ካዕባ አጠገብ ያለው የሰይዲና ኢብራሂም (ዐ.ሰ.) መቃም ተብሎ የሚጠራው ስፍራ ላይ ያለው የእግር አሻራ

Home የፈትዋ ገጽ ሐጅና ዑምራ ካዕባ አጠገብ ያለው የሰይዲና ኢብራሂም (ዐ.ሰ.) መቃም ተብሎ የሚጠራው ስፍራ ላይ ያለው የእግር አሻራ

ጥያቄ፡- መቃሙ ኢብራሂም (የኢብራሂም የመቆሚያ ስፍራ) ተብሎ የሚጠራው ቦታ ላይ ያለው የእግር አሻራ የራሳቸው የኢብራሂም የእግር አሻራ ነው?


መልስ፡- መቃሙ ኢብራሂም የሚባለው ስፍራ የጥንታዊው ቤተ-መለኮት (አል-በይቱል-ዐቲቅ) መሰረት ከቆመበት ጊዜ ጀምሮ አላህ እስካሁን ጠብቆ ያቆየው የኢስላም ቅርስ ነው። ቦታው ውዱ የአላህ ነብይ- ኢብራሂም- ካዕባን ሲገነቡ የቆሙበት ድንጋይ ነው። አላህ እንዲህ ይላል፡-

وَإِذْ يَرْفَعُ إِبْرَاهِيمُ الْقَوَاعِدَ مِنَ الْبَيْتِ وَإِسْمَاعِيلُ رَبَّنَا تَقَبَّلْ مِنَّا إِنَّكَ أَنتَ السَّمِيعُ الْعَلِيمُ

“ኢብራሂምና ኢስማኢልም «ጌታችን ሆይ! ከእኛ ተቀበል። አንተ ሰሚውና ዐዋቂው አንተ ነህና» የሚሉ ሲኾኑ ከቤቱ መሠረቶቹን ከፍ ባደረጉ ጊዜ (አስታውስ)።” (አል-በቀራ 2፤ 127)

የአላህ ነብይ የኢብራሂም የእግር ምልክት በኢስላም የመጀመሪያዎቹ አመታት ላይ ነበር። ከዚያም ሰዎች አብዝተው ሲዳብሱት ምልክቱ ታብሷል። አሁን ያለው ምልክት የመጀመሪያው የእግር አሻራ አይደለም።

የሳዑዲ ዐረቢያ ታዋቂ ዑለሞች መሀል የሆኑት ሸይኽ ሙሐመድ ሷሊህ አል-ሙነጂድ እንዲህ ይላሉ፡-

“የኢብራሂም መቃም ማለት- አል-ቢዳያ ወን-ኒሃያ የተሰኘው መፅሀፍ ላይ እንደተጠቀሰው- ‘ኢብራሂም (ዐ.ሰ) የካዕባ ግንብ ከቁመታቸው በላይ የሆነ ጊዜ ይቆሙበት የነበረ ድንጋይ ነበር።  ግንቡ ሲያድግ በርሱ ላይ ቆመው እንዲገነቡት ልጃቸው ኢስማዒል ያስቀመጡላቸው ድንጋይ ነው። ከዚያም ይህ ድንጋይ ላይ የእግራቸው አሻራ ተቀርጾ ቀርቶ ነበር። ይህ አሻራም እስከመጀመሪያው የኢስላም ዘመን ድረስ እንዳለ ተቀምጦ ነበር።”

ኢማም ኢብኑ ሐጀር እንዲህ ይላሉ፡- “መቃሙ ኢብራሂም ማለት የነብዩላህ ኢብራሂም የእግር አሻራ የተቀረፀበት ድንጋይ ነው።”

ኢብኑ ከሲር እንዲህ ይላሉ፡- “የእግራቸው አሻራ በግልፅ ድንጋዩ ላይ ታትሞ ነበር። ይህም-በጃሂሊያ ዘመን- ዐረቦቹም ያውቁት ነበር። ሙስሊሞቹም ደርሰውበት አይተውታል። አነስ ቢን ማሊክ እንዲህ ብለው ገልፀውታል፡- መቃሙ ኢብራሂም ላይ የኢብራሂም (ዐ.ሰ) ጣቶች እና ተረከዝ ታትሞበት አይቻለሁ።”

ነገርግን ይህንን ዋና አሻራ የሰዎች መተሻሸት አጥፍቶታል።

ኢብኑ ጀሪር እንደዘገቡት ቀታዳ

  

وَاتَّخِذُوا مِن مَّقَامِ إِبْرَاهِيمَ مُصَلًّى

“ከኢብራሂምም መቆሚያ መስገጃን አድርጉ።”

የሚለውን አንቀፅ ሲተነትኑ እንዲህ ይላሉ፡- “የመቆሚያ ስፍራው አካባቢ እንዲሰግዱ ነው የታዘዙት። እንዲተሸሹት አልታዘዙም። ይህ ህዝብ ከርሱ በፊት የነበረው ህዝብ ያልታዘዘውን በመስራት ራሱን አስጨነቀ። የነብዩ ኢብራሂምን የእግር አሻራ የተመለከቱ ሰዎች የዚህ ኡመት ሰዎች ናቸው እየተሻሹ ምልክቱን ያጠፉት።” ከተፍሲር ኢብኑ ከሲር የተወሰደ።

ዕውቁ የሳዑዲ ዓሊም ሸይኽ ኢብኑ ዑሰይሚን እንዲህ ይላሉ፡- “የኢብራሂም መቃም የታወቀ ስፍራ ነው። አሁን በመስታወት ታጥቆ ከካዕባ አጠገብ ያለው ስፍራ መሆኑም የተረጋገጠ ነው። ነገርግን አሁን በድንጋዩ ላይ ያለው ምልክት የእግር ምልክት አይመስልም። ምክንያቱም በታሪክ እንደሚታወቀው ይህ ምልክት በድሮ ዘመን ነው የጠፋው። ነገርግን አሁን ያለው ምልክት ለምልክት የተቀመጠ ቅርፅ ነው። ስለዚህ ይህ ድንጋይ ላይ ያለው ስንጥቅጣቂ የነብዩ ኢብራሂም የእግር አሻራ ነው ብለን መወሰን አንችልም።”

ወላሁ አዕለም!