ባሏ የሞተባት ሴት በ “ዒድ-ዳ” ጊዜዋ ላይ የምትከተለው የአለባበስ እና የጌጥ ስርዐት

Home የፈትዋ ገጽ ቤተሰብ ባሏ የሞተባት ሴት በ “ዒድ-ዳ” ጊዜዋ ላይ የምትከተለው የአለባበስ እና የጌጥ ስርዐት

ጥያቄ፡- ባሏ የሞተባት ሴት በ“ዒድ-ዳ” ጊዜዋ ላይ የምትከተለው የአለባበስ እና የጌጥ ስርዐት ምንድን ነው? በዒድ ቀንስ የተለየ ብይን ይሰጥ ይሆናል?


መልስ፡- ባሏ የሞተባት ሴት በዒድ-ዳ ጊዜዋ ላይ (አራት ወር ከአስር ቀን) እያለች ለጌጥ የሚሆኑ አልባሳትን ትከለከላለች። ያለምክንያት ከቤት መውጣትም ትከለከላለች። ነገርግን የተለየ ጌጥነት የሌለውን ጥሩ ልብስ ግን መልበስ ትችላለች። የአካሏን ንፅህናም ትጠብቃለች። ፀጉሯን ልታፀዳና ልታበጃጅ፣ ጥፍሮቿን ልትቆርጥ፣ ከሰዎች ጋር ልታወራ፣ አስፈላጊ ከሆነም ወንዶችን ልታነጋገር ትችላለች። እነዚህ ነገሮች ብዙዎች የሚከለከሉ ናቸው ብለው የሚያስቧቸው ናቸው።

ነገርግን አስፈላጊ ላልሆነ ምክንያት ከቤት መውጣት የለባትም። ለምሳሌ ፍርድ ቤት ጉዳይ ካላት ወይም ሆስፒታል መሄድ ካስፈለጋት ትሄዳለች። ለንግድ፣ ለስራ እና ለሌሎችም ዱንያዊ ጥቅም ላላቸው ጉዳዮቿ መውጣት ትችላለች። ይህ ሁሉ አይከለከልም።

ምክንያቱም ጃቢር ኢብኑ ዐብዲላህ እንዲህ ሲሉ ዘግበዋል፡-

“አክስቴ በሦስት ተፈታች። ከዚያም የተምር ፍሬዎቿን ለማስለቀም ወጣች። አንድ ሰውዬ ግን መንገድ ላይ አገኛትና ከለከላት። ይህንንም ለነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ነገረች። እርሳቸውም፡-

بلَى، فَجُذِّي نخلَكِ, فإنَّكِ عَسَى أَنْ تَتَصَدَّقي أو تَفْعَلِي معروفًا

“የለም! ተምርሽን አስለቅሚ። ምናልባት ሶደቃ ታደርጊ ወይም መልካም ትሰሪ ይሆናል።”

በዚህ ረገድ የዒድ ቀን የተለየ አይደለም። ዒዳዋ እስካላለቀ ድረስ በዒድ ቀንም በሌላ ጊዜ ላይ የምትከተለውን ስርዐት ነው የምትተገብረው።

አላህ የበለጠ ያውቃል!