ኢስላም በአሉባልታ ወሬ ላይ ያለው አቋም

Home የፈትዋ ገጽ ማህበራዊ ጉዳዮች አኽላቅና አዳብ ኢስላም በአሉባልታ ወሬ ላይ ያለው አቋም

ጥያቄ፡- ኢስላም አሉባልታን ስለማሰራጨት ያለው አቋም ምንድን ነው?


መልስ፡- ኢስላም እውነተኛ መሆንን ያሞግሳል፤ ውሸትን ያስጠነቅቃል። ከዐብዱላህ ቢን መስዑድ እንደተዘገበው የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-

إِنَّ الصِّدْقَ يَهْدِي إِلَى الْبِرِّ، وَإِنَّ الْبِرَّ يَهْدِي إِلَى الْجَنَّةِ، وَإِنَّ الرَّجُلَ لَيَصْدُقُ حَتَّى يُكْتَبَ صِدِّيقًا. وَإِنَّ الْكَذِبَ يَهْدِي إِلَى الْفُجُورِ، وَإِنَّ الْفُجُورَ يَهْدِي إِلَى النَّارِ، وَإِنَّ الرَّجُلَ لَيَكْذِبُ حَتَّى يُكْتَبَ كَذَّابًا (رواه البخاري ومسلم).

“እውነት ወደ በጎ ይመራል። በጎ ነገር ደግሞ ወደ ጀነት ይመራል። ሰውየው አላህ ዘንድ እውነተኛ ተብሎ እስኪከተብ ድረስ እውነት ከመናገር አይቆጠብም። ውሸት ወደ ጥሜት ይመራል። ጥሜት ወደ እሳት ይመራል። ሰውየው አላህ ዘንድ ውሸታም ተብሎ እስከሚፃፍ ድረስ ውሸት ከመናገር አይቆጠብም።” ቡኻሪይ እና ሙስሊም ዘግበውታል።

አሉባልታ አደገኛ ውሸት ነው። “እንዲህ ተባለ… እንዲያ ተባለ” እያሉ ማውራት (ቂለ ወቃለ) እጅግ ፀያፍ ነገር እንደሆነ የሚያስገነዝቡ አስፈራሪ ሐዲሶች ተዘግበዋል። ኢብኑ ከሲር እንዲህ ይላሉ፡-

“ቡኻሪና ሙስሊም ላይ ከሙጊራ ቢን ሹዕባ እንደተዘገበው የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) አሉባልታን ከልክለዋል። እንዲህ ነው ያሉት፡-

أي: الذي يكثر من الحديث عما يقول الناس من غير تَثبُّت، ولا تَدبُّر، ولا تبَيُّن

“አሉባልታ (ቂለ ወቃለ) ሰዎች የሚያወሩትን ሁሉ ሳያረጋግጡ፣ ሳያስተነትኑ እና ሳይመራመሩ ማውራት ነው።”

ኢስላም ሙስሊም የሆነ ሰው የመረጃ ምንጩን እንዲያጣራ ይገፋፋል። መረጃዎቹን ከተዛቡ ምንጮች እንዳይቀበል ያስጠነቅቃል። አሸናፊው ጌታ እንዲህ ይላል፡-

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا إِن جَاءَكُمْ فَاسِقٌ بِنَبَإٍ فَتَبَيَّنُوا أَن تُصِيبُوا قَوْمًا بِجَهَالَةٍ فَتُصْبِحُوا عَلَىٰ مَا فَعَلْتُمْ نَادِمِينَ

“እላንተ ያመናችሁ ሆይ! ነገረኛ ወሬን ቢያመጣላችሁ በስህተት ላይ ኾናችሁ ሕዝቦችን እንዳትጎዱና በሠራችሁት ነገር ላይ ተጸጸቾች እንዳትኾኑ አረጋግጡ፡፡” (አል-ሁጅራት 49፤ 6)

ሱረቱ አን-ኑር ላይ የእናታችን ዓኢሻን ክብር የነካውን አሉባልታ እንዲህ ሲል ገልጾታል፡-

إِنَّ الَّذِينَ جَاءُوا بِالْإِفْكِ عُصْبَةٌ مِّنكُمْ  لَا تَحْسَبُوهُ شَرًّا لَّكُم بَلْ هُوَ خَيْرٌ لَّكُمْ لِكُلِّ امْرِئٍ مِّنْهُم مَّا اكْتَسَبَ مِنَ الْإِثْمِ وَالَّذِي تَوَلَّىٰ كِبْرَهُ مِنْهُمْ لَهُ عَذَابٌ عَظِيمٌ

“እነዚያ መጥፎን ውሸት ያመጡ ከናንተው የኾኑ ጭፍሮች ናቸው፡፡ ለእናንተ ክፉ ነገር ነው ብላችሁ አታስቡት፡፡ በእውነቱ እርሱ ለእናንተ መልካም ነገር ነው፡፡ ከእነርሱ (ከጭፍሮቹ) ለያንዳንዱ ሰው ከኀጢአት የሠራው ሥራ ዋጋ አለው፡፡ ያም ከእነሱ ትልቁን ኀጢአት የተሸከመው ለእርሱ ከባድ ቅጣት አለው፡፡” (አን-ኑር 24፤ 11)

በዚሁ ሱራ ሌላ ስፍራ ላይም እንዲህ ብሎ ይገልፀዋል፡-

لَّوْلَا إِذْ سَمِعْتُمُوهُ ظَنَّ الْمُؤْمِنُونَ وَالْمُؤْمِنَاتُ بِأَنفُسِهِمْ خَيْرًا وَقَالُوا هَٰذَا إِفْكٌ مُّبِينٌ

“(ውሸቱን) በሰማችሁት ጊዜ ምእምናንና ምእምናት በጎሶቻቸው ለምን ደግን ነገር አልጠረጠሩም? ለምንስ ይህ ግልጽ ውሸት ነው አላሉም?” (አን-ኑር 24፤ 12)

ሙስሊሞች በአሉባልታ እንዳይነዱ የሚያደርግ የአላህ ነብይ ማስጠንቀቂያም እንዲህ ሲል መጥቷል፡-

كفى بالمرء كذبا (وفي رواية : إثما) أن يحدث بكل ما سمع

“ውሸታም ለመሆን ሰውየው የሰማውን ሁሉ ማውራቱ ይበቃዋል።” በሌላ ዘገባ “ኃጢያተኛ ለመሆን ሰውየው የሰማውን ሁሉ ማውራቱ ይበቃዋል።”

ስለዚህ ሙስሊም ግለሰብ ምንጩ ያልተረጋገጠ ወሬ ሲደርሰው ተከታዮቹን መርሆች የመከተል ግዴታ አለበት፡-

  • ራሱ ወሬውን በማሰራጨት ውስጥ እንዳይሳተፍ
  • የወሬውን ማስረጃ መገምገም፤ አላህ ሱረቱል-ሑጁራት ላይ “ፈተበየኑ!-አረጋግጡ!” ብሎ እንዳዘዘው።

አሉባልታ የሚነዛው በፊትና ዘመን ነው። ነገሮች በሚምታቱበት እና የሚያዝ የሚጨበጥ በሚጠፋበት የፈተና ጊዜ ነው የሚበረክቱት። ስለዚህ የመረጃ አውታር ባለቤት የሆኑ ሰዎች ትክክለኛ እና እውነተኛ ዘገባ ለተከታታዮቻቸው እንዲሰጡ ይጠበቃል። አሉባልታን የሚያጠፋው እና እውነትን የሚያነግሰው እውነትን ብቻ የሚዘግቡና የሚያስተላላፉ ሚዲያዎች ሲኖሩ ነውና በዚህ ረገድ ብዙ ሊሰራ ይገባል!

ወላሁ አዕለም!