ከዘዋል (ፀሀይ ወደ ምዕራብ ከመዘንበሏ በፊት) ጠጠር ስለመወርወር

Home የፈትዋ ገጽ ሐጅና ዑምራ ከዘዋል (ፀሀይ ወደ ምዕራብ ከመዘንበሏ በፊት) ጠጠር ስለመወርወር

ጥያቄ፡- የሐጅ ስነስርዐት ላይ- በተለይም ጠጠር በሚወረወርበት ወቅት ከፍተኛ ግፊያ እናስተውላለን። የተሸሪቅ ቀናት ላይ ጠጠርን ፀሀይ ወደ ምዕራብ ከመዘንበሏ በፊት ጠጠር መወርወር እንችላለን?


መልስ፡- የዙልሒጃ ወር አስራ አንደኛው፣ አስራ ሁለተኛው እና አስራ ሶስተኛው ቀን ወይም የተሸሪቅ ቀናት ተብለው በሚጠሩት ቀናት ላይ ጠጠር መወርወር የሚገባው ፀሀይ ወደ ምዕራብ ካጋደለች በኋላ ነው። ነገርግን አንዳንድ ዑለሞች ከፍተኛ ግፊያ የሚፈጠር ከሆነ ከፀሀይ ወደ ምዕራብ ከማጋደሏ በፊት ጠጠር መወርወር እንደሚፈቀድ ተናግረዋል። ይህ ደግሞ ፈትዋ ሊከተለው የሚገባውን የማግራራት እና ለሰዎች የማቅለል ሂደትን የተከተለ ነው። በተለይም አንዳንድ ጊዜ ሰዎች በግፊያ ምክንያት የሚሞቱበት ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን እያስተዋልን ባለንበት በዚህ ወቅት ይህን ሃሳብ ማራመድ የተሻለ መሆኑ ጥርጥር የለውም። አላህ ሰዎች እንዲቸገሩ አይሻም። እንዲህ ይላል፡-

وَمَا جَعَلَ عَلَيْكُمْ فِي الدِّينِ مِنْ حَرَجٍ

“በናንተም ላይ በሃይማኖቱ ውስጥ ምንም ችግር አላደረገባችሁም።” (አል-ሃጅ 22፤ 78)

ስለዚህ ፀሀይ ወደ ምዕራብ ከመዘንበሏ አስቀድሞ ጠጠር መወርወር ችግር የለውም። ዶክተር ዩሱፍ አል-ቀረዳዊይ (አላህ ያቆያቸው) በርካታ ጊዜ ሐጃጆች ጠጠር መወርወሪያ ስፍራ ላይ በግፊያ ምክንያት በእግር ተረጋግጠው በርካታ ሰዎች የመሞታቸውን አሳዛኝ ክሰተት በማስታወስ እንዲህ ይላሉ፡-

“የአላህ መልእክተኛ ሐጅ ላይ የማግራራት ስራን ሰርተዋል። ምንም ነገር በቅድሚያ መሰራት የነበረበት ነገር ዘግይቶ ተሰርቶ ሲያዩ ‘ችግር የለም ሥራህን ቀጥል’ ይሉ እንደነበር ተዘግቧል። የፊቅህ ሰዎችም ጠጠር የመወርወር ጉዳይ ላይ አግራርተዋል። እንደውም አንዳንዶቹ የሦስቱን ቀን በመጨረሻው ቀን ላይ መወርወር እንደሚፈቀድ ገልፀዋል። ችግር ያጋጠመው ሰውም መወከል እንደሚችልም አሳውቀዋል። ጠጠር ውርወራ የሚከናወነው የመጨረሻዎቹ ከሐጅ መፈታትን ከሚያስገኙት ስራዎች በኋላ እንደመሆኑ የማቃለል እና የማግራራት ስራ ሊሰራበት የሚቻልበት ክፍተት ሰፊ ነው።

ፀሀይ ወደ ምዕራብ ከመዘንበሏ በፊት ጠጠር መወርወር እንደሚቻል ከገለፁት ዑለሞች መሀል ትልልቆቹ ኢማሞች ይገኙበታል። ታላቁ የሐጅና ዑምራ ልሂቅ ዐጧእ ኢብኑ አቢ ረባሕ፣ የየመኑ ልሂቅ ጧዉስ- ሁለቱም የዐብዱላህ ኢብኑ ዐባስ ተማሪዎች ናቸው- እና አቡ ጀዕፈር አል-ባቁር ሙሐመድ ቢን ዐሊይ ቢን አል-ሑሰይን የአህሉል-በይቶች ዐሊም ይገኙበታል።

እንደው ይህን የፈቀደ አንድም የፊቅህ ምሁር የለም ቢባል እንኳን የችግር ጊዜ ላይ ሊያዙ የሚገቡ ግንዘዛቤዎች ሃሳብ ያስቀይራሉ። ለአላህ ባሮች ማግራራት እንዳለብን ይጠቁማሉ። ሙስሊሞችን ለሞትና ለአደጋ ከማጋለጥ ይልቅ በሃያ አራት ሰዐት ውስጥ በፈለጉት ወቅት ጠጠር እንዲወረውሩ መፍቀድ አለብን።

ሸይኽ ዐብዱላህ ቢን ዘይድ አል-መሕሙድን አላህ በጎ ምንዳቸውን ይክፈላቸው። ከሠላሳ ዓመታት በፊት -‘ዩስሩል-ኢስላም’ በተሰኘው መፅሀፋቸው ውስጥ ፀሀይ ከመዘንበሏ በፊት ጠጠር መወርወር እንደሚቻል ፈትዋ ሰጥተዋል።”

በሶርያ እና በሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች የፊቅህ እና የኡሱል መምህር የሆኑት ኡስታዝ ዶክተር ሙስጦፋ አዝ-ዙረቃ ለዚህ መሰል ጥያቄ እንዲህ የሚል መልስ ሰጥተዋል፡-

“በብዙ ዑለሞች የጥናት ውጤት መሰረት ጠጠር መወርወር በአራቱ ቀናት ሁሉ ጠዋት ፀሀይ ወደ ምዕራብ ከማጋደሏ በፊት ጀምሮ ይደረጋል። የቸኮለ ሰው ለማሳጠር ብሎ ሚናን ከሚለቅበት ቀን- ከየውሙን-ነፍር- ውጪ ያሉት ቀናትም ቢሆኑ እንዲሁ ነው የሚታዩት። ምክንያቱም ፀሀይ ወደ ምዕራብ ከመዘንበሉ በፊት መወርወር ለሰዎች የገራው መንገድ ነው። ይህ ሚናን በችኮላ ጥሎ ለሚሄድ ሰው ከተፈቀደ ሚና የሚቆየውም ሰው ይኸው የማግራራት ሂደት ያስፈልገዋል። ምክንያቱም በሃይለኛው ሙቀት ውስጥ ከሚከሰተው ከፍተኛ ግፊያ እራሱን ማዳን ይችላል። እንደሚታወቀው አንድ በራሱ ጥናት ላይ ተሞርኩዞ ሃሳብ መስጠት የሚችልበት ደረጃ ላይ ያልደረሰ ግለሰብ ቀቡልነት ያላቸውን ዑለሞች ሃሳብ ብቻ ተሞርኩዞ መጓዝ ይችላል። አላህም ይህን ድርጊቱን ይቀበለዋል። ‘ዲን ገር ነው።’ ሐዲሱ እንዳለው።”

ስለዚህ ማብራሪያችንን እንደሚከተለው እንዘረዝራለን፡-

  1. የዙልሒጃ አስረኛው ቀን ጠጠር ውርወራ (ጀምረቱል-ዐቀባ) የመጀመሪያው የተሸሪቅ ቀን በሆነው የዒዱል-አድሐ ቀን ጧት ላይ ከፈጅር ሶላት ይጀምራል። ይህ ዑለሞች ዘንድ ልዩነት የለበትም። እንደውም ሻፊዒዮች ዘንድ ከዒድ ለሊት አጋማሽ ይጀምራል። ይህን ውርወራ የመጨረሻው የተሽሪቅ ቀን ፀሀይ እስከሚጠልቅ ድረስ ይዘልቃል። ይኸውም ከዒዱ ቀን ጀምሮ አራተኛው ቀን ነው። ሐጀኛው በቀንም ሆነ በማታ በፈለገው ወቅት ይወረውረዋል። ይህ- ሻፊዒዮች ዘንድ- በወቅቱ የተሰራ -አዳእ- ነው።

ሐነፊዮች ዘንድ ከመጀመሪያው የተሸሪቅ ቀን ፈጅር ጀምሮ እስከ ሁለተኛው ቀን ፈጅር ድረስ ይዘልቃል። ከመጀመሪያው  ቀን የዘዋል ወቅት አለማሳለፍ ግን በላጭ ነው። ፀሀይ እስከሚጠልቅ ድረስ ማቆየትም ችግር የለውም። ነገርግን ፀሀይ ከጠለቀ በኋላ ማዘግየት ይጠላል።

  1. ሦስቱን ጠጠር የመወርወሪያ ስፍራዎች ላይ መወርወር፡-

ከመጀመሪያው ቀን በኋላ ሦስቱ ጠጠር የመወርወሪያ ስፍራዎች ላይ መወርወር የሚከወነው በየቀናቱ ፀሀይ ወደ መግቢያዋ ከተዘነበለች በኋላ እስከሚቀጥለው ቀን ፈጅር ድረስ ነው፤ እንደ አብዝሃኞቹ ዑለሞች።

ሻፊዒዮቹ ዘንድ ግን በየቀናቱ ፀሀይ ወደ ምዕራብ ከተዘነበለች ጀምሮ የተሸሪቅ ቀናት የመጨረሻው ቀን ፀሀይ እስከምትጠልቅ ድረስ ይቆያል። ነገርግን የአንዱን ቀን ሳይወረውሩ ለቀጣዩ ቀን መወርወር አይፈቀድም።

ሐነፊዮች ዘንድ ደግሞ አራተኛው ቀን ከዒድ ቀናት ውስጥ ታሳቢ ነው። የውሙን-ነፍሪል-አኺር (የመጨረሻው ሚናን የመልቀቂያ ቀን) ይባላል። በዚህ ቀን ላይ ጠጠር መወርወር የሚጀምረው ከንጋት (ፈጅር) ጀምሮ ነው። ፀሀይ እስከምትጠልቅ ድረስም ይቆያል። ስለዚህ በዚህ ቀን የቸኮለ ሰው ፀሀይ ወደ ምዕራብ ከመዘንበሏ በፊት ወርውሮ ሚናን መልቀቅ ይችላል።

ኢስሐቅ እንዲህ ይላሉ፡- “የመጀመሪያው ሚናን የመልቀቂያ ቀን (የውሙን-ነፍሪል-አወል) ከተሸሪቅ ቀናቶች ሦስተኛው ነው። ይህ ቀን እንደ አራተኛው ቀን ሁሉ ጠጠር የመወርወሪያው ወቅት የሚገባበት ከፈጅር ነው። ይህም የሆነው ያን ቀን ሚናን ለቆ መሄድ ለሚፈልጉ ሰዎች ለማግራራት ነው።” – “ነይሉል-አውጧር” የተሰኘው የኢማም ሸውካኒይ መፅሀፍ ላይ ተጠቅሷል።

ሁለተኛው የዒድ ቀን ላይ ጠጠር የሚወረወርበት ወቅት የሚገባው- እንደ አብዝሃኞቹ ዑለሞች- ፀሀይ ወደ ምዕራብ ከተዘነበለች በኋላ ነው። ፀሀይ ወደ ምዕራብ ከመዘንበሏ በፊት መወርወር አይፈቀድም። ምክንያቱም ሐጀኛ ያን ቀን ሚናን ጥሎ መሄድ አይፈቀድለትም።

ነገርግን ይህን ሃሳብ -“ቢዳየቱል ሙጅተሂድ” ላይ እንደተጠቀሰው- ኢማም አል-ባቁር ሙሐመድ ቢን ዐሊይ ተቃውመዋል። “ነይሉል-አውጧር” ላይ እንደተጠቀሰውም ከታቢዒዮች ዐጧእ እና ጧዉስም ተመሳሳይ ሃሳብ አላቸው። እነዚህ ዐሊሞች በሙሉ እንዲህ ይላሉ፡- “ሁለተኛው የተሽሪቅ ቀን ላይም ጠጠር የመወርወሪያ ወቅቱ ከፈጅር ይጀምራል። ስለዚህ በማናቸውም ቀናት ፀሀይ ወደ ምዕራብ ከመዘንበሏ በፊት ጠጠር መወርወር ይፈቀዳል ማለት ነው።”

ከታወቀው አቋማቸው በነጠል- ሐነፊዮች ዘንድ ባለ ሌላ ሃሳብ መሰረትም- “ሁለቱም ቀናቶች ላይ በሁለተኛውም ሆነ በሦስተኛው ቀን ላይ ፀሀይ ወደ ምዕራብ ከመዘንበሏ በፊት ጠጠር መወርወር ይቻላል።”

አላሁ አዕለም!