አስከሬንን ስለ መክፈት

Home የፈትዋ ገጽ ጤናና ህክምና አስከሬንን ስለ መክፈት

ጥያቄ:- በህክምና የትምህርት ክፍል ተማሪ ነኝ። አልፎ አልፎ ባለቤት የሌላቸው አስከሬኖችን እናገኛለን። እነዚያን አስከሬኖች ከፍቶ ለመማርና ማስተማር መጠቀም ይፈቀዳል ወይ?


መልስ: ለተመሳሳይ ጥያቄ የግብፁ ዳሩል-ኢፍታእ የሚከተለውን መልስ አስፍሯል፡-

የሸሪዓ መርሆና መንፈሱ እንደሚያመለክተው አንድ ነገር ማድረግ ያለው ጥቅም ጎልቶ የወጣ እንደሆነ ይፈቀዳል። አስከሬንን መክፈትና መጠቀምም እንዲሁ ነው። ይህ መሆኑ በሐዲሥ ከተላለፈው “كسر عظم الميت ككسره حيا – የሟችን አጥንት መስበር ሕያው ሆኖ ሣለ እንደመስበር ነው” ከሚለው መልዕክት ጋር አይጋጭም።

የሐዲሡ ዉጫዊ ገጽታ እንደሚያመለክተው ሙስሊም ሟች  በሕይወት እንደነበረው ሁሉ በሞተ ጊዜም ትልቅ ክብር ያለው መሆኑን ለመግለጽ ነው። አካሉን በመስበር፣ በመቅደድም ሆነ ሌላ ነገር በሱ ላይ በመፈጸም መበደልና ድንበር ማለፍ አይገባም። እጅግ አንገብጋቢና ጥቅሙ ጎልቶ ለሚታይ ነገር ካልሆነ በስተቀር። አስከሬንን መክፈትና መመራመር ሕይወትን ለመጠበቅ ወይም በሽታን ለማከም ወይም ደግሞ የአንድን ሰው የሞቱን ሰበብ ለማወቅና ለሌላም ለማህበረሰቡ ለሚኖረው ነገር እስከሆነ ድረስ እነኚህን ጥቅሞች ለመጠበቅ ሲባል ይፈቀዳል ማለት እንችላለን። ከዚህም በተጨማሪ መክፈቱ የሚፈፀመው በአንዳንድ ባለቤት በሌላቸው አስከሬኖች ላይ በመሆኑ ከዚያ አስከሬን አስፈላጊ የሆነን ነገር ለማግኘት መጠቀሙ ችግር ያለው ሆኖ አይታየንም። ይህንን ከሚደግፉ የሸሪዓ መርሆዎች መካከል “ሸሪዓው አንድን ነገር አስፈላጊና የግድ ያደረገ እንደሆነ ያ ነገር መሠረቱ ያደረገው ነገርም ግዴታ ይሆናል።” የሚለው ይገኝበታል።

ስለሆነም በማኅበረሰቡ ላይ ሊደርስ የሚችለው ጉዳት ሐኪሞች አስከሬኖችን በመክፈት በሙታን ላይ ከሚደርሰው ጉዳት የከፋ ከሆነ አስከሬኖችን መክፈትና መመርመር ይቻላል።

የእስልምና ሃይማኖት መርሆ በላጭ የሆነውን የሕብረተሰቡን ደህንነት በመጠበቅ ላይ የተመሠረተ ነው። ለሰፊው ሕዝብ ትልቁን ጥቅም ለማስገኘት ሲባልም ትንሽ ጉዳት ቢደርስ አይቃወምም።

በዚሁ መነሻነትም ቤተሰብ የሌላቸውን አንዳንድ አስከሬኖች ከነርሱ የበለጠ ትምህርትና የብዙሃኑን ጥቅም ለማስገኘት ሲባል መክፈት ይቻላል። ይህም ሲደረግ የአስከሬንን ክብር በጠበቀ መልኩ ግዴለሽ ሳይሆኑና የአስከሬኑን የሰውነት ክፍሎች ባለመበታተን እጅግ አስፈላጊ በሆነው ነገር ላይ ብቻ በመወሰን ማከናወን ይገባል።