ተራዊሕ መስገድ ከዒሻእ በኋላ ከሚሰገደው ሱና ሶላት ያብቃቃል?

Home የፈትዋ ገጽ ጾምና ኢዕቲካፍ ተራዊሕ መስገድ ከዒሻእ በኋላ ከሚሰገደው ሱና ሶላት ያብቃቃል?

ጥያቄ፡- ተራዊሕ መስገድ ከዒሻእ በዕዲያ ያብቃቃል። ተራዊሕ እርሱን የማይተካው ከሆነ ይች ሱና ሶላት መቼ ትሰገድ? የተራዊሕ ሶላት የወቅት መጀመሪያ እና መጨረሻ መቼ ነው?


መልስ፡- ቢስሚላሂር-ረሕማኒር-ረሒም አል-ሐምዱሊል-ላሂ ረብ-ቢልዓለሚን ወስ-ሶላትወስ-ሰላም ዐላ ረሱሊላህ

ከዒሻእ ሶላት በፊት ተራዊሕን መስገድ አይቻልም። የተራዊሕ ሶላት -ያለ ምንም የዑለሞች ልዩነት- ተቀባይነት የሚያገኘው ከዒሻእ ሶላት በኋላ ነው። የዒሻእን በዕዲያ ከሰገዱ በኋላ መሆኑ ደግሞ እጅግ የበለጠ ነው። የተራዊሕ ሶላት የዒሻእን በዕዲያ አይተካም።

የዒሻእን በዕዲያ ችላ ማለት አይገባም። ምክንያቱም የዒሻእ በዕዲያ በጣም ከጠበቁ ሱና ሶላቶች መሀል አንዱ ነው። ነገርግን የመስጂዱ ሰዎች በዒሻእ ሶላት እና በተራዊሕ መሀል ለባለ ሁለቱ ረከዐ የዒሻእ ባዕዲያ ጊዜን ካልተዉ በእርጋታ ከላይ ያሳለፍነውን ብይን ማስተማር ያስፈልጋል። እምቢኝ ካሉም በዚህ ምክንያት መጨቃጨቅና መጣላት አይገባም። የተራዊሕ ሶላት ካበቃ በኋላ የዒሻእን ባዕዲያ መስገድም ይቻላል። ወይም ከኢማሙ ተራዊሕ ጋር የዒሻእን በዕዲያ ነይቶ መስገድና በስተመጨረሻ ተራዊሑን ማሟላትም ይቻላል።

የዒሻእን በዕዲያ አጥብቆ መያዝ እንደሚገባ ከሚያስረዱት መረጃዎች መሀል ሶሒሕ ሙስሊም ላይ የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሚስት ከነበሩት ኡሙ ሐቢባ የተዘገበው ሐዲስ ይገኛል። እንዲህ ይላሉ፡- ‹‹የአላህ መልእክተኛን (ሰ.ዐ.ወ.) እንዲህ ሲሉ ሰምቻቸዋለሁ፡-

ما من عبد مسلم يصلي لله كل يوم ثنتي عشرة ركعة تطوعا، غير فريضة، إلا بني الله له بيتا في الجنة. أو إلا بني له بيت في الجنة

“ማንኛውም የአላህ ባርያ በቀን ውስጥ አስር ረከዐዎችን -ከፈርዶቹ ውጪ- በተጨማሪነት ከሰገደ በጀነት ውስጥ አላህ ቤት ይገነባለታል።”

ኡሙ ሐቢባ እንዲህ ይላሉ፡- “ከዚህ በኋላ እነዚህን ረከዐዎች መስገዴን አላቆምኩም።”

የኩዌቱ የፊቅህ ኢንሳይክሎፒዲያ ላይ እንዲህ የሚል አለ፡- “አብዝሃኞቹ ዑለሞች የረመዳን ቂያም (ተራዊሕ) ከዒሻእ በዕዲያ በኋላ የሚሰገድ ጥብቅ ሱና ነው። ተራዊሕ ከፈርድ ሶላት ጋር ተከታትለው ከሚሰገዱት ሶላቶች ጋር ይመደባል። ምክንያቱም እርሱም ከፈርድ ሶላት በኋላ የሚሰገድ ነውና። የተራዊሕ ወቅት የሚጀምረው የዒሻእ ሱና (በዕዲያ) ካበቃ በኋላ ነው። ጊዜው ከፈጅር በፊት ከተራዊሕ በኋላ ዊትር መስገድ የሚያስችል ወቅት እስከሚቀር ድረስ ይዘልቃል። ጀመዐ የሚያመልጠው ከሆነ ተራዊሕን አለማዘግየቱ ይወደዳል።”

ከዚያም ኢንሳይክሎፒዲያው የዑለሞችን ሃሳቦች እንደሚከተለው ዘርዝሮ አስቀምጧል፡-

“አብዝሃኞቹ ዑለሞች የተራዊሕ ሶላት ወቅት ከዒሻእ ሶላት በኋላ ከዊትር በፊት እስከ ፈጅር ድረስ መሆኑን ያምናሉ። ምክንያቱም ኸለፎች ከቀዳሚዎቻቸው ሰለፎች የዘገቡት ይኸውን ነው። ሶሐቦቹም የሰገዱበት ወቅት ይታወቃል። ይኸውም ነበር። ከዒሻእ በኋላ ከዊትር አስቀድመው ነው የሰገዱት። ደግሞም ተራዊሕ ዒሻእን ተከትሎ የሚሰገድ ሶላት እንደመሆኑ ከዊትር በፊት መሰገድ አለበት። ከመግሪብ ሶላት በኋላ ከዒሻእ ሶላት በፊት ቢሰግደው አብዝሃኞቹ ዑለሞች ዘንድ ተቀባይነት የለውም። ሐነፊዮቹም ጋር ትክክለኛው አቋም ይኸው ነው። ለተራዊሕ አይቆጠርለትም። ማሊኪዮች ዘንድ ደግሞ እንደማንኛውም ሱና ይቆጠርለታል።  ሐነፊዮቹ ዘንድ የተሻለ ከሚባለው አቋም በተቃራኒ ተራዊሑ ተቀባይነት ያገኛል የሚል ሃሳብ አለ። ምክንያቱም ሌሊቱ በሙሉ እስከ ንጋት ድረስ ከዒሻእ በፊትም ሆነ ከዒሻእ በኋላ የተራዊሕ ወቅት ነው። ምክንያቱም ተራዊሕ ከሌሊት ሶላቶች ይቆጠራል። በመሆኑም ሌሊቱ ባጠቃላይ ወቅቱ ነው።

ሐንበሊዮቹ ተቀባይነት እንደሌለው ለማስረዳት እንዲህ ብለዋል፡- ተራዊሕ ከፈርድ ሶላት በኋላ እንዲሰገድ የተደነገገ ሶላት ነው። ከዒሻእ ሶላት በኋላ ማለት ነው። ስለዚህ እንደ ዒሻእ በዕዲያ ሁሉ ከዒሻእ በፊት እርሱን መስገድ አይቻልም። እንደውም ተራዊሕ ከዒሻእና ከዒሻእ በዕዲያ በኋላ የሚሰገድ ሶላት ነው። አል-መጅድ -የሐንበሊያ መዝሀብ የፊቅህ ልሂቅ ናቸው- እንዲህ ይላሉ፡- የዒሻእን በዕዲያ ከተመረጠው የዒሻእ ወቅት ማዘግየት እንደሚጠላው ሁሉ ተራዊሕንም ከዒሻእ ምርጡ ወቅት አለመዘግየት ይወደዳል።”

ከዒሻእና ከዊትር ሶላት በኋላ ቢሰግደው -ሐነፊዮች ዘንድ- ትክክለኛው አቋም ያብቃቃዋል ይላል። ሐነፊዮችና ሻፊዒዮች የተራዊሕን ሶላት እስከ ሌሊቱ ሲሶ ወይም ግማሽ ድረስ ማዘግየት እንደሚወደድ ያምናሉ። ሐነፊዮች ከእኩለ-ሌሊት በኋላ ኸለደለሰኮደሰከጀከጀፊከሰሀጀከደሰሀጀከለደለከጀለከጀከለጀመስገድ በመቻሉ ዙርያ ልዩነት አላቸው። ይጠላልም ተብሏል። ምክንያቱም እርሱ የዒሻእ ተከታይ ነው። ልክ እንደ ዒሸእ በዕዲያ ማለት ነው። ነገርግን ትክክለኛው አይጠላም የሚለው ነው። ምክንያቱም ተራዊሕ የሌሊት ሶላት እንደመሆኑ እንደማንኛውም የሌሊት ሶላት አዘግይቶ መስገዱ የተሻለ ነው።

ሐንበሊዮች በመጀመሪያው ሌሊት መስገድ ይሻላል ይላሉ። ምክንያቱም በዑመር ዘመን ሶሐቦቹ የሚሰግዱት የነበረው በመጀመሪያው ወቅት ነበር። አሕመድ እንዲህ የሚል ጥያቄ ተጠየቁ፡- “ተራዊሕ ዘግይቶ በመጨረሻው ሌሊት ይሰገድ?” እርሳቸውም እንዲህ አሉ፡- “የሙስሊሞቹ ሱና እኔ ዘንድ ተወዳጅ ነው።”

አል-ኢንሷፍ የተሰኘው የሐንበሊዮቹ ኪታብ ላይ እንዲህ የሚል ሰፍሯል፡- “የተራዊሕ ወቅት ከዒሻእ ሶላት እና ከበዕዲያው በኋላ ነው። ይህ በሐንበሊያ መዝሀብ ትክክለኛው አቋም ነው። አብዝሃኞቹ ዑለሞችም የሄዱበት ጎዳና ነው። በዚህም ነው ሙስሊሞች የሚሰሩት። ከኢማም አሕመድ ከዒሻእ ሶላት በኋላ ከበዕዲያው በፊት ይሰገድ የሚል ተዘግቧል። ሐርብ ናቸው የዘገቡት። ዑምዳ የተሰኘው መፅሐፋቸው ላይ ኢማም ኢብኑ ቁዳማ በዚህ ሐሳብ ቆርጠዋል። አል-ወጂዝ የተሰኘው መፅሐፋቸውም ላይ ይህንኑ ሃሳብ እንደሚደግፉ የሚያመለክት ቃል ተጠቅመዋል። እንዲህ ነበር ያሉት፡- “ተራዊሕ ከዒሻእ ሶላት ጀመዐ በኋላ የሚሰገድ ነው።”

አል-ከሻፉል-ቂናዕ የተሰኘው የሐንበሊዮቹ መፅሐፍ ላይም እንዲህ የሚል ሰፍሯል፡- “ተራዊሕን ከዒሻእ በኋላ ከበዕዲያው በፊት ከሰገደ ተቀባይነት እንዳለው ጥርጥር የለውም። ነገርግን በላጩ ከዒሻእ በዕዲያ በኋላ ማድረግ ነው። ይኽም ኢማም አሕመድ በግልፅ ያስቀመጡት ነው።”

አላህ የበለጠ ያውቃል!