ከ120 ቀናት በኋላ ጽንስን ስለማስወረድ

Home የፈትዋ ገጽ ጤናና ህክምና ከ120 ቀናት በኋላ ጽንስን ስለማስወረድ

ጥያቄ፡- ካረገዝኩ ስድስት ወር ሆኖኛል። ጽንሱ ዕድገት የሚቀጥል ከሆነ ለሕይወቴ አስጊ መሆኑን ሐኪሞች ነግረውኛል። ይህንኑ የሚገልጽ የሐኪሞች ውሳኔ እንዲሠጠኝ አመልክቻለሁ። በዚህ ሁኔታ ላይ ጽንስን ማስወረድ አንዴት ይታያል?


መልስ:- ሙስሊም ምሁራን እንደተስማሙበት አንድ ጽንስ በእናቱ ሆድ ዉስጥ የ120 ቀን ዕድሜ ከሞላው (ሕይወት የሚነፋበት የጊዜ ርዝመት ነው) ጽንስን ማስወረድ አይቻልም። በዚህ ሁኔታ ላይ ጽንስን ማስወረድ ሙሉ በሙሉ የተከለከለ ነው። ምክንያቱም ያላግባብ እንዳትገድል አላህ እርም ያደረጋትን ነፍስ መግደል ነውና። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡-

وَلَا تَقْتُلُوا أَوْلَادَكُم مِّنْ إِمْلَاقٍ نَّحْنُ نَرْزُقُكُمْ وَإِيَّاهُمْ

“ልጆቻችሁንም ከድህንት (ፍራቻ) አትግደሉ። እኛ እናንተንም እነርሱንም እንመግባችኋለንና።” (አል-አንዓም 6፤151)

በሌላ የቁርኣን አንቀጽም እንዲህ ብሏል፡-

وَلَا تَقْتُلُوا النَّفْسَ الَّتِي حَرَّمَ اللَّهُ إِلَّا بِالْحَقِّ

“ያችን አላህ ያለግባብ አንዳትገደል እርም ያደረጋትን ነፍስ አትግደሉ።…” (አል-አስራእ 17፤33)

የጽንሱ ዕድሜ 120 ቀን (አራት ወር) ያልሞላው ከሆነ በማስጨንገፉ ጉዳይ ላይ በሙስሊም ምሁራን መካከል የተለያያ አቋም ተንፀባርቋል። አንዳንዶች ሐራም (ክልክል) ነው ያሉ ሲሆን ይህም የማሊኪያዎች መዝሀብ እና የዛሂሪያዎች አቋም ነው። ሌሎች ደግሞ እጅግ የተጠላ ነው ያሉ ሲሆን ከፊል የማሊኪ መዝሀብ ተከታዮች ይህንን አቋም አንፀባርቀዋል። ከአቅም በላይ በሆነ ችግር ምክንያት ይፈቀዳል ያሉት ደግሞ አንዳንድ የሐነፊያ እና የሻፊዒያ መዝሀብ ተከታዮች ናቸው።

በብይን በኩል ተመራጭ የሚመስለው ሸሪዓዉ በሚፈቅደው ከአቅም በላይ በሆነ ችግር ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ህይወት ከተነፋበት በኋላም ሆነ ሳይነፋበት በፊት ጽንስን ማስወረድ ክልክል ነው የሚለው ነው። ታማኝ እና ብቁ የሆነ ሐኪም የጽንሱ መቆየት በእናት ጤናም ሆነ ሕይወት ላይ አደጋ ያመጣል ብሎ ከወሰነ ያኔ ለእናት ሕይወት እና ለጤናዋ ሲባል ጽንሱን ማስጨንገፍ ይቻላል።

በመካ የሚገኘው የዓለም እስልምና ማህበር የኢስላማዊ ፊቅሂ ኮሚቴ (المجمع الفقهي الإسلامي لرابطة العالم الإسلامي/ Islamic Fiqh Council- Muslim World League) የሚከተለውን ውሳኔ አስተላልፏል፡-

“አንድ ጽንስ የ120 ቀናት ዕድሜ ከሞላው የሐኪም ማስረጃው አካሉ እክል እንዳለበት የሚገልጽ ቢሆን እንኳ በዘርፉ እውቅ በሆኑ ሐኪሞች አማካይነት የጽንሱ መቆየት በእናት ላይ ተጨባጭ የሆነ አደጋ ያስከትላል ብለው ካልወሰኑ በስተቀር ማስወረድ አይፈቀድም። የተረጋገጠ ከሆነ አካሉ ጤናማ ቢሆንም ባይሆንም ትልቁን አደጋ ለማስወገድ ሲባል ይፈቀዳል።”

በዚሁ መነሻነት የተጠየቀውን ጥያቄ ስንመልስ የሐኪም ውሳኔ የጽንሱ መቆየት በርግጠኝነት በእናት ጤና ላይ አደጋ ያስከትላል የሚል ከሆነ በዚህ ሁኔታ ላይ ማስወረዱ ይፈቀዳል። በሸሪዓ ምንም የሚከለክለው ነገር የለም። አላህ የተሻለ ያውቃል።