ኢሕራም ላይ ያለ ሰው ቀበቶ መታጠቅ ይችላል?

Home የፈትዋ ገጽ ሐጅና ዑምራ ኢሕራም ላይ ያለ ሰው ቀበቶ መታጠቅ ይችላል?

ጥያቄ፡- ገንዘብ እና ልዩልዩ መረጃዎቼን ለመያዝ እንዲመቸኝ የተሰፋ ቀበቶ መታጠቅ እችላለሁ?


መልስ፡- ብዙ ሰዎች ኢሕራም ላይ ያለ ሰው የተሰፋ ልብስን በምንም መልኩ መልበስ እንደማይችል ያስባሉ። ነገርግን ጉዳዩ እንዲህ በጥቅሉ ሳይሆን ማብራሪያ ይፈልጋል። ኢሕራም ውስጥ ባለ ሰው ላይ እርም የሚሆነው ልብስ በአካላት ልክ የተሰፋ- እንደ ሱሪና እና እንደ ቀሚስ ያለ ልብስ- ነው። ክር የነካውን ልብስ ሁሉ እርም ነው አይባልም። ኢሕራም ላይ ያለ ሰው ንብረቱን ወይም ገንዘቡን ለመጠበቅ ብሎ የሚያስረው ቀበቶ ኢሕራም ላይ ያለ ሰው ሊከለከለው ከሚገባው “የተሰፋ ልብስ” ውስጥ አይካተትም።

በፊሊስጢን- የጋዛ ኢስላማዊ ዩኒቨርሲቲ መምህር ኡስታዝ ዶክተር ዩኑስ አል-አስጠል እንዲህ ይላሉ፡-

“ሽርጥ ላይ ቀበቶ መታጠቅ ችግር የለውም። ጠያቂው ‘የተሰፋ’ ማለቱ ከተርታው ሰዎች የአስተሳሰብ ስህተት የተነሳ እንደሆነ እንረዳለን። ብዙዎች የተሰፋ ማለት ክር የነካው ማንኛውም ልብስ ማለት ነው ብለው ያስባሉ። ነገርግን ነገሩ እንደዚያ አይደለም። የዒልም ሰዎች ‘የተሰፋ ልብስ’ ሲሉ በሰውነት አካላት ልክ የተሰፋ ልብስ ማለታቸው ነው። (ሰውነትን እንዲያካብብ ተደርጎ የተሰራ ማለታቸው ነው።) ይህም እንደ ቀሚስ፣ ጀለቢያ፣ ካፖርት እና ሱሪ የመሰሉ ልብሶችን የሚገልፅ ነው። ሲሰራ የስፌት ክር የነካውን በሙሉ እርም ነው ማለታቸው አይደለም። ስለዚህ ሰውየው በተጣፈ ኩታ ወይም ጋቢ ኢሕራም ቢያደርግ ችግር የለበትም።”

ወላሁ አዕለም!