ከሴት ልጅ ብልት የሚወጣ ፈሳሽ ብይን

Home የፈትዋ ገጽ ጣሃራ ከሴት ልጅ ብልት የሚወጣ ፈሳሽ ብይን

ጥያቄ:- በእርግዝና ወራትም ሆነ በሌላ ጊዜ አንዳንድ ጊዜ ከሴት ልጅ ማህፀን የሚወጣ ፈሳሽ ብይኑ ምንድነው? ነጃሳ ነውን? ዉዱእ ማድረግን ያስገድዳልን?


መልስ:- ሴት ልጅ በንጽሕና ጊዜያት አሊያም በእርግዝና ወቅት ልጅ በሚወጣበት በኩል የሚፈሳት ፈሳሽ ጠሃራ (ንፁህ) ነው። ደም የተቀላቀለበት ካልሆነ በስተቀር። ዉዱእ ያበላሻል የሚል ማስረጃም የለም። በሽንት መውጫ በኩል የሚወጣው ፈሳሽ ግን ከሽንት መጣራቀሚያ ፊኛ ጋር የተገናኘ በመሆኑ የሽንትን ድንጋጌ ይይዛል። እንደ ሽንት ሁሉ ነጅስ ነው ማለት ነው። እንዲሁም ዉዱእ ያበላሻል። በሁለቱ መውጫ ቀዳዳ በኩል (በሰገራና በሽንት መውጫ) በኩል የሚወጣው ፈሳሽ ዉዱእ እንደሚያበላሽ ይታወቃልና።

በኩዌት የኢስላማዊ ቅርስ ጥበቃ ኮሚቴ የፈትዋ ድርጅት አባል የሆኑት ሸይኽ ሙሐመድ ኢብን ሐመድ አል-ሐሙድ እንዲህ ይላሉ፡-

ከሴት ልጅ የሚወጣ ፈሳሽ ሁለት መውጫዎች አሉት።

  1. የልጅ መውጫ ሲሆን ከማህፀን ጋር የተያያዘው ነው።
  2. የሽንት መውጫ ሲሆን የሽንት ፊኛ ጋር የተያያዘ ነው እሱም ነጅስ ነው።

በልጅ መውጫ (በማህፀን) በኩል የሚወጣው ፈሳሽ ትክክለኛ ብያኔው ጠሃራ (ንፁህ) እንደሆነ ነው። ደም ካልተቀላቀለበት በስተቀር። ኢብኑ ቁዳምም “አልሙግኒ” በተሠኘው መጽሐፋቸው ዉስጥ ይህንኑ ብይን መርጠዋል።

በሐዲሥ እንደተረጋገጠው ዓኢሻ (ረ.ዐ) ከነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ልብስ ላይ መንይ (የዘር ፈሳሽ) ትፈገፍግ ነበር። የዘር ፈሳሹ ሊታይ የሚችለው ከግብረሥጋ ግንኙነት በኋላ የታየ ነው። ምክንያቱም ነቢያት በህልማቸው የዘር ፈሳሽ አያፈሱምና። ስለሆነም መኒይ (ዘር ፈሳሽ) ደግሞ ከሴት ልጅ ብልት እርጥበት ጋር የተገናኘ ስለመሆኑ እሙን ነው።

ይህ የተጠቀሰው ጉዳይ በግልጽ የሚታይ ነገር ነው። በግብረሥጋ ግንኙነት ጊዜ ጭምር ከሴት ልጅ ብልት የሚወጣው እርጥበት ነጂስ አለመሆኑን ያመላክታል። ቢሆን ኖሮ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ከምትፈገፍገው እንድታጥበው ዓኢሻን (ረ.ዐ) ያዟት ነበር።

ይህ ጉዳይ እጅግ ለመከላከል አስቸጋሪ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው። ነጂስ ቢሆን ኖሮ ነቢዩም (ሰ.ዐ.ወ) ግልጽ ባደረጉ ነበር። ነጂስ ቢባል ደግሞ በወንድም ሆነ በሴት ላይ የሚያመጣው ጣጣ እጅግ ከባድ ይሆን ነበር። በዚህ ገር በሆነው የእስልምና ሃይማኖት ዉስጥ አስቸጋሪ ነገር አልተደነገገም።

ጠሃራ ነው (ነጂስ አይደለም) ያሉት ብዙሃኑ ሙስሊም ምሁራን ናቸው። ሐነፊያዎችም ይህንኑ ብለዋል (ሓሺየት ኢብን ዓቢዲን 1/349 ይመልከቱ)። ሻፊዒያዎች ደግሞ ከነርሱ የተገኘ ሁለት አባባል አላቸው። ከኢማም ነስር፣ አን-ነወዊ እና ከራፊዒ በተገኘው ዘገባ ጠሃራ ነው ተብሏል (አል-መጅሙዕ 2/571-572 ይመልከቱ)። ሐናቢላዎች ደግሞ ከዚህ ቀደም ባሳለፍነው የኢብን ቁዳማ አባባል ላይ አቋማቸውን አይተናል። ኢብን ሙፍሊሕም በ “አል-ፉሩዕ” (1/248) እንደዚሁም አል-በሁቲ “ሸርህ ሙንተሃ አል-ኢራዳት” (1/301) ዉስጥ ወደዚሁ ሀሳብ አዘንብለዋል። ሸይኽ ሙሐመድ ኢብን ዑሠይሚን ሸርሕ አል-ሙምቲዕ (1/390-392) ውስጥ ይህንኑ ደግፈዋል።

በብልት መርጠብ አሊያም ከብልት በሚወጣ ፈሳሽ ምክንያት የዉዱእ መበላሸት አለመበላሸት ድንጋጌ

በሽንት መውጫ በኩል የሚወጣው ፈሳሽ ዉዱእን ያበላሻል። ምክንያቱም ከሁለቱ ዉዱእን ከሚያበላሹ መውጫ መንገዶች በአንዱ ነውና የወጣው። ድንጋጌውም እንደ ሽንት ነው። ሆኖም ግን በንጽህና ጊዜያት አሊያም በእርግዝና ወቅት በልጅ መውጫ በኩል የሚወጣው ፈሳሽ ዉዱእ ያበላሻል የሚል ማስረጃ የለም።

ኢብን ሐዝም “አል-መሐሊ” በተሠኘው መጽሐፋቸው ዉስጥ እንዲህ ብለዋል፡-

“ከጠቀስነው ነገር ዉጭ ዉዱእ የሚያበላሽ የለም። ትውከት ይሁን ከሰውነት፣ ከጎሮሮ አሊያም ከጥርስ የሚወጣ ፈሳሽ የሆነ ደም አያበላሽም። ከሴት ልጅ ብልት የሚወጣ ነጭ ፈሳሽ፣ ብጫም ሆነ ድፍርስ አሊያም ደም መሰል ነገርም እንዲሁ።”

አክለውም “ዉዱእ አያበላሽም ማለታችን በቁርኣን እና በሐዲሥ እንዲሁም በሙስሊም ዑለሞች ስምምነት ዉስጥ እነኚህ ነገሮች ዉዱእ ያበላሻሉ የሚል ነገር ባለመምጣቱ ነው።”

ዉዱእ እንደማያበላሽ አቋም ከያዙት መካከል የማሊኪ መዝሀብ ተከታይ የሆኑት አቡ አልወሊድ ኢብን ሩሽድ አዝ-ዘኺራ በተሠኘው የአልቀራፊ መጽሐፍ ዉስጥ ገልፀዋል።

ይህንኑ ከሚያጠናክሩ ዘገባዎች መካከል የኡሙ ዐጢያ ሐዲሥ ይገኝበታል። እንዲህ ትላለች “ኩድራንም ሆነ ሱፍራውን ፈሳሽ ከምንም አንቆጥርም ነበር።” ብላለች (ቡኻሪ ዘግበውታል)። አቡ ዳዉድ ደግሞ “ከፀዳን በኋላ ከምንም አንቆጥርም” የሚለውን ሀረግ ጨምረዋል።

ኩድራ:- ወደ ጥቁረት የሚያደላ ፈሳሽ ሲሆን፤

ሱፍራ:- ደግሞ ሴት ልጅ መግል/እዥ በሚመስል መልኩ የሚወጣት ወደ ቢጫነት የሚያደላ ፈሳሽ ነው።

በዚሁ መነሻነት ሚዛን የሚደፋው አቋም ዉዱእ የማያበላሽ መሆኑ ነው። ሆኖምግን ሴት ልጅ ለጥንቃቄ ብላ ዉዱእ ያበላሻል የሚሉትን ዑለሞች አቋም ብትይዝ ችግር የለውም። አላህ ከሁሉ በላይ አዋቂ ነው።