ከሦስቱ መስጂዶች ውጭ ኢዕቲካፍ ማድረግ ይቻላል?

Home የፈትዋ ገጽ ዒባዳ ጾምና ኢዕቲካፍ ከሦስቱ መስጂዶች ውጭ ኢዕቲካፍ ማድረግ ይቻላል?

ጥያቄ፡- ከሦስቱ መስጂዶች ውጭ በሌሎች መስጂዶች ውስጥ ኢዕቲካፍ ማድረግ ይቻላል? ምንድን ነው ማስረጃው?


መልስ፡- ቢስሚላሂር-ረሕማኒር-ረሒም አል-ሐምዱሊል-ላሂ ረብ-ቢል ዓለሚን ወስ-ሶላት ወስ-ሰላም ዐላ ረሱሊላህ

ከሦስቱ መስጂዶች- ከመካው የሐረም መስጂድ፣ ከመዲናው የነብዩ መስጂድ እና ከአል-አቅሷ መስጂድ- ውጪ በሌሎች መስጂዶች ውስጥ ኢዕቲካፍ ማድረግ ይቻላል። ምክንያቱም ይህን የሚያስረዱ ጥቅል የሐዲስ እና የቁርኣን መረጃዎች ተገኝተዋል። ሦስቱን መስጂዶች ለይተው የመጡ የሐዲስ ዘገባዎች በላጭነታቸውን ለመጠቆም የመጡ ናቸው እንጂ ሌሎች መስጂዶች ውስጥ ኢዕቲካፍ ማድረግ አይቻልም የሚል መልእክት የላቸውም።

ሼኽ ዑሰይሚን እንዲህ ይላሉ፡-

ከሦስቱ መስጂዶች ውጪ ኢዕቲካፍ ማድረግ ይፈቀዳል። ማስረጃችንም ተከታዩ የአላህ ንግግር ነው፡-

وَلَا تُبَاشِرُوهُنَّ وَأَنتُمْ عَاكِفُونَ فِي الْمَسَاجِدِ

“እናንተም በመስጊዶች ተቀማጮች ስትኾኑ አትገናኙዋቸው፡፡” (አል-በቀራ 2፤ 187)

ይች አንቀፅ ሙስሊሞችን በሙሉ የምታናግር አንቀፅ ናት። መስጂዶቹ ሦስቱ መስጂዶች ብቻ ናቸው ካልን ግን አብዝሃኛዎቹ ሙሰሊሞች ይች አንቀፅ አታናግራቸውም ማለት ነው። ምክንያቱም አብዝሃኞቹ ሙስሊሞች ከመካ፣ ከመዲና እና ከአል-አቅሷ ውጭ ነው የሚኖሩት።

በዚህ መሰረት እንዲህ እንላለን፡- ኢዕቲካፍ በሁሉም መስጂዶች ውስጥ ይፈቀዳል።

ከአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ተከታዩ ተዘግቧል፡-

لا اعتكاف إلا في المساجد الثلاثة

“ከሦስቱ መስጂዶች ውጪ ኢዕቲካፍ የለም።”

ይህ ሐዲስ ሶሒሕ ከሆነ ትርጉሙ “የተሟላ እና በላጭ ኢዕቲካፍ” በሚል መንፈስ መታጠር አለበት። በሦስቱ መስጂዶች ውስጥ የሚሰገድ ሶላት በሌሎች መስጂዶች ከሚሰገደው እንደሚበልጥ ሁሉ በውስጣቸው የሚደረግ ኢዕቲካፍም በሌሎች መስጂዶች እንደሚበልጥ ጥርጥር የለውም።
በመስጂዱል-ሐረም ውስጥ የሚሰገድ ሶላት ከሌላው በመቶ ሺህ ይበልጣል። በነብዩ መስጂድ ውስጥ የሚሰገድ ሶላት ከሐረም ውጪ ከሌላው መስጂድ በአንድ ሺህ ይበልጣል። መስጂዱል-አቅሷ ውስጥ የሚሰገድ ሶላት በሌላ ቦታ ከሚሰገድ ሶላት በአምስት መቶ ይበልጣል።

ይህ ምንዳ ሰውየው በመስጂድ ውስጥ ቢፈፅማቸው የሚመረጡ ተግባራትን አስመልክቶ ነው። ፈርድ ሶላቶችን፣ ፀሃይ ወይም ጨረቃ ሲጋረዱ የሚሰገዱትን ሶላቶች፣ ተሒየቱል-መስጂድን እና በእዚህ አምሳያ በመስጂድ ውስጥ ቢፈፀሙ መልካም የሆኑ ስራዎች ላይ የተገደበ ቱሩፋት ነው።

በመስጂድ ውስጥ እንዲፈፀሙ ያልተደነገጉ ወይም ከመስጂድ ውጪ ቢፈፀሙ ተመራጭ የሆኑ ሶላቶች ግን እቤት ውስጥ መስራቱ የተወደደ ነው። ስለዚህ- ለምሳሌ- ከፈርድ ሶላት በኋላ ወይም በፊት የሚሰገዱ ሱና ሶላቶችን የሐረም መስጂድ ውስጥ ከመስገድ እቤት መስገድ ይበልጣል። የመዲናውም መስጂድ እንዲሁ ነው። ምክንያቱም በመዲና ውስጥ የኖሩት የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-

أفضل صلاة المرء في بيته إلا المكتوبة

“ከፈርድ ሶላት ውጪ የሰውየው ምርጡ ሶላት እቤቱ ውስጥ የሚሰግደው ነው።”

የተራዊሕ ሶላት ግን በመስጂድ ውስጥ በጀመዐ መሰገዷ እንደሚበልጥ የሚያስረዳ ድንጋጌ ስለመጣላት በእነዚህ መስጂዶች ውስጥ የተለየች ናት።

አላሁ አዕለም!