ከሶሐባ ውጪ በሌሎች ሰዎች ላይ “ረዲየሏሁ ዐንሁ” ማለት ይቻላል?

Home የፈትዋ ገጽ ዚክርና ዱዓ ከሶሐባ ውጪ በሌሎች ሰዎች ላይ “ረዲየሏሁ ዐንሁ” ማለት ይቻላል?

ጥያቄ፡- የነብዩ ሶሐባዎች ወይም ከነርሱ ውጭ ያሉ ደግ ሰዎች ስም ሲነሳ “ረዲየላሁ ዐንሁ” (ከነርሱ የሆነን መልካም ነገር ይውደድላቸው) ማለት ይቻላል?


መልስ፡- ቢስሚላሂር-ረሕማኒር-ረሒም አል-ሐምዱሊል-ላሂ ረብ-ቢል ዓለሚን ወስ-ሶላት ወስ-ሰላም ዐላ ረሱሊላህ።

የአብዝሃኞቹ ዑለሞች እና የፊቅህ ሰዎች ተግባር ይህ ነገር እንደሚፈቀድ ያሳያል። “ረዲየላሁ ዐንሁ” የሚለውን ዱዓ ከሶሐባ ውጪ የሆኑ የሙስሊሙ ቀደምት ደጋግ ሰዎች ላይም ያደርጉታል። ለሸይኾቻቸው እና ሌሎች ደጋግ ሰዎች ላይም ይህንን ዱዐ ያደርጋሉ። መፅሀፎቻቸው እና ኹጥባዎቻቸው ይህንን ያመለክታሉ።

ቀደምት መፅሐፍትንም ሆነ ዘመናዊ መፅሐፍትን የሚያነብ ሰው ዑለሞች እና የፊቅህ ሰዎች ብዙ የዲን መሪዎች ላይ እና ደጋግ ሰወች ላይ ይህንን ዱዓ ሲጠቀሙ ማስተዋሉ አይቀርም። ለምሳሌ አራቱ የፊቅህ ኢማሞች ላይ፣ ታላላቅ የሰለፍ ዘመን ደጋግ ሰዎች ላይ፣ ታላላቅ የተሰዉፍ ባለሙያዎች ላይ እና ሌሎችም ደጋጎች ላይ ይኸው ዱዓ በዑለሞች እጅ አገልግሎት ላይ ውሏል።

የሸሪዓ ዕውቀቶች ተመራማሪ የሆኑት ኡስታዝ ወስፊ ዓሹር አቡ ዘይድ እንዲህ ይላሉ፡-

በቅድሚያ በሶሐባዎች ላይ “ረዲየሏሁ ዐንሁ” የሚለውን ቃል ሲጠቀሙ ተከታዮቹን ሁለት ትርጉሞች ለመጠቆም ይሹበታል፡-

አንደኛ፡- አላህ ከሶሐቦቹ እንደወደደ መግለፅ ተፈልጓል። ይህም በቁርኣን የተረጋገጠ ውዴታ በመሆኑ ምንም ችግር የለውም። አላህ እንዲህ ይላል፡-

وَالسَّابِقُونَ الْأَوَّلُونَ مِنَ الْمُهَاجِرِينَ وَالْأَنصَارِ وَالَّذِينَ اتَّبَعُوهُم بِإِحْسَانٍ رَّضِيَ اللَّهُ عَنْهُمْ وَرَضُوا عَنْهُ

“ከስደተኞቹና ከረዳቶቹም ሲኾኑ የመጀመሪያዎቹ ቀዳሚዎች እነዚያም በበጎ ሥራ የተከተሏቸው አላህ ከእነሱ ወዷል ከእርሱም ወደዋል።” (አት-ተውባ 9፤ 100)
ሁለተኛው፡- አላህ ከነርሱ የሆነን በጎ ነገር ሁሉ እንዲወድላቸው እና በመልካሙ እንዲቀበላቸው መለመን ይታሰብበታል።

“ረዲየላሁ ዐንሁ” ዱዓእን የሚያመለክት መልእክት ጠቋሚ ዐረፍተ ነገር ነው። ልክ “ሶል-ለ-ሏሁ ዐላ ሙሐመድ” እንደምንለው ማለት ነው። “አላህ ሆይ በሙሐመድ ላይ ሶለዋት አድርግ” ማለት ነው ትርጉሙ። ስለዚህ በዚህም ትርጉሙ ለሶሐቦቹ “ረዲየላሁ ዐንሁ” ብሎ ዱዓ ማድረግ ችግር የለውም። እንደውም በዚህ ትርጉሙ ሶሐባ ባይሆንም ለማንኛውም ሙስሊም ይህንን ዱዓ ማድረግ ችግር የለውም። ይህ አብዝሃኞቹ ዑለሞች የሄዱበት መንገድ ነው። ምክንያቱም አላህ እንዲህ ይላል፡-

لَّا تَجِدُ قَوْمًا يُؤْمِنُونَ بِاللَّهِ وَالْيَوْمِ الْآخِرِ يُوَادُّونَ مَنْ حَادَّ اللَّهَ وَرَسُولَهُ وَلَوْ كَانُوا آبَاءَهُمْ أَوْ أَبْنَاءَهُمْ أَوْ إِخْوَانَهُمْ أَوْ عَشِيرَتَهُمْ أُولَٰئِكَ كَتَبَ فِي قُلُوبِهِمُ الْإِيمَانَ وَأَيَّدَهُم بِرُوحٍ مِّنْهُ وَيُدْخِلُهُمْ جَنَّاتٍ تَجْرِي مِن تَحْتِهَا الْأَنْهَارُ خَالِدِينَ فِيهَا رَضِيَ اللَّهُ عَنْهُمْ وَرَضُوا عَنْهُ أُولَٰئِكَ حِزْبُ اللَّهِ أَلَا إِنَّ حِزْبَ اللَّهِ هُمُ الْمُفْلِحُونَ

“በአላህና በመጨረሻው ቀን የሚያምኑትን ሕዝቦች አላህንና መልክተኛውን የሚከራከሩትን ሰዎች፤ አባቶቻቸው፣ ወይም ልጆቻቸው፣ ወይም ወንድሞቻቸው፣ ወይም ዘመዶቻቸው ቢኾኑም እንኳ የሚወዳጁ ኾነው አታገኛቸውም። እነዚያ በልቦቻቸው ውስጥ እምነትን ጽፏል። ከእርሱም በኾነ መንፈስ ደግፏቸዋል። ከሥሮቻቸውም ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች በውስጣቸው ዘውታሪዎች ሲኾኑ ያገባቸዋል። አላህ ከእነርሱ ወዷል። ከእርሱም ወደዋል። እነዚያ የአላህ ሕዝቦች ናቸው። ንቁ! የአላህ ሕዝቦቸ እነርሱ ምኞታቸውን የሚያገኙ ናቸው።” (ለል-ሙጃዲላ 58፤ 22)

አላህ በሌላ አንቀፅም እንዲህ ይላል፡-

إِنَّ الَّذِينَ آمَنُوا وَعَمِلُوا الصَّالِحَاتِ أُولَٰئِكَ هُمْ خَيْرُ الْبَرِيَّةِ * جَزَاؤُهُمْ عِندَ رَبِّهِمْ جَنَّاتُ عَدْنٍ تَجْرِي مِن تَحْتِهَا الْأَنْهَارُ خَالِدِينَ فِيهَا أَبَدًا رَّضِيَ اللَّهُ عَنْهُمْ وَرَضُوا عَنْهُ ذَٰلِكَ لِمَنْ خَشِيَ رَبَّهُ

“እነዚያ ያመኑትና መልካሞችንም የሠሩት፣ እነዚያ እነርሱ ከፍጥረት ሁሉ በላጭ ናቸው። በጌታቸው ዘንድ ምንዳቸው ከሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸው የመኖሪያ ገነቶች ነው። በውስጣቸው ዘለዓለም ዘውታሪዎች ሲኾኑ (ይገቡባቸወል)። አላህ ከእነርሱ ወደደ። ከእርሱም ወደዱ። ይህ ጌታውን ለፈራ ሰው ነው።” (ለል-በዪና 98፤ 7-8)

የአብዝሃኞቹ ዑለሞች አካሄድ ይህንን ያሳያል። “ረዲየላሁ ዐንሁ” የሚለውን ቃል ከሶሐባ ውጪ ለሌሎች ሰለፎች፣ ሸይኾቻቸው እና ለደጋግ ሰዎች ይጠቀሙታል።

የሐነፊዮች የፊቅህ ሊቅ የነበሩት አል-ሐስከፊይ እንዲህ ይላሉ፡- “ለሶሐቦቹ፣ እንደ ዙልቀርነይን እና ሉቅማን ያሉ ነብይነታቸው ላይ እርግጠኛ ያልሆንባቸው ደጋግ ሰዎች ላይ ‘ረዲየላሁ ዐንሁ’ ማለት ይወደዳል። የሶሐባን ዘመን ተከትለው የመጡ ዑለሞች እና ምርጦች ላይ ደግሞ ‘ረሒመሁላህ’ (አላህ ይዘንላቸው) ማለት ተወዳጅ ነው። ተቃራኒውም ይቻላል። ለሶሐቦቹ ‘ሪሒመሁላህ’ ለሌሎቹ ‘ረዲየላሁ ዐንሁ’ ማለትም ችግር የለውም። ይህ አል-ቀርማኒይ የመረጡት የተሻለው አቋም ነው። አል-ዘይለዒይ እንዲህ ይላሉ፡- የተሻለው ለሶሐቦቹ ‘ረዲየላሁ ዐንሁ’፣ ለታቢዖች ደግሞ ‘ረሒመሁላህ’ ማለት፣ ከታቢዖች በኋላ ላሉ ሰዎች ደግሞ ‘ገፈረላሁ ለሁ’ (አላህ ይማረው) ወይም ‘ተጃወዘላሁ ዐንሁ’ (አላህ ይቅር ይበለው) የተሻለ ነው።” (አድ-ዱር-ሩል-ሙኽታር፣ ቅፅ 6፣ ገፅ 754)

የማሊኪዮች የፊቅህ ልሂቅ የሆኑት አን-ነፍራዊይ አንዳንድ ዓሊሞችን ጠቅሰው እንዲህ ይላሉ፡- “በሶሐባም ሆነ ከነርሱ በኋላ በመጡ ደጋግ ሰዎች ላይ ‘ረዲየላሁ ዐንሁ’ ወይም ‘ረሒመሁላህ’ ማለት ይቻላል። ‘ረዲየላሁ ዐንሁ’ በሶሐቦቹ ላይ አይገደብም። ‘ረሒመሁላሁ’ የሚለው ዱዓም ከሶሐቦቹ ውጭ ባሉ ሰዎች ላይ አይታጠርም። አንዳንዶች ተቃራኒ ሃሳብ ቢኖራቸውም ልክ አይደሉም።”

የሻፊዒዮቹ ምሁር ኢማም አን-ነወዊይ እንዲህ ብለዋል፡- “በሶሐቦቹ፣ በታቢዖች እና እነርሱን ተከትለው የመጡ ዑለሞች እና ታላላቅ የዒባዳ ሰዎች እና ምርጦች ላይ ‘ረዲየላሁ ዐንሁ’ ወይም ‘ረሒመሁላህ’ ወይም ‘ረሕመቱላሂ ዐለይሂ’ የሚሉትን ዱዓዎች ማድረግ ይወደዳል። አንዳድ ዑለሞች ‘ረዲየላሁ ዐንሁ’ የሚለው ዱዓ በሶሐቦች ብቻ የተገደበ ነው፤ ከበስተኋላቸው የመጡ ሰዎች ላይ ‘ረሒመሁላህ’ ብቻ ነው የሚባለው ማለታቸው ስህተት ነው። አንቀበላቸውም። ትክክለኛው- እና ብዙ ዑለሞች የተጓዙበት መንገድ- ለሌሎቹም ‘ረዲየላሁ ዐንሁ’ ማለት የተወደደ መሆኑ ነው። ማስረጃዎቹም እጅግ የበዙ የማያልቁ ናቸው።” (አል-መጅሙዕ፣ ቅፅ 6፣ ገፅ 156 – 157)

ቀደምት መፅሐፍትንም ሆነ ዘመናዊ መፅሐፍትን የሚያነብ ሰው ዑለሞች እና የፊቅህ ሰዎች ብዙ የዲን መሪዎች ላይ እና ደጋግ ሰወች ላይ ይህንን ዱዓ ሲጠቀሙ ማስተዋሉ አይቀርም። ለምሳሌ አራቱ የፊቅህ ኢማሞች ላይ፣ ታላላቅ የሰለፍ ዘመን ደጋግ ሰዎች ላይ፣ ታላላቅ የተሰዉፍ ባለሙያዎች ላይ እና ሌሎችም ደጋጎች ላይ ይኸው ዱዓ በዑለሞች እጅ አገልግሎት ላይ ውሏል። ነገርግን ዱዓን በሚያመለክተው ትርጉሙ ታስቦ ነው።

ሰውየው “ረዲየላሁ ዐንሁ” የሚለው ከላይ በጠቀስነው በአንደኛው ትርጉም አስቦት- ዱዓ ሳይሆን አላህ እንደወደደለት ለመግለፅ ከሆነ- ከሶሐባ ውጪ ሌላ ሰው ላይ አይፈቀድም። ምክንያቱም ሶሐቦቹ አላህ እንደወደደላቸው የተነገረላቸው ናቸው። ከነርሱ ውጪ ያሉ ሰዎች ግን እንዲህ ዓይነት መለኮታዊ ሙገሳን እንዳገኙ አላህ አልተናገረላቸውም። ስለዚህ ሰውየው እነርሱ የአላህ ውዴታን ስለማግኘታቸው ማውራት አይችልም። ምክንያቱም የማያውቀው ነገር ስለሆነ።

ታላቁ ዓሊም ሸይኽ ዐጢያ ሰቀር- የቀድሞው የአል-አዝሃር የፈትዋ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት- እንዲህ ይላሉ፡-

“ረዲየላሁ ዐንሁ” (አላህ ከርሱ ወደደ) የሚለው ንግግር አንድን ሰው አላህ እንዲወደው እና ያበረከታቸውን ታላላቅ ተግባራት እንዲቀበለው ለመለመን የሚደረግ ዱዓ ነው። መልእክት ገላጭ አረፍተ ነገር (ጁምላ ኸበሪያ) ቢሆንም ዱዓንም ይጠቁማል። ልክ “አላህ ሆይ እገሌ ባርያህን ውደድ፤ የሰራውን በጎ ተግባር ተቀበለው” እንደማለት ነው። ልክ “ሶል-ለ-ሏሁ ዐላ ሙሐመድ” (አላህ በሙሐመድ ላይ ሰለዋት አደረገ) እንደምንለው ማለት ነው። “አላህ ሆይ! በሙሐመድ ላይ ሶለዋት አድርግ” ማለት ነው ትርጉሙ።

አል-አዝካር የተሰኘው መፅሐፍ ገፅ 121 ላይ ነወዊይ እንዲህ ብለዋል፡-

በሶሐቦቹ፣ በታቢዖች እና እነርሱን ተከትለው የመጡ ዑለሞች እና ታላላቅ የዒባዳ ሰዎች እና ምርጦች ላይ ‘ረዲየላሁ ዐንሁ’ ወይም ‘ረሒመሁላህ’ ወይም ‘ረሕመቱላሂ ዐለይሂ’ የሚሉትን ዱዓዎች ማድረግ ይወደዳል። አንዳድ ዑለሞች ‘ረዲየላሁ ዐንሁ’ የሚለው ዱዓ በሶሐቦች ብቻ የተገደበ ነው፤ ከበስተኋላቸው የመጡ ሰዎች ላይ ‘ረሒመሁላህ’ ብቻ ነው የሚባለው ማለታቸው ስህተት ነው። አንቀበላቸውም። ትክክለኛው- እና ብዙ ዑለሞች የተጓዙበት መንገድ- ለሌሎቹም ‘ረዲየላሁ ዐንሁ’ ማለት የተወደደ መሆኑ ነው። ማስረጃዎቹም እጅግ የበዙ የማያልቁ ናቸው።

የተጠቀሰው ሶሐባ- እንደ የዑመር ልጅ ዐብዱላህ፣ እንደ የዐባስ ልጅ ዐብዱላህ፣ እንደ ዙበይር ልጅ ዐብዱላህ፣ እንደ ኡሳማ ቢን ዘይድ- የሶሓባ ልጅ ከሆነ “ረዲየላሁ ዐንሁማ” (ከሁለቱም የሆነን መልካም ሥራ አላህ ይውደድ) ይባላል። የተጠቀሰውን ሶሐባ እስከአባቱ በዱዓ ለመጠቅለል ሲባል።

ሉቅማን እና መርየም ሲጠቀሱ እንደነብያት ሶለዋት ነው የሚደረገው? ወይስ እንደ ሶሐቦቹ እና እንደታላላቅ ሰዎች “ረዲየላሁ ዐንሁ” ይባላል? ወይስ ለወንድ “ዐለይሂስ-ሰላም” ለሴት “ዐለይሃስ-ሰላም” ይባላል? የሚሉ ጥያቄዎች ቢነሱ እንደሚከተለው እንመልሳለን።

አብዝሃኞቹ ዑለሞች እነዚህ ነብያት እንዳልሆኑ አረጋግጠዋል። ነብያት ናቸው ያሉ ሰዎች ተሳስተዋል። ንግግራቸውን ከምንም አንቆጥረውም። አንደገፈውም።

ይህ ከታወቀ ከአንዳንድ ዑለሞች ንግግር እንደምንረዳው “የሉቅማን ወይም የመርየም ስም ሲነሳ ‘ሶል-ለላሁ ዐለል-አንቢያእ ወዐለይሂ (ለወንድ ሲሆን) ወይም ወዐለይሃ (ለሴት ሲሆን) ወሰል-ለም’ ይባላል።” ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ከሶሐባ ደረጃ ከፍ ብለዋል። ምክንያቱም በቁርኣን ውስጥ ትልቅነታቸው ተጠቅሷል።

በእኔ እምነት ግን ይህ ችግር የለውም። የተሻለው ግን ለነርሱም ቢሆን “ረዲየላሁ ዐንሁ” ማለት ነው። ምክንያቱም ይህ ደረጃ ከነብያት ደረጃ ያነሰ ነው። ነብያት መሆናቸው እስካልተረጋገጠ ድረስ የነብይነት ደረጃ ካልተሰጣቸው ሰዎች ጋር ነው በአንድነት መታየት ያለባቸው። በእርግጥም ኢማሙል-ሐረመይን መርየም ነብይ ላለመሆኗ የዑለሞች ስምምነት እንዳለ “አል-ኢርሻድ” የተሰኘው መፅሐፋቸው ላይ ጠቅሰዋል። ነገርግን ለወንድ “ዐለይሂስ-ሰላም” ለሴት “ዐለይሃስ-ሰላም” ቢባልም ችግር የለውም ማለት የተሻለ ነው። ወላሁ አዕለም!” እዚህ ድረስ የኢማም ነወዊይ ንግግር ነበር። ማብራሪያቸው በቂ ነው።

አላህ የተሻለ ያውቃል!