ባለማወቅ የሚፈጽም በአላህ የማጋራት ወንጀል ከሀዲ ከመባል ያድን ይሆን?

Home የፈትዋ ገጽ ዐቂዳ ባለማወቅ የሚፈጽም በአላህ የማጋራት ወንጀል ከሀዲ ከመባል ያድን ይሆን?

ጥያቄ፡- ባለማወቃቸው (በጀህል) የተነሳ ትላልቅ የሺርክ (በአላህ የማጋራት ወንጀል) ተግባራት ስለሚፈጽሙ ሙስሊም ሰዎች እስልምና ያለው አቋም ምን ይመስላል? በዚህ ድርጊታቸው ከእስልምና ሊወጡ ይችላሉን?


መልስ፡- ሁሌም ቢሆን ሰዎችን ለማክፈር (ሙስሊም አይደለህም ለማለት) አለመቸኮል ተገቢ ነው፡፡ በሰዎች ላይ በክህደት (ከእስልምና መውጣት) መፍረድና መወሰን የሚቻለው እጅግ ግልጽ የሆነ አሳማኝና ጽኑ መረጃ ከተገኘ ብቻ ነው፡፡ በግልጽ ማስረጃ ድርጊቱ ከተረጋገጠና ወንጀሉን የሚፈጽመውም ሰው የወንጀሉን ብይን እያወቀ በእንቢተኝነቱና በትዕቢቱ ከገፋ፣ ድርጊቱም ከእስልምና የሚያስወጣ ትላልቅ የክህደት (ኩፍሩል-አክበር) ወይም በአላህ የማጋራት ትላልቅ ወንጀል (ሺርኩል-አክበር) ከሆነ በዚህን ጊዜ በአላህ ክዷል ልንለው እንችላለን፡፡

ሳዑዲ ዐረቢያ በሚገኘው ኡሙል-ቁራ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶ/ር ኡስማን ቢን ጁምዐተ-ዱመሪያ እንዲህ ይላሉ፡-

አላህን (ሱ.ወ) በብቸኝነቱ ማምለክ (ተውሒድ) የሁሉም የአላህ መልዕክተኞች አቢይ ጥሪ ነው- በሁሉም ላይ የአላህ እዝነትና ሰላም ይስፈን፡፡ ስለሆነም የተውሒድ ጉዳይ እጅግ አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን ልናውቅ ይገባል፡፡ ለክህደትም ሆነ በአላህ ለማጋራት ከሚዳርግ የትኛውም ዓይነት ድርጊት ዉስጥ ከመውደድ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ እንዲሁም አንድ ሰው በሙስሊም አማኝ ላይ ክህደትን ሊያፀድቅ አሊያም በአላህ አጋርቷል ብሎ ለመፍረድ ሊቻኮል አይገባም፡፡ የግድ ማድረግ ካለበትም የማክፈር መስፈርቶች (ሹሩጥ አት-ተክፊር) እና ሌሎችም ሰውዬውን ከእስልምና የሚያስወጡ እግዶች ከፈረሱ በኋላ (ኢንቲፋእ መዋኒዕ አት-ተክፊር) መሆን አለበት፡፡ ማንም ሰው ተነስቶ በአንድ ሙስሊም ላይ ኩፍርን (ክህደትን) መወሰን ሥልጣን የለውም፡፡ ይህ ንግግር፣ ድርጊት ወይም ሥራ ኩፍር/ክህደት ነው ልንል እንችላለን፡፡ ነገርግን ፈፃሚውን ካፊር/ሙሽሪክ ለማለት ግን መስፈርቶች ሊሟሉና እግዶች ሊፈረሱ ይገባል፡፡

ያለ ዕውቀት የኩፍር/ሽርክ ድርጊቶችን ስለሚፈጽመው ሰው ደግሞ- ይህ ድርጊቱን ፈፃሚ ምናልባትም ድርጊቱን የፈፀመው አንድም ሙስሊሞች በሌሉበት አገር በመኖሩ፣ አሊያም ስለ ሃይማኖታቸው ጠንቅቀው በማያውቁ ሰዎች ሀገር ዉስጥ የሚኖር በመሆኑ ምክንያት ወይም ደግሞ ስለ ሃይማኖታቸው ጉዳይ በጥልቀት አውቀው በዝርዝር የሚያሳውቁ ሰዎች ባለመኖራቸው የተነሳ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህም የተነሳ የሚፈጽመው ድርጊት የክህደት ወይም በአላህ የማጋራት ድርጊት መሆኑን እስካላወቀ ድረስ ባለዑዝር (ባለሰበብ) ይሆናልና ከሀዲ/ሙሽሪክ አንለውም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏልና-

وَمَا كُنَّا مُعَذِّبِينَ حَتَّىٰ نَبْعَثَ رَسُولًا

“መልዕክተኛንም እስከምንልክ ድረስ የምንቀጣ አይደለንም፡፡” (አል-ኢስራእ 17፤ 15)

ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ምንም ዓይነት መልካም ሥራ ስለሌለው ስለ አንድ ሰው ለሶሓቦቻቸው ሲተርኩ፡- ሰዉየው በሞተ ጊዜ እንዲያቃጥሉትና አመድ ከሆነ በኋላም ግማሹ ባህር ላይ ግማሹን የብስ ላይ እንዲበትኑ ለቤተሰቦቹ ተናዘዘ፡፡ ምክንያቱም ወንጀሌ በዝቷል ብሎ በመስጋቱና አላህ (ሱ.ወ) ከያዘኝ አይቀጡ ቅጣት ይቀጣኛል ብሎ በመስጋቱ ነበር፡፡ በሞተ ጊዜና እንተደተናዘዘው ከተደረገለት በኋላ አላህ (ሱ.ወ) የብስን አዘዘና በሷ ላይ የተበተነውን (አካሉን) ሰበሰበ፡፡ እንዲሁ ባህርንም አዘዘና በዉስጡ ያለው ተሰበሰበ፡፡ ከዚያም ሰውዬውን “ይህን ያደረግከው ለምንድነው?” ሲል ጠየቀው፡፡ ሰውየውም “ላንተ ያለኝ ፍራቻ ነው፡፡ ይህንን ደግሞ ከማንም በላይ አንተ ታውቃለህ” በማለት መለሠ፡፡ አላህም ምህረቱን ሠጠው፡፡ (ቡኻሪና ሙስሊም አቢ ሁረይራን በመጥቀስ እንደዘገቡት፡፡)

ይህ ሰው ምንም የማያውቅ መሃይም (ጃሂል) ሰው ነበር፡፡ ያም ሆነ ይህ ያለግልጽ ማስረጃና የጠራ ነገር ሳይኖር ሰዎችን ለማክፈር መቸኮልም ሆነ በአንድ ግለሰብ ላይ የሽርክን ታፔላ ለመለጠፍ መጣደፍ ተገቢ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ሰውየው የሚፈጽመው ድርጊት ከእስልምና የሚያስወጣ ትልቁ ክህደት (ኩፍሩል-አክበር) ወይም በአላህ የማጋራት ትልቁ ወንጀል (ሺርኩል-አክበር) መሆኑን እያወቀ በግብዝነት ሆንብሎ ድርጊቱን የሚፈጽም ከሆነ በዚህን ጊዜ ከእሰልምና የወጣ ሙሽሪክ ነው ልንለው እንችላለን፡፡ አላህ እጅግ አዋቂ ነው፡፡