትን ያመጣል።”
በዚህ መርህ መሰረት የተቃኙ ብዙ ማግራራቶች እና ማቃለያዎች አሉ።

ስለዚህ ዑዝር ያለበት ሰውዬ ለፈርድ ሶላት አንድ ዉዱእ ማድረግ ይበቃዋል። ዉዱእ ሲያደርግ ሶላት እንዲፈቀድልኝ የሚል ኒያ ያደርጋል። ከሶላት የሚያግደው ነገር (ሐደስ) እንዲወገድልኝ ብሎ አይነይትም። ምክንያቱም እርሱ በቋሚነት ያለማቋረጥ ሶላት የሚያግድ ነገር እየተከሰተበት ነው። ለየሶላቱ ወቅቱ ከገባ በኋላ ዉዱእ ያደርጋል። ከዚህ በኋላ ከውስጡ የሚወጣው ነገር ችግር የለውም።

ይህ ከማሊኪዮች ውጪ የአብዝሃኞቹ ዑለሞች አቋም ነው። ማሊኪዮቹ ግን ለየሶላቱ ወቅቱ ከገባ በኋላ ዉዱእ ማድረግ ግዴታ አይደለም ብለው ያምናሉ። ዑዝር ከሆነበት ውጪ ዉዱእ የሚያስፈታ ሌላ ነገር እስካልተከሰተ ዉዱእ ማድረግ ይወደዳል እንጂ ግዴታ አይደለም። ስለዚህ ባለዑዝሩ ሰውዬ-ማሊኪዮች ዘንድ- ወቅት ከመግባቱ በፊት ዉዱእ ማድረግ ይችላል ማለት ነው። አብዝሃኞቹ ዑለሞች ግን ዉዱእ ማደስ ግዴታ ነው ብለው ያምናሉ።

የሽንት አለመቋረጥ፣ አጣዳፊ ተቅማጥ፣ የፈስ አለማቋረጥ እና መሰል ችግሮች ሰውየውን ባለዑዝር የሚያደርጉ የማይቋረጡ እንከኖች ናቸው። ስለዚህ ይህ ሰው በዉዱእ እና በተመሳሳይ አምልኮዎች ላይ በልዩ መመሪያዎች ይተዳደራል። ከለሎች ጤናማ ሰዎች የተለየ ብይንም ይኖረዋል።
ዑለሞች ባለ ዑዝርን የበሽታ ደም (ኢስተሃዳ) በማይቋረጥላት ሴት መስለውታል። ሐነፊዮች የበሽታ ደም ያለባት ሴት፣ ሽንት የማይቋረጥለት፣ አጣዳፊ ተቅማጥ ያለበት፣ ፈስ የማይቋረጥለት፣ የማይቆም ነስር ያለበት ወይም ደሙ የማይጠፍፍ ቁስል ያለበት ሰው ለየሶላቱ ዉዱእ ያደርጋል ይላሉ። ዉዱእ ማድረግ ያለበት ደግሞ የሶላቱ ወቅት ከገባ በኋላ እንደሆነም ይገልፃሉ። ምክንያቱም የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

الْمُسْتَحَاضَةِ أَنَّهَا تَتَوَضَّأُ لِكُلِّ صَلاَةٍ

“የበሽታ ደም ያለባት ሴት ለየሶላቱ ዉዱእ ታደርጋለች።” አቡዳዉድና ቲርሙዚይ ዘግበውታል። በዚህ መሰረት ዉዱእ ለመያዝ የሚቸገር ሰውም የበሽታ ደም ባለባት ሴት ይመሰላል።

እንደአብዝሃኞቹ ዑለሞች ባለዑዝሮች ለየሶላቱ ወቅቱ ከገባ በኋላ ዉዱእ ማድረግ አለባቸው። በዚህ ዉዱእ በወቅቱ ብዙ ፈርዶችን እና ሱናዎችን መስገድም ይችላሉ። የዚያ ፈርድ ሶላት ወቅት ሲወጣ ግን ዉዱኡ ይፈርሳል።

ሁለት መስፈርቶች ከተሟሉ ዉዱኡ በዚያ የፈርድ ሶላት ወቅት ሳይፈርስ ይቆያል።

1. ሰበቡ በተገኘበት ሁኔታ ዉዱእ ማድረግ አለበት
2. ዉዱእ የሚያፈርስ ሌላ ምክንያት አለመገኘት

የሐንበሊዮች ኪታብ በሆነው “አል-ኢንሷፍ” ላይ የበሽታ ደም ያለባትን ሴት አስመልክቶ እንዲህ የሚል ተገኝቷል፡- “ከዉዱእ በኋላ ደም የፈሰሳት ከሆነ ለየሶላት ወቅቱ ዉዱእ ታደርጋለች። ከዉዱእ በኋላ ምንም ካልፈሰሳት ግን በትክክለኛው-የመዝሃቡ አቋም መሰረት- ዉዱእ አታደርግም። አል-ሙግኒ፣ አሽ-ሸርሕ እና ሌሎችም መፅሀፍቶቻቸው ላይ- ኢማም ኢብኑ ቁዳማ- ይህን ሃሳብ ብቻ በመጥቀስ በዚህ ወስነዋል።

አል-ፉሩዕ ላይ ደግሞ ከሌሎች ሃሳቦች እርሱን አስቀድመዋል። የማይቋረጥ ሽንት ያለበትን ሰው ብይንም በዚህ መልኩ አብራርተዋል።
አል-ፉሩዕ ላይ- ኢብኑል-ሙፍሊሕ እንዲህ ይላሉ፡- “ደም ካልፈሰሳት ዉዱእ አታድስም። የማይቋረጥ ሽንት ያለበትን ሰውም በዚህ መልኩ አብራርተዋል። ምንም ነገር ባይፈሳትም ዉዱእ ማደስ ግዴታዋ ነውም ተብሏል። የጀመዓዎቹ ሃሳብም በገሃዱ ወደዚህ ይሄዳል።
ይህ ዉዱእ የሚያስፈታው ነገር ያለማቋረጥ የሚፈሰው ከሆነ ነው። እየመጣ የሚጠፋ ከሆነ ግን ሶላቱን ንፁህ በሆነበት ጊዜ መስገድ ግዴታ ይሆንበታል። በመጀመሪያው ወቅት ከሆነ ፈሳሹ (ወይም ዉዱእ የሚያፈርሰው ነገር) የሚጠፋው በፍጥነት ሶላቱን መስገድ ግዴታው ነው። በመጨረሻው ወቅት ከሆነ ደግሞ ሶላቱን ያዘገየዋል።”

የማሊኪዮች መፅሐፍ የሆነው ሐሺየቱስ-ሷዊይ ላይ እንዲህ የሚል ተገኝቷል፡- “ሽንት ያለማቋረጥ የሚፈስበት ጊዜ የሚታወቅ ከሆነ- ለምሳሌ ከዚህ በፊት ባለው ልምድ በሶላቱ ወቅት መጨረሻ መቋረጡ የተለመደ ከሆነ- ሶላቱን ማዘግየት ግዴታ ይሆንበታል። የመጀመሪያው ወቅት ላይ የሚቋረጥ ከሆነም እንደዚሁ በቅድሚያ ወቅቱ እንደገባ መስገድ አለበት። መድሃኒት ተጠቅሞ ሽንቱን ማቆም የሚችል ከሆነም መድሃኒቱን መጠቀም ግዴታ ነው። እስኪድን ድረስ ያለው ጊዜ ብቻ ይቅር ይባላል።”

ወላሁ አዕለም!