እንቅልፍ እያንገላጀው ለሶላት መቆም

Home የፈትዋ ገጽ ሰላት እንቅልፍ እያንገላጀው ለሶላት መቆም

ጥያቄ፡- ሱብሒን ስሰግድ ከፋቲሓ በኋላ ረዣዥም አንቀጾች እቀራለሁ። አንዳንዴ ግን እንቅልፍ ያስቸግረኛል። ቁርኣኑን እያነበብኩም አንጎላጃለሁ። ይህ እንዴት ይታያል? ቁርኣንን በማንበቤ የማገኘውን ምንዳ ያመክንብኝ ይሆን?


መልስ፡- አዎን! ቁርኣን እየቀሩ ማንጎላጀት ምንዳው ላይ ተፅዕኖ አለው። ከባድ ማንጎላጀት ካስቸገረውና መቋቋም ካልቻለ ቂርኣቱን ማርዘም አይገባም። ምክንያቱ ንባቡ ላይ ይሳሳታል። ጣዕምም አይኖረውም።

ማንጎላጀት ያስቸገረው ሰው ሶላቱን አያርዝመው። ያሳጥረው። ከፋቲሓ በኋላ አጭር ሱራዎችን ወይም ከሦስት አንቀጾች ያልበለጠ ብቻ ይቅራ። ልቡ ባልተሰበሰበበት ሶላትን ከማርዘም ይልቅ ሶላቱን አሳጥሮ ቀልብን መሰብሰብ ይበልጣል።

ይኸውም ማንጎላጀቱ ቀላል ከሆነ ነው። ማንጎላጀቱ ኃያል ሆኖ የእንቅልፍ ደረጃ ላይ ከደረሰ ሶላቱን ትንሽ ያቆየው። ምክንያቱም የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) እንቅልፍ ያየለው ሰው ሶላት እንዳይሰግድ ከልክለዋል። ለጥቂት ሰዐት ተኝቶ እንቅልፉን ካቃለለ በኋላ ተነስቶ ይስገድ ብለዋል። እንቅልፍ ላይ ሆኖ የሚናገረውን ሳያውቅ በተሳሳተ መንገድ አምልኮውን ሊከውን ይችላል።

ቡኻሪይ ከዓኢሻ (ረ.ዐ) እንደዘገቡት የአላህ መልክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

إذا نعس أحدكم وهو يصلي فليرقد ، حتى يذهب عنه النوم ، فإن أحدكم إذا صلى وهو ناعس ، لا يدري لعله يستغفر فيسب نفسه 

“እያንዳንዳችሁ እየሰገዳችሁ ሳለ ማንጎላጀት ካስቸገራችሁ እንቅልፋችሁ እስከሚወገድላችሁ ተኙ። ምክንያቱም እያንጎላጃችሁ ከሰገዳችሁ አላህን ምህረት ሲለምን ሳያውቀው ነፍሱን ሊሰድብ ይችላል።”

ከአነስ (ረ.ዐ) በተገኘው ሌላ ዘገባ የአላህ መልክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

إذا نعس أحدكم في الصلاة فلينم ، حتى يعلم ما يقرأ 

“በሶላት ውስጥ ሆናችሁ ካንጎላጃችሁ የምታነቡትን መረዳት እስከምትችሉ ድረስ ተኙ።”

ቡኻሪይ ዘንድ ያለው የዘገባ ቃል እንዲህ ይላል፡-

لعله يدعو على نفسه وهو لا يدري 

“ምናልባት ሳያውቅ (ዱዓ አደርጋለሁ ብሎ) ነፍሱን ሊራገም ይችላል።”

አላህ የበለጠ ያውቃል!