አህለልኪታብ (የመፅሃፉ ሰዎች) የምንላቸው የትኞቹ ናቸው?

Home የፈትዋ ገጽ ዐቂዳ አህለልኪታብ (የመፅሃፉ ሰዎች) የምንላቸው የትኞቹ ናቸው?

ጥያቄ፡- እንደ አረዳዴ ከሆነ ቁርዓን አህለልኪታብ (የመፅሃፉ ሰዎች) የሚላቸው ከነሱ መካከል የተውሂድ እምነትን የያዙትን ነው። ከአንድ በላይ አምላክ በማመን የጠመሙትን አጋሪዎች አይመለከትም። ነገር ግን አህለልኪታብን ከመለየት አንፃር ለኔ የተጋጨብኝ ነገር አለ። “የመፅሃፉ ሰዎች” የሚለው ስያሜ የሚያጠቃልለው በስላሴ የሚያምኑትንና “ኢየሱስ አሊያም ኢዝራ የአምላክ ልጅ ነው” የሚሉትን ስለማካተቱ በርካታ ሙስሊሞችና ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች የሚያወዛግብ እንደሆነ እገምታለሁ። በዚህ ዙሪያ ከቁርዓንና ከሀዲስ ተጨማሪ ማብራረሪያ ቢሠጠኝ?


መልስ፡- መልሱን አስመልክቶ የሰሜን አሜሪካው የፊቅህ ካውንሲል ሊ/መንበር ዶክተር ሙዘሚል ሲዲቂ እንዲህ ብለዋል፡-

“አህለልኪታብ” (የመፅሃፉ ሰዎች) የሚለው በቁርዓን ውስጥ ሠላሣ አንድ ጊዜ ያህል መጥቷል። ሌላው ገለፃ “አለዚነ ኡቱል-ኪታበ” (መፅሃፉን የተሠጡ ሰዎች) የሚለው ደግሞ አሥራ ስምንት ጊዜ ወርዷል። እነኚህን አንቀፆች ስናነብ ሁለት ነገሮችን መዘንጋት የለብንም።

አንደኛ፡- አንዳንድ ሰዎች “የመፅሃፉ ሰዎች” አሊያም “መፅሃፉን የተሠጡ ሰዎች” ተብለው የተጠሩ እንደሆነ የግድ ትክክለኞቹ የአላህ መንገድ ተከታዮች ናቸው ብለን መጠበቅ የለብንም። ይህ ገለፃ አንዳንዴ descriptive (ለገለፃ ያህል) እንዳንዴ ደግሞ exhortative (ለምክር) ሊሆን ይችላል።

ሁለተኛ፡- ገለፃዎቹ ሁሉ የሚያመለክቱት አይሁዶችን እና ክርስቲያኖችን ነው። የመፅሃፉ ሰዎች ሲባል አይሁዶች እና ክርስቲኖች ስለመሆናቸው በሙስሊም ምሁራን መካከል ሙሉ ስምምነት አለ። ይህም የሚያጠቃልለው በነቢዩ ሰላለሁ ዐለይ ወሠለም እና ከዚያ ዘመን በኅላ የኖሩትን ሁሉ ነው። “የመፅሃፉ ሰዎች” አሊያም “መፅሃፉን የተሠጡ ሰዎች” የሚለው ቃል ዝም ብሎ እነሱን ለመግለፅ (descriptive) ያህል ብቻ ሲሆን ሀሣቡም የሚያመለክተው ከአላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ በነቢያቶቻቸው አማካይነት መፅሃፍ የተሠጣቸው ሰዎች መሆኑን ነው።

በርግጥ መፅሃፎቹን በአጠቃላይ መልኩ ዛሬ ላይ ሆነን ስንገመግማቸው ትክክለኛ እና እውነተኛ አይደሉም ማለትም ተቀንሰዋል አሊያም ተጨምሮባቸዋል /ተበርዘዋል/።  ነገር ግን ከአላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ የሆኑ የተወሰኑ እውነታዎችም አይጠፏቸውም። ሥያሜው በአንድ በኩል exhortative እንደመሆኑ የክብር ስያሜም ነው። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ በጥሩ ሥያሜ የጠራቸው ሲሆን ይህም ስህተታቸውን ለማስታወስ እና ወደ ኢስላምም ለመጋበዝ ነው። ይህም ያማረ የሆነ ኢስላማዊ ስብከት ነው። ሌላው ቀርቶ እነኚያ መጥፎ ነገር የሚሰሩትም ጭምር በኩራትና ትእቢት ተነሣስተው የአላህን መልእክት ካልገፉ በስተቀር በቁርዓን ውስጥ በጥሩ ሥም እና ስያሜ ነው የተጠሩት።

ቁርዓንን በጥንቃቄ ያነበብን እንደሆነ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ መናፍቃንን እንኳን “እናንተ ያመናችሁ ሆይ!” ብሎ እነሱን የሚገልፅበትን ሁኔታ እናስተውላለን።

መናፍቃን አማኞች ናቸው ሊባሉ የሚችሉ አይደሉም። እነሱ እውነተኛ አማኞች አይደሉምና። ነገር ግን አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ በዚህ ባማረ ሥያሜ ገለፃቸው። በአፋቸው የሚናገሩትና በተግባር የሚያሳዩት ለየቅል መሆኑን ለማሣወቅ። ለምሣሌ ሱረቱ አስ-ሶፍ ላይ ያለውን የቁርዓን አንቀፅ እንመልከት። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ ይላል፡-

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا لِمَ تَقُولُونَ مَا لَا تَفْعَلُونَ

“እላንተ ያመናችሁ ሆይ! የማትሠሩትን ነገር ለምን ትናገራላችሁ?” (አስ-ሶፍ 61፤ 2)

ይህ አንቀፅ በርግጥ ስለ ጥሩ ምእመናን አይደለም የሚናገረው። በሌላ የቁርዓን አንቀፅ ደግሞ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ ይላል፡-

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا مَا لَكُمْ إِذَا قِيلَ لَكُمُ انفِرُوا فِي سَبِيلِ اللَّهِ اثَّاقَلْتُمْ إِلَى الْأَرْضِ أَرَضِيتُم بِالْحَيَاةِ الدُّنْيَا مِنَ الْآخِرَةِ  فَمَا مَتَاعُ الْحَيَاةِ الدُّنْيَا فِي الْآخِرَةِ إِلَّا قَلِيلٌ

“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በአላህ መንገድ (ለመታገል) ውጡ በተባላችሁ ጊዜ ወደ ምድር የምትወዘፉት ለእናንተ ምን አላችሁ? የቅርቢቱን ሕይወት ከመጨረሻይቱ ይበልጥ ወደዳችሁን? የቅርቢቱም ሕይወት ጥቅም በመጨረሻይቱ (አንጻር) ጥቂት እንጂ አይደለም፡፡” (አት-ተውባ 9፤38)

ከላይ በምሣሌ እንዳየነው ሁሉ ቁርዓን አንዳንድ አካላትን “የመፅሃፉ ሰዎች” ብሎ ሲጠራ እነሱ የግድ ትክክለኛ የአላህ መፅሃፍ ተከታዮች ወይንም እውነተኛ አማኞች ናቸው ማለትን አይሠጥም። ይህም የማበረታታት እና ወደ እውነታው እንዲመጡ የመጋበዝ ስልት ነው። ይህም ማለት “እናንተ መለኮታዊ መልእክት መለኮታዊ መፅሃፍ ወርዶልናል የምትሉ ሰዎች ሆይ! ለምንድነው ትክክለኛውን መልእክት የማትከተሉት? ለምንድነው የመጨረሻውን እና የነቢያት ሁሉ መደምደሚያ የሆነውን ነቢይ የማትቀበሉት?” እንደማለት ነው። ለዚህም ምሣሌ ሱረቱ አን-ኒሳእን እንመልከት።

يَا أَهْلَ الْكِتَابِ لَا تَغْلُوا فِي دِينِكُمْ وَلَا تَقُولُوا عَلَى اللَّهِ إِلَّا الْحَقَّ إِنَّمَا الْمَسِيحُ عِيسَى ابْنُ مَرْيَمَ رَسُولُ اللَّهِ وَكَلِمَتُهُ أَلْقَاهَا إِلَىٰ مَرْيَمَ وَرُوحٌ مِّنْهُ فَآمِنُوا بِاللَّهِ وَرُسُلِهِ وَلَا تَقُولُوا ثَلَاثَةٌ انتَهُوا خَيْرًا لَّكُمْ إِنَّمَا اللَّهُ إِلَٰهٌ وَاحِدٌ سُبْحَانَهُ أَن يَكُونَ لَهُ وَلَدٌ لَّهُ مَا فِي السَّمَاوَاتِ وَمَا فِي الْأَرْضِ وَكَفَىٰ بِاللَّهِ وَكِيلًا

“እናንተ የመጽሐፉ ሰዎች ሆይ! በሃይማኖታችሁ ወሰንን አትለፉ፡፡ በአላህም ላይ እውነትን እንጅ አትናገሩ፡፡ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ዒሳ የአላህ መልክተኛ ወደ መርየም የጣላት ‘የኹን’ ቃሉም ከእርሱ የኾነ መንፈስም ብቻ ነው፡፡ በአላህና በመልክተኞቹም እመኑ፡፡ ‘(አማልክት) ሦስት ናቸው’ አትበሉም፡፡ ተከልከሉ፤ ለእናንተ የተሻለ ይኾናልና፡፡ አላህ አንድ አምላክ ብቻ ነው፡፡ ለእርሱ ልጅ ያለው ከመኾን የጠራ ነው፡፡ በሰማያትና በምድር ያለ ሁሉ የርሱ ነው፡፡ መመኪያም በአላህ በቃ፡፡” (አን-ኒሳእ 4፤ 171)

ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ ይላል:-

يَا أَهْلَ الْكِتَابِ لِمَ تَكْفُرُونَ بِآيَاتِ اللَّهِ وَأَنتُمْ تَشْهَدُونَ * يَا أَهْلَ الْكِتَابِ لِمَ تَلْبِسُونَ الْحَقَّ بِالْبَاطِلِ وَتَكْتُمُونَ الْحَقَّ وَأَنتُمْ تَعْلَمُونَ

“የመጽሐፉ ባለቤቶች ሆይ! እናንተ የምታውቁ ስትኾኑ በአላህ አንቀጾች ለምን ትክዳላችሁ? የመጽሐፉ ሰዎች ሆይ! እውነቱን በውሸት ለምን ትቀላቅላላችሁ? እውነቱንም እናንተ የምታውቁ  ስትኾኑ ለምን ትደብቃላችሁ?” (አሊ ዒምራን 3፤ 70-71)

የነሱን ሴቶች ማግባትን እና ያረዱትን እንሠሣ ምግብ መብላትን በተመለከተ ደግሞ ይህ ጉዳይ አይሁዶች እና ክርስቲኖች ላይ ብቻ የተወሠነ ነው። ይህም ፈቃድ ወደሌሎች ቡድኖች የማይሰፋ ስለመሆኑ ሙስሊም ምሁራን በሙሉ ድምፅ የተስማሙበት ጉዳይ ነው። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ ይላል:-

الْيَوْمَ أُحِلَّ لَكُمُ الطَّيِّبَاتُ وَطَعَامُ الَّذِينَ أُوتُوا الْكِتَابَ حِلٌّ لَّكُمْ وَطَعَامُكُمْ حِلٌّ لَّهُمْ وَالْمُحْصَنَاتُ مِنَ الْمُؤْمِنَاتِ وَالْمُحْصَنَاتُ مِنَ الَّذِينَ أُوتُوا الْكِتَابَ مِن قَبْلِكُمْ إِذَا آتَيْتُمُوهُنَّ أُجُورَهُنَّ مُحْصِنِينَ غَيْرَ مُسَافِحِينَ وَلَا مُتَّخِذِي أَخْدَانٍ وَمَن يَكْفُرْ بِالْإِيمَانِ فَقَدْ حَبِطَ عَمَلُهُ وَهُوَ فِي الْآخِرَةِ مِنَ الْخَاسِرِينَ

“ዛሬ መልካሞች ሁሉ ለናንተ ተፈቀዱ፡፡ የእነዚያም መጽሐፍን የተሰጡት ሰዎች ምግብ (ያረዱት) ለእናንተ የተፈቀደ ነው፡፡ ምግባችሁም ለነሱ የተፈቀደ ነው፡፡ ከምእመናት ጥብቆቹም ከእነዚያ ከእናንተ በፊት መጽሐፍን ከተሰጡት ሴቶች ጥብቆቹም፤ ዘማዊዎችና (ዝሙተኞች) የምስጢር ወዳጅ ያዢዎች ሳትኾኑ ጥብቆች ኾናችሁ መህሮቻቸውን በሰጣችኋቸው ጊዜ (ልታገቡዋቸው የተፈቀዱ ናቸው)፡፡ ከእምነትም የሚመለስ ሰው በእርግጥ ሥራው ተበላሸ፡፡ በመጨረሻም ቀን እርሱ ከከሳሪዎቹ ነው፡፡” (አል-ማኢዳ 5፤5)

ይህ ፈቃድ የተሠረዘ (የተሻረ/መንሱኽ) አይደለም። ሙስሊም ምሁራን ይህን ሸሪዓዊ ድንጋጌ በተመለከተ በራሣቸው ግንዛቤና ትንታኔ አንዳንድ መስፈርቶችንና ገደቦችን አስቀምጠዋል።