ኢዕቲካፍ፡- ድንጋጌው፣ መስፈርቶቹ፣ የሚያበላሹት እና ጊዜው

Home የፈትዋ ገጽ ዒባዳ ጾምና ኢዕቲካፍ ኢዕቲካፍ፡- ድንጋጌው፣ መስፈርቶቹ፣ የሚያበላሹት እና ጊዜው

ጥያቄ፡- ብዙ ጊዜ ኢዕቲካፍ የማድረግ ልምድ ቢኖረኝም በተጨባጭ ስለኢዕቲካፍ የማላውቃቸው ነገሮች ሞልተዋል። በኢዕቲካፍ ወቅት የሚፈቀድልኝ ነገሮች ምንድን ናቸው? በኢዕቲካፍ ወቅት ሐራም የሚሆኑብ ነገሮችስ ምንድን ናቸው? ለስራ እየወጣሁ ተመልሼ መግባት እችላለሁ?…


መልስ፡- ቢስሚላሂር-ረሕማኒር-ረሒም አል-ሐምዱሊል-ላሂ ረብ-ቢል ዓለሚን ወስ-ሶላት ወስ-ሰላም ዐላ ረሱሊላህ

ኢዕቲካፍ ወደ አላህ የሚያቃርብ መልካም ተግባር ነው። ሱናም ነው። በተለይም በረመዷን ውስጥ እጅግ ከሚወደዱ ተግባራት መሀል አንዱ ነው። በተለይም ደግሞ በረመዷን የመጨረሻዎቹ አስርት ቀናት እጅግ የጠበቀ ሱና ነው። ምክንያቱም ለይለቱል-ቀድር (የውሳኔዋ ለሊት) ያለችው በእነዚህ አስርት ቀናቶች ውስጥ ነውና።

ኢዕቲካፍ እንደማንኛውም አምልኮ መስፈርቶች (ሹሩጥ)፣ ስነስርዐቶች (አዳብ)፣ የሚያፈርሱት ነገሮች እና በውስጡ የሚፈቀዱ ነገሮች አሉት።

በፊሊስጢን ውስጥ በሚገኘው ኢስላማዊ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ኡስታዝ፣ ዶክተር ሳሊም አሕመድ ሰላማ እንዲህ ብለዋል፡-

ኢዕቲካፍ ማለት፡-

በቋንቋ ትርጉሙ አንድን ነገር አጥብቆ መያዝ ማለት ነው። በሸሪዓ ትርጓሜው ደግሞ መስጂድን አለመልቀቅ፣ ወደ አላህ ለመቃረብ በሚል ኒያ እርሱ ውስጥ መቆየት ማለት ነው።

የኢዕቲካፍ ድንጋጌ

ኢዕቲካፍ በሸሪዓው ውስጥ የተደነገገ ስለመሆኑ በዑለሞች መካከል ስምምነት አለ። ኢዕቲካፍ ስለጾም የተጠቀሱ አንቀጾች መሀል በቁርኣን ውስጥ ተጠቅሷል። አላህ እንዲህ ይላል፡-

وَلَا تُبَاشِرُوهُنَّ وَأَنتُمْ عَاكِفُونَ فِي الْمَسَاجِدِ

“እናንተም በመስጊዶች ተቀማጮች ስትኾኑ አትገናኙዋቸው፡፡” (አል-በቀራ 2፤ 187)

ነብዩም (ሰ.ዐ.ወ.) የረመዷን የመጨረሻዎቹ አስርት ቀናት ላይ ኢዕቲካፍ ያደርጉ እንደነበር ተዘግቧል። ባረፉበት የመጨረሻው ዓመት ላይ ግን- አቡሁረይራ እንዲህ ይላሉ- “የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) በረመዷን አስርት ቀናት ኢዕቲካፍ ያደርጉ ነበር። ባረፉት አመት ላይ ግን ሃያ ቀናት ኢዕቲካፍ አድርገዋል።”

የኢዕቲካፍ ብይኑ (ሁክም)፡-

ኢዕቲካፍ ወደ አላህ የሚያቃርብ ሱና የአምልኮ ዘርፍ ነው። በተለይም በረመዷን ጥብቅ አምልኮ ነው። በተለይም በመጨረሻዎቹ አስርት ቀናት ውስጥ በጣም የጠበቀ ሱና ነው። ምክንያቱም በእነዚህ አስርት ቀናት ውስጥ ለይለቱል-ቀድር ትገኛለች። ነገርግን ስለት ባደረገ ሰው ላይ ግዴታ ይሆናል። ማለትም ሰውየው ኢዕቲካፍ ለማድረግ ከተሳለ ዋጂብ ይሆናል።

የኢዕቲካፍ ሸርጦች፡-

 1. ሙስሊም መሆን
 2. አዕምሮ ጤነኛ መሆን
 3. የመለየት እድሜ (ተምዪዝ/ስድስት ወይም ሰባት ዓመት መሙላት)
 4. ኒያ ማድረግ
 5. መስጂድ ውስጥ መሆኑ
 6. ከወር አበባ፣ ከድህረ ወሊድ ደም እና ከጀናባ ንፁህ መሆን

በኢዕቲካፍ ወቅት የሚወደዱ ነገሮች (ሙሰታሃባት)፡-

 1. የአምልኮ ተግባራት ማብዛት። ሶላት፣ ቁርኣንን ማንበብ፣ የዒልም ሰዎችን መፅሀፍት ማንበብ፣ በመስጂዱ ውስጥ የሚሰጡ ምክሮችን እና ትምህርቶችን መከታተል።
 2. ዋዛ ነገርን (ማላ የዕኒን) መተው። ከክርክር፣ ከስድድብ፣ ከትችት፣ ከሃሜት እና ነገር ከማሳበቅ መራቅ።
 3. በመስጂዱ ውስጥ አንድ ስፍራን አጥብቆ መያዝ። ቦታ አለመቀያየር።

በኢዕቲካፍ ወቅት የሚፈቀዱ ነገሮች (ሙባሃት)፡-

 1. የግድ ለሆኑ ጉዳዮቹ መውጣት። ለምሳሌ፡- ለመፀዳዳት፣ ህመም ላይ ካለ ለህክምና፣ ኢዕቲካፍ ያደረገበት መስጂድ ጁሙዓ የማይሰገድበት ከሆነ ጁሙዐ ለመስገድ…
 2. መስጂድ ውስጥ መብላት፣ መጠጣት እና መተኛት ይችላል። ነገርግን የመስጂዱን ንፅህና መበከል ሐራም ነው።
 3. የሚፈቀዱ ንግግሮችን መናገር ይቻላል።
 4. ፀጉር ማበጠር፣ ጥፍር መቁረጥ፣ አካሉን ማፅዳት፣ ጥሩ ልብስ መልበስ እና ሽቶ መቀባትም ይቻላል።

በኢዕቲካፍ ጊዜ የሚጠሉ ነገሮች (መክሩህ)፡-

 1. መሸጥና መግዛት
 2. ኃጢያት ያለበትን ነገር መናገር
 3. አምልኮ ነው ብሎ አስቦት ከሆነ ዝም ማለት

ኢዕቲካፍን የሚያፈርሱት ነገሮች (ሙብጢላት)፡-

 1. አውቆ- ያለጉዳይ- ከመስጂድ መውጣት
 2. ወሲብ መፈፀም
 3. በእብደት ወይም በስካር አዕምሮን መሳት
 4. የወር አበባ እና የድህረ ወሊድ ደም መከሰት
 5. አላህ ይጠብቀንና ከኢስላም መውጣት (ሪድ-ዳ)

የኢዕቲካፍ መጀመሪያ እና መጨረሻው፡-

ሰውየው ወደ መስጂድ ገብቶ ኢዕቲካፍ መስጂድ ውስጥ በመቆየት ወደ አላህ ለመቃረብ ከነየተ እስከሚወጣ ድረስ ኢዕቲካፍ ላይ እንዳለ ይቆጠራል። የመጨረሻዎቹን አስርት የረመዷን ቀናት ኢዕቲካፍ ለማድረግ ከነየተ ኢዕቲካፍ ወደሚያደርግበት ስፍራ በአስራ ዘጠነኛው ቀን ፀሃይ ከመጥለቋ በፊት መግባት አለበት። ሲወጣም የወሩ መጨረሻ ላይ ፀሀይ ከጠለቀች በኋላ- ማለትም በዒድ ለሊት- መውጣት አለበት።

የኢዕቲካፍ ጥቅሙ፡-

ኢዕቲካፍ ማድረግ የነብዩን ሱና ህያው ማድረግ ነው። ተከታታይ የአምልኮ ተግባራት ላይ በማሳተፍም ልብን ህያው ያደርጋል። ሰውየው ከራሱ ጋር የመገለል እና እስትንታኔ የማድረግ እድል ያገኝበታል። ያለፈውን ሂደቱን ገምግሞ እርምት ለመውሰድ እና መጪውን ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ወደ አላህ የመቅረብ ወኔ እንዲያገኝ ያስችለዋል። ኢዕቲካፍ የልብ ብርሃን ነው። ብዙ መልካም ነገሮች ያስገኛል። በአላህ እዝነትም ከፍታና ደረጃንም ይጨምራል። በተለይም በአስርቱ የረመዷን የመጨረሻ ቀናት ሲሆነ ለይለቱል-ቀድርን ያስገኛል። ለይለቱል-ቀድርን ያገኘ ሰው ከአንድ ሺህ በላይ የሆኑ ወራትን አግኝቷል።

አላሁ አዕለም!