ኒቃብ ግዴታ ነው?

Home የፈትዋ ገጽ ማህበራዊ ጉዳዮች ቤተሰብ ኒቃብ ግዴታ ነው?

ጥያቄ፡- ኒቃብ መልበስ ወይም ፊትን መሸፈን ግዴታ ነው? ሸሪዐዊ ሒጃብን የማትለብስ ሴት ቅጣቷ ምንድን ነው?


መልስ፡- ቢስሚላሂር-ረሕማኒር-ረሒም አል-ሐምዱሊል-ላሂ ረብ-ቢልዓለሚን ወስ-ሶላትወስ-ሰላም ዐላ ረሱሊላህ

ቀዳሚው ጉዳያችን፡- የኒቃብ ብይን ምንድን ነው?

ዑለሞች በሙሉ ለዓቅመ ሄዋን የደረሰች ማንኛዋም ሴት ከፊትና ከመዳፏ በስተቀር መላ አካላቷን መሸፈን ግዴታዋ እንደሆነ ያምናሉ። በመሀላቸውም ልዩነት የለም። በማንኛውም መልኩ ሴት ፈታኝ አካሏን ማጋለጥ እንደማይፈቀድላትም ያምናሉ። ፊትና መዳፍን በመሸፈን ዙርያ ግን የተለያየ አቋም አንፀባርቀዋል። ሴት ፊቷን እና እጇን መሸፈን ግዴታዋ ነው? አንዳንድ ዑለሞች ሁለቱንም መሸፈን ግዴታ ነው በሚል አጠቃለዋል። አንዳንድ ዑለሞች ደግሞ በአንድ አንድ ሁኔታዎች በተገደበ መልኩ ግዴታ ነው ብለዋል። አንዳንዶቹ ደግሞ በማንኛውም ሁኔታ ላይ ፊትን እና እጅን መሸፈን ግዴታ አይሆንም ይላሉ።

ዑለሞች የተለያዩበትን ምክንያት ሲያስረዱ ኢብኑ ሩሽድ “ቢዳየቱል-ሙጅተሂድ” የተሰኘው መፅሐፋቸው ላይ እንዲህ ይላሉ፡- “… ሦስተኛው ጉዳይ – የሴት ሀፍረተ ገላን መጠን የተመለከተ ነው። ብዙ ዑለሞች ከፊት እና ከእጅ በስተቀር የሴት መላ አካል ሃፍረተ ገላ ነው ይላሉ። አቡ ሐኒፋ ግን እግሯ ዐውረት አይደለም ይላሉ። አቡበክር ኢብኑ ዐብዲር-ረሕማን እና አሕመድ ደግሞ መላ ሰውነቷ – ፊቷን እና እጇን ጨምሮ- ዐውረት ነው ይላሉ።

የልዩነታቸው ምክንያት ተከታዩን አንቀፅ የተረዱበት ምክንያት ነው፡-

وَلَا يُبْدِينَ زِينَتَهُنَّ إِلَّا مَا ظَهَرَ مِنْهَا

“ጌጣቸውንም ከእርሷ ግልጽ ከኾነው በስተቀር አይግለጡ።” (አን-ኑር 24፤ 31)

ይህ አንቀፅ ላይ የተቀመጠው ፍልቅታ/exception ምንን ያካትታል? ውስን አካላቶችን ለመየት ነው ወይስ መሸፈን የማይቻሉትን (ቁመቷን እና ግዝፈቷን) ብቻ ነው የሚያመለክተው?

በእንቅስቃሴ ወቅት መሸፈን የማይቻለውን አካል ለማለት እንደሆነ ያመኑት ዓሊሞች የሴት መላ አካል ዐውረት ነው ብለዋል። የዚህ ሃሳብ ባለቤቶች ተከታዩን አንቀፅ መረጃ አድርገዋል፡-

يَا أَيُّهَا النَّبِيُّ قُل لِّأَزْوَاجِكَ وَبَنَاتِكَ وَنِسَاءِ الْمُؤْمِنِينَ يُدْنِينَ عَلَيْهِنَّ مِن جَلَابِيبِهِنَّ ذَٰلِكَ أَدْنَىٰ أَن يُعْرَفْنَ فَلَا يُؤْذَيْنَ وَكَانَ اللَّهُ غَفُورًا رَّحِيمًا

“አንተ ነቢዩ ሆይ! ለሚስቶቸህ፣ ለሴቶች ልጆችህም፣ ለምእምናን ሚስቶችም ከመከናነቢያዎቻቸው በላያቸው ላይ እንዲለቁ ንገራቸው። ይህ እንዲታወቁና (በባለጌዎች) እንዳይደፈሩ ለመኾን በጣም የቀረበ ነው። አላህም መሓሪ አዛኝ ነው።” (አል-አሕዛብ 33፤ 59)

ነገርግን አንቀፁ ፍልቅታ/ኤክሰፕሽን ያደረገው በተለምዶ የማይሸፈኑትን እጅና ፊትን ነው ብሎ ያመነው የዑለሞች ቡድን ግን ፊትና እጅን መሸፈን ግዴታ አይደለም ብሎ ያምናል። ይህ ቡድን ሴት በሐጅ ወቅት ፊቷን እንዳትሸፍን መከልከሏን እንደመረጃ አቅርቧል።

የቁርኣን እና የሐዲስ መረጃዎች ኒቃብ ዋጂብ መሆኑን ይደግፋሉ ብሎ ያመነው ወገን ዋጂብ ናቸው ብሎ በይኗል። ይህንን ሃሳብ የሐንበሊያ መዝሀብ ዑለሞች እና አንዳንድ ሻፊዒዮች ይወክሉታል። ሐነፊዮች እና ማሊኪዮች ደግሞ ሴት ፊትና እጆቿን መሸፈን ግዴታ አይሆንባትም ብለው ያምናሉ። አብዝሃኞቹ ሻፊዒያዎች ኒቃብ ግዴታ አይደለም ብለው ያምናሉ። እንደውም እነርሱ ዘንድ ኒቃብ ከሚፈቀዱ (ሙባህ) ነገሮች ዝርዝር ነው የሚመደበው።

ሸይኹል-ኢስላም ዘከሪያ አል-አንሷሪይ “አስነል-መጧሊብ” የተሰኘው መፅሐፋቸው ላይ እንዲህ ይላሉ፡-

“በሶላት ወቅት ወይም ከሶላት ውጪ ብትሆንም ባዳ ወንዶች ባሉበት የጨዋ ሴት ዐውረት ከፊትና – ከላይኛውም ሆነ ከውስጠኛዎቹ መዳፎቿ- በስተቀር መላ አካላቷ ዐውረት ነው።”

የኩወይቱ የፊቅህ ኢንሳይክሎፒዲያ ላይ እንዲህ የሚል ሰፍሯል፡-

“አብዝሃኞቹ ዑለሞች ከመዳፎቿና ከፊቷ በስተቀር የሴት ልጅ አካል ሙሉ ለሙሉ ዐውረት ነው ብለው ያምናሉ። ምክንያቱም ሴት ከወንዶች ጋር የሚያገናኙ ጉዳዮች ይኖሯታል። እቃ ልትቀበል፣ ልትሰጥ ትችላለች። ስለዚህ ማንነቷን ለማወቅ ስለሚያስቸግር ፊቷን መሸፈን ግዴታ ነው አይባልም። ነገርግን ፊቷን መግለጥ የተፈቀደላት ከፈተና አማን መሆኑ በተረጋገጠ ጊዜ ብቻ ነው። ነገርግን ታዋቂው የአሕመድ ኢብኑ ሐንበል አቋም የሴት ሁለመና ዐውረት እንደሆነ ያስረዳል። ጥፍሮቿ ሳይቀሩ ዐውረት ናቸው የሚል ሃሳብ አላቸው። ከኢማም አሕመድ እንዲህ ማለታቸው ተዘግቧል፡- `ከሚስቱ ጋር የተፋታ አብሯት ሊበላ አይችልም። ምክንያቱም አብሯት ከበላ መዳፏን ያያልና።`”

ኒቃብ – በአንዳንድ ሁኔታዎች ላይ- ተወዳጅ ወይም ዋጂብ ሊሆን ይችላል። ፈተና በተፈራ ሰዐት ኒቃብ መልበስ ግዴታ ነው ብለው ያምናሉ ማሊኪዮች። ሐነፊዮቹም እንደዚሁ ይላሉ።

ኢብኑ ነጂም (ረ.) “አል-በሕሩር-ራኢቅ” የተሰኘው መፅሐፋቸው ላይ እንዲህ ይላሉ፡-

“ፊት ሀፍረተ ገላ ነው በማለት እና ፊትን መመልከት ይፈቀዳል በማለት መሀል ጥብቅ ትስስር የለም። ፊቷን ማየት መፈቀዱ ስሜት ከመፈጠሩና ካለመፈጠሩ ጋር ነው የሚያያዘው። ዐውረት ባይሆንም ስሜት ከተፈጠረ መመልከት እርም ነው።… `ሸርሑል-ሙንያ` ላይ አንዳንድ ሸይኾቻችን እንዲህ ማለታቸው ተዘግቧል፡- `በዘመናችን ወጣት ሴት በወንዶች ፊት ፊቷን መግለጥ እርም ይሆንባታል። ምክንያቱም ፈተና በዝቷል`።”

ሸይኽ አል-ኸጥ-ጣብ የማሊኪያ መዝሀብ ልሂቅ ናቸው “መዋሂቡል-ጀሊል” የተሰኘው መፅሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል፡-

“ፈተና ይፈጠራል ተብሎ ከተሰጋ ሴትየዋ ፊቷን እና መዳፏን መሸፈን ግዴታዋ እንደሆነ እወቅ። ይህ ቃዲ ዐብዱል-ወሃብ ያሉት ነው። ሸይኽ አሕመድ ዙር-ሩቅ `ሸርሑር-ሪሳላ` የተሰኘው መፅሐፋቸው ላይ አስፍረውታል። `አት-ተውዲሕ` ላይ በግልፅ የተቀመጠው አቋምም ይኸው ነው። ይህ በርሷ ላይ ግዴታ ነው።”

አብዝሃኞቹ ዑለሞች ዘንድ ፈተና በማይሰጋበት ሁኔታ ላይ ፊትና መዳፎችን መሸፈን ግዴታ አይደለም። ሙስሊም ሴት ልትለብሰው የሚገባው አለባበስም ፈታኝ አካላቶቿን – ቅርፅዋን እና የቆዳዋን ቀለም- የማያሳይ መሆን እንዳለበትም ይስማማሉ። ከፊትና ከመዳፍ ውጪ ልብሷ ሁለመኗዋን የሚሸፍን መሆን አለበት። ልብሷ የሰዎችን እይታ የማይስብ እና ፈተና የማይቀሰቅስ መሆን ይገባዋል። እነዚህን መስፈርቶች የሚያሟላ ማንኛውም ዓይነት ልብስ -ለሴት- ይፈቀዳል። ለብሳው ከቤቷ ልትወጣም ትችላለች። በሸሪዓውም የተፈቀደ የአለባበስ ስርዐት ነው ብሎ መደምደም ይቻላል። ነገርግን ሴትየዋ የሐንበሊዮችን እና የጥቂት ሻፊዒዮችን ሃሳብ መከተል ከፈለገች እና ኒቃብን በራሷ ላይ ግዴታ ማድረግ ከፈለገችም በሩ ክፍት ነው። ጉዳዩ የዑለሞች ልዩነት ያለበት ስለሆነ ለጥላቻና ለመወቃቀስ የሚያበቃ ጉዳይ አይደለም።

ሁለተኛው ጉዳያችን፡- ውበትን መግለጥ (ተበሩጅ) ነው

የፊቅህ ልሂቃን ተበሩጅ -በማንኛውም ዓይነቱ- እርም መሆኑን ይስማማሉ። ልብስን የተጋነነ በማድረግም ይሁን በንግግርም ይሁን በሌሎች ሁኔታዎች ተበሩጅ እርም ነው። ምክንያቱም አላህ እንዲህ ብሏል፡-

وَقَرْنَ فِي بُيُوتِكُنَّ وَلَا تَبَرَّجْنَ تَبَرُّجَ الْجَاهِلِيَّةِ الْأُولَىٰ

“በቤቶቻችሁም ውስጥ እርጉ። እንደ ፊተኛይቱ መሃይምነት ጊዜ መገለጥም በማጌጥ አትገለጡ።” (አል-አሕዛብ 33፤ 33)

በሌላም አንቀፅ ልዑሉ አላህ እንዲህ ብሏል፡-

وَلَا يَضْرِبْنَ بِأَرْجُلِهِنَّ لِيُعْلَمَ مَا يُخْفِينَ مِن زِينَتِهِنَّ

“ከጌጣቸውም የሚሸፍኑት ይታወቅ ዘንድ በእግሮቻቸው አይምቱ።” (አን-ኑር 24፤ 31)

የኩወይቱ የፊቅህ ኢንሳይክሎፒዲያ ላይ እንዲህ የሚል አለ፡-

“ሴት በማንኛውም መልኩ መጋለጧ እርም ነው። ለማይፈቀድለት ሰው ጌጧን በማሳየትም ሆነ፣ አካሏን በመግለጥ ወይም በሌላ መልኩ ውበቷን ማሳየቷ ልዩነት የለውም። በማንኛውም ሁኔታ -ተቃራኒ ጾታን ለማማለል መገላለጥ -ተበሩጅ ማድረግ- እርም ነው። ይህ በአካሄድም ሊሆን ይችላል። እየተንጎማለለች በመሄድ፣ ቆዳዋን የሚያሳይ ስስ ልብስ በመልበስ፣ መተጣጠፊያዎቿን የሚያሳዩ ጠባብ ልብሶችን በመልበስ ወይም በሌላ ሁኔታ የወንዶችን ስሜት የሚያነሳሱ መገለጫዎችን መላበስ እርም ነው። እነዚህን ድርጊቶች ለባሏ ካልሆነ በስተቀር ለሌሎች ሰዎች ልታደርጋቸው አይገባም።”

ሦስተኛ ጉዳያችን፡- የምትገላለጥ ሴት ወልይ ግዴታ

የምትገላለጥ ሴት ወልይ -አባትም ሆነ ወንድም ወይም ሌላ- ሴትየዋ ከድርጊቷ እንድትታቀብ ሊመክራት ይገባዋል። ቡኻሪይ እና ሙስሊም ላይ ከናፊዕ ኢብኑ ዑመርን ዋቢ በማድረግ ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንደተዘገበው እንዲህ ብለዋል፡-

أَلاَ كُلُّكُمْ رَاعٍ وَكُلُّكُمْ مَسْئُولٌ عَنْ رَعِيَّتِهِ فَالأَمِيرُ الَّذِى عَلَى النَّاسِ رَاعٍ وَهُوَ مَسْئُولٌ عَنْ رَعِيَّتِهِ، وَالرَّجُلُ رَاعٍ عَلَى أَهْلِ بَيْتِهِ، وَهُوَ مَسْئُولٌ عَنْهُمْ، وَالْمَرْأَةُ رَاعِيَةٌ عَلَى بَيْتِ بَعْلِهَا وَوَلَدِهِ، وَهِىَ مَسْئُولَةٌ عَنْهُمْ، وَالْعَبْدُ رَاعٍ عَلَى مَالِ سَيِّدِهِ، وَهُوَ مَسْئُولٌ عَنْهُ. أَلاَ فَكُلُّكُمْ رَاعٍ، وَكُلُّكُمْ مَسْئُولٌ عَنْ رَعِيَّتِهِ..

“ሁላችሁም እረኞች ናችሁ። ሁላችሁም በጠበቃችሁት ነገር ትጠየቃላችሁ። በሰዎች ላይ የተሾመ መሪ እረኛ ነው። ስለጠበቀውም ነገር ተጠያቂ ነው። ሰውየውም በቤተሰቦቹ ላይ እረኛ ነው። ስለነርሱም ይጠየቃል። ሴትም በባሏ ቤት ላይ እና በልጆቹ ላይ እረኛ ናት። ስለነርሱም ትጠየቃለች።… ሁላችሁም እረኞች ናችሁ ስለጠበቃችሁት ነገርም ትጠየቃላችሁ።”

የኩዌቱ የፊቅህ ኢንሳይክሎፒዲያ ላይ እንዲህ የሚል አለ፡- “አባት በተቃራኒ ጾታ ለመከጀል የበቃችን ልጁን ከተበሩጅ መከልከል አለበት። ባዳ የሆነ ወንድም እርሷን መንካት እና ማየትም አይፈቀድለትም። ይህም ፈተናን ለማራቅ የተደነገገ ነው። በርሱ ስር ያለች ሴት ልጁንም -እስካላገባች ድረስ- በተመሳሳይ እንዳትገላለጥ መከልከል አለበት። ምክንያቱም አባት ሴት ልጁን በማናቸውም የአላህ ትዕዛዛት የማዘዝና ከማናቸውም ክፉ ነገሮች የመከልከል ግዴታ አለበት። እንደ አባት ሁሉ ሌሎችም የሴት ወልዮች ተመሳሳይ ግዴታ አለባቸው። ባልም ሚስቱን ከተበሩጅ መከልከል አለበት። ምክንያቱም ሚስቱን ከኃጢያት ማቀብ ግዴታው ነው።… “

አራተኛው ጉዳይ፡- ራሷን የምትገልጥ – ሙተበር-ሪጅ – ሴት የሚገጥማት አኺራዊ ቅጣት፡-

የምትገላለጥ ሴት በአኺራ ላይ ቅጣት እንደሚያገኛት የሚጠቁሙ ብዙ ዘገባዎች ተገኝተዋል። ከነዚህ ሐዲሶች መሀልም ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) -አቡሁረይራ (ረ.ዐ) በዘገቡት ሐዲስ- የእሳት ሰዎችን ሲዘረዝሩ እንዲህ ማለታቸውን እናገኛለን፡-

صِنْفَانِ مِنْ أَهْلِ النَّارِ لَمْ أَرَهُمَا قَوْمٌ مَعَهُمْ سِيَاطٌ كَأَذْنَابِ الْبَقَرِ يَضْرِبُونَ بِهَا النَّاسَ. وَنِسَاءٌ كَاسِيَاتٌ عَارِيَاتٌ، مُمِيلاَتٌ مَائِلاَتٌ، رُءُوسُهُنَّ كَأَسْنِمَةِ الْبُخْتِ الْمَائِلَةِ، لاَ يَدْخُلْنَ الْجَنَّةَ، وَلاَ يَجِدْنَ رِيحَهَا، وَإِنَّ رِيحَهَا لَيُوجَدُ مِنْ مَسِيرَةِ كَذَا وَكَذَا..

“እኔ የማላያቸው የእሳት ሰዎች የሆኑ ሁለት ዓይነት አሉ፡- (አንደኞቹ) እንደ በሬ ጅራት የሆነ አለንጋ ያላቸው ሰዎች ናቸው። ሰዎችን ይማቱበታል። (ሁለተኞቹ) የለበሱ ግን የተራቆቱ፣ እየተወዛወዙ የሚራመዱ፣ አናታቸው እንደተዘናፈለ የግመል ሻኛ የተቆለለ ሴቶች ናቸው። ጀነት አይገቡም። ሽታዋንም አያገኙም። ሽታዋ ረዥም ዘመን ከሚያስኬድ ርቀት ጀምሮ ይገኛል።” አሕመድ እና ሙስሊም ዘግበውታል።

ማጠቃለያ

የፊቅህ ልሂቃን በአንድነት መሸፈን እንዳለበት የተስማሙበት አካል ከፊት እና ከመዳፍ ውጪ ያለው የሴት አካልን በሙሉ ነው። ፊትና መዳፍ ላይ ግን ልዩነት አለ። አንዳንዶቹ ግዴታ ነው ብለዋል። ሌሎች ደግሞ ግዴታ አይደለም ብለዋል። ተበሩጅ (ውበትን ማሳየት እና የተቃራኒ ጾታን ስሜት ለመቀስቀስ የሚደረጉ ተግባራት በሙሉ) እርም መሆኑንም ዑለሞች በአንድነት አፅድቀዋል። የሴት ልጅ ኃላፊ የሆነ ማንኛውም ሰው በሥሩ የምትገኘውን ልጁን፣ እህቱን ወይም ሚስቱን ከእንዲህ አይነት ተግባር ማቀብ አለበት።

አላህ የበለጠ ያውቃል!